እንደ መግቢያ
በጥር ወር1995 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳመለከተና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቅድመ-ሁኔታዎችን ለማሟላት ሽር-ጉድ ይል እንደነበር ይታወቃል። በጊዜው ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ አባል ብትሆን የምትጎዳው ነገር የለም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል በሚል የኢትዮጵያን መንግሥት ጥድፊያ ይቃወሙ በነበሩ ኃይሎችና አባል መሆን በሚፈልጉ መካከል የጦፈ ክርክር እንዳካሄዱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋረጠው ድርድር እንደገና እንዲጀመር የዓለም ንግድ ድርጅትን እንደጠየቀ ሪፖርተር ጋዜጣ ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል ። አሁን ግን እንደከዚህ ቀደሙ ክርክር ቀርቶ ጉዳዩን በአግባቡ የሚያነሳ አካል ያለ አይመስልም። የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ሲሰጡበትም አይታዩም። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ አገር አንድ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት፣ አንደኛ አገዛዙ የአገሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ አለበት፤ ሁለተኛ በምን ዓይነት ቲዎሪ ወይም የአሠራር ሥልት የኢኮኖሚውን አወቃቀር እንደሚተነትን ቢያንስ ሊከታተልና ሊገባው ለሚችለው የሕብረተሰብ ክፍል ማቅረብ አለበት። ይህም ማለት አገሪቱ የምትገኝበትን የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስና የማህበረሰብ የዕድገት ደረጃ ማሳየት አስፈላጊ ነው። ሦስተኛ ለምን የአንድ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት አባል መሆን እንደሚያስፈልግ ወደ ውጭ በመውጣት ለህዝቡ ግልፅ ማድረግ አለበት።
በምሁሩ ዘንድም ክርክር እንዲደረግ መጋበዝ አለበት። ይህም ማለት አንድን አገር የሚመለከት ትልቅ ፕሮጀክት በተዘጋ ቤት መጠናቀቅ የለበትም። ይህም ገፊ ምክንያት ሆኖን ርዕሰ ጉዳዩን አንስተን የዘርፉ ባለሙያዎች ሐሳብ እንዲሰጡበት አድርገናል። ለዚህም የዘርፉ ባለሙያና ፀሐፊ ፍቃዱ በቀለ (ዶ/ር) እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁንን ሐሳብ መሰረት አድርገን የዓለም ንግድ ድርጅትን ታሪካዊ አመጣጥ በማሳየት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ምን ትጠቀማለች? ምን ትጎዳለች? የአገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ያመቻል ወይ? የውስጥ ወይስ የውጭ ገበያ ነው የአንድ አገር የዕድገት መሰረት? የሚሉ ነጥቦችን አንስተን የሚከተለውን ጽሑፍ አዘጋጅተናል።
የዓለም ንግድ ድርጅት ታሪካዊ አመጣጥ
ዛሬ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) በመባል የሚታወቀው የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም ሲሆን፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ብቅ ያለውን የኃይል አሰላለፍ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ በርካቶች ያስረዳሉ። እንደሚታወቀው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ የተከሰተው አዲስ የኃይል አሰላለፍ የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊተሪ ተቋማት በአዲስ መልክ ማዘጋጀት እንዳለበት ታመነበት።
ይህ በአሜሪካ የሚመራው አዲስ የኃይል አሰላለፍ ከዚህ ቀደም የነበረውንና እ.ኤ.አ ከ1929 እስከ 1945 ዓ.ም ድረስ እየተዳከመ የመጣውን የዓለም አቀፍ የሥራ-ክፍፍልና (International Division of Labor) የንግድ ልውውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ንግድን ለማስፋፋትና የተወሰነ ሀብትን ከበለፀጉ አገሮች በዕድገታቸው ኋላ ወደቀሩ አገሮች ማስተላለፍ ያስፈልጋል በሚለው ሽፋን ሥር በአዲስ መልክ መደራጀት እንዳለበት ተገነዘበ። በዚህም አማካይነት የበላይነቱን (Hegemony) ማስፈን እንደሚችልና የየአገሮችን የዕድገት አቅጣጫ ለመወሰን እንዲችል የነፃ ንግድ አስፈላጊነት ግልፅ ሆነ።
በመጀመሪያ እ.ኤ.አ በ1944 ዓ.ም ሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች፣ የዓለም ባንክና (WB) የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አሜሪካን አገር በብሬተን ውድስ ከተማ ሲመሰረቱ፣ እ.ኤ.አ በ1948 አጠቃላይ የንግድና የታሪፍ ስምምነት (General Agreement on Trade and Tarif)፣ እ.ኤ.አ ከ1994 ጀምሮ ደግሞ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ተብሎ በመጠራት የሚታወቀው በመጀመሪያ 23 አገሮች አባል የሆኑበት ድርጅት ተመሰረተ። በአሁኑ ወቅት የንግድ ድርጅቱ አባላት ቁጥር 164 ሲሆኑ፣ 23 አገሮች ደግሞ በተመልካችነት የተቀመጡ ናቸው። በጊዜው ከደቡቡ ዓለም አስራ አንድ የሚሆኑ በዕድገታቸው ወደፊት ያልገፉ አገሮች አባል ሆኑ።
እንደ ዶክተር ፍቃዱ በቀለ ገለፃ በእነዚህ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተመሰረቱት ድርጅቶች መካከል ግልፅ የሆነ የሥራ-ክፍፍል ሲኖር፣ በተጨማሪም ሦስቱም ድርጅቶች የሚመሩበት የርዕዮተ-ዓለምና የቲዎሪ መሰረት በእነ አዳም ስሚዝ፣ ከ1880ደግሞ በኒዎ-ክላሲካል፣ ከ1938ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል በሚታወቀው በነፃ ንግድና ገበያ ስም በዳበረው “ “ቲዎሪና„ ርዕዮተ-ዓለም መሰረት ነው። የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ መመሪያዎች ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1950ጀምሮ በረቀቀ መልክ በመዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአገሩ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ የሆኑና፣ አማራጭና ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ይመስል ሁሉም አገሮች አሜን ብለው እንዲቀበሉት የተደረጉ፣ ከዕውነተኛ ዕውቀት ይልቅ ርዕዮተ-ዓለምን የሚያስተጋቡ ናቸው።
በዚህ መልክ በቅኝ- ግዛት ዘመን ሰፍኖ የነበረው የሥራ ክፍፍል ከአዲሱ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በመቀናጀት የሦስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች የጥሬ-ሀብትና፣ በተለይም በኢንዱስትሪ አገሮች ሊበቅሉ የማይችሉ የእርሻ ምርት ውጤቶች አቅራቢ ሆነው እንዲቀሩ የተቀነባበረ ሴራ ነው ማለት እንደሚቻል ዶክተሩ ያስረዳሉ። በቲዎሪው መሰረትም እያንዳንዱ አገር በዓለም ንግድ ውስጥ ሊሳተፍ የሚችለው ባለው ሀብት ላይ ብቻ ትኩረት ካደረገ ብቻ ነው።
ወደ ዛሬው አጠቃላይ የነፃ-ንግድ ልውውጥና በአባል አገሮች መካከል ገበያውን ሙሉ በሙሉ ልቅ ማድረግ ያስፈልጋል ወደሚለው መደምደሚያ ላይ ከመደረሱ በፊት የመጀመሪያው የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርና ወደ ስምምነት መድረስ ያተኮረው በኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች ላይ ሲሆን፣ ይህም ከውጭ ወደ ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለውን ከፍተኛ ቀረጥ መቀነስ ነበር። ድርጅቱ ከተቋቋመ እ.ኤ.አ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የኬኔዲ ድርድር ወይም ዙሪያ (Kennedy Round) በመባል በሚታወቀው ድርድርና ስምምነት አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄደው በራሳቸው በኢንዱስትሪ አገሮች መካከል ሲሆን፣ ታሪፍን በመቀነስ ውጤት ላይ ተደርሷል። እ.ኤ.አ እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ በአብዛኛዎቹ ምርቶች ላይ የታሪፍ ቅነሳ ሲጠናቀቅ፣ ከ1970ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ልዩ ዓይነት የኢኮኖሚ ቀውስና የዘይት ዋጋ መናር ድርድሩን አጠቃላይና የጠለቀ እንዲሆን አደረገው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለይም ታሪፍ-ነክ ባልሆኑና የንግድ ልውውጥን ያደናቅፋሉ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ መደራደርና ወደ አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት።
እነዚህም የየመንግሥታትን የውስጥ ፖሊሲ የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ ለኢንዱስትሪዎች የሚሰጠውን ድጎማ፣ ወደ ውጭ በሚላኩ ዕቃዎች ላይ የሚደረገውን ልዩ ድጋፍና ብደር (Export Subsidy and Credits)፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ንግድን ያደናቅፋሉ ተብለው የሚገመቱ ሕጎችና ሥርዓቶችን ማስወገድ ነበር። ይህ ድርድር ከረጅም ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም ስምምነት ተደረሰበት።
እ.ኤ.አ ከ1986ዓ.ም ጀምሮ እስከ1994ዓ.ም ድረስ ኡራጋይ ዙሪያ (Uruguay Round) የተደረገው ድርድርና ስምምነት የዓለም ንግድ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ እራሱን የቻለ ተቋም ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሻ ምርትንና ምግብን የሚያጠቃልልና የነፃ ንግድን በአባል አገሮች መካከል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ሥር እየሰደደ የመጣው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ቀውስና የኢንዱስትሪ አገሮች መንግሥታት በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች (Multinational Companies) ቁጥጥር ሥር መውደቅና የነሱን ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊነቱ እየጎላ ሲመጣ የዓለም የንግድ ድርጅት በአዲስ መልክ መዋቀሩና አጠቃላይ ነገሮችን መያዙ አስፈላጊ እየሆነ መጣ።
ተጨባጭ ሁኔታዎች እንደሚያረጋግጡት፣ በተለይም የኢንዱስትሪ አገሮች መንግሥታት ቀስ በቀስ ከአጠቃላይ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅና የትላልቅ ኩባንያዎችን፣ የባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የበለጠ ትርፋማና ሀብት አካባች ለማድረግ፣ እንዲሁም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥና ከሌላው ተሽሎ ለመገኘት ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩት የኒዎ- ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።
በዚህም መሰረት ወደ ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ግፊትና ተሰሚነት እየጎላ በመምጣት መንግሥታትን መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቱ ላይ በማንፀባረቅ፣ በተለይም ጥቂት የእርሻ ዘርንና ምግብን የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የወደፊት ሩጫና የበላይነትን መቀዳጀት ድል የተነሳ በንግድ ድርጅቱ አባል አገሮችና ወደፊትም አባል ለመሆን በሚሹ አገሮች መካከል የውጭ ንግድን ለመቆጣጠር የተጣሉ እገዳዎች (Protectionist Measures) ሙሉ በሙሉ ማንሳት እንደሚያስፈልግ ስምምነት ተደረሰበት።
ማንኛውም አገር የየራሱን ሕገ-መንግሥትና ሌሎች ሕጎችን በመጣስና የህዝቡን የወደፊት ዕድል በማጨለም የዓለም ንግድ ድርጅትንና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ድንጋጌ ሳያወላውል በተግባር መመንዘር እንዳለበት ዶክተር ፍቃዱ ይናገራሉ። ይህንን በሚመለከት በተዘጋ ቤት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅቱና የዓለምን ዘርና ምግብ የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል 170 የሚሆኑ አከራካሪ ነጥቦችና ሕጎች ላይ ድርድር ተካሂዷል። በዚህም መሰረት ማንኛውም አባል አገር የዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነትን የሚጥስ እርምጃ ከወሰደ ከፍተኛ ቅጣት ይደርስበታል።
የንግድ ድርጅቱ ውጤት
ቅጣቱን የተመለከተ ስምምነት ከመደረሱና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በኢንዱስትሪ መስክ በተደረገው ስምምነት ሠራተኞችና ተጠሪዎቻቸው ከፍተኛ ግፊት ተደርጎባቸዋል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ መስኮች ወድመዋል። ተጨባጭ ደሞዝ በብዙ እጅ ቀንሷል። አነስተኛ ደሞዝንና አመቺ የማምረቻ ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ ከኢንዱስትሪ አገሮች እየተነቀሉ ወደ አንዳንድ የባሪያ ደሞዝ የሚስተካከል ክፍያ የሚከፈልባቸው የሦስተኛው ዓለም አገሮች የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ የሥራ-አጥ ቁጥሩ እንዲጨምር ከማድረግ አልፎ የሠራተኛው የመግዛት ኃይል እየተዳከመና የመንግሥታቱን በጀት እያዛባው መጥቷል።
በሌላ ወገን ግን በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ሥር ያሉትና በሦስተኛው ዓለም አገሮች የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች ለየአገሮች ዕውነተኛ ዕድገት አለማምጣታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራው ሠራተኛ ደመወዙ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የመግዛት ኃይሉ በጣም ደካማ ነው። ሠራተኛው በሚያገኘው ደመወዝ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደርና ልጆቹንም ወደ ትምህርት ቤት የማይልክበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ሠራተኛው ለባርነት ሥራ የተፈጠረ ይመስል በነፃ ንግድና በነፃ ገበያ ሽፋን ሥር ዕውነተኛ ነፃነቱ እንዲገፈፍ ተደርጓል። ይህን የመሰለ አስከፊ ሁኔታ አባል በሆኑ ደካማ አገሮች እንደታየ ዶክተሩ ያብራራሉ።
እንደዶክተር ፍቃዱ ገለፃ በንግድ ድርጅቱና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻ ምክንያት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ገበሬዎች ኑሮአቸው ተናግቷል። እራሳቸውንም የገደሉ አሉ። ስለሆነም የእርሻው መስክ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶበታል። ከትውልድ ትውልድ ከሚፈለገው ሰዓት በላይ እየሠራ በመሰረቱ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ሙያውን እንደባህል ያደረገውና ተፈጥሮን እየተንከባከበ ጤናማ የእርሻ ምርት ለተጠቃሚው ህዝብ የሚያቀርበው ትናንሽ የገበሬ የሕብረተሰብ ክፍል መስኩን እንዲዘጋና መንደሩን እየለቀቀ እንዲሰደድ ተገዷል።
በአዲሱ የንግድ ስምምነት መሰረት በአብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ አገሮችም ውስጥ ማህበራዊ መዛባት ሊከሰት ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን የቀሩት ገበሬዎች በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ሥር በመውደቅ ሦስት የዓለምን የዘር ባንክ በሚቆጣጠሩ ኩባንያዎች ሥር ፍዳቸውን እንዲያዩ ተገደዋል። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ገበሬ ከትውልድ ትውልድ በሙከራና በልምድ ያዳቀለውን የእህል ዘር የመዝራት ዕድል የለውም። ከብድር ጀምሮ እስከ ዘርና የኬሚካል ማዳበሪያዎች፣ እንዲሁም የተባይ ማጥፊያዎች ድረስ በባንኮችና በኩባንያዎች ቁጥጥር ሥር የወደቀ በመሆኑ ገበሬዎች በቀጥታ የሚሠሩት የኩባንያዎችንና የባንኮችን ሀብት ለማካበት ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የወደቁት ገበሬዎች ከድህነት ለመላቀቅና አዲስ
ህይወት የመኖር ዕድል በፍፁም የላቸውም። የነፃ ገበያ ውድድርና ይህ ዓይነቱ የተወሳሰበ ጥገኝነት ብዙ ሰዓትን መሥራትንና ራስን ከሚገባው በላይ ማስጨነቅን ስለሚጠይቅ ነው።
ይሁንና የነፃ ንግድን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ቢደረስም፣ በአንድ በኩል በአሜሪካና በብዛት የእርሻ ምርትን ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት የኬይርነስ ተወካይ አገሮች (Cairns- Groups) ማለትም፣ አርጀንቲናና አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ብራዚል፣ ኒው ዘላንድ፣ እሩጓዋይ፣ ቺሌ፣ ኮሎምቢያ፣ ፓራግዋይ፣ ማሌዢያ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንድና ፊሊፒን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአውሮፓ አንድነት አገሮች መካከል የጦፈ ክርክር ተካሄደ። የውጭውን ንግድ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ፣ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ የሚደረገውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ፣ ለንዑስ መስኮች የሚደረገውን ክፍያና ማስተካከያ ማቆም የሚሉት ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ የአውሮፓው አንድነት አሻፈረኝ ሲል፣ አሜሪካ በጥንቃቄ “እየተቀበለው„ መጥቷል።
ስምምነቱ ከተደረሰ ጀምሮ በተለይም እንደ ብራዚል ያሉት አገሮች የስኳርን ምርት በዓለም ገበያ ላይ በማራገፍ የተሻለ ዕድል ቢያጋጥማቸውም፣ እንደ ኡራጓዋይ የመሳሰሉት አገሮች ደግሞ አባል ሆነውም በስምምነቱ መሰረት የተሻለ የገበያ ዕድልና ወደ ውስጥ ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ብሔራዊ ሀብትን ሊያዳብሩና ሕዝቦቻቸውም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ በተለያዩ ዘዴዎች የእርሻ ምርቶቻቸውን ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች የመላክ፣ በተለይም ደግሞ ወደ አውሮፓ አንድነት ገበያ ላይ የማስገባቱ ዕድል እየጠበባቸው መጥቷል።
በሌላ አነጋገር እ.ኤ.አ በ1994ዓ.ም የእርሻ ምርትንና ምግብን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ካለገደብ ለማራገፍ የተደረሰበት ስምምነት ይበልጥ የጠቀመው የአውሮፓውያንን አንድነት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ብራዚል በስኳር ምርት ላይ ብቻ በማትኮሯና ለምግብ የሚሆነው እርሻ አትኩሮ ስላልተሰጠው በጊዜው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተከስቶ ስለነበር ወደ አርባ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በምግብ እጥረት ይሰቃይ ነበር። በስኳር ምርት የተነሳና መሬት በጥቂት ኦሊጋርኪዎች በመያዙ ሊያርሱ የሚችሉ ትናንሽ ገበሬዎች የማረስ ዕድል በፍፁም አላገኙም። በጊዜው ሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሉላ ከዚህ ሀቅ በመነሳት ከተመረጡ በኋላ እያንዳንዱ ብራዚሊያዊ ቢያንስ በቀን ሦስት ጊዜ በልቶ እንዲውል አደርጋለሁ ብለው የገቡት ቃል እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ሊሳካላቸው ችሏል። ይኸውም ለማሕበራዊ መስክ የሚወጣውን በጅት ከፍ በማድረጋቸው ብቻ ነው።
ከላይ በተጠቀሱት አገሮችና በአውሮፓ አንድነት መካከል የሚደረገው ድርድር እራሱን የነፃ ገበያ አራምዳለሁ የሚለውን የአውሮፓ አንድነትን ቅራኔ ውስጥ ከቶታል። የአውሮፓ አንድነት ለገበሬው በየዓመቱ ወደ ስልሳ ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ በድጎማ መልክ ይሰጣል። የኢንዱስትሪ አገሮች በአጠቃላይ ለገበሬዎቻቸው ወደ ሦስት መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጎማ ያደርጋሉ። ይህንን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ማንሳት ማለት ከፍተኛ የማሕበራዊና የፖለቲካ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደመፍጠር ስለሚቆጠር እነዚህ አገሮች ደፍረው ይህንን ዓይነት እርምጃ በፍፁም አይወስዱም።
በተለይም ኢኮኖሚው እንደሰንሰለት የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን ድጎማ የሚቀነስ ወይም እንዳለ የሚነሳ ከሆነ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሃት አለ። ይህ ጉዳይ በአንድ በኩል በምርት ብዛት የተወጠረውን የአውሮፓ አንድነት፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደፈለገው በሦስተኛው ዓለም አገሮች ገበያ ላይ ምርቱን ለማራገፍ የሚያደርገውን ሩጫ ለማመቻቸት ያለውን ቀዳዳ ለመጠቀም ያለመቻል ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ከቶታል። ይህ ጭንቀት10 አዲስ አባል አገሮች የአውሮፓን አንድነት ከተቀላቀሉ በኋላ ልዩ መልክ እየያዘ መምጣቱን ዶክተሩ ያስረዳሉ። አዲሶቹ አባል አገሮች ገበያቸውን ክፍት ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን እነሱም የብስኩቱ ተካፋይ እንደመሆናቸው መጠን የእርሻ ምርቶቻቸውን እንደመጀመሪያዎቹ አባል አገሮች መላክ አለባቸው። በዚህም ሌላ አዲስ የታቀደ ቅራኔ መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በደንብ ያልተደራጀ የእርሻ መስክ ያላቸውና የዓለም ንግድ ድርጅት እንግባ እያሉ የሚፍጨረጨሩ አገሮች፣ የአውሮፓው አንድነት፣ የአሜሪካና ሌሎች የድርጅቱ አባል አገሮች ገበያ ላይ ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ያላቸው ዕድል በጣም የጠበበ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በተለይም የአውሮፓ አንድነት ሰበብ እየፈለገ ገበያውን ማጥበቡ የማይቀር ጉዳይ ነው። ከነዚህ ውስጥ የጥራት ጉዳይና ከምርቶች ጋር ተያይዘው ይመጣሉ ተብለው የሚገመቱ በሽታዎች እንደምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።
የአውሮፓ አንድነት ገበያውን ለመዝጋት ሲል ብቻ ሳይሆን ከጤንነት አንፃርም ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በደንብ ይቆጣጠራል። በሌላ ወገን ግን ወደፊት እየሰፋ የሚመጣው የንግድ ልውውጥ፣ ማለትም የአገልግሎትና የጤንነት መስኩን ልቅ ማድረግ፣ የውሃና የትምህርት መስኩን በሚመለከት ለዓለም አቀፍ ተዋንያኖች ክፍት ማድረግ፣ … ወዘተ. እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው በንግድ ድርጅቱም ሆነ በአውሮፓ አንድነት ታምኖበታል። በየአገሩ ገብተን እንደፈለግን እንፈትፍት የሚለው ዐይን ያወጣ ውትወታ በኢኮኖሚያቸው ደካማ የሆኑ አገሮችን በጣም አስጨንቋቸዋል። ወደፊት አምባገነን የሆነ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ሊመሰረት ነው የሚል ፍርሃት ትችታዊ አመለካከት ባለቸው የሲቪል ማህበራት እንቅስቃሴዎች ዘንድ ሰፍኗል። ወደፊት ድርድሩና ስምምነቱ ሁሉንም መስክ የሚያጠቃልል በመሆኑ በተለይም የደካማ አገሮች ብሔራዊ-ነፃነት በከፍተኛ ደረጃ መገፈፉ የማይቀር ጉዳይ መሆኑንም የዶክተር ፍቃዱ እምነት ነው ።
ከዚህ ስንነሳ በሀገራችን ውስጥ ያለው አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አፍጦና አግጦ በሚታይበት ወቅትና፣ አብዛኛው ህዝብ በዋጋ መናርና በሥራ እጦት በሚንገሸገሽበት ጊዜ ከዓለም የንግድ ድርጅቱ ጋር መደራደር አለብን ማለት ምን ውጤት ላይ ለመድረስ ነው? የሀገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች በዚህ ዓይነቱ ስምምነት ሊቀረፉ ይችላሉ ወይ? ስምምነት ላይ ቢደረስስ በዚህ ዓይነቱ የንግድ ልውውጥ ጠንካራ ሕብረ-ብሔር መገንባት ይቻላል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎችንና ሌሎች ለአንድ አገር እንደ ባህላዊ አገር ለመገንባትና ተከታታይነት እንዲኖረው በሚያደርጉ ነገሮች ላይ መወያየቱና መከራከሩ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚም ነው። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ያመቻል ወይ የሚለውን ለማየት እንሞክር።
የአገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ያመቻል ወይ?
አንድ አገር አንድ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በስፋትና በጥልቀት መመልከት፣ ማጥናት፣ መወያየት፣ ግንዛቤ መፍጠር የግድ ይላታል። ከዚህ አንፃር ያለውን ነባራዊ ሁናቴ እንመልከት ። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የለባትም ብለው ፅኑ አቋማቸውን ከሚያንፀባርቁት መካከል አንዱ የምጣኔ ሀብት
ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው። ለአቋማቸውም ትክክለኝነት ዝርዝር ማሳያዎችንና ምክንያቶችን አቅርበው ይሞግታሉ። እንደእሳቸው ገለፃ ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም በተለይ ከሰለጠነው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም ስላልፈጠረች የንግድ ድርጅቱ አባል ስትሆን ገበያዋን በጣም ስልጡን ለሆኑ፣ የካፒታል ክምችት ላላቸው፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ለሚጠቀሙ አገራት አሳልፋ እንደመስጠት ይቆጠራል። በገበያ ውድድሩ ኢትዮጵያ ሳትሆን ሌሎች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቱ አባል ብትሆን በማቆጥቆጥ ላይ ያለውን ኢንዱስትሪ ድምጥማጡን ያጠፋዋል የሚል እምነት ባለሙያው አላቸው። በእኛ አገር ያሉ የግሉም ሆነ የመንግሥት ኢንዱስትሪዎች እንኳን ከተቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ቀርቶ በሀገር ውስጥ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አምርቶ ለሕብረተሰቡ ማቅረብ ያልቻለ ኢኮኖሚ ነው ያላቸው።
እንኳንስ በምናመርተው ምርት ተወዳዳሪ ሆነን ዶላር ልናስገኝ ቀርቶ በሀገር ውስጥ እንኳን መሰረታዊ ፍጆታዎችን ማሟላት አልቻልንም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አቅም ወይም የኢኮኖሚው ጥርስ ገና የህፃን በመሆኑ አምራችነቱ ገና ያልተረጋገጠለት ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ራሱን አለመቻሉን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በብድርና በዕርዳታ የሚሠሩ ናቸው። ስለሆነም የካፒታል ክምችት ስለሌለ ኢትዮጵያ በብድርና በዕርዳታ ያለች አገር ነች።
ለምሣሌ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀብቷ አንድ ትሪሊዮን ብር ነው ብለን ብንወስድ፤ ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አለባት። ይህ አጠቃላይ ካለው ሀብቷ ሲሶውን የሚይዝ ነው። ያላት ሀብትና ያለባት ዕዳ ሲወዳደር በዓለም የንግድ መድረክ ላይ ለመወዳደር ቀርቶ ከዕዳ ሥጋት ለመላቀቅ ምን ያህል ዓመት ይወስዳል የሚለው እራሱ እንደሚያሳስብ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያብራራሉ። በመሆኑም እንዲህ ባለው የአገሪቱ ሁኔታ ተወዳዳሪ መሆን አትችልም ባይ ናቸው።
እንደ አቶ ሸዋፈራሁ ማብራሪያ አገራችን መስፈርቱን እንኳን አሟልታ አባል ብትሆን አሁን ያለውን አንፃራዊ ጠቀሜታ (ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ) የግሉን ዘርፍ ድምጥማጡን ያጠፈዋል። ይህንን ለማለት ያስደፈራቸውን ምክንያት ‹‹ እኔ እና አንተ ለመወዳደር ያለን የካፒታል መጠን፣ ክህሎት፣ ቀደም ሲል የነበረን የአምራችነት ታሪክ፣ እነዚህ ሁሉ ይወስናሉ። እነዚህ ሁሉ እኔ ካሉኝ ካንተ ይልቅ እኔ በብዙ እጥፍ የመብለጥ ዕድል አገኛለሁ። ንግድ እንደ ጨዋታ ሕግ (ጌም ቲዎሪ) ነው። የጨዋታ ሕግን ይጠቀማል። አንተ የጨዋታ ሕጉን ተከትለህ በደምብ እየሠራኽው ከሆነ፣ የምታውቀው ከሆነ፣ ዝግጅነቱና ችሎታው ካለህ የምታሸንፈው አንተ ነህ።››
በማለት አስረድተዋል። ለአብነት ያህል ገበያቸውን በተለይ በፋይናንስ ዘርፍ ለዓለም ክፍት ያደረጉ ኬኒያንና ናይጄሪያን አንስተው ሲያብራሩ እንደጠቀሱት ባንኮችን ወደ ግል እንዲዞሩ አድርገው የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ፈቀዱ። በሁለት ዓመታት ውስጥ የኬኒያ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ወደቁ። የተወሰኑ የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን ውጠዋቸዋል። መነሻው ግን የሀብት ክምችት ይፈጠራል፣ የባንክ ዘርፉ ክህሎትን ያዳብራል፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ይፈጠራል በሚል እሳቤ ነበር። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ የናይጄሪያና የኬኒያ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ወደቁ። እንዲያውም አንዱ ግምት የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል በሚል ነበር በራቸውን ክፍት ያደረጉት። ነገር ግን የውጭ ኩባንያዎች የሚያገኙትን ሀብት ቀጥታ ወደ አገራቸው ነው የሚልኩት።
በአገራችንም የውጭ ምንዛሬ እናገኛለን በሚል ምክንያት አቅማችንን ከማይመጥኑ አገሮች ጋር መወዳደር ጉዳቱ የበዛ መሆኑን አቶ ሸዋፈራሁ ያስረዳሉ። ከዚህ ይልቅ የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበትን ሌሎች አማራጮች አሟጠን መጠቀም ያስፈልጋል። ለዚህም በምሣሌነት ያነሱት በዓመት 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መሸለማቸውንና የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ አንዱ ስልት አድርገን አለመጠቀማችንን ነው ። አትሌት መሰረትን እንኳን ብንወስድ በዓመት 200 ሺህ ዶላር ትሸለማለች። ችግሩ የኛ አትሌቶች የሚያገኙትን የሽልማት ገንዘብ ዶላሩ፣ ፓውንዱ ወደ አገር ውስጥ አይገባም። የአትሌቶቹ ማናጀር የሀገር ውስጥ ወኪላቸው አማካኝነት ተመንዝሮ በብር ነው የሚሰጣቸው።
ምርት ገበያችንን ለውጭ ክፍት አድርገን ከግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት መወዳደር ቀርቶ የአትሌቶቻችንን ገቢ ተቆጣጥረን ለአገር ገቢ ማስገባት የሚያስችል ስልት አልዘረጋንም። ይህ ሁኔታ ሲታይ ሌሎች አገራት ካፒታል፤ እውቀት፣ ክህሎት አላቸው፤ ድርጅቶቻቸው በዓለም ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከጀመረ 50 እና 60 ዓመታት ሆኗቸዋል። አንድ ዕቃ የተሠራበት አገር ኢትዮጵያ ከሚለው ይልቅ የሌሎች የአደጉት አገራት ስም ተመራጭ ነው።
ከዚህ አንፃር ሲታይ ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ሌሎች አገሮች አብሶሊዩት አድቫንቴጅ ያመዘነ ነው። ስለዚህ ልክ ሁለት ቡጤኞች ግጥሚያ ሲያደርጉ አንደኛው በአንድ ቡጢ ሌላኛውን በመጀመሪያው ዙር ቢዘርረው እኛ እንደተዘራሪው ነው የምንሆነው። ገና የቤት ሥራችንን ሠርተን አልተወጣንም። እንደውጭው ገበያችንን ክፍት ማድረጋችን ከመጀመሪያው ዙር የምንዘረር መሆናችንን ማየት ይቻላል። እነሱ ጦንቻቸው ፈርጣማ ሲሆን የኛ የፈረጠመ አይደለም። አሁን ባለንበት ሁኔታ የድርጅቱ አባል ብንሆን የእነሱ ምርት የገበያ ሥፍራ እንደምንሆን የአቶ ሸዋፈራሁ ሙሉ እምነት ነው።
የመስኮቹ ተግዳሮት
የአገራችንን የኢንዱስትሪ መስኩን ስንመለከት አብዛኛው ኢንዱስትሪ ቀላል ኢንዱስትሪ የሚባለው ነው። በዚህ መስክ ውስጥ በብዛት የሚመረቱት ምርቶች ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ እንደምግብ ነክ ነገሮች፣ ቀዝቃዛና የአልክሆል መጠጦች፣ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችና ጫማ ናቸው። ቀላል የሜታለርጂና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም እንዳሉ ግልፅ ነው። ይሁንና ግን አገሪቱ ስትራቴጅክ የሚባሉ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪና የማኑፋክቱር ወይም የማሽን ኢንዱስትሪዎች የላትም። ከዚህም በላይ ኃይልን ሊያመርቱ የሚችሉና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኢንዱስትሪዎች የላትም።
በዚህም ምክንያት የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብሔራዊ ባህርይ ያለው ሳይሆን የተዝረከረከና ለመባዛት ወይም ሊስፋፋ የሚችል አይደለም። በተለይም አንድ አገር የማሽን ኢንዱስትሪ ከሌላት እንደ ባቡር ሐዲድና ባቡር የመሳሰሉትን ለአንድ አገር ዕድገት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ልታመርት አትችልም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መካከል የሥራ-ክፍፍልና ውስጣዊ ግንኙነት (Linkages) የለም። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ይህ ዓይነቱ ውስጣዊ ይዘቱ በጣም ደካማ የሆነ የኢንዱስትሪ መስክ ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች ሊዳከም ይችላል። የምርት ክንውን ከቀዘቀዘ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የተወሰነውን የሠራተኛ ኃይል ለመቀነስ ይገደዳሉ። ይህ በራሱ ደግሞ ከሥራው በተባረረው ሠራተኛና በቤተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የሥነ- ልቦና ቀውስ ሊደርስበት ይችላል። የሥራ-አጥ አበል በሌለበት እንደኛ ባለ አገር ከሥራው የተባረረው ሠራተኛ ወደ ድህነት ዓለም መገፍተሩ የማይቀር ጉዳይ እንደሆነ ዶክተር ፍቃዱ ያስረዳሉ።
የእርሻውን መስክ ስንመለከት ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ከእጅ ወደ አፍ በሚመረት የአስተራረስ ዘዴ ላይ የሚመካ ነው። እንደ ዶክተር ፍቃዱ ገለፃ አብዛኛው ገበሬ የመሬቱን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አይጠቀምም። የመግዛት ኃይሉ እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ አዳዲስ የማረሻ መሣሪዎችን በመግዛት ሥራውን በማቃለል ከፍተኛ ምርት ሊያገኝ አይችልም። ስለሆነም የኢትዮጵያ እርሻ ሳይንሳዊ ባህርይ የሌለው ነው ማለት ይቻላል።
ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ስንመለከት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በጥቂት የእርሻ ምርቶች ላይ የሚመካ ሲሆን፣ የቡና ምርት ስልሳ በመቶው የሚሆነውን ይይዛል። የአገሪቱ ገበያ ለውጭ የእርሻ ምርት ውጤት ልቅ ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳው ገበሬው ነው። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው የአውሮፓና የአሜሪካ ገበሬዎች ከፍተኛ የመንግሥት ድጎማ ይደረግላቸዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ምግብ በአጠቃላይ በየአገሮች ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ሲላክ በጣም ርካሽ ነው።
የአገራችን ገበሬ በድጎማ ከሚመረተው የአውሮፓና የአሜሪካ ምርት ጋር ስለማይወዳደር በ90ዎች መጨረሻ ላይ እንዳየነው ገበሬው ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል። በሌላው ወገን ደግሞ ምግብ-ነክ ወዳልሆኑ እንደ ጫት በመሳሰሉት የዕፅ ተከላ ላይ ሊሰማራ ይችላል። ገሚሱ ደግሞ ወደ ከተማ በመሰደድ በሥራ እጦት ይሰቃያል። ከዚህ ባሻገር ከውጭ የሚመጡ የእርሻ ምርት ውጤቶችና የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችንና ሆርሞኖችን ያዘሉ ናቸው። ይህም ማለት ባለፉት ዓመታት ከነፃ ገበያና ንግድ ጋር ተያይዘው የገቡ የምግብ ዓይነቶች ያደረሱት የጤንነት ቀውስ እየተስፋፋና ሰፊውን ህዝብ እያዳረሰው ሊመጣ ይችላል።
የአገልግሎት መስኩን ስንመለከት በጣም የተዝረከረከና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተያያዘ አይደለም። በገበያ ውስጥ የሚሽከረከሩ ምርቶች አብዛኛዎች ከውጭ የሚመጡ ናቸው። ከዚህ ውጭ የአገሪቱን ገበያ የሚቆጣጠረው ኢንፎርማል መስክ እየተባለ የሚጠራው የተሰበጣጠረና ዕርስ በዕርሱ
ያልተያያዘ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መስክ ነው። ስለሆነም ከውጭ የሚመጣው ዕቃና ገበያውን ያጣበበው በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ያዛባና፣ የፈጠራ ሥራ እንዳይኖር ያገደ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ዕድል ቢያጋጥማት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ልትገነባ በፍፁም እንደማትችል ዶክተሩ ከማመናቸው ባለፈ እንደ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲናና ብራዚል፣ እንዲሁም በተቀሩት የመካከለኛውና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚታዩት የህብረተሰብ መዝረክረክና ቀውሶች በአገራችንም ምድር ሊከሰቱ እነደሚችሉ ያስረዳሉ።
የአንድ አገር የዕድገት መሰረት የውስጥ ወይስ የውጭ ገበያ ነው ?
በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አንድን ህብረተሰብ ለመገንባት የሚደረገው ክርክር የተለያየ ዝንባሌ ባላቸው የየአገሩ ምሁራን ሳይሆን፣ የየአገሮች መንግሥታት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ከውጭ የመጡና በህዝቡ ትከሻ ላይ የሚጫኑ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በእኛ ኢትዮጵያውያንም ሆነ በአብዛኛዎቹ አፍሪካ መንግሥታት ዘንድ ካላንዳች ክርክርና ምርምር ከውጭ የመጣን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ባህል ተወስዷል።
ከውስጥ በአንዳንድ ክሪቲካል አመለካከት ባላቸው ምሁራን የተሻለ አስተያየት በሚቀርብበት ጊዜ የቀረበውን ሃሳብ እንዳልሰሙ በመጣል በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተደነገገው ፖሊሲ ተግባራዊ ይሆናል። እንደምናየው ውጤቱ የተወሳሰቡና በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ የማይችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ውድቀት ውስጥ ከቶናል ማለት ይቻላል ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ በበኩሉ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ የንግድ ድርጅቱ አባል ብትሆን ታገኘዋለች ተብሎ የሚታሰበው አንዱ ነገር ታክስ ነው። በእርግጥም ታክስ ይገኝበታል። ነገር ግን ከውጭ ካፓኒዎች የምናገኘው ታክስ እና እነሱ የአገራችንን መፃኢ ዕድል የሚወስነውን ኢኮኖሚ ከመያዝ አንፃር ሁለቱን በማወዳደር የትኛው ጥቅም ለአገራችን ይበልጣል ተብሎ መታየት አለበት። ከዚህ አንፃር ሲታይ ታክስ የማግኘቱ ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ።
ሌላኛው በቅኝ ግዛት የመገዛት መልክም አለው። ለምሣሌ ኬኒያ ናይሮቢ እና ኡጋንዳ ካምፓላ የተባሉት ከተሞች በቅኝ ግዛት የተያዙ ስለሆነ ያ የቀኝ ግዛት አሻራ አርፎባቸዋል ፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ነፃ አገር ስለሆነች ባህሏም የተለየ ነው። የነፃነት ባህል ስላለን ቶሎ ዓለም አቀፋዊ የገበያውን አውድ ለመቀበል ዝግጁነቱ ያለ ስለማይመስል ትንሽ የጥሞና ጊዜ እንደሚያስፈልገን ባለሙያው ያስባል። ለዚህም መንግሥት መጀመሪያ የሥራ፣ የቁጠባ፣ የንባብ፣ የእውቀት ባህል እንዲስፋፉ የባህል አብዮት ማካሄድ እንዳለበት ያምናል።
ከዚያ በኋላ ነው ከተቀረው ዓለም ጋር ለመወዳደር የሚያስችል ቁመና የምንይዘው። ይህን መሰል ቁመና ሲኖረን የውጭ ባለሀብት ወደ አገር እንዲገባ ቢፈቀድ ያንን የሚገባውን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀት መቀበል የሚያስችል የማህበረሰብ አቋም ይገኛል። አሁን እንደሚታየው የባህል ኢምፔራሊዝም ቤቱን ሠርቷል። በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ምርታማ በሆነ ሥራ ላይ ነው ወይ የሚያሳልፈው? ተብሎ ሲታይ የሚንደፋደፉ በጣም ጥቂት ወጣቶች ናቸው። በገበሬውም ዘንድ እንደዚሁ ትንሽ የሚጥሩ አሉ። ሁሉንም ባማከለ መልኩ የአገሪቱን የሥራ ባህል፣ ቁጠባ ባህል የሚያሻሽል ወጥ የሆነ ቅርፅ እንዲኖረው የሚያደርግ እንዲሆን ስረ መሰረቱ መጀመሪያ በመንግሥት መጠረግ እንዳለበት አቶ ሸዋፈራሁ ያስረዳል።
እንደ መፍትሄ
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ያዘጋጁት ምክረ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት መፍትሄ ነው ብለው ያምናሉ። በምክረ ሀሳባቸው መሰረት ኢትዮጵያ የገበሬ አገር ነች። 80 በመቶ በላይ በግብርና 15 እና 20 በመቶው በከተማ የሚኖር ነው። ኢትዮጵያ ያላት ሀብት አንዱ ሰፊ መሬት ነው። ገበሬውም የሚጠቀምበት መሬት ለዕለት ኑሮ ብቻ የሚሆነውን ነው። የማይጠቀምበት መሬት ሰፊ ነው። በመሆኑም አንዱ በእጃችን ያለው መሬት ነው። እንዴት ነው ይህንን መሬት ወደ ምርታማነት ቀይረን የምንጠቀምበት የሚለውን ማሰብ ግድ ነው። ሌላው ‹‹እርካሽ ጉልበት ›› ማለት ከሞራል አንፃር ተገቢ ባለመሆኑ ገና ያለማ የሰው ኃይል በስፋት አለን። ስለዚህ የሰው ኃይላችንን ማብቃት ማልማት ያስፈልጋል። መጀመሪያ የሰው ኃይላችንን አልምተን ወደ መሬታችን ልማት መግባት አለብን። እነዚህን የምርታማነት ዋና ግብአቶች የሆኑትን ሁለት ሀብቶቻችንን በደንብ አቀናጅተን የአግሮ ኢንዱስትሪ በስፋት ማምጣት ስንጀምር ደግሞ ይህ አግሮ ኢንዱስትሪ በከተማ ለሚቋቋሙ አንዳንድ የፋብረካ ኢንዱስትሪዎች መሰረት ይጥላል። መሰረት ይጥላል ማለት እርሾ ይገኛል ማለት ነው። ለምሣሌ ማኑፋክቸር ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ቴክኖሎጂ፣ ክህሎት፣ ካፒታል፣ ማሽን ያስፈልጋል።
እነዚህ ነገሮች ውድ በመሆናቸው የምንገዛበት ገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም መጀመሪያ ግብርና ላይ መሰረት ያደረገ ሀብት ካልፈጠርን የተጠቀሱትን ነገሮች መግዛት አንችልም። እንደዚህ ሀብት ሳንፈጥር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የሄድነው ወደ ብድር እና ዕርዳታ ውስጥ ነው የገባነው። እነዚህም ፕሮጀክቶች በአግባቡ አልተተገበሩም። ምክንያቱም የሰው ኃይል ስላልተገኘ። መጀመሪያ መደላድሉ አልተፈጠረም። መደላድሉ ሳይፈጠር ነው ቀጥታ ወደ ብድር የተገባው። በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ሳይሳኩ ቀሩ አገሪቷም ዕዳ ውስጥ ገባች። ስለዚህም ነው መጀመሪያ ቅድመ ሁኔታዎች ይሟሉ የሚባለው።
ስለ ዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ከማሰባችን በፊት ማሟላት የሚገባንን ነገሮች ማሟላት አለብን። ቤታችንን፣ ጓዳችንን ማሳመር ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን። ብቁ የሰው ኃይል ማዘጋጀት፣ መሬቱን ማልማት፣ መሬቱ ደግሞ የሚለማው በገበሬ ብቻ አይደለም። አቶ ሸዋፈራሁ ያዘጋጁት ምክረ ሀሳብ መሬት እንዴት ይልማ የሚለውን ይመልሳል። አንድ ገበሬ፣ ሁለት የግል ባለሀብት፣ ሦስት መንግሥት ተቀናጅተው በየወረዳው ሼር ካምፓኒ ያቋቁማሉ። በመጀመሪያ እንደ ሙከራ በተወሰኑ ወረዳዎች ሊጀመር ይችላል። ለምሣሌ ገበሬ አንድ ሄክታር ካለው እና 500 ሺህ ብር የሚተመን ከሆነ ይህ የብር መጠን አክሲዮን ውስጥ ትመዘገብለታለች። ከዚያ በኋላ መሬቱ የኔ ነው ማለት አይችልም። ገበሬው አክሲዮኑ ውስጥ ይገባል። እዛውም ይቀጠራል። ይቀጠራል ማለት ደመወዝ ያገኛል። እዚያ ሲሠራ የኢንዱስትሪ አሠራርን ይለምዳል። በዚህ መንገድ ይሸጋገራል። የግል ባለሀብቱ ደግሞ ካፒታልና ማሽኖችን ይዞ አክሲዮኑ ውስጥ ይገባል።
መንግሥትም ብድር በማቅረብና ገበሬው ስለኢንዱስትሪ አሠራር ልምድ ስለሌለው ሀብቱ እንዳይበዘበዝ ሚዛናዊ ለማድረግ መንግሥት የተወሰነ ድርሻ ይይዛል። የሚል ምክረ ሀሳብ ነው ያዘጋጁት። እንደዚህ ሲሆን ግብርናችን እየለማ ሄዶ ወደ ፋብረካ እንመጣለን። ከዛ በኋላ መደላድሉ እየተፈጠረ ሲሄድ ወደ ዓለም ገበያ መሄድ ስላለብን ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት እንገባለን።
በዛን ጊዜ ክፍት ብናደርግ ለመወዳደር አቅም ይኖረናል። እናም የዕድገት ሂደትን የተከተለ መሆን አለበት። ዕድገት ማለት ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ ከቀላል ወደ ከባድ ወደ ውስብስብ የሚሄድ ነገር ነው። ሂደቱን ሳይከተል ስለ ኢኮኖሚ ማረጋጋት ማውራት ሲገባን ስለ ዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት እናወራለን፤ ስለ ግብርና ማውራት ሲገባን ስለፍብረካ እናወራለን። ይህ አካሄድ ተገቢ ባለመሆኑ ቅደም ተከተሉን ጠብቀን መጓዝ እንዳለብን አጠንክረው ይመክራሉ።
በአጠቃላይ እንደ ባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳብ አገራችን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ እራሷን ከውስጥ ማጠናከር አለባት። ወደ ውስጥ ያተኮረና ህዝቡን ሊያሰባስብ የሚያስችልና ጥንካሬም የሚሰጠው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አንድ ቦክሰኛምም ሆነ አንድ አገር ተፎካካሪዎቻቸውንና ጠላቶቻቸውን በደንብ ሊቋቋሙና በአሸናፊነት ሊወጡ የሚችሉት በመጀመሪያ ራሳቸውን ሲያዘጋጁና ጥንካሬ ሲያገኙ ብቻ ነው። ቦክሰኛው ካለአቅሙ በክብደትም ሆነ በጥንካሬ ከሚበልጠው ጋር ዝም ብሎ የውድድር መረብ ውስጥ ገብተን እንታገል አይልም። አቅሙን ማወቅ አለበት። አንድ አገርም እንዳትወረር ከተፈለገ በደንብ የተደራጀና የተማረ የወታደር ኃይል ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ መሰረት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ትግል እናድርግ ማለት ራስን ለጠላት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።
ዘመን መፅሄት መጋኒት 2011
በሣሙኤል ይትባረክ