አዲስ አበባ፡- መንግሥት በጎርፍ፣ በግጭትና በድርቅ ለተጎዱ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በሁለት ዙር 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ርዳታ ማድረሱን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አታለለ አቡሀይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች በርካታ ሰዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡
ክልሎች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን በጎርፍ፣ በድርቅና በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በመለየት ባሳወቁት መሠረት መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት ሁለተኛ ዙር የምግብ ርዳታ ማድረሱን አቶ አታለለ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አታለለ ገለጻ፤ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለርዳታ ፈላጊዎች በአርባ አምስት ቀን ልዩነት በሁለት ዙር ለ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ርዳታ ማድረሱን ጠቁመው፤ በዚህም መሠረት በሰሜን ጎንደር፣ በዋግህምራና በትግራይ ክልል ሶስት ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ርዳታ ተሰራጭቷል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የገንዝብ ርዳታ የተደረገላቸው ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ምግብ ነክ ድጋፎች እንደተደረገላቸው አቶ አታለለ ጠቁመው፤ ርዳታው በገንዘብ ሲተመን 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አታለለ እንዳሉት፤ በሁለተኛው ዙር ርዳታ 610 ሺህ ኩንታል እህል እንዲከፋፈል ተደርጓል። እንዲሁም 54 ሺህ ኩንታል አልሚ ምግብና አንድ ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለእናቶች ለህጻናትና ለነፍሰጡር የማዳረስ ሥራ ተሠርቷል። ከዓለም ባንክ በተገኘ ርዳታም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች እንዲከፋፈል ተደርጓል።
እንደ አቶ አታለለ ማብራሪያ፤ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር በጎርፍ ምክንያት በሶማሊያ ክልልና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የተፈናቀሉ ወገኖችን አያካትትም።
ከሰሞኑ በሶማሊያ ክልል በተከሰተው ጎርፍ መንግሥት አንድ ሺህ 821 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና ሩዝ ተልኳል ያሉት አቶ አታለለ፤ 9 ሺህ 200 ኪት ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችም ድጋፍ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሄሊኮፕተር በመጠቀም የሰዎችን ሕይወት የማዳን፣ የምግብ ቁሳቁሶችን፣ መድሃኒት፣ አጎበርና የውሃ ማጣሪያ ኬሚካል የማሰራጨት ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ አታለለ ጠቁመው፤ ሌሎች ድጋፎች እየቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በሶማሌ ክልል ችግር ለገጠማቸውን ዜጎች ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ 16 ሺህ 648 አባ ወራዎችና እማ ወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቁመው፤ ለነዚህ ዜጎች የሚሆን 3 ሺህ 140 ልዩ ልዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ተልከዋል ብለዋል።
በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ወደፊት ምን አይነት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ኮሚሽኑ እንደሚያደርግም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አታለለ ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም