የበጀት ዓመት መዝጊያ ሲቃረብ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በግዥ ሲጠመዱ ይታይ ነበር። የተረፈ ገንዘብ ለመንግሥት ላለመመለስ በሚልም የማይገዛ እቃ እንዳልነበረም ይታወሳል።
በዕቅድ እመራለሁ የሚል ማንኛውም ተቋም ዓመቱን በእለት ተእለት ሥራ ውስጥ ተጠምዶ እያሳለፈ ግዥን ያህል ነገር በመጨረሻዎቹ ወራት ለመፈጸም መሯሯጥ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲስፋፋ መፍቀድ ነው ። ይህ የመንግሥት ሀብት በከንቱ የሚባክንበት አሰራር ሲተች ቆይቶ መፍትሄ ከተቀመጠለት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የማዕቀፍ ግዥ በሚል የተቀመጠው አሰራር እንደተጀመረም መንግሥት በተናጠል ግዥ ሊያጣ ይችል የነበረውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ማስቀረት ተችሏል። ግዥ በወቅቱ እንዲፈጸምም አስተዋጽኦ አድርጓል። የማዕቀፍ ግዢው አንዱ አላማ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው መስሪያ ቤቶች ግዥ በአንድ ላይ ሲፈጸም መንግሥት የተሻለ ዋጋና ጥራት እንዲያገኝ ማስቻል እንደመሆኑም ከዚህ አኳያ አሠራሩ ውጤት እንዳስገኘ መረዳት ይቻላል።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግዥው ሂደት በርካታ ችግሮች እንዳሉበት እየተጠቆመ ነው። በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2011 የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት እንደተገለጸውም፤የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የግዥ አካሄድ ችግር እየታየበት ነው ።ለፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሚደረገው የማእቀፍ ግዥ ጥራቱን ጠብቆ በወቅቱ እየተከናወነ አይደለም።
ግዥው ከተፈቀደላቸው መስሪያ ቤቶች በርካታ የሚሆኑት ግዥውን መንግስት ባስቀመጠው አሰራር መሰረት እየገዙ አለመሆናቸው፣ የጥራት የመጠንና በወቅቱ በተጠየቀው ልክ ያለመድረስ ችግሮች እንደሚስተዋሉም ተጠቁሟል፤ ይህን አይነቱ አሰራር ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍት በመሆኑም የህዝብና የመንግስት ሀብት ለብክነት እንደሚዳርግና ጠንከራ ክትትል ማድረግን እንደሚጠይቅም ተገልጿል።
በተቋማት በኩል የግዥ ፍላጎት በወቅቱ አለማሳወቃቸው፣ አቅራቢዎች አሸናፊ ከሆኑ በኋላ ውል ገብተው የዋጋ ማቅረቢያ ሰነድ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣በወቅቱ እቃ ማቅረብ አለመቻላቸው እንዲሁም በመጋዘን እቃ እያላቸው የለንም ማለታቸውና የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የጥራት ጉድለት፣ደረጃ መስጠት ያለበት አካል በወቅቱ ደረጃ አለመስጠት፣የሰው ሀይል እጥረት የሚሉት የማእቀፍ ግዥው ፈተናዎች ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ። ችግሮቹ ብዙ ናቸው።
በዚህ የተነሳም ግዥ በጣም እየተጓተተ ሲሆን፣ይባስ ብሎም እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት የአንዳንድ ተቋማት ግዥ በማእቀፍ መካሄዱ ቀርቶ በህግና መመሪያው መሰረት በየተቋማቱ እንዲካሄድ የተደረገበት ሁኔታ ታይቷል።እርምጃው የተወሰደው ተቋማት ግዥውን ባለመፈጸማቸው ሳቢያ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር መፍታትን ታሳቢ በማድረግ ሊሆን ይችላል።ይህ መሆኑ ተቋማቱ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር በጥቂቱ ቢያስቀረውም ፣የማእቀፍ ግዥው ቢፈጸም መንግሥት ያገኘው የነበረውን ገቢ የሚያሳጣ፣ ለሙስናና ለጥራት መጓደል በር የሚከፍት አሰራር መሆኑ ግን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል።ችግሩ በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተቀመጠለትም አሰራሩን ወደቀድሞው ሊመልሰው ይችላል።
ሌሎች በግዥው ሂደት እየታዩ ያሉ ችግሮችም መንግሥትን በእጅጉ የሚጎዱ ናቸው። ጥራት የሚመለከተው ተቋሙን ብቻ መሆን የለበትም።ተቋማት በጥራት ላይ የሚደራደሩበት ሁኔታ ካለ አሠራሩ እሳት ካየው ምን ለየው የሚያሰኝና የቀድሞውን አሰራር መልሶ እንደማምጣት ይቆጠራል።አንዱ የመንግሥት ሀብት የሚመዘበርበት መንገድ ጥራት ያለው እቃ እንደሚያቀርቡ አሳውቆ ባለማቅረብ ነው።
የማእቀፍ ግዥው በተጓተተ ቁጥር ሥራ ይበደላል።እቅድ በጊዜ ላይ ተመስርቶ የሚሰራ እንደመሆኑ የግዥ ሂደት ከተጓተተ በእቅድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይከተላል።በጊዜ ሰሌዳ የተቀመጡ ስራዎች እንዲጓተቱና የሚፈለገው ደረጃ እንዳይደረስም ያደርጋል።
ተቋማት ግዥያቸውን በወቅቱ የማያሳውቁ ከሆነም ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ብሎም የሚያከናውኑት ግዢ የሚሰጡትን አገልግሎት ብቻ ታሳቢ ያደረገ እና ብክነትን የሚቀንስ መሆን ይኖርበታል።አቅራቢዎች ጋር ያለው ውልም በስርዓቱና ወቅቱን ጠብቆ መምራት አለበት።
ችግሮቹ ከስር ከስር ቢፈቱ ይህን ያህል ውስብስብ ባልሆኑ ነበር።አሁን የባለሙያ፣የጥራት፣የግዥ ጥያቄ ፣ወዘተ በሚሉት ላይ ያለው ክፍተት ሲንከባለል የመጣ እንደመሆኑ በትኩረት ሰርቶ መፍትሔ ማስቀመጥን ይጠይቃል።
በመሆኑም የግዢውን ችግሮች ለመፍታት የገንዘብ ሚኒስቴር፤ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፤ ግዢውን የሚፈፅመው አገልግሎት ሰጪና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ርብርብ በማድረግ አሠራሩ ሲጀመር ወደነበረበት በመመለስ የመንግሥትን ሀብት ከብክነት መታደግ ይኖርባቸዋል፤ግዥዎች በወቅቱ ባለመፈጸማቸው የተነሳ የሚደርስ የሥራ መጓተትን ማስቀረትም ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011