
ግብርና በሀገሪቱ ከፍተኛ የሰው ሃይል የተሰማራበትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ ቀዳሚ መስኮች መካከል ተጠቃሽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ በዋናነት ከሚነሱ የጥራጥሬ ምርቶች በተጨማሪ በቅመማ ቅመምና ፍራፍሬ ረገድ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል ይነገራል። በዚህ ረገድ ዕምቅ አቅም እንዳላቸው ከተለዩት አካባቢዎች አንዱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋነኛው ነው። እኛም ለዛሬው ዝግጅታችን በክልሉ ከንባታ ዞን አደሩ ጦንጦ ዙሪያ ወረዳ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሀብታሙ ዮሐንስ (ዶ/ር) ጋር ያደረገነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ ወረዳው በከፍተኛ የተፈጥሮ ጸጋ የተትረፈረፈ ከመሆኑ ባሻገር መሬቱና የአየር ሁኔታው ለሁሉም ተክሎች ተስማሚ ነው። በተለይ መሬቱ እጅግ ለም በመሆኑ በአካባቢው የማይበቅል የእጽዋት ዝርያ የለም። በውሃ ሀብት ረገድም የተትረፈረፈ ሀብት አለ። በአሁኑ ወቅት በወረዳ በስፋት እየተመረቱ ካሉ የሰብል አይነቶች መካከል የቅመማ ቅመም ምርት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ቅመማ ቅመም በወረዳው ሁሉም አርሶ አደር በየደረጃው የሚያመርት ሲሆን፤ ከሌላው በበለጠ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆንበትና በቤተሰብ ኑሮ ላይ ለውጥ ማስመዝገብ የተቻለበት ነው።
በወረዳ ደረጃ እየለማ ያለው የማሳ ሽፋን አምስት ሺህ ሰባት መቶ ሄክታር ይደረሳል። ይህንን በማስፋት በሚቀጥለው ዓመት በቡና እና ቅመማ ቅመም እስከ ስድስት ሺህ ሄክታር ለማልማት የኤክስቴንሽንና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል። እንደ አጠቃላይ የቅመማ ቅመም ምርት በሞዴል አርሶ አደሮች ደረጃ የማሳ ትመና ተሠርቶ ከአንድ ሄክታር ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻል ተለይቷል። ይሁንና ይህ የምርት መጠን እንደየ አርሶ አደሩ የማሳ እንክብካቤ ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል።
ቁጥሩ አሁን ባለው የገበያ ትስስር በትንሹ ከሦስት ሚሊዮን እስከ አራት ሚሊዮን ብር በአንድ ሄክታር ገቢ ሊያስገኝ የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል። በአካባቢው በሌላ አዝእርት በስድስትና በሰባት ወር ውስጥ በዚህ ልክ ገቢ ማግኘት የሚችል በአርሶ አደር ደረጃ የለም። ይሄ ከወርቅ ምርት የማይተናነስ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ፤ በአካባቢው ቅመማ ቅመም ወርቅ ነው ይባላል።
ከቅመማ ቅመም መካከል በአካባቢው በስፋት የሚመረተው አንዱ ዝንጅብል ነው። ዝንጅብል ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሲሆን ለጁስ፣ ለኬክ፣ ለከረሜላ እና ለሌሎችም ይውላል። አቅርቦቱን በተመለከተ በዱቄት መልክ በደረቅ በእርጥበት ተደርጎ በተለያየ መልክ ታሽጎ ለገበያ ሊቀርብ ይችላል። ይህን ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀ ኢንዱስትሪ ማቋቋም ይጠብቃል። ዛሬ በአንዳንድ የውጭ ሀገራት ሱፐር ማርኬቶች የሚቀርበው ዝንጅብል ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያና ሶማሌ ላንድ የሚወጣ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ያመለክታሉ።
እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ እነዚህ የጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ በጥሬ የቀረበላቸውን በፋብሪካ እያመረቱ የራሳቸውን አርማ በመለጠፍ ለዱባይና ለሌሎች አረብ ሃገራት ይልካሉ። ኢትዮጵያም በዚሁ ልክ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ራሷ አምርታ የራሷ መለያ አድርጋ ለወጪ ንግድ ማቅረብ ብትችል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማግኘት ይቻል ነበር። ከላይ የተጠቀሰው የምርት መጠን በእዚህ ወረዳ ብቻ የሚመረት ነው። በዙሪያው ወደ ስድስት እና ሰባት ወረዳዎች አሉ። እነሱም ተመሳሳይ ሽፋን ያለው መሬት ያላቸው በመሆኑ ብዙ ጥቅም ማግኘት የሚቻልበት እድል አለ።
ይህ ሆኖ ከገበያ ትስስር ጋር በተያየዘ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች ነበሩ። በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል በሚጠበቀው ደረጃ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ አይደለም። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ የሚያቀርበው በሦስት ደረጃ ደላላ አልፎ ገዢውን በማግኘት ነው። በዚህ ሂደት ደላሎች ወሳኝ በመሆን ማሳ አይተው አርሶ አደሩን፤ ‹‹ከፈለክ ሽጥ፤ ካፈለክ አትሽጥ›› እስከማለት ስለሚደርሱ ብዙዎች ተስፋ እንዲቆርጡ ሲያደርጉ ቆይተዋል። እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራ አንደኛ መንግሥት የሚገባውን ገቢ ያገኛል፡፡
ሁለተኛ አርሶ አደሩም ልፋቱን የሚመጥን በቂ ክፍያ የሚያገኝበት እድል ይፈጠራል ሲሉ ይናገራሉ።
በማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቅመማ ቅመም ምርትን ለመጨመር የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል «የማይበላውን በመንቀል የሚበላውን መትከል» የሚል ኢኒሼቲቭ አለ። በወረዳው እስካሁን በሚለሙ መሬቶች ላይ የማይበሉ በተለይ እንደ ባሕር ዛፍ ያሉ ተክሎች በብዛት የተከላሉ። ይህንን ለማስተካከል በረሃማነትን በማያስፋፋ መልኩ የማይበሉትን ዛፎች በሚበሉ ተክሎች መተካት በሚል ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። ይሄ አንዱ ክፍል ነው።
ሁለተኛ አዲስ የሚለማ መሬት አካባቢ ባሕር ዛፍ በመትከል ሌላኛው የቅመማ ቅመም አካባቢ ማድረግ ነው። ዛሬ ላይ በወረዳ ደረጃ ሁለት መቶ ሃምሳ ሄክታር ባሕር ዛፍ ተነቅሎ ቅመማ ቅመምና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና እንዲተክል እየተደረገ ነው። ይሄ እየቀጠለ ወደፊት በማይለሙ አካባቢዎች እና ቦረቦራማ በሆኑ ቦታዎች በደን አግሮ ፎረስት ተራራን ማላበስ ሌላው ስትራቴጂ ነው።
በወረዳ ደረጃ ከፍተኛ ፍራፍሬ የማምረት አቅም አለ። በ15ቱም ቀበሌዎች ፍራፍሬ እየተመረተ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አሁን በተግባር እየተመረቱ ካሉት ሙዝ፣ አቮካዶ ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ እና ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል። ይህንን በማስፋፋ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ለማግኘት በወረዳ ደረጃ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ አለ። በአካባቢው ያለው ሥነ ምህዳር ደግሞ ለዚህ እጅግ ምቹ ነው። ጥራጥሬ ስጋን ይተካል ይባላል። ነገር ግን ፍራፍሬም ስጋን ይተካል በሚባለው ደረጃ በእነርሱ አካባቢ የፍራፍሬ ንጉሥ ወይም ጃክ ፍሩት የሚባል ተክል መኖሩን ይጠቀሳሉ።
እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ የፍራፍሬ ንጉሥ የተሰኘው ተክል ካንሰር ላለባቸው ሰዎች ካንሰር የመከላከል አቅም አለው፡፡ የሰውነት በሽታን የመቋቋም አቅም እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪ የደም ግፊትና የደም ማነስ ለማስተካከል፤ የጨጓራ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም ጉልበት ለማግኘት ይጠቅማል። ይህ ፍሬ ከመድኃኒትነት አልፎ ለምግብነትም የሚውል ነው። የፍራፍሬ ንጉሥ (ጃንክ ፍሩት) መብቀል ከጀመረ በኋላ በተፈጥሮ በቀላሉ የሚደርስ ሲሆን፤ በአንድ ፍሬ ውስጥ ከአርባ እስከ ስልሳ ዘር አለ። ይህም ለማባዛት ምቹ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
አንድ ባሕር ዛፍ ተተክሎ ሰባት ዓመት ከቆየ በኋላ፤ የሚሸጠው አምስት መቶ ብር ነው። በዚህ መነሻ በአንድ ሄክታር ላይ በተሠራ ትመና በአንድ ሄክታር ላይ የሚገኝ ባሕር ዛፍ ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ይሸጣል። በአንድ ዓመት ደግሞ በአንድ ሄክታር ላይ የሚለማ የቅመማ ቅመም ምርት ጠንካራ በሆነ ሞዴል አርሶ አደር ማሳ ላይ እስከ አራት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዋጋ ሊያወጣ ይችላል። ስለዚህ የሰባት ዓመት ስሌት ሲሠራ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ወደ ሃያ ስምንት ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ይችላል። ባሕር ዛፍ በሚተከልበት ጊዜ ግን የሚገኘው ሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ብቻ ቢደርስ ነው። ይሄ በቤተሰብም በሀገር አቀፍ ደረጃም ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ ማመጣት የሚያስችል መሆኑን አመላካች ነው ይላሉ።
በወረዳው ጥምር ግብርናን የመከተል ባህል በ15ቱም ቀበሌዎች እየተካሄደ ይገኛል። በአካባቢው ከብት የሌለው ሰው በአመለካከት ድሃ ነው የሚል አስተሳሰብ በመኖሩ፤ አንድ ሰው ከብት አለው ከተባለ በኢኮኖሚው የተረጋጋ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም መነሻ ጥምር ግብርናን መሠረት ያደረገ እንዲሁም አፈራርቆ መዝራትና በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ በስፋት እየተተተገበረ ይገኛል ሲሉም ይገልፃሉ።
ከአምስት ዓመት ወዲህ በዝንጅብል ላይ አፈር ወለድ ተህዋስያን ተከስቶ ነበር። በዚህ ረገድ እስከ አሁን እየተሠራ ያለው የማዳን ሳይሆን የመከላከል ሥራ ነው። ለዚህም ቢሆን አሁን እየተረጨ ያለው የፈንገስ መድኃኒት ሲሆን፤ በሽታው ባክቴሪያ ነው። ይህ እንደ ስጋት የሚነሳ ጉዳይ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅድመ መከላከልን መሠረት ባደረገ መልኩ የመጀመሪያ ህክምና ለማካሔድ አርሶ አደሮች የሚከተሉት አካሄድ አለ። በዚህም ዘንድሮ በተከሉበት መሬት ላይ ቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ምርት አይተክሉም ሲሉ አካሄዱን በተመለከተ ይናገራሉ።
ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ በሁለተኛ ደረጃ ተፈጥሯዊ በሆኑ መንገዶች ማለትም ከቡና ገለባ ከተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ተመሳሳይ ግብዓቶችን በመጠቀም መሬቱን ያክሙታል። አሁን ባለው ሁኔታ ይፋ የወጣ ይሄን መድኃኒት ተጠቀሙ የሚል ምክር ባይኖርም፤ አጠቃላይ በሽታው ምን እንደሆነ ለመለየት ተችሏል። ይህንን ተከትሎ መድኃኒት እንዲፈለግለት በክልል ደረጃ በግብርና ሚኒስቴር በኩል በትኩረት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።
በተመሳሳይ ከማንጎ ጋር በተያያዘ ያለው ደግሞ «ዋይት ስኬል» የሚባል በሽታ በአካባቢው ተከስቷል። ለዚህም በአንድ ሥራ ፈጣሪ ልጅ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ኬሚካል ተሞክሮ ውጤት በማሳየቱ ጥቅም ላይ እንዲውል በባለሙያዎች አቅጣጫ ተሰጥቷል። ይህ ውጤታማነቱ አመርቂ የሚሆን ከሆነ የማስፋፋትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ በቀጣይ የሚከናወን ይሆናል።
በሌላ በኩል የአርሶ አደሩን ውጤታማነት እውን ለማድረግ ከሀገር ውስጥ የምረት ተደራሽነት ባለፈ ለውጪ ገበያም ማቅረብ ይጠበቃል። ያሉት ሀብታሙ (ዶ/ር) ለዚህም አንደኛው በስፋት ማምረት ሲሆን፤ ሌላኛው የጥራት ደረጃን ከፍ ማድረግና በዛው ተጠብቆ እንዲቀጥል ማስቻል ነው። ለዚህ መንግሥት ትኩረት በመስጠት ሀብትን ማሳወቅ ላይ ሊሠራ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
እንደ ሀብታሙ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ከድንጋይ ማዕድናት ጀምሮ እስከ ቅመማ ቅመም ድረስ ያሉ ጸጋዎች በሚጠበቀው ደረጃ አልተዋወቁም። እነኚህ መውጣትና እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቃል። ይህ አካባቢ ቡና አምራች በመሆኑ የከንባታ ቡና ተብሎ መንግሥትም እውቅና በመስጠቱ፤ በዚህ ረገድ በሀገር ደረጃ ለውጪ ገበያ ለመወዳደር የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡
ይሁንና ዋናው የአካባቢው ጸጋ ዝንጅብል ነው። እዚህም ላይ በተመሳሳይ ትኩረት በመስጠት ለወጪ ንግድ በቂ በሚያደርግ ደረጃ እውቅና እንዲኖረው መሥራት ይጠበቃል ሲሉ የተናገሩት ሀብታሙ (ዶ/ር) ፤ በወረዳው በአሁኑ ወቅት በመሠራት ላይ ያሉ ሥራዎችን አስመልክተው ባካፈሉን መረጃም የሚከተለውንም ጨምረዋል።
በመኸር እርሻ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ዘጠና አንድ ሄክታር ማሳ ለማልማት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል። በአሁኑ ወቅት አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ሄክታሩ የማሳ ዝግጅት ተጠናቋል። በአካባቢው በመኸር ከሚዘሩት መካከል ከጥራጥሬ ባቄላ፣ ስንዴ፣ ገብስ ሲሆኑ፤ በበልግ ቅመማ ቅመሞች እና ሌሎች ስራ ስር ተክሎች ይለማሉ። በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ሰባት ወራት ዝናባማ ከመሆኑ የተነሳ ከሶስት ወቅት በመላቀቅ በአምስት ወቅቶች ለማልማት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።
ፍራፍሬ ዓመቱን ሙሉ የሚለማ ነው። በመኸር እርሻ አደንጓሬ እና በቆሎን የማልማት ሥራ ይካሄዳል፡፡ ባቄላ ከሰኔ 15 ጀምሮ በክላስተር እየተዘራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ስንዴ መቶ ሃምሳ አምስት ሄክታር፤ ጤፍ ደግሞ ሁለት መቶ ዘጠና ሦስት ሄክታር በክላስተር እየለማ ይገኛል። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ምርትን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የአካባቢው ትልቁ ችግር ግብዓት ነበር። እስከ ቅርብ ጊዜ ለዝንጅብል ተብሎ የሚቀርብ በመንግሥት ደረጃ አራት ሺህ ብር የሚሸጠው ማዳበሪያ፤ በጥቁር ገበያ እስከ አስራ አራት ሺህ ብር ይሸጥ ነበር። ይህም የፖለቲካ አጀንዳ ተደርጎ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት እስከ መሆን ደርሶ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ አቅርቦት አንዱ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ፤ በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ የግብዓት እጥረት የለም ሲሉ ይናገራሉ።
በበልግ ወቅት በተጠየቀው መሠረት አስራ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ ወደ ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ዳፕ እና ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዩሪያ ለበልግ መጠቀም ተችሏል። ለመኸር ደግሞ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ኩንታል ዳፕ እና ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ኩንታል ዩሪያ በእያንዳንዱ መጋዘን ገብቷል። በፍጥነት ወደ ስርጭት የሚገባ ይሆናል። ይህ ለአርሶ አደሩ ረፍት በመሆኑ ትልቅ ውጤት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም