የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ማዕከል ያደረገ የመንገድ ልማት

መንገድ የሚወደደውንም የሚጠላውንም ለማምጣት የሚያስችል መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ፤ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ ›› ይባላል። መንግሥትም ለመንገድ ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል። ሕዝቡም ሳያሳዩት ቀድሞ የሚመለከት ነውና ያሻውን ለማምጣት መንገድ እንዲሠራለት አጥብቆ ይጠይቃል። አስፈፃሚውም ጥያቄ መኖሩን በተመለከተ ዕውቅና ይሠጣል። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒም “በሕዝብ ዘንድ የመንገድ ትልቅ ፍላጎት አለ።” ሲሉ ይናገራሉ።

የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ መንግሥት በቻለው አቅም ለመንገድ ትኩረት በመሥጠት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሁንና የታዘቡትን በተመለከተ ‹‹ስለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት›› በሚል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በድሬዳዋ ከተማ በተካሔደው መድረክ ላይ ይገልፃሉ። ‹‹ለምሳሌ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ኮንክሪት መንገድ ብቻ ነው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። ‹‹ያደጉት አገራትም ቢሆኑ ሁሉም መንገዳቸው ሙሉ ለሙሉ ኮንክሪት አስፓልት አይደለም።›› በማለት ላቀረቡት ጥያቄ ራሳቸው መልስ ይሠጣሉ።

የተትረፈረፈ ምርት ባይኖርም እንደበፊቱ የግንባታ ዘርፉ በሲሚንቶ እጥረት ላይ አይደለም። ሲሚንቶ እየቀረበ ነው። ይሁንና ሁሉንም መንገዶች በኮንክሪት መሥራት አዳጋች ነው። ስለዚህ የኮንክሪት መንገድ እጥረት ቢኖርም፤ ሌሎች አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል ሲሉ ይናገራሉ። መንግሥት ኮንክሪት ባይሆኑም በተለይ በገጠር በስፋት መንገድ እየሠራ መሆኑን ያብራራሉ። በየአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን በማስታወስ፤ ምርት ለማንቀሳቀስ የሚያስችል መንገድ ከተሠራ መንገድ እንዳልተሠራ ሊቆጠር አይገባም ይላሉ።

እንደሚንስትሯ ገለፃ፤ በእርግጥ ቀድሞ የነበረው የገጠር መንገድ ተደራሽነት መሠረታዊ መዋቅር አልተሠራለትም። ከአሁኑ መንገድ ጋር በእጅጉ በመጠን የተለያየ ሲሆን፤ ከትራንስፖርት ልማት አኳያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከአመራርና ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዘርፉ ዕድገት እየተሻሻለ መጥቷል። ይህን ተከትሎ የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ትልቅ ለውጥ እየመጣ ነው።

በገጠር እየተሠራ ያለው የመንገድ ሥራ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑን ደጋግመው የሚያመለክቱት ሚኒስትሯ፤ በተለይ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚኖረው የዕድገት ሽግግርም ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን፤ በፕሮግራሞች ታቅፈው ያልነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የምርት አቅም ኖሯቸው ምርታቸውን በቀጥታ ገበያ ማድረስ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። ይህ የቆየውን የግብርና ምርት እያለ መንገድ በማጣት ምርት ማውጣት የማይቻልበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቀየር በገጠር ትስስር ፕሮግራም ከክልሎች ጋር በስፋት እየተሠራ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

ይህንን ችግር ለማቃለል ከዓለም ባንክ በተገኘ የ417 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ወረዳን ከወረዳ የሚያስተሳሰር መንገድ በስፋት በመገንባት ላይ ይገኛል። ይሁንና ወረዳን ከወረዳ ለማገናኘት ቢሠራም፤ አሁንም ወረዳን ከወረዳ በማስተሳሰር ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያውያን አሠፋፈር በመሬት አቀማመጣቸው ብቻ ተነጥለው የሚኖሩ ማህበረሰቦች መኖራቸው ሥራው ሙሉ ለሙሉ ሁሉንም ሕብረተሰብ ያካተተ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሯል ይላሉ።

በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥ የመንገድ ግንባታ ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ትራንስፖርት ከተማ ውስጥ መኖሩ ከምርታማነት እና ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑን ተከትሎ በስፋት እየተሠራበት እንዳለ ያመላክታሉ።

የገጠርም ሆነ የከተማ የመንገድ ግንባታ ጥቅም መታየት ያለበት በብዙ መልኩ ነው ሲሉ የሚናገሩት ሚንስትሯ፤ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር በስፋት ሊዘረዘር የሚችል ጥቅም እንደሚያስገኝ ጠቁመው፤ በሌላ በኩል በተለይ ከከተማ አንፃር የመንገድ አቅርቦት አንደኛው ጥቅሙ የትራፊክ መጨናነቅን መቀነስ መሆኑም ሊዘነጋ እንደማይገባ ያመለክታሉ።

ሌላኛው ዜጎች ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሰውን እና ሰው ከመኪና ተለያይቶ መሔድ የማይችልበትን የከተማ ሁኔታ መቀየር ነው። ይህን ችግር ለማቃለል ብዙ ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት ተጀምሯል ይላሉ።

እንደሚንስትሯ ገለፃ፤ በከተሞች አካባቢ ሰው ወጥቶ መግባት ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎች በእግራቸው እየተራመዱ እና ቁጭ ብለው የሚያስቡበት እንዲሁም ከአካባቢው ጋር የሚስማሙበት ቦታ እየተገነባ ነው። እንዲሁም ፍትሓዊ የሃብት አጠቃቀም የተፈጠረ ሲሆን፤ በግለሰብ ባለሃብቶች ታጥረው የነበሩ አካባቢዎች የሕዝብ የጋራ መጠቀሚያ ሆነው ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው ልጃቸውን ይዘው የሚዝናኑበት፤ ሁሉም የከተማ ነዋሪ የሚጠቀምበት ዕድል ተፈጥሯል።

የመንገድ ግንባታ እና ትራንስፖርት ከተማ ውስጥም ሆነ ገጠር በስፋት አለ ማለት ከምርታማነት እና በቀጥታ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋርም ግንኙነት ያለው በመሆኑ፤ በስፋት እየተሠራ ነው። በተለይ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉና ወደመጠናቀቅ የደረሱ የፍጥነት መንገዶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ይህ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ወደ ፊትም የሚቀጥል መሆኑንና በተለይም ከአስር ዓመት የልማት ዕቅድ አኳያ የተቀመጡት በፍጥነት የሚሠሩበት ሁኔታ ይኖራል። በተጨማሪም አዳዲስ ዕቅዶች መኖራቸውን አመልክተው፤ በቀጣይ የመንገድ ግንባታው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የታቀዱ እቅዶች መንግሥትን በመጠበቅ ብቻ የሚሠራ አለመሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ጫልቱ፤ የግል ዘርፉ በፍጥነት መንገድም ሆነ በሌሎች የመንገድ ግንባታዎች ላይ ሊያግዝ እና ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል። ለዚህም በግል እና በመንግሥት አጋርነት የግል ዘርፉ እንዲሳተፍ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ሥራው ተጀምሯል። ዘርፉ ላይ መሳተፍ ትርፋማ የሚያደርግ በመሆኑ መንግሥት እና የግል ዘርፍ ባለሃብቱ የሚሠራው እንዳለ ሆኖ የማህበረሰቡም ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሚንስትሯ እንቅፋት ብለው ከጠቀሷቸው መካከል የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጋነን አንደኛው ነው። በዚህ በኩል ሕዝቡ ሊያግዝ ይገባል። አንዳንድ ቦታ ላይ የአንድ መንገድ ፕሮጀክት የግንባታ ወጪ አንድ ቢሊየን ብር ሆኖ ለካሳ ክፍያ ግን እስከ ሁለት ቢሊየን የሚጠየቅበት ሁኔታ አለ። የወሰን ማስከበር ጉዳይ የመንገድ ግንባታ ትልቅ እንቅፋት በመሆኑ ሕዝቡ ጉዳዩን በደንብ ማየት እና ያሉ ክፍተቶች የሚጠቡበት ሁኔታ ላይ ማገዝ የግድ መሆኑን አመላክተዋል። ሕዝብ ሲያግዝ መንገድ የመገንባት ማነቆ መቀነስ እንደሚችል እና ሕዝቡም በመንገድ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፕሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው እንዳመላከቱት፤ ሀገራዊ የመንገድ ግንባታ ባለፉት ስድስት አመታት ቀደም ሲል ከነበረበት 26 ሺ ኪሎ ሜትር ወደ 275 ሺ ኪሎ ሜትር አድጓል ። ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከ550 በመቶ በላይ ነው። ይህ እጅግ መበረታታት ያለበት እና ይቀጥል የሚያሰኝ ውጤት ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በፍጥነት ካደጉ እና እያደጉ ከመጡ መሠረተ ልማቶች የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሽ መሆኑን ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ይሁንና ከአገሪቱ ሥፋት እና ከመንገድ መሰረተ ልማት አስፈላጊነት አንፃር አሁንም በዘርፉ ብዙ መስራት እንደሚቀር መካድ እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ከመንገድ ልማት አንፃር ያለችበትን ደረጃ አስመልክቶ ሲያስረዱ፤ አፍሪካዊ በሆነ መስፈርት በአንድ ሺ ካሬ ሜትር ስኩዌር 204 ኪሎ ሜትር ወይም 37 በመቶ አማካኝ የመንገድ ሽፋን ሊኖር ይገባል። የኢትዮጵያ መንገድ ዘርፍ ልማትም ሆነ አጠቃላይ የሀገሪቱ የመንገድ ሽፋን ከዚህ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አሁንም የመንገድ መሰረተ ልማት ኢትዮጵያ ወደ ኋላ የቀረች ናት። በዘርፉ በቀጣይ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ያመላክታሉ ።

በተለይ ክልሎችን ከክልሎች፤ ከተማን ከከተማ እንዲሁም የገጠሩን አካባቢ እርስ በእርስ ለማገናኘት የሚያስችሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በስፋት መሠራት አለባቸው የሚል ፅኑ ዕምነት ያላቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከአስፓልት እና ከጥርጊያ መንገድ በተጨማሪ በሌሎች አማራጮችም መንገድ መስፋፋት አለበት ይላሉ።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው 759 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የባቡር መሰረተ ልማት ሰዎችን ከማመላለስ በተጨማሪ የወጪ እና ገቢ ምርቶችን በማመላስ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ያመላክታሉ። ይህን ተከትሎ ምርቶችን በአየር እና በመኪና ለማጓጓዝ የሚያስወጣውን ወጪ ከ60 በመቶ በላይ መቀነስ ማስቻሉን ጠቁመው፤ በመንገድ ልማት ዘርፍ የባቡር መሥመር ዝርጋታ ከፍተኛ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ።

ሁለቱም አመራሮች እንደጠቆሙት፤ የመንገድ ዘርፉ ላይ በጉልህ ሊታይ እና ሊጠቀስ የሚችል የመንገድ ግንባታ አለ። አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመተግበር በኢትዮጵያ የገጠሪቷ ክፍል የሚመረቱ ምርቶችን አጓጉዞ ገበያ እና ገበያተኛን ለማገናኘት፤ የግብርና ምርትን ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት እሴት የታከለበት ምርት ለአገር ውስጥ እና ለውጭ አገር ገበያም ለማቅረብ መንገድ እየተሠራ መሆኑን መካድ አይቻልም።

ይሁንና አመራሮቹም እንዳመላከቱት ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት እና የህዝብ አሰፋፈር አንጻር የመንገድ ኔትወርክ ሽፋን አሁንም ጥያቄ ውስጥ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ካላት እቅድ አንጻር በተለይ ምርት ሰጪ ከሆኑ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ማዕከል የሚያዳርሱ መንገዶች ሽፋን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት አያጠያይቅም።

በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ደግሞ ከአስፓልትም ሆነ ከኮንክሪት ግንባታ ጎን ለጎን ባቡር ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ የሚሆንበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የባቡር መስመር ዘርግቶ በመጠቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ካላት የቆዳ ስፋት እና የህዝብ አሰፋፈር ስብጥር አኳያ ገጠሩን እና ከተማውን በማስተሳሰር በኩል የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆን የሚችለው የባቡር መሥመር ዝርጋታ ላይም መንግሥት ከግል ባለሃብቱ እና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት በሰፊው መሠራት ይኖርበታል። ለአስፓልትም ሆነ ለኮንክሪት መንገድ ግንባታ መንግሥትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባለሃብቱ እና በአጠቃላይ ሕዝቡ ተባብሮ መንገድ በስፋት ሊሠራ ይገባል የሚለው የዕለቱ መልዕክታችን ነው። ሰላም!

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You