ርዕስ፡- ነቅዐ መጻሕፍት
ደራሲ፡- ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ
የህትመት ዘመን፡- 2011 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 365
የመጽሐፉ ዋጋ፡- 220 ብር
ፈረንሳይ ውስጥ በዚሁ ወር በተነበበ አንድ ዜና እንጀምር።
‹‹በፈረንሳይ 230 ዓመታትን ያስቆጠረ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ማንበብ ለቻለ 2000 ፓውንድ ሽልማት ተዘጋጀ›› ይላል። ዜናውን ትንሽ ዘርዘር እናድርገው፤
በፈረንሳይ 230 ዓመታትን ያቆጠረ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ከዓመታት በፊት ተገኝቷል፤ 20 መስመሮችን የያዘውን ይህን የድንጋይ ጽሑፍ እስከአሁን ማንበብ የቻለ ሰው አልተገኘም። በድንጋይ ጽሑፉ ላይ 1786 እና 1787 የሚሉ ዘመናት ተጠቅሰዋል። እነዚህ ጊዜያት ደግሞ ከፈረንሳይ አብዮት ቀደም ያሉ ጊዜያት ናቸው።
ከጽሑፉ ጋር መርከብና መርከበኞች፣ የመስቀል ቅርጽ፣ የተሰበሩ የልብ ቅርጾችና ሌሎችም ምሥሎች ተገኝተዋል። ጽሑፉን ማንበብ የሚችል ስለጠፋ ማንበብ ለቻለ ዳጎስ ያለ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
ሁለት ነገር እንረዳ
አንድ፤ ለጥንታዊ ነገሮች ትኩረት አለመስጠት ታሪክን እንደሚያስረሳ። ይሄ ፈረንሳይ ውስጥ የተገኘ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የሚያነበው ያጣ የዚያ ዓይነት አጻጻፍ ተረስቶ ነው።
ሁለት፤ አገራት ለታሪካቸው ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ። ፈረንሳይ የዚህን ጽሑፍ ምንነት ማወቅ ስለፈለገች ነው ይህን ያደረገች።
አሁን ወደ አገራችን እንመለስ። ለታሪክ ትኩረት ባለመስጠት እንታማለን፤ በተለይም የዚህ ትውልድ ወጣት እየታማ ነው። ሀሜቱን ትክክል የሚያደርጉት ማሳያዎች ደግሞ አሉ። ስንቶቻችን ነን የአባቶቻችንን ታሪክ የምናውቀው? አለፍ ሲል በጥንት ቋንቋዎች የተጻፉ ነገሮችን ስንቶቻችን እናውቃለን? አሁን እንኳን በማገልገል ላይ ያለውን በተለምዶ ‹‹የግዕዝ ቁጥር›› የሚባለውን ኢትዮጵያዊ ቁጥር ስንቶቻችን እናውቀዋለን?
ከወጣቱ ወቀሳ በፊት ምሁራንስ ምን ሠርተዋል? ለመሆኑ በዚህ ዘርፍ ምሁርስ አለን ወይ? ምሁራን ራሳቸው የሚሠሩት ጥናት በፈረንጅ ቋንቋ አይደል?
ዛሬ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል አንድ መጽሐፍ ልናስተዋውቃችሁ ወደድን። መጽሐፉ የሚያስተምረው ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ቋንቋ ራሱ ያስተምረናል። በጥቂቱ እንቃኘው።
ዛሬም ‹‹ሰው ሥራውን ይመስላል›› ማለት እወዳለሁ። ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ስላደጉ ለታሪክ ቅርብ ሆኑ። የኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ ሥረ መሰረቱ ሃይማኖት ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊዮሎጂ(ጥንታዊ ፅሑፍ ጥናት ዘርፍ) ተመርቀዋል። የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም ጣሊያን አገር በሚገኘው ፍሎረንስ ዩኒቨርሲቲ በጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጥናት አድርገው ነው የተመረቁት። አሁንም ሌላ የዶክትሬት ዲግሪ፤ እዚያው በጣሊያኑ ፍሎረንስ ዩኒቨርሲቲ በግዕዝ ስነ ልሳን ዘርፍ ምርምር አድርገው ተመርቀዋል።
ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምህርነት፤ ከዚያም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለየዩ ቦታዎች ላይ በኃላፊነት እንዲሁም ኮልፌ በሚገኝ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አካዳሚክ ዲን በመሆን አገልግለዋል።
እኝህ ሰው በቅርቡ አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ‹‹ነቅዐ መጻሕፍት›› ይሰኛል ርዕሱ።
በመጽሐፉ ሁለተኛ ቅጠል ላይ እንደተብራራው ‹‹ነቅዐ መጻሕፍት›› ማለት ‹‹የመጻሕፍት ምንጭ፣ የመጻሕፍት መገኛ›› ማለት ነው።
መጽሐፉ እንደ ስሙ ነው። ይህን መጽሐፍ ማንበብ ማለት ቤተ መጽሐፍ ውስጥ ገብቶ ብዙ መጽሐፎች እንደማንበብ ማለት ነው። ቤተ መጽሐፍ ውስጥ ገብተን ባናነበው እንኳን ያሉ መጽሐፎችን እናውቃለን፤ ያ ማለት ሌላ ጊዜ አስበንበት ለፈለግነው መጽሐፍ እንመጣለን ማለት ነው። የቀሲስ ዶክተር አምሳሉ መጽሐፍ እንደዚያ ነው። ብዙ መጽሐፎችን ይጠቁመናል። ከ600 በላይ በግዕዝ የተጻፉ የኢትዮጵያ መጽሐፎች ዝርዝር ከማብራሪያ ጋር ተዘርዝረውበታል
በዚህ መጽሐፍ ላይ ቅኝት ሳደርግ ስነ ጽሑፋዊ አጻጻፉንም ሆነ ይዘቱን መገምገም አይደለም፤ መጽሐፉ እንደ ፖለቲካ መጽሐፍ የግል እይታ የሚገባበትም አይደለም። የመጽሐፉ አብዛኛው ይዘት እውነታ (Fact) ነው። የደራሲው ግላዊ እይታ እምብዛም አይታይም። እናም ይህን መጽሐፍ መገምገም ሳይሆን ይዘቱን ማስተዋወቅና አንባቢን ለመጠቆም ነው። አንድ ነገር ግን አሳስባለሁ። ደራሲው ለግዕዝ ቅርብ ስለሆኑ ይመስላል አገላለጻቸው የግዕዝ ጫና አለበት። ያንን እኔ በአማርኛ ልገልጸው እችላለሁ። ለምሳሌ መጻሕፍት የሚለውን የግዕዝ አገላለጽ መጽሐፎች በሚል የአማርኛ አገላለጽ እጠቀማለሁ።
አምስት ምዕራፎች ያሉት መጽሐፉ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ሰፋፊ ንዑስ ርዕሶች አሉት። የመጽሐፉ አብዛኛው ክፍል ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ቢሆንም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው። ስለቅርሶቻችን ብዙ ነገር ይነግረናል። የብራና መጽሐፎችን ያስተዋውቀናል።
ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ
አካባቢ ‹‹አነሣሽ ምክንያት››
በሚል ያስቀመጡት ነገር
አለ። መጽሐፉን
ለማዘጋጀት ካነሳሷቸው ነገሮች አንዱ ምሁራን በአገር ውስጥ ቋንቋ ጥናት አለመሥራታቸው ነው። በዚህም ምክንያት በተለይም እንደ ብራና ላይ ያሉ ጽሑፎች እየተረሱ ነው። ምሁሩ ይህን በማጥናት መጽሐፍ አዘጋጅተውልናል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ‹‹ጽሑፍ እና መጻሕፍት በኢትዮጵያ›› ይላል። በንዑስ ርዕስ ‹‹የጽሑፍ ታሪክ በሀገራችን›› ይላል። ይህ ምዕራፍ ለስነ ጽሑፍና ለታሪክ መነሻ የነበሩ የብራና ላይ የጽሑፍ ሀብቶቻችንን ከነመገኛቸው ይነግረናል።
ኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ሀብቶቿ ከውጭ የተተረጎሙ እንጂ የራሷ አይደሉም የሚል የአንዳንዳንድ ምሁራን ሀሜት አለ። ለዚህ ሃሳባቸው ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ በማስረጃ መልስ አላቸው። ከማንም የውጭ አገር ጋር የማይመሳሰል የራሷ የፊደል ገበታ ያላት ሀገር ስነ ጽሑፍ የላትም ማለት ምኑም የሚያስኬድ አይሆንም። ምስክር የሚሆኑትም በድንጋይ ላይ፣ በመቃብር ላይ፣ እንጨት ላይ፣ ግድግዳ ላይ፣ የመቀመጫ ዙፋን ላይ ወዘተ… ተጽፈው የተገኙ ጽሑፎች ናቸው። በተለይም በ300 ዓ.ም አካባቢ የተጻፉ ጽሑፎችን መጽሐፉ ይነግረናል። እንግዲህ በዚያን ዘመን እነዚህ አሁን የሥልጣኔ ተምሳሌት የምናደርጋቸው አገራት ምን ላይ እንደነበሩ ታሪካቸውን መለስ ብሎ ማየት በቂ ማስረጃ ነው።
ስለብራና መጽሐፎች ምንነት፣ እንደት መያዝ እንዳለባቸው፣እንዴት እንደሚጠፉና እንዴት እንደሚሰረቁ ከነገሩን በኋላ የብራና ጽሑፎች የሚገኙባቸውን አገራት ይዘረዝሩልናል። በአገራቱም መቼ እንደተወሰዱ፣ እንዴት እንደተወሰዱና በእያንዳንዱ አገር ምን ያህል መጽሐፎች እንዳሉ ይነግሩናል። ዝርዝሩን ከመጽሐፉ አንብቡትና እኔ አገሮችን ብቻ ልጥቀስ።
የብራና መጽሐፎች በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በኢየሩሳሌም፣ በአሜሪካ፣ በስዊድን፣ በኦስትሪያ፣ በቤልጂየም፣ በዴንማርክ፣ በካናዳ፣ በግብፅ፣ በፊንላንድ፣ በሩሲያ፣ በአየርላንድ፣ በኔዘርላንድ፣ በፖላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ በኖርዌይ እና በስፔን ይገኛሉ።
ምዕራፍ ሁለት ‹‹ትርጓሜያት›› ይላል። ይህ ክፍል በአመዛኙ ሃይማኖታዊ ነው። ሆኖም ግን ብዙ ታሪካዊ መረጃዎችን ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከየት ወደት እንደተተረጎሙ፣ ሰማንያ አንዱ ቅዱሳት መጽሐፎች እና ለአንደምታ ትርጓሜ በምንጭነት ያገለገሉ መጽሐፎች ዝርዝር አለበት።
ሦስተኛው ምዕራፍ የገድል መጽሐፎችን ይነግረናል። ይህ ክፍል ሃይማኖታዊ ብቻ አይደለም፤ ታሪካዊ እውነታዎችን ይነግረናል። እንደሚታወቀው ከደርግ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ሃይማኖታዊ ይዘት የነበረው ነው። ንጉሥ ሆነው አገር የሚያስተዳድሩት ቅድስና የነበራቸው ናቸው። ለምሳሌ ነገሥታት ሆነው በቅድስናቸው የሚታወቁትና ገድል የተጻፈላቸው፤ አብርሃ ወአጽብሐ፣ ንጉስ ካሌብ፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ነአኩቶለአብ፣ ንግስት መስቀል ክብራ(የላሊበላ ባለቤት)፣ አጼ ገላዲዎስ፣ ታላቁ ኢያሱ(አድያምሰገድ) ይጠቀሳሉ።
ከሊቃውንትም ገድል የተጻፈላቸው አሉ። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሲጫ እና ቅዱስ ያሬድ ይጠቀሳሉ። መጽሐፉ እነዚህን ሁሉ ያስተዋውቀናል።
በታሪክ፣ በሊቅነትም ሆነ በሃይማኖታዊ ይዘታቸው ብዙ ገድሎችን ያሳውቀናል። መጽሐፉ ከገጽ 99 እስከ ገጽ 211 ድረስ (112 ገጽ ማለት ነው) የሚነግረን የገድሎችን ዝርዝር እና ማብራሪያ ነው። በዚህ ርዕስ ሥር 472 ገድሎች ከነማብራሪያቸው ተዘርዝረዋል።
ከዚህ ቀጥሎ የምናገኘው የመጽሐፉን ምዕራፍ አራት ነው። ይህ ምዕራፍ ‹‹ድርሳናት እና ሌሎች የትምህርት መጻሕፍት›› ይላል። 128 መጽሐፎችን እየዘረዘረ ያብራራል። የተቀመጡትም በይዘታቸው ተለይተው ርዕስ እየተሰጣቸው ነው። ርዕሶቻቸውን ብቻ ልጥቀስ።
ድርሳናት፣ ሃይማኖትን የሚያብራሩ መጽሐፎች፣ የዜማ፣ የቅዳሴ፣ የጸሎት፣ እና ስነ ልሳን፣ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው መጽሐፎች ተብለው በሰባት ክፍል ቀርበዋል።
እንደ ደራሲው አጻጻፍ እነዚህ መጽሐፎች ከ472ቱ የገድል መጽሐፎች የሚቀጥል ነው። 473 ብሎ ይቀጥልና እስከ 600 ድረስ ይዘልቃል። 600 መጽሐፎች ተብራርተዋል ማለት ነው። ይህ ሲሆን እንግዲህ በአንድ ገጽ ብቻ ከአምስት በላይ መጽሐፎች እንደማጣቀሻ እየተጠቀሱ ነው። በገጹ ግርጌ ላይ ያሉ የህዳግ ማብራሪያዎች ደግሞ በተለያየ ቋንቋ የተጻፉ ተዛማጅ መረጃዎችን ይጠቁሙናል።
ምዕራፍ አምስት የመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ ነው። ርዕሱም ‹‹የተብራሩ መጻሕፍት›› ይላል። በዚህ ክፍል ውስጥም ብዙ መጽሐፎች ተብራርተዋል።
ይህ መጽሐፍ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ቋንቋም ያስተምረናል። ደራሲው በመግቢያው ላይ እንደተናገሩት ጥናቶችና ምርምሮች የሚደረጉት በውጭ አገር ቋንቋ ነው። በዚህም ምክንያት ለአገርኛ ቃላት ባዕድ ሆኗል። ይህ የቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ መጽሐፍ በውጭ ቋንቋ ስማቸውን የለመድናቸውን ቃላት በአማርኛ ይነግረናል። ምናልባት አዲስ እንደሚሆንብን ገምተው ይመስላል የተለመደው የእንግሊዝኛ ወይም የሌላ የውጭ ቋንቋ መጠሪያውን በቅንፍ ውስጥ ያስቀምጡልናል።
መጽሐፉን ማንበብ ብዙ ነገር ያስገኛልና አንብቡት!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ዋለልኝ አየለ