ክልሉን ማስተሳሰር የሚያስችሉ ዲጅታል አሠራሮችን ለማስፋፋት

ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፤ ይህን ተከትሎም ለውጦችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ:: ለዚህም የመብራትና የመሳሰሉት የአገልግሎቶች፣ የነዳጅ ግዥ ፣ የግብር ክፍያዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተፈጸሙ ያሉበትን ሁኔታ በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል::

ይህን ዲጂታል ቴክኖሎጂ የበለጠ ለማስፋፋት ኢትዮ-ቴሌኮም በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: ድርጅቱ ከበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የዲጅታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስምምነቶች በማድረግ አሠራሮቻቸው ዲጅታል እንዲሆኑ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ነው::

በቅርቡም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑና የዘመናዊ ከተማ /የስማርት ሲቲ/ ትግበራን እውን የሚያደርጉ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት አድርጓል:: በስምምነቱ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ ክልሉ ማህበራዊና ተቋማዊ አገልግሎቶችን በስፋት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ የመንግሥት አሠራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር የያዘውን እቅድ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ለማሳካት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል::

የቢሮ ሃላፊዋ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለማዘመን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተናጠል ብዙ ሥራዎች ሠርተዋል:: ከእነዚህም ስምምነቶች አንዱ ድርጅቱ ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ጋር የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን ያካሄደው ስምምነት ይጠቀሳል፤ በዚህ ስምምነት መሠረት የተሰሩ ተግባራትም ውጤታማ ናቸው::

በሌሎችም ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ የቢሮ ሃላፊዋ ጠቅሰው፣ እነዚህም በአሠራር ሥርዓት ውጤት አምጥተዋል ብለዋል:: የክልሉ መንግሥት አሁንም ማንኛውም የቴክኖሎጂና አገልግሎት የማዘመን ጥያቄ እንደ ክልል ለመመለስ የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮቴሌኮም ጋር ማድረጉን አመላክተዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ መንግሥት አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎት አሰጣጡ ውጤታማ እንዲሆን ቀልጣፋ፣ ጊዜ ቆጣቢና ግልጽ በሆነ መንገድ መስጠት ይጠበቅበታል፤ ዜጎች ይህንን አገልግሎት የሚጠይቁ በመሆኑ መንግሥት ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፤ ይህንን ከማድረግ አንጻር የክልሉ መንግሥት ከክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግሥት መዋቅሮችን በመረጃ አያያዝና ልውውጥ ያለባቸውን ክፍተት ለማሟላት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዝ አሠራር እንዲኖር ይፈልጋል::

ክልሉ በተለይም የትምህርት፣ የጤና፣ የቱሪዝምና መሰል አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ አሠራሮች በማስረጽ ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት ዋነኛው ሥራው ነው ሲሉ አስታውቀዋል::

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ተቋሙ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የተቋማትን የዲጂታል አገልግሎቶች ማስፋት ላይ በትኩረት መሥራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል:: ከክልሉ ጋር የተፈረመው ስምምነትም በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ዘመናዊነትን ለማረጋገጥ ያስችላል:: በዚህ ስምምነት ከሚከናወኑት መካከልም በዲጂታላይዜሽን ተቋማትን በማስተሳሰር የትምህርት ተደራሽነት፣ የማዕድን ሀብት ልየታና ምርትና ምርታማነትን ማዘመን እንዲሁም የግብርና ሥራን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራዎች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የጤና፣ የመሬት አስተዳደርና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ /ስማርት ሲቲ/ ግንባታንም እንዲሁ በቴክኖሎጂ ማዘመን የስምምነቱ አካል ናቸው ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል ።

ስምምነቱ የክልሉን ሀብት በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል በእጅጉ የሚያግዝና የዜጎችን የዕለት ተዕለት  እንቅስቃሴ የሚያቃልል እንደሆነም የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በስምምነቱ መሠረት ሥራዎችን ለማከናወን ኢትዮ-ቴሌኮም በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ መሠረተ ልማት ስትራቴጂና ኦፕሬሽን ፕሮጀክቶች የማኔጀመንት ኦፊስ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ጌታሁን ኢትዮ-ቴሌኮም በቀጣይ ከኦሮሚያ ክልልና ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር የሚኖሩትን ሥራዎች አስመልክቶ በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ ድርጅቱ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚሠሩ አስታውቀዋል::

እሳቸው እንደሚሉት ፤ ክልሉ 20 የሚሆኑ ዞኖችና 180 የሚሆኑ ወረዳዎች እንዲሁም 30 የሚሆኑ ከተሞች አሉት፤ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎችም ያሉት ክልል ነው:: ይህ ሁሉ ከቴክኖሎጂ አንጻር ሲታይ በዚህ ውስጥ ያሉትን አምራቾችን፣ ኢንዱስትሪዎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን እና ማህበረሰቡን መጀመሪያ ማሰብ ያስፈልጋል:: እነዚህንም በመለየት ዘመናዊ በሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮች በኔትወርክ እርስ በርስ በማስተሳሰር በኔትወርክ የተሳሰሩ ዞኖች፣ ከተማዎች እና ወረዳዎች መፍጠር ያስፈልጋል::

ክልሉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቴክኖሎጂ ተናብቦ መሥራት ካልቻለ የሚፈለገውን አገልግሎትም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን አዳጋች ይሆንበታል፤ ይህም ክልሉን ለአላስፈላጊ ወጪም ይዳርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የክልሉን ዞኖች፣ ከተሞች እና ወረዳዎችን በኔትወርክ ማስተሳሰር ከፍተኛ ወጪ መቀነስ ያስችላል፤ የሥራ ቅልጥፍናን ይጨምራል፤ ውሳኔ አሰጣጥን ያቀላል፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል::

እሳቸው እንደገለጹት፤ በኔትወርክ የተገናኙ ቢሮዎችን ለመፍጠር እና ለማገናኘት የሚያስችሉ የሶፍትዌር እና የሀርድ ዌር ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተዘጋጁ ናቸው:: የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ፣አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎቶችን በመለየት ማዘመን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ ሌላው በኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የትራፊክ ማኔጀመንት ሲስተም ለመተግበር የሚያስችለውና በቀላሉ እየተሠራበት ያለው ሁሉንም ከተሞች የማገናኘት ሥራ ነው:: አሁን ላይ በብዙ ከተሞች የቪዲዮ ካሜራዎች እና የሰርቪላንስ ካሜራዎች እየተተከሉ ይገኛሉ:: ይህ ወደ ሥራ ሲገባ የመንገድ ደህንነት ስጋት ይቀንሳል፤ በዚህ በኩልም አሠራሩን በጣም ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::

በትምህርት ዘርፉም የኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የትምህርት ሲስተምን ለመዘርጋት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ሲሉ አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ 15ሺ 44 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 556ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች አሉ፤ እነዚህ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ተግባር ይከናወናል:: ይህም ውጤታማ ትምህርት ቤቶችን በመውሰድና ግብዓቶችን በመስጠት እንደሚጀመር ጠቁመው፤ ከዚያም ወደ ሌሎች እየሰፋ እንዲሄድ እንደሚደረግ አመላክተዋል::

በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓትን ለመዘርጋት የተደረገው ሙከራ ውጤታማ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስታውቀዋል፤ ይህ ሲስተም በተለያዩ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ እየተሰራበት መሆኑንም ጠቅሰው፣ በክልሉ ትምህርት ሥራ ላይ ለመተግበር ከክልሉ ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል::

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ 30 ፖሊቴክኒክ ኮሌጆችና 323 የሚሆኑ ኮሌጆም ይገኛሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በእዚህ ደረጃም ዘመናዊ ትምህርት መስጠት የሚያስችል ሲስተም ለመዘርጋት እንደሚሠራ ይናገራሉ:: ይህም ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት እየተከናወነ ላለው ተግባር እንደሚረዳ አስረድተዋል::

ሀብትን አሟጦ ለመጠቀም በአይአርፒ (IRP) ሶሊሽን የፋይናንስ አሠራር የታገዘ አሠራር መዘርጋት በጣም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚሉት አቶ ዮሐንስ ፤ የኢአርፒ አሠራርን መዘርጋት ተጀምረው የቀሩ ሥራዎች እንዳይኖሩ ማድረግ ያስችላል::

አንዳንድ የታሰቡ ሥራዎች ወደ ፈጻሚ (ውጤት) ሳይደርሱ የሚቀሩበት ምክንያት የኢአርፒ ሲስተም ካለመኖሩ የተነሳ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የኢአርፒ ሶሊሽን ተግባራዊ ማድረግ በአጠቃላይ በክልሉ ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል አስታውቀዋል:: ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር እንዲሁም የክፍያ ሥርዓቶችን በማዘመን መሥራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል::

የቴሌ ክላውድ ሶሉሽን መዘርጋት ሌላኛው ከክልሉ ጋር የሚሠራ ሥራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: ከመረጃ አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር የሚያቀለው የቴሌ ክላውድ ሶሊሽን መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ ሁሉንም የክልል ተቋማት ሊመለከት የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል:: ትምህርትን፣ ግብርናን፣ መሬትን እና የሰው ኃይልን የተመለከቱ በጣም ብዙ ዳታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እነዚህን በቴሌ ክላውድ ሶሊሽን ለማስቀመጥ እንደሚሠራ አመልክተዋል:: በዚህም በኩል ብዙ ወጪን መቀነስ እና ቴክኒካል እገዛን ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ የቴሌ ክላውድ ሶሉሽን አገልግሎት ክልሉን ለማዘመን ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ አስታውቀዋል::

ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው የቴሌ ብር አገልግሎት በክልሉ የክፍያ ሥርዓቶችን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል አቶ ዮሐንስ ጠቅሰው፣ ቴሌ ብር በአሁኑ ወቅት በጣም በርካታ አገልግሎቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች እየሠጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: ኢትዮ-ቴሌኮም ካሉት 128ሺ ኤጀንቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚገኙት በኢሮሚያ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፣ ከክፍያ ሥርዓት ጋር ተያይዞ በእያንዳንዱ የአርሶ አደር ኪስ ድረስ ዘልቆ መግባት የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል:: በዚህ የተነሳ የአግሪ ፋይናንስና ቴክኖሎጂ /ፊንቴክ/ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻልም ጠቁመዋል::

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ዘመናዊ ግብርና የሚጀመረው ዘመናዊ በሆነ የክፍያ ሥርዓት በመሆኑ መሠረታዊ የሆኑት የማዳበሪያ ስርጭት፣ የዘር እና የመሳሰሉትን አቅርቦቶች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ከቴሌ ብር የክፍያ ሥርዓት ጋር ለማያያዝ ይሠራል:: ሊበረታቱ የሚገባቸው እንደ ስንዴ ያሉ የማምረት ሥራዎችን ማስተዋወቅ እንዲሁም የገበያ ትስስር ማምጣት የሚቻልባቸው ሲስተሞችን መዘርጋትም ይቻላል:: የግብር ባለሙያ ድጋፍ መስጠት የሚችልባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚቻልም ጠቅሰው፤ ከምርት ሂደት ጋር የተያያዙ ስጋቶችን እና መረጃዎችንም እንዲሁ ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎችም ይሠራሉ ብለዋል::

ከክልሉ ጋር ለመሥራት የታሰቡ በርካታ ሶሉሽኖች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ አንዳንዶቹ የተዘጋጁ ሌሎቹ ደግሞ የክልሉን መሠረታዊ ችግሮች በመውሰድ ገና እንደሚሠሩ ጠቁመዋል::

ዘመናዊ የሸገር ከተማን በመገንባት/ሸገር ስማርት ሲቲ/ በኩል የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ የሸገር ሲቲ ራሱን የቻለ የስትራቴጂ ዶክመንት እንደተዘጋጀለትም ገልጸዋል:: የሸገር ከተማ 12 ክፍለ ከተሞች፣ 36 ወረዳዎች እና 40 ቢሮዎች ያሉት ሲሆን፤ የተጀመረውን የዘመናዊ ከተማ /የስማርት ሲቲ/ ፕሮጀክት ለመጀመሪያ ጊዜ የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ::

ሁሉንም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች በአንድ ላይ በማስተሳሰር ተጠሪ ቢሮዎችን ሳይቀር የሚያገናኝ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችለው ቅኝት /ሰርቬይ/ ማለቁንም አስታውቀዋል:: ከተሞች መግቢያ በር፣ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎችና ዋና ዋና ተቋማት በር ላይ ቪዲዮ ካሜራዎች መትከል ደህንነቱ የተጠበቀ ስማርት ሲቲ መገንባት ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ዘመናዊ ከተማ /ስማርት ሲቲ/ ለመገንባት የኔትወርክ ዲዛይን ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀጣይ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል:: ይህም ተገልጋዩ የሚያነሳቸውን የኔትወርክ ፍጥነት ቅሬታዎችን በመቅረፍ ፍጥነት ያለው የኔትወርክ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ያስችላል:: የሸገር ከተማ ዲጂታል ቢሮዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ይህም በየትኛውም ጊዜ፣ ቦታና በየትኛውም ዲቫይስ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ያስችላል::

አሁን የሚገነባው ሸገርን ዘመናዊ ከተማ /የስማርት ሲቲ/ የማድረጉ ሥራ ነገ የሚመጡ የተለያዩ የከተማው አሠራሮችንም ማዘመን የሚችሉ ነገሮችን የሚያካትት ነው የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ይህም ከተማዋ በዲጂታል በኩል የሚያስፈልጋትንና ማግኘት ያለባትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሙሉ ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ አመላክተዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You