ተወልደው ያደጉት በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በቀድሞው አሩሲ ክፍለ ሀገር ከአሰላ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ዶሻ የገበሬ ማህበር ውስጥ ሲሆን በወቅቱም በነበረው የስውዲን ሚሲዮን ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ስለነበሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሶስት ዓመት ውስጥ አጠናቀው ነበር ወደቀጣዩ ደረጃ የተሸጋገሩት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቸውን ወደራስ ዳርጌ (አሰላ አጠቃላይ) ትምህርት ቤት በመግባት አጠናቀዋል።
ጌታቸው ድሪባ ዶ/ር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸው የጀመሩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩሊቲ ሲሆን ከዛም ምህንድስናን ለማጥናት ቢፈልጉም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ምርጫቸውን ወደ ህክምና አዞሩ፤ ሁለት ወር ያህል ከተማሩ በኋላም ስላላስደሰታቸው ፊታቸውን ሲሰሩ ወዳደጉት የግብርና ዘርፍ በማዞር ግብርናን መርጠው ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፤ በዛም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ጌታቸው ዶ/ር በመቀጠል የማስተርስ ዲግሪያቸውን በጀርመን ሀገር ዶርትሙንድ ዩኒቨርሲቲና በጋና ኩማሲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመግባት አጠናቀዋል። በመቀጠልም እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው የኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ የእድገትና ልማት ጥናት ትምህርት ቤት በግብርና ኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
ጌታቸው ዶ/ር መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በልዩልዩ ተቋማት በበርካታ ሀገሮች ተዘዋውረው ሠርተዋል፤ ከእነዚህም መካከል በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በኤሽያና መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ በመዘዋወር በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ውስጥም አገልግለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ግልጋሎትን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በግብርና ሚኒስቴር በብሔራዊ የግብርና አማካሪ በቡድን አባልነት፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር በዋና ሥራ አስፈጻሚነት፣ የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት የዘላቂ የልማት ግቦች ለማስፈጸም በተዋቀረው ቡድን ውስጥ ዋና አማካሪና የቴክኒካል ኮሜቴ አባል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ነው።
እኛም በዘመን እንግዳ አምዳችን ላይ በተለይም “ኢትዮጵያ ከግብርናና ከምግብ ቀውስ ነጻ ስለ መውጣት” በማለት በጻፉት መጽሃፍና የግብርናችን ሁኔታ በሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርገናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ በግብርናው ዘርፍ ተምረው ወደሀገርዎ ሲመጡ ምን ለውጥ ለማምጣት አቅደው ነው?
ጌታቸው ዶ/ር፦ በእኛ ጊዜ ውጪ ሀገር ሄደን ምንም ዓይነት ትምህርት ብንማር መጨረሻችን ሀገራችን ገብተን ማገልገል ነበር፤ እዛው ለመቅረት የሚያስብ ሰው አልነበረም። እኔም የውጭ ሀገር የትምህርትና የሥራ ሃላፊነቴን ጨርሼ ስመጣ ትልቅ ፍላጎት የነበረኝ የግብርና ሥራው ላይ የሆነ ነገር ማበርከት ነበር። ለምንድን ነው እኛ ዓለም ከደረሰችበት የግብርና ሥራ ዝመና መድረስ ያቃተን? የሚለው ሁልጊዜ በአእምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ የሚፈጠርብኝ ነገር ነበር።
ሌሎች ሀገሮችም ሲሄድ ምን ጊዜም የሚያስገርመኝና ለሀገሬ ቢሆን ብዬ የምመኘው የደረሱበትን የግብርና ዝመና ደረጃ ነበር። ከዚህ አንጻር እኤአ በ1995 የመጀመሪያውን “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመንትያ መንገድ “በማለት የቁጭት መጽሐፌን ጻፍኩ። መጽሐፉ ሲጻፍ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የምገብ ርዳታ ፈላጊው ቁጥር 8 ሚሊዮን ገደማ ነበር፤ አጋርና ለጋሽ አካላት በየቀኑ ዓመቱን ሙሉ እነዚህን ሰዎች የመቀለብም ሃላፊነት ነበረባቸው፤ ታዲያ እኔ በመጽሀፌ ይህ ለምን ሆነ ? መሬት አጥተን ነው? የሚሠራ ሰው ጠፍቶ ይሆን ወይ? በማለት ለመጠየቅ ሞክሬያለሁ። በወቅቱ የነበረው ረሃብና ችግር አላፊ ተደርጎ ነበር የተወሰደው ። ነገር ግን የንጉሡን ሥርዓት እስከመገርሰስ የደረሰ ሃይል ነበረው። ይህም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየተባባሰ የርዳታ ጠባቂው ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ሄደ እንጂ ሲቀንስ ደግሞ አላየነውም።
እኔ እንግዲህ ቁጭቴን መግለጽ የቻልኩት ምን ቢደረግ ይሻላል? ምን እየሆነ ነው ያለው? የሚለውን ለማስረዳት መጽሃፍ ጻፍኩ። እዚህ ላይ ሁላችንም መረዳት ያለብን ጉዳይ ግብርና ሩቅ ያለው ገበሬ አልያም ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የግብርና ሥራ ከሌለ ሁላችንም መኖር አንችልም። በመሆኑም ይህ ሥራ የሁላችንም ሃላፊነት በመሆኑ እከሌ አጠፋ እነከሌ አላለሙም ብለን ሃላፊነታችንን የምንሸሽበት ሊሆን አይገባም።
በሌላ በኩልም ምግብ ከሉዓላዊነት፤ ከነጻነት ጋር ሰፋ አድርገን ነው ማየት ያለብን። በአንድ ጥረትና ትንፋሽ መፍትሔ የሚያገኝ አይደለም። ከፍ ካለም ራሱ ሀገራዊ ምክክርን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል።
እንደ አንድ የገበሬ ልጅ እንዲሁም በሬ ጠምዶ አርሶ በማጭድ አጭዶ በአውድማ ወቅቶ ተሸክሞ በልቶ እንዳደገና ዛሬ ደግሞ ተምሮ የተሻለ እውቀትና የኑሮ ደረጃ ላይ እንዳለ ባለሙያ የአርሶ አደሩን ብሶት መናገር አችላለሁ የምል ሰው ነኝና በተቻለኝ መጠን ቁጭቴን በአገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ለማስተላለፍ እየሞከርኩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በግብርና ሥራችን ላይ መዘመን ያቃተን ወይንም ደግሞ በሚፈለገው ደረጃ ምርት አምርተን ዜጎቻችንን በአግባቡ መቀለብ ያልቻልነው ምን ሥላልተሠራ ነው?
ጌታቸው ዶ/ር፦ አንዱ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ እያቀበለ ነው የሚሄደው ፤ በትውልዱ መካከል ያለው ፍጥነት ነው ላለመለወጣችን ምክንያቱ፤ ይህንን ለማስተካከል ደግሞ አራት ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ ።
አንደኛው ጊዜ ነው፤ እኛ እንደ ሕዝብና ሀገር በጣም ሰፊ ነገር ያለንና የምናበላሸው የማንጠቀምበት ጊዜ ነው። ግብርና ደግሞ በጊዜ ይለካል። ወቅቶች ሲለዋወጡ እነሱን ተከትሎ መሥራት ለግብርና ሥራው ወሳኝ ነው። ነገር ግን ጊዜ ብለን ደግሞ የተፈጥሮ ኡደትን ብቻም መከተል ላይኖርብን ይችላል ፤ ነገር ግን ጊዜ ያመጣቸውን ነገሮች እየተጠቀሙ ዓመቱን ሙሉ ማልማት አንዱ የጊዜ ጥቅም ይሆናል።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ግብርናን ከፈጠሩ ሀገሮች አንዷ ነበረች፤ ይህ ብቻም አይደል በጊዜው ለግብርና ሥራ መዋል ይችላሉ የተባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንም ትጠቀም ነበር። በመሆኑም የኢትዮጵያ ግብርና ከጊዜ ከፈጠራ እድገትና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር መታየት ይፈልጋል።
ሁለተኛው ደግሞ መዋቅር ነው፤ ይህ ደግሞ የአንድ ዘመን የግብርና ሥርዓትን ቀይረን ወደአዲሱ ማምጣት ነው። ለምሳሌ የዶማ ፤ የበሬ ግብርና አለ፤ የአርብቶ አደር እርሻም ሌላው ነው፤ እነዚህ ሁሉ መዋቅር ከመሆናቸው አንጻር በአንድ ወቅት እጅግ የላቁ እንደውም ዘመናዊ የሚባሉ ነበሩ ። እኛ ግን እነሱን እያሳደግን እና እያዘመንን መምጣት አልቻልንም። ዓለም እየተወን እየሄደ ተደላድለን ቁጭ አልንባቸው። በመሆኑም ይህንን ለዘመናት የተደላደልንበትን መዋቅር መቀየር ያስፈልገናል።
ሶስተኛው ተቋም ነው፤ ይህም ሲባል እውቀትን፤ አስተውሎትን፤ ለውጥን መፈለግና አለመፈለግን ያካትታል። አራተኛው ውጤት ነው። ሁሉም አካል የሚለፋው የሚተጋው ገበሬው ቢዘራ ቢለፋ ነጋዴው ቢነግድ ዋናው ነገር ሕይወቱ መለወጡ እና ውጤት ማሳየቱ ነው።
ነገር ግን ዘንድሮ ብቻ በአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በርካታ ሰዎች አስቸኳይ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም በቋሚነት ብዙ ሕዝብ ችግር ውስጥ እንዳለ ይነገራል። በእውነት ይህ የሥራችን ውጤት ቢሆንም እንኳን በሌላ ጎኑ ደግሞ አሳዛኝም ነው። ይህ ሕዝብ በጣም ሠራተኛ ነው፤ ለምን እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ ልመና ባህላችን ሆነ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በመሆኑም ውጤት ላይ መሥራት የግድ ነው።
ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ለውጥ አሳይታለች፤ እኔ ገበሬ በነበርኩበት ወቅት ከአንድ ሄክታር የሚገኘው ምርትና ዛሬ ላይ እየተገኘ ያለው ምርት አይገናኝም። በጣም ጨምሯል፤ ግን ደግሞ ዛሬም ድረስ ከችግር አልተላቀቅንም፤ በመሆኑም ውጤት ያሳጣንን ነገር መመርመር ማወቅ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ረገድ እያመጣች ያለችውን ለውጥ እንዴት ያዩታል?
ጌታቸው ዶ/ር፦ ስንዴ ሰፋ ያለ ትንታኔን የሚጠይቅ ነገር ነው። አሁን እያየን ያለነው የስንዴ ምርታማነት እውነት ነው። እኔ በግሌ እንደውም ሀገራችን ስንዴን ማምረት አቅቷት ነወይ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር ለአውሮፓውያኑ ቀለብ የምንሰጠው የምል ነበርኩና አሁን ላይ በተሠራው ሥራ ስንዴን ከውጭ ማምጣት ትተን ምርታማ መሆናችንን ሳይ እንደ ባለሙያ ደስተኛ ነኝ። በሌላ በኩል ግን ይህ ውጤት ሕዝቡ ጋር ደርሷል ወይ? ወይስ ውጤታማነቱ ማን ጋር ነው ያለው? የሚለውን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል። እናም እንደ መንግሥት ልማቱ ጥሩ ነው። ምናልባትም በዚህ ሁኔታ ማምረት ባንችል ኖሮ የራሺያና ዩክሬን ጦርነት ብቻ ከፍ ያለ ችግር ውስጥ ይከተን ነበር። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ካልነበረን ተነስተን አሁን እዚህ መድረሳችን የሚበረታታ ነው።
አሁንም ግን እነማናቸው እያመረቱ ያሉት? የት ነው ሥራው በሰፊው የሚሠራው? ማነው ትራክተር አግኝቶ እያረሰ ያለው? የሚለው ሊታይ የሚገባው ከመሆኑም በላይ ምርቱ ሁላችንም ጋር ደርሶ ጠግበን የምናድርበት ሁኔታ ሊፈጠር የግድ ነው። ያን ጊዜ ስለምርቱም ሆነ አመራረቱ ሕዝቡ ሊረዳው ይችላል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ ነገሮች ግልጽ ባልሆኑበት እንደ ልቡ በቤቱ ዳቦ ባልበላበት ሁኔታ ስንዴ እየተመረተ ነው ከውጭ የምናስገባውንም አስቀርተናል ብንለው ብዙም ላይዋጥለት ይችላል።
በመሆኑም አሁን በሠራነው ሥራ ያገኘነውን ውጤት በማስፋት ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ ማድረግ፤ ምርቱም በብዛት እንዲመረት ያለመንግሥት ድጋፍ ገበሬው ራሱን ችሎ የሚሠራበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና የግብርና ኤከስቴንሽን ሥራ እንዲዳረስ ማድረግ ይገባል።
ለማንኛውም አንዳንድ ሰዎች ስንዴን ፖለቲካ አድርጎ ቢያዩትም ለእኔ ግን ፖለቲካ ሳይሆን ህልውና ነው። የሚታይ ውጤት ተገኝቷል። በተደረጉ ጥረቶች ስንዴን ከፖለቲካነት ወደ ዳቦነት መለወጥ ችለናል። ግን ደግሞ መላው ሕዝብ ጋር የደረሰ አይደለም። ያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያን ታድጓታል፤ ፈተናዋን ቀንሶላታል፤ ሉዓላዊነቷን ሙሉ በሙሉ አስረክባ እንዳትሰጥ አድርጓታል። በቀጣይ ግን ሥራው ሰፍቶ ሁሉም ዘንድ መድረስ አለበት። በዚህ ሁኔታም ቢታይ በጣም ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አርሶ አደሩ በአቅም ጎልብቶ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለሀገሩ እንዲተርፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ጌታቸው ዶ/ር፦ አዎ የአርሶ አደሩ አቅም እንዲያድግ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ አንዱ ብድር ሲሆን ሌላው ደግሞ የመድን ዋስትና ነው። ብድር ማለት ደግሞ ለቴክኖሎጂ ቅርበትን መፍጠር ይመስለኛል። ለምሳሌ ገበሬው ብድር ቢያገኝ ትራክተር ይከራያል፣ መሬት ይኮናተራል፣ ማዳበሪያ ይገዛል ነገር ግን ገንዘቡ ከሌለ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ማድረግ አይችልም። ስለዚህም አርሶ አደሩ መደገፍ አለበት። አርሶ አደሩ ሲደገፍ ፤ ሀገር ትደገፋለች።
በጣም የሚገርመው ነገር አዲስ አበባ ላይ ያሉት ባንኮች ለሪልስቴት ብቻ የሚያበድሩ ናቸው። ገንዘቡ ገጠር ገብቶ ግብርናውን ለሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች መዋል የማይችል ከሆነ በአንጻሩ ደግሞ እህል ተወደደ ብለው እሪ የሚሉ ከሆነ አንድ የተምታታ ነገር አለ ማለት ነውና ይህንን ማጥራት ያስፈልጋል።
በመሆኑም የሚያስፈልጉን ሩቅ አሳቢ መሪዎች ነው። አሁን ይህንን ዓይነት መሪ ያገኘን ይመስለኛልና ሥራውን እየሠራን ሁሉንም ኢትዮጵያ ማዳረስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ በርካታ ሀገራት ውስጥ እንደመስራትዎ ከሌሎች ሀገራት የምንወስዳቸው ልምዶች ይኖሩ ይሆን?
ጌታቸው ዶ/ር፦ እኔ በተዓምር አምኜ አላውቅም፤ ግን ደግሞ በዓለም ላይ አንድ ተዓምር አለ ብዬ ባምን የማምነው ቻይናዎች የሀገሬውን ሕዝብ ሕይወት የቀየሩበት መንገድን ነው። እንደ ሀገርም ራሳቸውን ቀና አድርገው በዓለም ላይ እኛ ነን ብለው መኖር የጀመሩትን ሁኔታ ሳይ ተዓምር ነው የሆነብኝ።
ቻይናውያን በረሃብ የተጎዱ ወገባቸው የጎበጠ ድሆች ነበሩ፤ ነገር ግን ቻይናውያን በ20 ዓመት ውስጥ በሠሩት ሥራ በተለይም ግብርናቸው ላይ ትኩረት አድርገው ባደረጉት ኢንቨስትመንት በአንድ ጊዜ ተቀይረው ሀብታም ከተባሉት ሀገራት ጎራ መሰለፍ ችለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ብራዚሎች በግብርናው ዘርፍ የደረሱበት ደረጃ የሚያስደንቅ ነው፤ ሌሎችም እንደዛው ናቸው። ስለዚህም ግብርና የእድገት መሠረት መሆኑንና መንግሥትም የጀመረውን ግብርናን ማዘመኑን ሥራ ሊቀጥልበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ሀገር የዛሬ መቶ ዓመት ቀዳሚ ሆነን በጀመርነው የግብርና ሥራና የአስተራረስ ዘዴ ላይ ቆመን የቀረን ነን፤ ነገር ግን እርስዎ አይተዋት እንዳጓጓቾት ቻይና በአንድ ትውልድ እድሜ ቀና ብለን ለመሄድ ምን ማድረግ አለብን ይላሉ ?
ጌታቸው ዶ/ር፦ እዚህ ላይ በንጽጽር ቻይና ከኢትዮጵያ ያነሰ ሀብት ያላት ሀገር ናት። በግብርና አትወዳደረንም፤ መጠቀም ባንችልም ፈጣሪ በጣም ጥሩ ሀገር ላይ አስቀምጦናል። ከሠራን በአጭር ጊዜ እንደ ቻይና ውጤት የማናሳይበት ምንም ምክንያት አይኖርም። በነገራችን ላይ የግብርና ሥራ የባከኑ ጊዜያትን ሁሉ የሚክስ ዘርፍ ነው፤ ትራክተሩን፣ ማጨጃውን ሌላውንም ሌላውንም ነገር ማቅረብና ማሰራጨት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት የምንቸገር አይደለንም።
በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችን ገበሬ በጣም የሚያኮራ፤ ባልተመቻቸ ሁኔታ ሠርቶ የሚያበላን፤ ሳይማር የተማረ፤ በጣም አዋቂ፤ ሥራ ወዳድ ከመሆኑ አንጻር ነገሮችን የማመቻቸት ሥራ ብንሠራ ቻይና የደረሰችበት ደረጃ ላይ በአጭር ዓመት ውስጥ የማንደርስበት ምክንያት የለም።
ለምሳሌ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስንዴ ልማቱ ላይ የወሰዱት ርምጃ ምን ያህል አመርቂ ውጤትን እንዳመጣ ስንመለከት ከሠራን ቻይና ላይ የማንደርስበት ምክንያት እንደሌለ አመላካች ነው።
እንግዲህ ምን እናድርግ ወይም ማን ምን ያድርግ ብለሽ ለጠየቅሽኝ ጥያቄ አጭር ምላሽ የለውም ፤ ነገር ግን የመለወጥ ፍላጎት ካለን መቶ ዓመት ወደኋላ ሄደን የቱ ጋር ነው የተሳሳትነው ? የቱጋርስ ነው ቆመን የቀረነው? የሚለውን ማየት፤ እኔም ለዚህ ምላሽ ይሆናል የምለው ደግሞ የጻፍኳቸውን ሁለት መጻህፍት መመልከት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሀገር ቁጭ ተብሎ የቱጋር ነው ምርታማነት ያለው? የቱስ ጋር ነው ክፍተቶች ያሉት ? ብሎ አንዱን ከአንዱ ማገናኘትም ሌላው ሥራ ሊሆን ይገባል። የግብርናን ጉዳይ ስናነሳ ወደሁላችንም ጭንቅላት የሚመጣው ያቺ ዘር የምታበቅለው ማሳ ናት፤ ግን እሷ በጣም ትንሿ ታሪክ ናት፤ እዛ ለመድረስ የሚያስፈልገን ቴክኖሊጂ ፈጠራ እውቀት አርሶ አደሩ ጋር እንዴት እናድርሰው የሚለው በሚገባ መታየት አለበት።
አዲስ ዘመን፦ በግብርና ሥራው ኋላ ቀር ለመሆናችን ይህ ነው ብለን ማስቀመጥ የምንችላቸው ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን?
ጌታቸው ዶ/ር፦ አዎ አንዱና ዋነኛው ምክንያት በየጊዜው በሚታዩ ትንንሽ ለውጦች መኩራራታችን ነው። ለምሳሌ አሁን ላይ በሄክታር 30 ኩንታል ማምረት ችለናል ግን ደግሞ ከበሮ የሚያስመታ አይደለም፤ ከዛ ይልቅ ብንሠራ፤ ብንተጋ የቱጋር መድረስ እንችላለን የሚለውን ራቅ አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል።
በተለይም ወጣቱ እስካሁን የመጣንባቸውን መንገዶች መቀየር መቻል አለበት ፤ ህልሙንና የማደግ ፍላጎቱን አቀናጅቶ ወደ ሥራ መግባት ይገባዋል። በማህበራዊ ሚዲያው ውስጥ ተዘፍቀው ሀገርን ከሀገር ሕዝብን ከሕዝብ በሚያባሉ አካላት ተጠልፎ መቅረትም አያስፈልግም። ይህ ከሆነ ግብርናውም አይዘምንም፤ ሀገርም አትለወጥም እኛም እንኳን ቻይና የደረሰችበት አሁን እንዳለው እንኳን መቀጠል ላንችል እንችላለን። ስለዚህ ሁሉም ሰው የግብርና ሥራ ይመለከተኛል በማለት አቅሙን ሀብቱን እውቀቱን አቀናጅቶ መሰማራት ይገባዋል።
ሌላው የግሉ ዘርፍ በብዛት በግብርናው ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ መንግሥት የጀመረውን ማበረታታት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ባለሀብቱም በተቻለ መጠን ወደዘርፉ መግባት ይኖርበታል፤ ይህ ሳይሆን ግን ከተሞች ቢያምሩ፤ ዘመናዊ ህንጻዎች ቢገነቡ፤ እህል መሆን አይችሉም፤ አንድ ዳቦም አይወጣቸውም። በመሆኑም ባለሀብቶች ወጣ እያሉ ገበሬውንና ግብርናውን ማገዝ በሥራውም ላይ መሠማራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ በመንግሥት የተጀመሩረው የሌማት ትሩፋት ያለውን ጠቀሜታ እንዴት ያዩታል ?
ጌታቸው ዶ/ር፦ ግብርና ማለት የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር የሉዓላዊነታችን ዋስትናን የምናረጋግጥበት ነው። እኛ ደግሞ እንደ ሌሎች ሀገሮች ነዳጅ አልያም ሌላ ነገር ሸጠን በዓለም ላይ ከምግብ ጀምሮ የፈለግነውን እናመጣለን የምንል ሕዝቦች አይደለንም። ህልውናችን የተመሰረተው በግብርና ላይ ብቻ ነው። በመሆኑም በዚህ መልኩ በቅረብም በሩቅም ግብርናው እንዲለመድ ሁሉም በየአቅራቢያውና በየጓሮው የሚችለውን ነገር እያለማ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲመግብ መስመር ማሳየት በእውነት የሚደነቅ ሥራም ነው። በተለይም ወጣቱ ሞራሉን አሰባስቦ በትንሽ ቦታ ላይ ወደሥራ የሚሠማራበት ነው። ከወዲሁም የሌማት ትሩፋት በርካታ ለውጦችን እያመጣ ነው። የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋትና በምግብ እራስን ከመቻል አንጻር ጅምሩ የሚበረታታ ነው።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ግብርና ሚኒስቴር ግብርናውን ለማዘመን ምን አቅዷል ? ሃላፊነቱስ እስከምን ድረስ ነው?
ጌታቸው ዶ/ር፦ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትልቁ ሃላፊነት ሥራዎችን መምራት ነው። ከዛ ውጪም በአዋጅ የተሰጡት በርካታ ሥራዎች አሉት። በሌላ በኩልም አዳዲስ ግኝቶችን እና ፈጠራዎችን ከእርሻ ምርምርና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ወደክልሎች ማድረስ ሥራው ነው።
ሌላው እንግዲህ መፍትሔው በቅንጅት መሥራት ነው። አሁን ላይ ሁሉም ‹‹እኔ እኔ ይላል›› ቅንጅታዊ አሠራሩ ብዙም አይታይም። ነገር ግን በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ሁላችንም ተደምረን ውጤት ለማምጣት መሥራት ይገባናል።
እንደ እኔ ግብርና ሚኒስቴር የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ አዳዲስ ግኝቶችን ማውጫ ማዕከል መሆን አለበት፤ በእርግጥ እነዚህንም ለይቶ እየሠራባቸው እንደሆነ አውቃለሁ። በሌላ በኩልም በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል። ይህ ፎረምም ሌላኛው የግብርና ህዳሴ ሊባል የሚችል ነው። በዚህም በግብርናው ዙሪያ ማነቆ የሆኑ ነገሮችን ለመለየት የሀገር ውስጡንም የውጭውንም ኢንቨስተር በማምጣት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የሚሆን መድረክም ይሆናል ተብሏል።
ለምሳሌ በሀገራችን ዶሮን ያስወደደው ምንድን ነው? ዋነኛው መኖ ነው። ይህ መኖ በሀገር ውስጥ የሚመረትበትን መንገድ እንቀይሳለን። የአንድ ቀን ጫጩቶች ከውጭ እናስመጣለን ዋናው ምክንያታችን ለእነሱ የሚሆን መኖ ማጣታችን ነው፤ ይህም ይቀረፋል። አሁን ባሉት ሚኒስትርም ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ ብዙ ባለሙያዎችም እየተረባረብን የልማት አጋሮቻችንም እያገዙን በመሆኑ ችግሩን አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንሰጠዋለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ ግብርናን ለማዘመን ከሚያግዙ ነገሮች መካከል አንዱ ትራክተር ነው፤ ለአርሶ አደሩ ትራክተር የማዳረሱን ጥረት እንዴት ያዩታል ?
ጌታቸው ዶ/ር፦ አዎ ትራክተር ዘመናዊ የግብርና መሣሪያ ነው። አሁንም በእሱ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች አሉን። ግን ማስተዋል ያለብን ነገር ትንንሽ መሬት ያላቸው ገበሬዎች ምን ዓይነት ትራክተር ነው የሚያስፈልጋቸው? ያልን እንደሆነ የእነሱን ጉልበት የሚቆጥብ አስተራረሱንም ዘመናዊ የሚያደርግ በእጅ የሚያዝ ትራክተር ነው፤ እሱን መከራየት የሚችሉበት አቅም ከመፍጠረም ባሻገር አቅርቦቱን ማሳደግና የመከራያ ቦታዎችን ማመቻቸት ይገባል። ይህም ይደረጋል።
በሌላ በኩል አርብቶ አደሩ ከብቶቹን በተሻለ ሁኔታ ለማርባትና በከብት ሀብታችንም የሚፈለገውን ጥቅም እንድናገኝ በዘመናዊ መንገድ የእርባታ ሥራው እንዲሠራ በርካታ ዝግጅቶች እንዳሉ አውቃለሁ። ከላይ የጠቀስኩት ፎረምም ይህንን ሁሉ የሚመልስ ነው የሚሆነው።
እኛ ከዚህ በኋላ ባለፈው መቆጨታችንን ትተን አሁን ከዜሮ እንደመነሳት ቆጥረን ቅድሚያ መስጠት ስላለብን ነገሮች ቅድሚያ ሰጥተን ተባብረን አሁን የደረሰብንን የምግብ ፈተና ታሪክ አድርገን ማለፍ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ እስከ አሁን ካነሳናቸው ሃሳቦች ተነስተን ሀገራችን በግብርናው ከየት ተነስታ የት ደረሰች? ወደፊትስ የት ትደርሳለች ብለን ማለት እንችላለን?
ጌታቸው ዶ/ር፦ ከአዳኝነት ወደግብርና ከተዞረበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ግብርና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ ነች። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ዓለም ጥሎን እንዲሄድ ሆኗል። ነገር ግን አሁንም እምቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን፤ ታሪካችንን፤ ሕዝባችንን ተጠቅመን ከሠራን እውነት ለመናገር ትልቅ ቦታ ላይ እንደርሳለን።
እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎችን ማስቀጠል፤ ግብዓቶችን በሀገራችን ለማምረት ጥረት ማድረግ ፤ከምንም በላይ ግን ፖለቲካዊ አመራሩ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ጌታቸው ዶ/ር ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም