ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ነው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለፁ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ያሉ ብዥታዎችን ለማጥራት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ  የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በማስጠበቅ ረገድ በዘላቂነት ለመሥራት የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር ያለመ የምክክር መድረክ ትናንት ተካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ነው ብለዋል።

የብሪክስ አባል መሆን ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ አማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭን ለማስፋትና አጋርነትን ለማጎልበት ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ስታደርግ የቆየች፣ ዓለም አቀፍ የጋራ ትብብርን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ልምድ ያላትና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የምትንቀሳቀስ ሀገር መሆናንም አውስተዋል።

አንደ አምባሳደር ምስጋኑ ገለፃ፤ ብሪክስ ሁሉንም አይነት አመለካከት ያቀፈ ግማሽ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ የያዙ ሀገራት የተካተቱበት ስብስብ ነው። 30 በመቶ ያህል የዓለም ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴን የሚያካሂዱ ሀገራትም የሚገኙበት ኅብረት ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህን ስብስብ መቀላቀሏ የምትገኝበትን ቀጣና፣ አፍሪካን እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በተመለከተ ድምጿን ማሰማት የምትችልበት ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር ትልቅ የዲፕሎሚሲ ስኬት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ማንንም ለማስደሰትና ለማስከፋት አይደለም ያሉት አምባሳደር ምሥጋኑ፤ አንዳንዶች እንደሚሉትም የፖለቲካ ካምፕ አይደለም የተቀላቀለችው ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ከየትኛውም ጎራ የመወገን ፍላጎትም እንደሌላት ነገር ግን ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስከብር ማዕቀፍ ውስጥ ሁሉ ገብታ እንደምትሠራ አብራርተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመንግሥት በጀት በማይሸፈኑ ማህበራዊ ልማቶች ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛና የማይተካ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በኩልም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ለወደፊቱም በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በብሪክስ አባልነት ጉዳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መፈጠሩ ማህበራቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሳተፉበት መድረክ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን በተመለከተ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘንድ ያለውን አረዳድ እንዲሁም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የሚኖረውን ፋይዳ የዳሰሱ ሁለት ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ በይፋ ተቀባይነት ያገኘው ከአራት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት 15ኛ ጉባዔ መሆኑ ይታወሳል። ከመጪው ጥር ወር ጀምሮም የብሪክስ ሙሉ አባል ትሆናለች።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 21ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You