ስኬቶች ወደታች ይውረዱ

ኢትዮጵያ በግጭቶች፣ መከራዎችና ረሃብ ስትፈተን የቆየች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ ግን ካለፈው ትምህርት ወስዳ ሁኔታዎቹን ወደ ዕድል እየቀየረች ያለች ሀገር ነች፡፡ ቀደም ሲል በጦርነት፤ በርሃብና ድርቅ የሚታወቀውን ስሟን የሚለውጡ ሥራዎችንም በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡

በተለይም ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በግብርና፤ በአረንጓዴ ዐሻራ፤ በኃይል አቅርቦት እና በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች በምግብ ሰብል እራሷን ከመቻል አልፎ ስንዴን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ትገኛለች፡፡

2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የለውጥ ወቅት ነው፡፡ ለውጡ ደግሞ ሁለንተናዊ ነው፡፡ ለውጡ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት አንስቶ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎችን ያጠቃለለ ነው፡፡ ላልቶ የነበረውን ማህበራዊ እሴት ከማጥበቅ ጎን ለጎን ለሙስናና ብልሹ አሠራሮች የተጋለጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም የማዳን ተግባር የተከናወነበት ነው፡፡

የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ ለዘመናት ሲጓተቱ የነበሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ከማብቃት ባሻገር የተጀመሩትን በፍጥነት የማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በሚገርም ፍጥነት ለውጤት ማብቃት ተችሏል። ከዓመታት በፊት ተጀምረው በመጓተት ብሎም በመክሰም ሂደት ውስጥ የነበሩትን የዓባይ እና የኮይሻ ግድቦችን ወደላቀ ደረጃ ማድረስ ተችሏል፡፡ የንግድ ባንክን ሕንፃ ከመቆም ታድጎ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የኢንሳ መሥሪያ ቤቶች አምረውና ደምቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡

አዲሱ አመራር ነባር ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ አልፎ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በመጨረሻ የብዙዎችን ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ገበታ ለሀገር ተብለው ከተጀመሩና ለመዲናዋ መስህብ ከሆኑት ፕሮጀክቶች ውስጥ የአንድነት፤ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ተጠናቀው የአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋል፡፡ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትም የከተማዋ አንዱ የስበት ማዕከል ለመሆን በቅቷል፡፡ በገበታ ለሀገር የተጀመሩ የኮይሻ እና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች በመገባደድ ላይ ናቸው፡፡ ወንጪ ተጠናቆ በርካታ ቱሪስቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና የአፍሪካ መዲናነቷንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በኢኮኖሚ ዘርፉም ቢሆን ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱን ከበርካታ ውጣ ውረዶች የታደጉና በጦርነትም ውስጥ ሆና የከፋ ችግር እንዳይከተል ያደረገ ነው፡፡

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ካየቻቸው አምርታዎች መካከል የወጪ ንግድ ያሳየው አምርታ ነው፡፡ ከ2010 ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ከወጪ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች። ከአገልግሎት ዘርፉና ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ የገቢ መጠን ቀደም ባሉት ጊዚያት ፈጽሞ የሚታሰብ አልነበረም፡፡

ሀገሪቱ ፍጹም ሰላም በነበረችባቸው ዓመታት እንኳን ከወጪ ንግድ ሲገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ ከ3ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ዘሎ አያውቅም፡፡ ከ2003 እስከ 2008 በነበሩት ዓመታትም የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ በየዓመቱ በ0ነጥብ 3 በመቶ እያሽቆለቆለ ሄዶ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ቆይታለች፡፡

ከ2010 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች እንድታጤንና ለውጭ ገበያም በስፋት እንድታቀርብ ዕድል በመክፈቱ የወጪ ንግድ ከገባበት ቅርቃር ተላቆ በየዓመቱ ከ7 በመቶ ዕድገት በላይ የሚያስመዘግብበት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ተገብቷል፡፡

የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን የሀገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን 84 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ 184 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ተችሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ የዕዳ ጫናም ከአጠቃላይ ምርቱ 59 በመቶ የነበረ ሲሆን ይህን በአሁኑ ወቅት ወደ 24 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡

ለዚህ የኢኮኖሚ መሳለጥ ዋነኛ ድርሻ የነበረው የግብርና ዘርፉና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ናቸው፡፡ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ነው፡፡

ከ2011 ጀምሮ በተከናወነ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በታሪክ መዝገብ ላይ ማስፈር ችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 569 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታትም ከ31 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከልም በበረሃማነትና በአየር ጸባይ ለምትሰቃየው ዓለማችን መድህን መሆን ችለዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት እምርታዊ ለውጥ ካመጡት ዘርፎች መካከል ግብርናን የሚስተካከለው የለውም፡፡ በግብርናው ዘርፍ ላይ በመጣው ለውጥ ስንዴ ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሩዝ ዘርፍም እየተከናወነ ያለው ተግባርም ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይነት ወደ አስመጪነት የሚያሸጋግራት ነው፡፡

ለ13 ዓመታት የቆየው የሕዳሴ ግድብ በርካታ ተግዳሮት ወደ ሞት አፋፍ ቢጠጋም መንግሥት ከሞት ታድጎ ብርሃን ለመስጠት አብቅቶታል፡፡ በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው በመገባደድ ላይ የደረሰው የዓባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜካላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆን ችሏል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት አንገትን ቀና የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም ለውጡን የተሟላ እንዳይሆን የሚያደርጉ የአፈጻጻም ጉድለቶች አሉ፡፡ የአንድ አንድ ሴክተሮች አፈጻጸም ጉድለትና እስከ እላይኛው እርከን ላይ በተገኘው ልክ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ በውጤታማነት አለመፈጸም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የተወሰኑ ሴክተሮችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የፍትህ ፍላጎት አለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛውን ጊዜ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በመሬት፣ በተለያዩ ወንጀሎች፣ ከጎረቤትጋር በሚኖሩ ያለመግባባቶች፣ ከቤተሰብ እና ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር በተያያዙ ችግሮች፣ ከገንዘብ ጋር በተያያዙ አለመግባባቶች እና ከሥራ ጋር በተያያዙ የሕግ ጉዳዮች ያጋጥሙታል። ሆኖም እነዚህን ቸግሮች በሕግ አግባብ ለመፍታት የሚሄድበት መንገድ አታካች ከመሆኑም በላይ በሕግ አግባብ እልባት የሚያገኙት ጥቂቱ ብቻ ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በየዓመቱ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የሕግ ጉዳይ አጋጥሟቸው ወደ ፍርድ ቤቶች ቢሄዱም ከእነዚህ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኙት ከ30 በመቶ በታች ናቸው፡፡ 70 በመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ሕጋዊ መፍትሔ ካለማግኘታቸውም በላይ በሚኖራቸው ምልልስ የጊዜና የኢኮኖሚ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል፡፡ በየዓመቱ የሚተላለፉ መዝገቦች መብዛት አንድን ጉዳይ እልባት ለመስጠት የሚወስደውን ጊዜ የተራዘመ በመሆኑ የዜጎችን ፍትህ በጊዜው የማግኘት መብትን የሚጥስ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል እንደሚባለው የሕግ ጉዳይ አጋጥሞት ወደ ፍርድ ቤቶች የሄደ ሰው ጉዳዩ እስኪፈጸምለት በርካታ ዓመታት ይቆጠራሉ፡፡ በዚህም ሕዝብ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጓል፡፡ እንደ አጠቃላይም ፍትህ ለዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለሰላም እና ለልማት ሊወጣ የሚገባውን ሚና እንዲቀጭጭ አድርጎታል፡፡

ሌላው የኑሮ ውድነት ጉዳይ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ አሁን አሁን መልክ እያየዘ የመጣ ቢሆንም አሁንም ግን ህብረተሰቡን አስተባብሮ ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ የሆኑ ነጋዴዎችን የማጋለጡ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ከተገቢው በላይ የሚያጦዙና ከህብረተሰቡ ችግር ማትረፍ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥና ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ የሚቻለው ሕዝብ ሲተባበር ብቻ ነው፡፡

በህብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙ ሕገወጥ ነጋዴዎች በሰዓታት ልዩነት የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ህብረተሰቡን ለምሬት መዳረጋቸው የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ቢሆንም ይህ ተግባራቸው ሊቀጥል የቻለው በምልጀሃና በጉቦ ጭምር ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ሕዝብን እናገለግላለን ብለው የተቀመጡ አካላት ከሕዝብ ጥቅም በተጻራሪ ከነጋዴ ጋር በመሞዳሞድ ሕዝቡን የስግብግብ ነጋዴዎች እራት ሲያደርጉት ማየት በጣም ያሳምማል፡፡

ስለሆነም ለእነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎችም ሆነ በምልጀሃ የሕዝብ አመኔታ የሚሸጡ አካላትን መታገስ የበለጠ ዋጋ ያስከፍላልና ሕዝቡ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡

ሕገወጥነት በተስፋፋበት ሁሉ ሰላም ይደፈርሳል፤ ሕግ ይዛባል፤ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ይስተጓጉላል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ሕገወጦችና ሙሰኞች ምቹ መደላደል ይፈጠርላቸዋል፡፡ እንደልባቸው ሕዝብን እያማረሩ ሀብት ያጋብሳሉ፤ መደላድላቸውን ያጠናክራሉ፤ የሴራ ገመዳቸውን ያጠብቃሉ፡፡

ስለዚህም እነዚህን ሕገወጦችንና ሕገወጥ ተግባራትን ሳይዘናጉ ማስተዋልና ችግሮች ተፈጥረው ሲገኙም አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ሕዝቡም ሲሆን ሕገወጦችን የሚታገስበት አንጀት ሊኖረው አይገባም፡፡ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሳወቅና አጥፊዎችም የእጃቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

ሕገወጦች ነፍስ የሚዘሩት ምንቸገረኝነት ሲሰፍን ነው፡፡ ሀገር የዜጎች ናትና ሕገወጥነትን አይቶ እንዳለየ ማለፍ ዜግነትን አሳልፎ መስጠትና ሕገወጥነት እንዲስፋፋ መፍቀድ መሆኑም መረዳት ይገባል። በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎችም ቢሆኑ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚመጡ ጥቆማዎችን ዋጋ በመስጠት አጥፊዎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በወረዳዎች እና ሌሎች የታችኛው መዋቅር ላይ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች በስፋት መታየቸው ጉዳዩን አሳቢ ያደርገዋል፡፡ ዛሬ መታወቂያ ለማውጣት ወደ ቀበሌና ወረዳ ጎራ ያለ ሰው እጁን በኪሱ ካልከተተ በስተቀር አገልግሎት የሚያገኝባቸው ዘርፎች እየጠበቡ ነው፡፡

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎቶቻቸው ሲስተጓጎሉ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብለው የሚቀመጡ፤ በማን አለብኝነትና በምንቸገረኝነት የተወጠሩና ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ተቆርቋሪነት የማይታይባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡን በማስተጓጎል ሌብነትና ብልሹ አሠራር እንዲሰፍን ታትረው የሚሰሩና አገልግሎትን በምልጃና በትውውቅ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የታችኛውን መዋቅር መፈተሻው ጊዜ አሁን ነው፡፡

መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች እንግልት ደረሰብን፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር ተሰቃየን፤ ውጣ ውረዱ አንገላታን የሚሉ አቤቱታዎችን ማዳመጥና ይህንኑ ተግባር የፈጸሙ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ርምጃ መወሰድ የሚጠበቅ ሲሆን ከዛ በመለስ ግን ቢያንስ ለተስተጓጎሉ አገልግሎቶች ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ግን ሊለመድ የሚገባው አሠራር መሆን አለበት፡፡

ይህ ሲሆን በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ይኖራል፡፡ የመንግሥት ዕቅዶች የመተግበር አቅማቸው ያድጋል፤ ልማት ይፋጠናል፤ ብልሹ አሠራር ይቀንሳል፤ ዕድገት ይፋጠናል፤ የዜጎችም ሕይወት ይለወጣል፡፡

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You