አቶ ንዋይ መገርሳ የኬኛ ቢቨሬጅ ፕሮጀክት ማናጀርና የኦሮሚያ ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ የክልሉን መንግሥት ሲያግዙ ቆይተዋል፡፡ ስለ ኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮትና ተያያዥ ጉዳዮች ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት ለምን?
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮትን በተመለከተ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ መንግሥት በተለያየ መድረክ የሀገሪቷን ሁኔታ ገምግሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ለውጥ የሚፈልጉ ነገሮች እጅግ በርካታ ቢሆኑም አንዱ የህብረተሰቡ ጥያቄ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነበር፡፡ ህብረተሰቡን ከታች ጀምሮ በኢኮኖሚ ማሳተፍ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ተብሎ ስለታመነበት በኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ አብዮት ለማምጣት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የኢኮኖሚ አብዮቱ አላማ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ልማት ማረጋገጥ ነው፡፡ የሁለት ዓመታት ጉዞ ዳሰሳ
ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ድርጅቶችን ማቋቋም ተችሏል፡፡ ኬኛ ቢቨሬጅ ካምፓኒን እንደ ምሣሌ ቢነሳ በትልቅ ካፒታል የተቋቋመ ነው፡፡
በሦስት ቢልዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ነው የተቋቋመው፡፡ ከኬኛ ቢቪሬጅ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሌሎች አምስት የሚሆኑ ድርጅቶችም አሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የኢኮኖሚ አብዮቱ መልክ እየያዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች በጥምረት ፋይናንስ እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ የታቀዱት አምስቱ ኩባንያዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ቡልቡላ ላይ ትልቅ ኢንዳስትሪ ፓርክ እየገነባ ያለው ወላቡ ኮንስትራክሽን እንደ ምሣሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ወላቡ የኢኮኖሚክ አብዮቱ አንዱ አካል ነው፡፡
ሌላው ኬኛ አግሪካልቸራል ማሽነሪስ የሚባል ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ድርጅት የግብርና መሣሪያዎችን የሚያመርት ሲሆን፤ በቅርቡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት በሻሼመኔ ላይ ተመርቋል፡፡ ኦዳ ኢንቴግሬትድ ትራንስፖርት ደግሞ አውቶብሶችን እያመረተና የነዳጅ ዴፖዎችንም እያስገነባ ይገኛል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ኩባንያዎች አሉ፡፡ እነዚህን የክልሉ መንግሥት መልክ አስይዞ ፖሊሲዎችን እና አዋጆችን አውጥቷል፡፡ የሚመራቸውም ቢሮ ተቋቁሟል፡፡ ኩባንያዎቹ የአክሲዮን ሽያጩን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ባለሀብቶች እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ ኩባንያዎች አክሲዮን በመግዛት ላይ ናቸው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሞላ ጎደል ያለው እቅስቃሴ ይህን ይመስላል፡፡
የኢኮኖሚ አብዮቱ ብዙ ጥረት የሚፈልግ ነው፡፡ አሁን የክልሉ መንግሥት ያቋቋመው የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ጥምረት ቢሮ የመንግሥት እና የግሉን ቅንጅት በማጠናከር አቅም በፈቀደ ደረጃ ለህዝብ እና ለመንግሥት የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ተቋማት ማቋቋሙን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የኢኮኖሚ አብዮቱ አሁን ወደ ግል እና የመንግሥት ጥምረት (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) ደረጃ ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል፡፡
የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ቅንጅት
የኢኮኖሚ አብዮቱ ግብ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ኢኮኖሚን በመገንባት የህብረተሰቡን ህይወት ማሻሻል ነው፡፡ ይህንን ማሳካት የሚቻለው መንግሥትንና የግሉ ባለሀብት በማቀናጀት ሲሆን፤ የሁለቱ ዘርፎች ቅንጅት ግቡን ለማሳካት መንገድ ይጠርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከ80 ቢልዮን የአሜርካን ዶላር በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ በመንቀሳቀስ ላይ ነው ያለው፡፡ አገራት የግል እና የመንግሥት ዘርፍ ጥምረትን በስፋት ይጠቀሙበታል፡፡ በተለይም መካከለኛ ገቢ ውስጥ የገቡ አገራት ይህን ጥምረት ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ኮርያና የላቲን አሜርካ አገራት እንዲሁም አውሮፓ ውስጥም መካከለኛ ገቢ ውስጥ ያሉ አገራት ይህን ጥምረት ጥቅም ላይ ያውሉታል፡፡ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ጥምረት ተቋማዊ ማድረግንና የሕግ ማዕቀፍን ይፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ ቢሰራበት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ለልማት ትልቁ ፈተና ፋይናንስ ማድረግ አለመቻል ነው፡፡ ፋይናንስን ደግሞ ከሦስት ምንጮች ማግኘት ይቻላል ማለት ነው፡፡ መንግሥት በራሱ ለዜጋው ህይወት መሻሻል ሲል በጀት ይይዛል፤ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችንም ያደርጋል፡፡ መንግሥትና የግል ባለሀብት ጥምረት ማምጣት ከተቻለ ለልማት ፈንድ ለማግኘት ያግዛል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን መንግሥት የውጭ ባለሀብትንም መሳብ ይቻላል፡፡ ሦስቱ ኃይሎች መጣመር ከቻሉ ለልማት አስፈላጊውን ፈንድ ለማግኘት፤ በዚህም ሥራ አጥ የሆነውን ወጣት ወደ ሥራ ማስገባት ይቻላል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ይህ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡
ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ በፕራይ ቬታይዜሽን ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን የሚፈታ ነው፡፡ ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ በርካታ ሞዴሎች አሉት፡፡ የሰርቪስ ኮንትራት ሊሆን ይችላል፤ ማነጅመንት ኮንትራት ሊሆን ይችላል፡፡ ሰርቪስ ኮንትራትን ለአብነት ብናነሳ፤ መንግሥት የሆነ ሥራ ለመሥራት ከፈለገ ሰርቪስ ኮንትራት ይሰጣል፡፡ በዚህ መንገድ ከግሉ ባለሀብት ጋር በቴክኖሎጂ፣ በማኔጅመንት፣ በልምድ፣ በፈጠራ እንዲሁም ለገንዘብ ዋጋ ሰጥቶ ይሠራል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ መንግሥት ጋር ደግሞ በጀትና ስልጠናዎችን ማመቻቸት ይችላል፡፡ ሁለቱ ሲቀናጁ ቢሮክራሲውን የማቅለል አቅም አላቸው፤ ሁለቱ አቅሞች ሲቀናጅ ፍሬያማ የሆነ ሥራ መሥራት ይቻላል ነው፡፡ ለአብነት ያህል በሀገራችን ውስጥ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች በመንግሥትና በግሉ ቅንጅት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ኩባንያዎችን የመፈጠር ዕድል አለ፡፡ በተለይም ተቋማዊ የማድረግ እንቅስቃሴው ከተጠናከረ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡
በክልሉ መንግሥት በኩል የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ግን የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የመንግሥት እና የግሉ ቅንጅት ውጤታማ እንዲሆን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ የግዥ ሥርዓቱን ቀልጣፋ ማድረግ ነው፤ ለዚህ የሀገሪቱን የግዥ ሥርዓት ለማዘመን በትኩረት መሰራት አለበት፡፡ የሕግ ማዕቀፉን ማደራጀት እና ግልፅነት እየፈጠሩ መሄድ አስፈላጊ ይሆናል፡
የኤሌክትሪክና የስልክ አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ከተቻለ በተለይም ዓለም አቀፍ ፈንድ መሳብና ለሀገሪቷ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በኦሮሚያ ክልል አሁን የተቋቋሙት አምስት የሚሆኑት ኩባንያዎች በጆይንት ቬንቸር ነው እየተዳደሩ ያሉት፡፡ መንግሥት እና የግሉ ባለሀብት በጋራ ፈንድ እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ጥቅሙ ለሀገሪቷ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ነጋዴ አይሆንም፡፡ የመንግሥት ሥራው ኩባንያዎችን በማቋቋም ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ብሎም ዜጋን የዕድገቱ ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ እያሰፋን ስንመጣ ግን የተለያዩ የግሉና የመንግሥት ቅንጅት ሞዴሎችን ቀስ በቀስ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትም እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት እንዲጠናከር ይፈለጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው መሰረተ ልማት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ይህም የሚያሳየው ቅንጅቱ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ እንዲህ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ተሳትፏቸው እያደገ ነው ሲሆን፤ የሁለቱ ቅንጅት በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ትኩረት እንዳይደረግ ያግዛል፡፡ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፖሊሲም የግሉ ዘርፍ እና የመንግሥትን ቅንጅት አጣጥሞ የሚያስኬድ ሲሆን፤ ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ የሁለቱን ቅንጅት የሚደግፍ ነው፡፡
የወጣቱ ተጠቃሚነት ሁኔታ
የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ መልካም እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ በወላቡ ኮንስትራክሽን በርካታ ወጣቶች በቀጥታ እየተሳተፉና ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ በቀጥታ የጉልበት ሠራተኛን ከማሳተፉም ባሻገር ኮንትራት ወስደው የሚሰሩ በርካታ ወጣቶች አሉ፡፡ ኬኛ ቢቨሬጅ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ በጣም ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ በፋብሪካው ላይ ተቀጥሮ መሥራት ብቻም ሳይሆን ምርቶቹን በማከፋፈል፣ በመሸጥ እንዲሁም ባለሀብት ሆኖ በመሳተፍም በጣም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እየታየ ነው፡፡
ኬኛ አግሪካልቸራል ማሽነሪስ በርካታ ሰዎችን እያሳተፈ ከመሆኑም በላይ ፋብሪካው የሚያመርተው ምርት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በባሌ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በወረፋ የተመረተውን ትራክተር እየወሰዱ ነው፡፡ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ያሉትም በርካቶች ናቸው፡፡ ኦዳ ትራንስፖርትን በምናይበት ጊዜ በርካታ ሾፌሮች ተቀጥረው ስልጠና እየወሰዱ ናቸው፡፡ ማደያው እንደዚያው ነው፡፡ እስካሁን ዓላማውን አልሳተም፡፡ የመንግሥት ዋናው ዓላማው ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርና የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ነው፡፡ ይህንንም ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት መነሻ ኢኮኖሚያዊ ወይስ ፖለቲካዊ ?
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት ሲጀመር ሲሰነዘር ከነበሩ ትችቶች መካከል አብዮቱ ከኢኮኖሚያዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊ ነው የሚል ነበር፡፡ የተነሳውን የአመፅ ማዕበል ማርገቢያ ነው ብለው የተቹም ነበሩ፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲታይ የነበረው የወጣቱ መንገድ ላይ ወጥቶ መቃወም፤ መብቴ አልተከበረልኝም ሲል ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱ መነሻ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡
መንግሥት ይህን ተረድቶ ችግሩ እንዴት ነው መፍታት የምንችለው ብሎ የባለሙያዎችን ቡድን አዋቅሮ አጥንቶ ኩባንያዎችን ካቋቋመ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተቋቋሙት የቢዝነስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል የሚረዱ ከሆነ እና ሌላ ጉዳት የማያስከትል ከሆነ ፖለቲካም ቢሆን እንኳን ክፋት አይኖረውም፡፡ ሰው ፖለቲካ ነው ብሎ ለምን አሰበ ብሎ መኮነን ግን አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው የተለያዩ አመለካከት አለውና፡፡
ግን አንድ ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ መንግሥት ገብቶ እንደዚህ አይነት ትልቅ ካፒታል የሚፈልጉ ቢዝነስ ካላንቀሳቀሰ ቢዝነሱ እየተፈራ ነው የሚኖረው፡፡ ቢዝነሱ በጣም ብዙ ካፒታል እና እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ የግሉ ባለሀብት ያለ መንግሥት እገዛ እጁን አያስገባም፡፡ ያለ መንግሥት ድጋፍ የግል ባለህብቱ ግባ ቢባል አይገባበትም፡፡ የአቅምም ችግር አለ፤ ሥጋትም ይኖራል፡፡ የመንግሥት ጉልበት ሲቀላቀል ግን ለሌሎችም ማበረታቻ ይሆናል፡፡ የመንግሥት ሥራ ኩባንያዎቹ አቅም እስኪፈጥሩ እና በራሳቸው መንቀሳቀስ እስኪችሉ ድረስ ማገዝ ነው እንጂ ወደ ፖለቲካ የሚወሰድ አይደለም፡፡
መላ ኢትዮጵያዊያንን አሳታፊ የማድረግ ጥረት
በተቋቋሙት ኩባንያዎች ውስጥ ማንም የአክሲዮን ድርሻ መግዛት ይችላል፡፡ የሀገሪቱ ሕግም ይህንኑ ይፈቅዳል፡፡ ኩባንያዎቹ እንደ ክልሉ ላይ ትኩረት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ክልሉ ላይ መሥራት ያዋጣኛል የሚል ሰው ትርፋማነቱን አይቶ የአክሲዮን ድርሻ ሲሸጥ መግዛት ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ ቀን የአክሲዮን ሽያጮች የተገመተው ካፒታል በመሙላቱ ምክንያት አክሲዮን ቶሎ ማለቁ በችግርነት ይነሳል፡፡ ኩባንያዎቹ አክሲዮን ዝም ብለው መሸጥ ስለማይችሉ የተገመተው ካፒታል ሲያልቅ ለማቆም የሚገደዱበት ሁኔታ አለ፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ ምንድን ነው ?
የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባከሄደው ስብሰባ በኢኮኖሚ የተደገፈ ፖለቲካን ለመፍጠርና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ አብዮት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር የተቀዛቀዘ መስሏል፡፡ አዲሱ አቅጣጫ የተቀዛቀዘ የመሰለውን እንቅስቃሴ ተጨማሪ ኃይል በመጨመር ባለሀብቱን እና መንግሥትን አቀናጅቶ ሌላ ዙር እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል፡፡ ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ያልገቡ አንዳንድ ተግባራትን ወደ ሥራ ማስገባት ላይ መንግሥት ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ በእነዚህ ዙሪያ ከዚህ ቀደም የተጀመሩትን ተግባራት አጠናክሮ የመቀጠል ሥራ ይሠራል፡፡
ያጋጠሙ እክሎች
በሀገሪቷ ውስጥ የነበሩ ችግሮች ለኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮትም ችግር ነበሩ፡፡ ክልሉ በጣም ሰፊ እንደመሆኑ ከጫፍ እስከ ጫፍ የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖርም ሰዎችን አንቀሳቅሶ ስብሰባዎችን ለማከሄድ እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ በነበረው የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት የመንግሥት ባለሥልጣናት በሥራ እንዲጠመዱና ወደ ፖለቲካው እንዲያደሉ ማስገደዱም በችግርነት ይነሳል፡፡
አቶ ንዋይ መገርሳ
መላኩ ኤሮሴ