«የፕሪቶሪያው ስምምነት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል» – አረጋዊ በርሄ ዶ/ር) የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር

ለሰው ልጆች አስፈላጊ ከሚባሉ መሠረታዊ ነገሮች መካከል የሰላም ድርሻው ከፍ ያለ ነው። ሰላም ካለ መማር ፣ማደግ ፣ሰርቶ መለወጥ፣ ወልዶ ማሳደግ ብቻ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ቀላል ነው። በአንጻሩ ግን የሰላም መደፍረስ ከተከሰተ ወጥቶ መግባት እንኳን ፈተና ነው የሚሆነው፡፡

እንደ ሀገር በርካታ የሰላም እጦቶችን አስተናግደናል በቅርቡም ለሁለት ዓመታት ያህል በሕወሓትና በመንግሥት መካከል የተካሄደው ጦርነት ተጠቃሽ ነው፡፡ይህ ጦርነት ደግሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃ ዘንድ ሁለቱም ኃይሎች በውጭ አሸማጋዮች አማካይነት ሰላም አውርደው የሰላም ስምምነት ተፈራርመው ጦርነቱ ከቆመ ከዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

በመንግሥትና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረገውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ በዘላቂነት ከተገታ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ሁለቱ ወገኖች ባለ 12 ነጥብ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል፤ ጦርነቱም ቆሟል። ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው ስምምነት በተለያዩ ሁኔታዎች ተፈጻሚ እየሆነም አንዳንድ ጉድለቶችንም እያስተናገደ እዚህ ደርሷል።

የሰላም ስምምነቱ በተለይ ለሁለት ዓመታት ያህል በከባድ ጦርነት ስር ሆኖ ለቆየው ለትግራይ ሕዝብ ታላቅ ተስፋን የፈጠረ ሲሆን ፤ ከዚያም በኋላ በክልሉ ጦርነት እና የጦርነትን ወሬ ሳይሰማ አንድ ዓመት ማስቆጠሩ ብዙዎችን አስደስቷል።

በክልሉ ለረጅም ጊዜ ተቋርጠው የነበሩት የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እንደ ስልክ፣ ባንክ እና መብራት ሥራቸውን ቀጥለዋል። የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ባሉት ዓመታትም በትግራይ ክልል መደበኛ ሕይወት እና እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረቶች እየተደረጉም ነው።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው የክልሉ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲ ሕወሓት ከሽብርተኛ መዝገብ ውስጥ ስሙ የተፋቀ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደበኛ የሥራ ግንኙነት ጀምሮ ጊዜያዊ አስተዳደርም አቋቁሟል።

በዚህም በአሜሪካ እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ እና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት የተለያየ መልክ እና የተደበላለቀ ስሜት ይዞ ለአንድ ዓመት ቆይቷል። ሆኖም ከትጥቅ አፈታት ፣ከታጣቂዎች ብተናና ሌሎች ታያያዥ ጉዳዮች አንጻር ሚነሱ ክፍተቶች ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል፡፡

እኛም ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር ምን መልክ አለው ክፍተቶቹ የቱ ጋ ናቸው ለተግባራዊነቱ ከማን ምን ይጠበቃል ስንል የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት ለዶክተር አረጋዊ በርሔ ጥያቄዎችን አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፦ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዴት ያዩታል?

ዶክተር አረጋዊ፦ የፕሪቶሪያው ስምምነት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለሰላም ተብሎ የተከፈለ ዋጋ ወይም ጥረት ብለን መውሰድ የምንችለው ስምምነት ነው። እነዚያ ሁሉ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ተሰብስበው የችግሩ ግንባር ቀደም ተዋናያን ተገኝተው የሕዝቡን ሰቆቃ ስቃይ መከራ የሰላም እጦት ተገንዝበው ችግሩን ባለበት አቁሞ መፍትሔ ለማምጣት የተደረገው ጥረት የሚጨበጥ የነበረ፤ ሕዝቡም በጣም የሚፈልገው እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ስንጠብቀው የነበረ ነገር በመሆኑ ስምምነቱን በደስታ ነበር የተቀበልነው።

በነገራችን ላይ በዓለም ላይ ከጥቂቶች በቀር ሰላምን የሚጠላ ስለሌለ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ስምምነቱን በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበለው።

መንግሥትም ቀድሞ የስምምነቱ ፈራሚ በመሆኑ ምስጋናም ይገባዋል። ባለ 12 አንቀጹ የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ከማስቆም ባለፈ የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ መልሶ ግንባታ እንዲካሄድ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና በጦርነት እና በረሃብ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ያለመ ነው።

በጦርነቱ ወቅት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቤት ንብረታቸውም ተፈናቅለው ለችግር ተጋልጠዋል። አሁን ላይ ጦርነቱ ቆሟል፤ ግን ሰላም ምንድን ነው? ጦርነትስ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው። “ጦርነት በድሮን እና በሚሳይል ብቻ አይደለም፤ ሰላም ማለት የሰው ልጅ አእምሮ ነፃ ሆኖ ብዙ ሰዎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሲገቡ እና ወደ ተለመደው ኑሯቸው ሲመለሱ ነው። በተግባር ግን የትግራይ ሕዝብ የቀጥታ ጦርነት ቀረለት እንጂ አሁንም መከራ ውስጥ ነው ያለው። ምክንያቱም  የፕሪቶሪያ ስምምነት እስከ አሁን ድረስ መሬት ነክቶ ውጤቱ እየታየ ስላልሆነ።

ስምምነቱ የሰላም ተስፋ ነው። ይህም ቢሆን ግን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ አሁንም የተኩስ ድምጽ ቀርቶ ጦርነት አብቅቶ ይሆናል እንጂ በስምምነቱ የተፈረሙና ሕዝቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮች አልተከናወኑም።

አዲስ ዘመን ፦ ትጥቅ ማስፈታት እና ዳግም ማቋቋም የስምምነቱ አንድ አካል ይመስሉኛል ይህ ግን ተግባራዊ ሆኗል ማለት ይቻላል?

ዶክተር አረጋዊ፦ከፕሪቶሪያው ስምምነት ዋነኛው ሃሳብ የተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎችን መልሶ ማቋቋም የስምምነቱ አንድ አካል ነው። የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች፣ የማዕከላዊው መንግሥት እና የትግራይ መሪዎች እንዳረጋገጡት፤ የትግራይ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት የከባድ መሳሪያ ትጥቆቻቸውን ፈትተው ለፌዴራል መንግሥት አስረክበዋል። ነገር ግን የትግራይ ኃይል አባላትን በተሀድሶ ወደ ኅብረተሰቡ የመቀላቀል ሂደት አለመፈጸሙ አነጋጋሪ ሆኖ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅሬታዎችን እያስነሳ ነው።

ይህንን ሥራ ለማቋቋም የፌዴራል መንግሥቱ ያዋቀረው ኮሚሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 400 ሺ የሚጠጉ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም አላማ እንዳለው ቢገልጽም እስካሁን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ አላገኘም።

አዲስ ዘመን፦ የፕሪቶሪያ ስምምነት የአተገባበረ ጉድለቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?

ዶክተር አረጋዊ ፦ አዎ ከላይ እንዳልኩት ስምምነቱ መላው ኢትዮጵያውያን ብሎም የዓለም ሕዝብ የሚፈልገውና የሚጠብቀው ከተፈረመ በኋላም ከፍ ያለ ደስታን የፈጠረ ነው። ነገር ግን አተገባበሩ ላይ ብዙ ክፍተቶች አሉበት።

አንደኛው በተደራዳሪ ወገኖች መካከል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት እና ፈቃደኝነት አለመኖሩ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ሰላም ሰፍኗል፤ ሁሉም ነገር አብቅቷል ብሎ ትኩረቱን በመቀየሩ አተገባበሩ ላይ ችግር ሊከሰት ችሏል። ሌላው ደግሞ በሀገሪቱ እዚህም እዚያም ብቅ ጥልቅ የሚሉ የሰላም መደፍረሶች ተጽዕኖ አሳድረዋል ማለት ይቻላል።

ዋናውና ሁሉንም ነገር የሚጠቀልለው ግን አካታች የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሰረታል የሚለው አንቀጽ 10 ተግባራዊ አለመሆኑ ነው። ይህ አንቀጽ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ ምንም ውጤት የሚያመጣ ሥራ ሊሠራ አይችልም።

በተለይም እንደ አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረው የትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም ሠራዊቱን የተሃድሶ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት አሁን ችግሮች ያሉበት ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት የሰላም ተስፋ ቢፈጥርም በወረቀት ላይ ተንሳፎ የቀረ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። አሁንም ቢሆን ሁለቱ ወገኖች ቆም ብለው በማሰብና ስምምነቱን መሬት አስይዘው ተግባራዊ ቢያደርጉት ሕዝቡ ይጠቀማል ሀገርም ከቀውስ አረፍ ትላለች።

በመሆኑም ከላይ ያነሳኋቸውና በአንቀጽ 10 ላይ የሚገኙ ነገሮች በሙሉ ትክክለኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አድሏዊነት በሌለው ሁኔታ የሚፈጸሙ ከሆነና ዘላቂ ሰላም እንዲያገኝ ከሆነ የሚፈለገው ሌላ ምንም ማድረግ ሳያስፈልግ አካታች የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት አለበት የሚለው ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።

ይህም ሲባል ሁሉም የሚመለከተው አካላት በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የበኩሉን እየተወጣ በትክክለኛው መስመር ቢጓዝ አለመጓዙን በአግባቡ እየተከታተለ እርስ በእርሱ እየተናበበና ከስር ከስር የስራዎችን አካሄድ እየተከታተለ እያረመና እያስተካከለ እንዲሄድ አንቀጽ 10 ከፍ ያለ ሚና ያለው በመሆኑ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።

አሁን ላይ ይመሰረታል የተባለው አካታች የጊዜያዊ አስተዳደር ቀርቶ መንግሥት ሁሉንም ሚና ለሕወሓት ሰጥቶ ነው ያለው። የሕወሓት አመራሮች በሀገርና በሕዝብ ላይ ያንን ሁሉ ችግር ፈጥረው አሁንም አስተዳደራዊ ሁኔታውን መስጠት ከባድ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ አንቀጽ 10 ተደጋግሞ የተነሳ ነገር ነውና እንደው በዚህ ልክ አስፈላጊ ከሆነ ተግባራዊ እንዳይሆን ማነው እንቅፋት እየፈጠረ ያለው?

ዶክተር አረጋዊ፦ እውነት ለመናገር መንግሥትም ከመፈረም ባሻገር ስምምነቱ ገቢራዊ እንዲሆን የሚገባውን ያህል ርቀት ተጉዟል ብዬ አላምንም። በሚፈለገው ልክ ተጉዞ ቢሆን ኖሮ ይህ ስምምነት በተለይም አንቀጽ 10 ተግባራዊ ለመሆን ይህንን ያህል ጊዜ አይወስድበትም ነበር።

መንግሥት የሚገባውን ያህል ርቀት ተጉዞ አንቀጽ 10ን ተግባራዊ ቢያደርግ ኖሮ ችግሮች በአጭሩ መቋጫን ያገኙ ነበር። የሚገርመው ነገር እኮ መንግሥት ራሱንም ነው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ መመስረትና አባልነት ያገለለው። ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ በሙሉ እንደመሆኑ መጠን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥም አባል መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን ራሱን አግሎ የሕወሓትን አመራሮች ብቻ አምኖ ነው የሰጣቸው።

ይህ ደግሞ ትልቅ ጥፋት ከመሆኑም በላይ ለችግሩ እልባት አለማግኘት ከፍ ያለ ሚናን እየተወጣ ነው። ሕዝቡም የሰላም ስምምነት ተፈረመ ተባለ እንጂ የሚጠብቀውን አይነት እፎይታና ለውጥ እያገኘ አይደለም። በመሆኑም መንግሥት ራሱን ከማግለል ተቆጥቦ አንቀጽ 10ን ተግባራዊ አድርጎ ከሕወሓት መሪዎች ጋር ተባብሮና ትግራይም አንዷ የኢትዮጵያ ክልል መሆኗን አውቆ መሥራትና ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ የሚፈለገውን ሰላም ማምጣት ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ የፕሪቶሪያው ስምምነት በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ተግባራዊ ቢሆን እንደ ሀገርና ሕዝብ ልናተርፍ የምንችለው ነገር እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር አረጋዊ ፦ ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። በመጀመሪያም ያ ሁሉ የዓለም ማህበረሰብ አደራዳሪ ሆኖ ብዙ ውጣ ውረዶች ታይተው እዚህ መሰሉ የሰላም ስምምነት ላይ እንድንደርስ የሆነው እኮ አስፈላጊነቱ በእጅጉ ወሳኝ በመሆኑ ነው። አስፈላጊነቱ ደግሞ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ከፍ ያለ ሚና ያለው፤ ሰላሙን የሚያስጠብቅለት ፤የተቋረጠ ህይወቱን ዳግም እንዲቀጥልና ተረጋግቶ ወደ ሥራው ተመልሶ እየሠራ የሚኖርበት እና ክልሉን ብሎም ሀገሩን ለማሳደግ የሚተጋበት ይሆን ነበር።

በሌላ በኩልም ይህ ስምምነት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር ሕዝቡ እንዲሁም ሀገር በጦርነቱ ወቅት የተጎዱትን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ኪሳራዎች በማከም ሕዝቡ ወደነበረበት አቋሙ እንዲመለስም የማድረግ ኃይሉ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

እንደ ሀገር እያሰብን ላለነው የሽግግር ፍትህ ሥርዓትም የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ንግግር የሚፈልገው እርስ በእርስ መታረቅ የሚፈልገው በጠቅላላው ሰላምን የሚፈልግ ሁሉ የሚስተናገድበት በመሆኑና ሁሉንም የማቀራረብ ኃይሉም ቀላል ባለመሆኑ ለሽግግር ፍትሁም ገቢራዊነት ሚናው ላቅ ያለ ይሆን ነበር።

በጠቅላላው ሰዎች ከነበራቸው የዓመታት ጭንቀት ውጥረት የቤተሰብና የንብረት ውድመት ከሥራ መፈናቀልና ችግርን ማስተናገድ በሙሉ ይፈቱ ነበር። የሰላምና የእድገት ሂደትም ይጀመር ነበር። ነገር ግን ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ ባለመተግበሩ አሁንም ተንጠልጥለው የቀሩ ነገሮች በርካታ ናቸው። ይህ ደግሞ ሕዝቡን አሁንም ላልተፈለገ ችግርና ዋጋ መክፈል እያስገደደው ነው።

አዲስ ዘመን፦ እርስዎ በፖለቲካው መድረክ ብዙ ዓመታትን ያሳለፉ እንደ መሆንዎ አሁን በሁለቱ አካላት መካከል የተፈረመውን ስምምነት መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሆኖ ሕዝብና ሀገርን ከችግር ያላቅቅ ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ዶክተር አረጋዊ፦ ዞሮ ዞሮ ወደ አንቀጽ 10 መመለሳችን አይቀርም፤ በመሆኑም ብዙ ጥፋትና ውድመት ሳይከሰት በፍጥነት አካታች ወደሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር ምስረታ መግባት ያስፈልጋል። ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሕወሓት መወጣት ያለባቸው የየራሳቸው ሚና እንዳለ ሆኖ በተለይም በአካባቢው ላይ ያሉ ሁሉ በይመለከተኛል መንፈስ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል።

በመሆኑም የፖለቲካ ድርጅቶች ሲቪክ ማህበረሰቡ የሃይማኖት መሪዎች ሽማግሌዎች ብቻ በጠቅላላው የሰላም ጉዳይ የማይመለከተው ስለሌለ በተቻለ መጠን እነሱን ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈጥሮ ወደ ቋሚ መንግሥትነት የሚሸጋገርበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል።

ይህ ካልሆነ ግን አሁንም የተሟላ ሰላም የለም፤ ዝርፊያው ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ነገር ደግሞ አድጎ መቀጠሉ የማይቀር ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ከችግር እንዲወጣ ከገባበትና ወደፊትም ከሚገባበት ችግር እንዲላቀቅ ከታሰበ አንቀጽ 10ን ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን ፦ እንግዲህ እንደ ችግር ያልተሻገርናቸው ብዙ ችግሮች ያሉብን ሕዝቦች ነንና አሁንም እዚህም እዚያም የተለያዩ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በማንገብ ወደ ግጭት የሚገቡ፤ ሕዝብንም ችግር ውስጥ የሚጥሉ ወገኖች መፈጠራቸው አልቀረምና እንደው ካለፈው ምን ሊማሩ ይገባል ይላሉ?

ዶክተር አገራዊ፦ በጣም ጥሩና በጣም መሠረታዊ ጥያቄ ነው፤ እስከ ዛሬም እንደምናውቀው ወደፊትም እንደሚሆነው በግጭት የሚመጣ ለውጥ ወይም እድገት ፍጹም የማይታሰብ ነው። እንደ ሀገር ከዚህ ቀደም ብዙ ዓይነት ግጭቶችን አሳልፈናል፤ ነገር ግን ምንም የፈየደልን ነገር የለም። በግጭት፤ በጦርነት የሚመጣ ሰላምም ሆነ ፍትህ የለም፤ ከዛ ይልቅ ወገንን ማጣት ፣ሀገርን ባዶ ማድረግ ፣ኢኮኖሚን ማድቀቅ፣ ሀብትን ማባከን ለዓመታት የተደከመባቸውን መሠረተ ልማቶች አውድሞ በብዙ ዓመታት ወደኋላ መመለስ ነው። ይህ ደግሞ የመጣንበት ሂደት ራሱ የሚያሳየን በመሆኑ ምንም ምስከር የሚያስፈልገው ነገር አይደለም።

እስከ አሁን የነበሩን ጦርነቶች በሙሉ ያሳዩን ነገር ቢኖር ጥፋትን፣ ውድመትን ፣ ውድቀትን ፣ኋላ ቀርነትን ነው። ልዩነት መሠረታዊና የሚጠበቅ ነገር ነው። እንኳን የእኛን ያህል ሰፊ ሀገር ይቅርና በጣም ትንሽ ሕዝብ የያዙ ሀገሮችም በውስጣቸው ሰፋፊ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ እሱን ትተሽው በአንድ ቤተሰብ በአንድ እናትና አባት ልጆች መካከል እንኳን ልዩነቶች ይኖራሉ፤ ነገር ግን ልዩነቶችን ሁሉ በጦርነት እንፈታለን፤ በግጭት መልስ እንሰጣለን ማለት አግባብነት የሌለው ተግባር ነው።

ዋናው ሊሰመርበት የሚገባው ነገር በጦርነት የሚፈታ ችግር ሳይሆን የሚባባስ ችግር ነው ያለው፤ ስለዚህ እኛ የአንድ እናት ልጆች አንድ የሆንን ሕዝቦች ነን ያሉብንን ችግሮችና ልዩነቶች በሰከነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ለመፍታት መሞከር ይገባናል፡፡ ስለሀገራችንና ስለሰላማችን ማሰብ፣መነጋገር በመነጋገር ውስጥ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል።

አሁን በዚህ ዘመን ጦርነት ያዘው ቁረጠው ፍለጠው ሳይሆን የሚያስፈልገን የሃሳብ ልዕልና ሲባል ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም የበሰለ ሃሳብ ማምጣት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በተለይም ምሁራን ልሂቃን ዳር ቆመው እኛን እስካልነካን ድረስ ማለታቸውን ትተው ቆም ብለው በማሰብና የአንበሳውን ድርሻ ይዘው ሕዝቡን በማሳመን የውይይት መንፈስን በማስረጽ በኩል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ዶክተር አረጋዊ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You