ፎቢያ መጠነኛ ወይም ምንም ጉዳት ለማያመጡ ነገሮች/ዕቃዎችና ከፍታ ቦታ ከመጠን ያለፈና ምክንያት የለሽ ፍራቻ ሲኖር የሚመጣ ሲሆን በዚህ የተነሳ ጭንቀትና ያንን ነገር የመሸሽ ነገር ይታያል። ፎቢያ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣አካላዊና ስነልቦናዊ ምላሽ ያለውና በሥራ ቦታ እንዲሁም በማህበራዊ መስተጋብርዎ ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል ነው።
ብዙ የፎቢያ ዓይነቶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች ሰፊና ትልቅ ክፍል ይፈራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ በጣም ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ እባብ፣ ሊፍት፣ ከፍታ ቦታንና ከፍታ ቦታ ላይ መብረርን (በአዉሮፕላን) ከመጠን በላይ ይፈራሉ።
ምልክቶች
ፎቢያ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል።
• የተወሰነ/የተለየ/ ፎቢያ (Specific phobias):- ይህ ከተለምዶ ወጣ ያለና ከልክ ያለፈ፣ ምክንያት የሌለውና ዘላቂነት ያለውፍራቻ ለዕቃዎች ወይም ለነገሮች/ሁነቶች ሲኖረን ነው። ይህም በአውሮፕላን መጓዝ ወይም በተወሰነ ቦታ መወሰንን፣ ተፈጥሯዊ የሆኑ እንደ ከፍታ ቦታ ወይም ነጎድጓድ፣ እንስሳትንና ነፍሳትን(ዉሻ፣ሸረሪት)፣ ደም፣ መርፌ መወጋትን ወይም አደጋዎች( ቢላዋ ወይም የህክምና ዘዴ) የመሳሰሉትን መፍራት ያጠቃልላል።
• ሶሻል ፎቢያ (Social phobia)፡- ይህ ከማፈር በላይ የሆነ በተለምዶ ሰው ሊኖርባቸው/ ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ ቦታዎችን ከመጠን በላይ መፍራት ሲሆን ግለሰቡ ሰዎች አይቀበሉኝም/በጥሩ ሁኔታ ሰዎች አያዩኝም ወይም በመጥፎ ጎን ይመዝኑኛል ብሎ ከመጠን በላይ ከመጨነቅ/ከመፍራት የሚመጣ ነው።
• የክፍት/ገላጣ ቦታዎች ፎቢያ ( Fear of open spaces (agoraphobia)፡ ይህ አግራፎቢያ ይባላል። ይህ በእውን ያለ ወይም ይኖራሉ ብለን በምንገምተው ሁኔታዎች ለምሳሌ ገላጣ በሆኑ ወይም ዝግ በሆኑ ቦታዎች፣ በረድፍ አሊያም ጥቅጥቅ ያለ ቦታ መቆም ወይም ከቤት ውጪ ለብቻ ሲሆኑ ከመጠን ያለፈ ፍራቻ ያላቸውን ያጠቃልላል።
የህክምና ባለሙያ ማማከር የሚገባው መቼ ነው?
ምክንያት የሌለው ከመጠን ያለፈ ፍራቻ ካለዎ፤ ከፍራቻ/ጭንቀት የተነሳ በሥራዎና ማህበራዊ መስተጋብርዎ ላይ ጫና ከተፈጠረ የህክምና ወይም የስነልቦና አገልግሎት ማግኘት ይመከራል።
ለፎቢያ የሚያጋልጡ ነገሮች፡- ለፎቢያ ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
• ዕድሜ፡- ሶሻል ፎቢያ በዋናነት የሚከሰተው በልጅነት ዕድሜዎ ሲሆን በብዛት 13 ዓመት ላይ ይታያል።
• ቤተዘመድዎ/ ጓደኛዎ፡- በቤተሰብዎ ውስጥ አንድ ሰው የተወሰነ የፎቢያ ዓይነት ካለ እርስዎም ያን ነገር የመፍራት እድልዎ ይጨምራል። ይህ ከቤተሰብ ሊወረስ ይችላል አሊያም ልጆች ቤተሰቦቻቸው ለተወሰነ ነገር ፎቢያ ካላቸው ልጆቻቸውም ያንን ነገር ይዘው ሊያድጉ ይችላሉ።
• ተፈጥሮዎ/ባህሪዎ፡- ባህሪዎ ስስ ወይም ለነገሮች ያለዎ ከተለመደው በተቃራኒው ከሆነ ለፎቢያ ተጋላጭነትዎ ይጨምራል።
• ከዚህ በፊት የደረሰብዎ ጉዳት ከነበረ፡- ከዚህ ቀደም ከሚፈሩት ነገር ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳት ደርሶቦት ከነበረ(በሊፍት መያዝ አሊያም በእንስሳት ተባረው ከነበረ) በፎቢያ የመያዝዎ ዕድል ይጨምራል።
ፎቢያን ለመቋቋም የሚረዱ
በፍራቻዎ ምክንያት እራስዎን እንዳያስሩ ባለሙያዎች የሚያደርጉሎት ምክርና ህክምና ከችግሩ እንዲወጡ ያግዙዎታል። እርስዎም በራስዎ የሚወስዱት ዕርምጃ ችግሩን ለመልመድና ለመቋቋም ይረዳዎታል። ሁሉም ፎቢያዎች ህክምና ላያስፈልጋቸው ይችላል።
• የሚፈሩትን ቦታዎች/ነገሮች መሸሽ አይገባም፡ – ለዚህም ቤተሰብዎ፣ ጓደኞችዎና የህክምና ባለሙያዎችዎ ሊያግዙዎት ይችላሉ።
• መድሃኒትዎን በታዘዘልዎ መሰረት መውሰድ፡- የህክምና መድሃኒትዎን የህክምና ባለሙያዎን ሳያማክሩ ያለማቋረጥ
• ለራስዎ እንክብካቤ ማድረግ፡- በቂ ዕረፍት ማግኘት፣ጤናማ አመጋገብ መከተልና የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ
መከላከያ
ምክንያት የለሽ ፍራቻ ካለዎ የስነልቦና ምክር ማግኘት(በተለይ ልጆች ካለዎ)። ምንም እንኳ ፎቢያ በዘር የመተላለፍ ዕድል ቢኖረውም በተደጋጋሚ የእርስዎን ፍራቻ/ፎቢያ ልጆችዎ ሲያዩ ፎቢያ ሊይዛቸው ይችላል። ስለሆነም የእርስዎን ፎቢያ በመቆጣጠር ወደ ልጆችዎ የመተላለፉን ዕድል መቀነስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011