ወንጀል ፈፃሚዎቹ በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ አካላዊ ጥንካሬ እና ትኩስነት የሚታይባቸው ሲሆን፤ ወጣትነታቸውን በሥራ እና በትጋት ማሳለፍ የግድ መሆኑን ዘንግተዋል፡፡ ከእነርሱ አልፎ ወጣትነት የማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ጌጥ እና ውበት እንዲሁም የዕድገት ሚስጥር መሆኑን አልተረዱም፡፡
የወጣትነት አቅማቸውን በበጎ ሥራ ላይ አውለው መልካም መዓዛ እንዳለው ሽቶ ለሁሉም በአስደሳች መልኩ ከመድረስ ይልቅ፤ የሰው ጥሪት ነጣቂ፣ ማሕበረሰቡን አስለቃሽ እና በሁሉ የተጠሉ መሆኑን ምርጫቸው አድርገዋል። ፊሊሞንና ቸርነት በዚህ ምርጫቸው ደግሞ ምንም አይነት የፀፀት ስሜት ሲሰማቸው አይታዩም።
ጥምረት ለጥፋት
ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም በሀያዎቹ የዕድሜ ክልል የመጀመሪያ ዓመታት ገደማ ላይ ይገኛሉ። ተጣብቀው ሲያወሩ የተመለከታቸው እስከ ሞት የማይለያዩ ምርጥ ጎደኛሞች መሆናቸውን ለመገመት ይገደዳል። በእርግጥም እነርሱም በጭራሽ መለያየት አይፈልጉም፤ መኖሪያቸው የተለያየ ቤት ቢሆንም፤ ለአዳር ሲለያዩ በካባድ ቅሬታ ውስጥ ገብተው ነበር።
በጎደኛ የፍቅር መለኪያነት እስኪጠሩ ድረስ እነ እንቶኔን መሆን ነው አይለያዩም የማይላቸው አልነበረም። በትምህርታቸው ከአስረኛ ክፍል መዝለል ያልቻሉት እነዚህ ወጣቶች፤ የትምህርትን ነገር ተከድኖ ይብሰል በማለት ወደ ሱሱ ዓለም ከገቡ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ያገኙትን አብረው አጥፍተው መልሰው ሌላ ለሱሳቸው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ተፍ ተፍ ማለትን የእለት ከእለት ተግባራቸው ካደረጉ ሠነባብተዋል።
አሁን ግን ትንንሽ ብሮች እያገኙ ጫት ሲቅሙና ሲያጨሱ መዋል ብሎም ሲጠጡ ማምሸት ሰልችቷቸዋል። የተሻለ ብር የሚያገኙበትን እቅድ ማውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ለእቅዳቸውም መሳካት ምን ምን ያስፈልጋል? እነኚህ አስፈላጊ ነገሮችንስ ለማግኘት ምን መስራት አለብን? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን እያነሱ ምላሽ ለመስጠት ማጥናት እና ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
አሁን ግን እቅዱም መስመር እየያዘ ላሰቡት ስራ መሳካትም የሚያገለግሉ ቁሶችም እየተገኙ መምጣት ጀመሩ። ለማስፈራራት የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎች፤ የዘረፉትን የሚጭኑበት መኪና አግኝተው ተዘጋጁ። ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ለጥፋት የመሰረቱት ጥምረት ሰምሮ ወደ ተግባር የሚቀየርበት ቀን ደረሰ።
ተደጋጋሚው ጥፋት
ከዚህ ቀደም ለእቅዳቸው መሳካት ኢላማ ውስጥ በገባው አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ የዝርፊያ ተግባራቸውን የጀመሩት ወጣቶች ማንም ሳይደርስባቸው ሙሉ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ እቃ ዘርፈው ጭነው ሸጠዋል። በቀደመው የዘረፋው ተግባር የልብ ልብ የተሰማቸው ወጣቶች አንድ ሌላ የኤሌክትሪክ መሸጫ ሱቅ አይናቸው ገብቷል።
የኤሌክትሪክ እቃዎች እጃቸው ቢገባ የተሻለ ገንዘብ ሊያስገኝላቸው እንደሚችሉ አምነዋል። ለእዚህ ስራም ሁለቱ ብቻ በቂ አለመሆናቸውን ተገንዝበው ሌሎች ለዚህ ስራ ብቁ ናቸው የሚሏቸውን ሰዎች አዘጋጅተዋል። አይን የተጣለበትም ከአክሱም ሕንፃ ጎን የሚገኝ ኤቨር ግራንድ ሕንፃ ላይ ያለ ፌሰል ዲኖ የኤሌክትሪክ እቃዎች መሸጫ ሱቅ ነበር፡፡ በቅድሚያ ለመዝረፍ በቂ ጥናት አደረጉ።
ጥናቱም ዝግጀቱም ተጠናቆ በሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት አስር ሰዓት ሲሆን፤ ቂርቆስ ክፈለ ከተማ ወረዳ 01 በሚገኘው ፌሰል ዲኖ የኤሌክትሪክ እቃዎች መሸጫ ሱቅን በር ገንጥለው በመግባት በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችና የኤሌክትሪክ አቃዎች ዝርፊያ ፈፀሙ። ከዝርፊያው በተጨማሪ በጥበቃ ላይ የነበረ ሰራተኛ ላይ አደጋ አድርሰው ተሰወሩ።
ተጎጂው የጥበቃ ሰራተኛ
አቶ ያዕቆብ ጀልዱ ይባላሉ። የሁለት ልጆች አባት ለፍቶ አዳሪ ጎልማሳ ናቸው። ቀን ቀን ያገኙትን ሥራ እየሠሩ ምሽቱን በጥበቃ ሰራ ላይ ያሳልፋሉ። ልጆቻቸው ቢናፍቋቸው እንኳን ለእነሱ የተሻለ ሕይወት ለመስጠት ሲሉ፤ ሳያገኙዋቸው ባላቸው እውቀት እና አቅም ልክ ሌት ከቀን ይለፋ ነበር። ከልጆቻቸው ጋር የሚገናኙት በሳምንት አንድ ቀን እረፍት ሲሆን ብቻ ነበር። በዛ እለትም እንደተለመደው ከልጆቻቸው አጠገብ ሳይሆኑ እንደውም ሳይገናኙ ቀኑን አሳልፈው ማታ ወደ ጥበቃ ሥራቸው ገቡ።
አቶ ያዕቆብ በማግስቱ ግን የእረፍት ቀናቸው ስለነበር ከልጆቹ ጋር ውለው እንደሚያድሩ እያሰቡ ደስታ ተሰምቷቸው ነበር። በዚህ ስራቸውን በትጋት በሚያከናውኑበት ጊዜ፤ የደሞዝ ጭማሪ ማግኘታቸው ደግሞ ደስታቸውን አጥፍ ድርብ አድርጎላቸው ነበር። ምሽት ጥበቃ ላይ እያሉ አካባቢው ላይ በንቃት ያለውን አንቅስቃሴ ሲመለከቱ ቆይተው፤ ድካም ስለተሰማቸው ወደ ማረፊያ ገብተው አረፍ ብለው ነበር። ዘራፊዎቹ በክትትላቸው የጥበቃ ሰራተኛው በዛ ሰዓት ለማረፍ እንደሚገቡ ያውቁ ነበር። ጥበቃው ግን እንደተለመደው ገብተው ቢተኙም እንቅልፍ ቶሎ አልወሰዳቸውም ነበር፡፡
የሰው እግር ኮቴ ድምፅ ሲሰሙ ጆሯቸውን ቀስረው ማዳመጥ ጀመሩ፡፡ ከእግር ኮቴው ድምፅ በኋላ የበር መገንጠል ድምፅ ሲሰሙ ተነስተው በመሮጥ ድምፁን ወደሰሙበት አቅጣጫ አመሩ። ሆኖም ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ፊሊሞን የተሰኘው ዘራፊ ጥበቃው ሳይሰነዝሩ ቀድሞ በፌሮ ብረት ሁለት ጊዜ ጭንቀላታቸውን መታቸው፡፡
ደም ሲፈሳቸው ራሳቸውን ስተው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ ሁለተኛው ዘራፊ ቸርነት በበኩሉ አቶ ያዕቆብ ጀልዱ ሲነቁ፤ በወደቁበት እንዳይንቀሳቀሱ ያለበለዚያ በያዘው ትልቅ ሳንጃ የሞት አደጋ እንደሚያደርስባቸው እየዛተ ነገራቸው፡፡ ጩቤ በማውጣት ‹‹ እንዳትነቃነቅ ካለበለዛ እገድልሃለሁ፤›› በማለት አስፈራራቸው። በእርግጠኝነት የሞት አደጋ እንዳንዣበበባቸው የተረዱት ጥበቃ፤ ዘራፊዎቹ በመሳሪያ በማስፈራራት ሲያንገላቷቸው ምላሻቸው ዝምታ ሆነ፡፡
ዘራፊዎቹ የሰረቁትን ዕቃ በመኪና ጭነው ከአካባቢው ተሠወሩ፡፡ በእለቱ ጥበቃ ላይ የነበሩት፤ አቶ ያዕቆብ ጀልዱም ሲነጋ ሰዎች አግኝተዋቸው፤ በሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ ካዛንችስ ጤና ጣቢያ መወሰዳቸውን እና ሕክምና እግኝተው ከሞት መትረፉቸውን የወንጀል ምርመራው መዝገብ ያመለክታል፡፡
የፖሊስ ወንጀል ምርመራ
ቡድን አዋቅሮ ወንጀሉ የተፈፀመው እንዴት እና በማን እንደሆነ ሲያጣራ የነበረው የፖሊስ መርማሪ ቡድን፤ ድርጊቱን የፈፀመው አንደኛ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የቤት ቁጥር አዲስ በሆነ ቤት ውስጥ የሚኖረው ፊሊሞን የተሰኘ የ25 ዓመት ወጣት መሆኑን አረጋገጠ። ወጣት ፊሊሞን ትዳር እንዳልመሠረተ እና ቸርነት ከተሰኘ የ22 ዓመት ወጣት እንዲሁም ከሌሎች ጋር ተባብረው ድርጊቱን መፈፀማቸው የፖሊስ የምርመራ ቡድን አወቀ፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ የረር ጎሮ አካባቢ የሚኖረው እስከ 10ኛ ክፍል ተምሮ በኋላም ወደ ሥርቆት የገባው ቸርነትም አድራሻው በፖሊስ የምርመራ ቡድን ደንብ ታወቀ፡፡ ሁለቱ በዝርፊያው ላይ መሳተፋቸው የተደረሰባቸው ፊሊሞን እና ቸርነት ከሌሎቹ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለእራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ዘረፋ ማከናወናቸውን ፖሊስ መረጃውን አሰባሰበ።
በሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 10 ሰዓት ሲሆን፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው አክሱም ሕንፃ ጎን ኤቨር ግራንድ ሕንፃ ላይ የግል ተበዳይ ፌሰል ዲኖ የኤሌክትሪክ እቃዎች መሸጫ ሱቅ በሩን ገንጥለው ወደ ውስጥ በመግባት መስረቃቸው በማስረጃ ተረጋገጠ፡፡
በኤሌክትሪክ እቃ መሸጫ ቤት ውስጥ የነበረ ባለ 2 ነጥብ 5 የኤሌክትሪክ ገመድ ብዛቱ 48 ጥቅል የሆነ የአንዱ ጥቅል ወጋ ብር 4 ሺህ 200 ጠቅላላ ብር 201 ሺህ 600 ብር የሚያወጣ ንብረት መስረቃቸው ታወቀ፡፡ በተጨማሪ ውፍረቱ ባለ 1 ነጥብ 5 ብዛቱ 55 ጥቅል የሆነ የአንዱ ጥቅል ዋጋ 2 ሺህ 460 ብር የሚያወጣ በጠቅላላ ብር 132 ሺህ ብር የሚያወጣ የኤለክትሪክ ገመድ መዝረፋቸውን የምርመራ ቡድኑ አረጋገጠ፡፡ ባለ ስድስት የሚባል 12 ጥቅል የኤሌክትሪክ ገመድ እና ውፍረቱ ባለ 3 የሚባል እንዲሁም ባለ አራት የተሰኘ 3 ጥቅልና ሌሎችም የመሳሰሉትን መዝረፋቸውን ፖሊስ አረጋገጠ።
እነ ፊሊሞን በአጠቃላይ የዋጋ ግምቱ ብር 623 ሺህ 600 ብር የሚገመት ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቻቸው ወይም ንብረት በሚወስዱበት ጊዜም ሆነ በአወሳሰዱ ወቅት የገጠማቸውን ተቃውሞ ለማስቆም የጥበቃ ሰራተኛው ላይ ጉዳት ማድረሳቸው በማስረጃ ተደግፎ በምርመራ ቡድኑ ተረጋግጦ በዝርዝር ተቀመጠ።
አንደኛ ተከሳሽ ፊልሞን ጥበቃ ላይ የነበሩትን አቶ ያዕቆብን በፌሮ ብረት ሁለት ጊዜ ጭንቀላታቸውን በመምታት ደም እንዲፈሳቸውና ራሳቸውን ሰተው መሬት ላይ እንዲወድቁ ማድረጉ በዝርዝር በምርመራ መዝገቡ ተካተተ፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ ቸርነት ወንዶ ጥበቃው አቶ ያዕቆብ ጀልዱ በወደቁበት ትልቅ ሳንጃ ጩቤ በማውጣት ‹‹እንዳትነቃነቅ ካለበለዛ እገድልሃለሁ፡፡›› ብሎ በማስፈራራት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ንብረቶችን በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 – 42430 ኦሮ መኪና ጭነው በሁለተኛ ተከሳሽ በቸርነት አሽከርካሪነት የወሰዱ መሆኑን አረጋግጦ ለፌዴራል አቃቤ ሕግ መዝገቡን አስተላለፈ፡፡
የፌደራል አቃቤ ሕግ በበኩሉ ከፖሊስ የመጣለትን ማስረጃ አደራጅቶ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1) (ሀ) እና 671 (1) (ለ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ በፈፀሙት ከባድ የውንቡድና ወንጀል ክስ መሠረተባቸው፡፡
ውሳኔ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ግንቦት 18 ቀን 2015 በዋለው ችሎት ክሰና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ፊልሞን ባንቶ በተከሰሰበት ከባድ የውንብድና ወንጀል 14 ዓመት ፅኑ አስራት ይገባዋል ሲል ውሳኔውን አሳለፈ፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ቸርነት ወንዱም በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖ መዝገቡ ተዘጋ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016