አንድ ለእናቱ በሆነው የሕዝብ መታጠቢያ ወትሮም ወረፋው ከበድ ይላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየባሰበት ነው። ለመታጠብ ከተለያዩ ስፍራዎች የሚመጡ ተገልጋዮች እንግልት እየበዛባቸው ክፉኛ ያማርራሉ። ከዓመታት በፊት አገልግሎቱ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የሞከረው የፍል ውሃ አስተዳደር የኮምፒውተር ሥርዓት ከዘረጋ በኋላ በር ላይ የአገልግሎት ክፍያ ፈጽሞ ደረሰኝ የሚቀበል ደንበኛ ምን ያህል ሰው እንደሚቀድመው ያውቃል። በእርግጥ በስክሪኑ ላይ የሚነበበው መረጃና ውስጥ ተገብቶ የሚገኘው እውነታ የሚቃረኑበት ጊዜ ቢበዛም አሠራሩ የሰለጠነ ሆኗል።
ከሰሞኑ ደግሞ ሲስተሙ እየተስተጓጎለ አገልግሎቱ ወደ ኋላ ተመልሷል። የደንበኞች ሮሮ ከወረፋው ይጀምራል። ለመታጠብ የሔደ ሰው ሙሉ ቀን ወረፋ በመጠበቅ የሚባክንበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ወረፋውን ካልታገሰ “ሌላ ቀን መጥተህ ታጠብ” ተብሎ ካስተባባሪዎች ምክር ቢጤ ይሰጠዋል። ገላን መታጠብ በራስ ምርጫና ዕቅድ የሚከወን መሆኑ ተረስቶ እንደ ቀልድ “ነገ ብትመጣ ጥሩ ነው፤ በዚሁ ቲኬት ትስተናገዳለህ” መባል ብስጭት ይፈጥራል።
«እንዴትʔ» ብሎ የሚከራከር ተገልጋይ ካለ “እኛ ምን እናድርግ” ከሚሉ ሠራተኞች ጋር አተካራ ከመግጠም ውጭ ምንም አይተርፈውም። ብዙ ጊዜ ትዕግስታቸውን ያጡ ተገልጋዮች ለጸብ ሲጋበዙ አይተናል። «የከፈልነው ገንዘብ ይመለስልን» ብለው ከካሸር ጋር ዱላ ቀረሽ አምባ ጓሮ ሲከፍቱ “ቫት ከፋይ ነን፤ አንዴ ለተቆረጠ ደረሰኝ ብር አንመልስም” እያሉ ሠራተኞች ንዴታቸውን ተቋቁመው ይመልሳሉ። ውስጥ ደምበኛን ተቀብለው የሚያስተናግዱትም በሚያማርሩ ሰዎች ተከበው ይጨነቃሉ። መፍትሔ ያጡ ተገልጋዮች ቁጣቸውን ይዘው እስከ ሥራ አስኪያጁ ድረስ በመሔድ አቤቱታቸውን በጩኸት ያቀርባሉ።
ወረፋውን ታግሶ መታጠብ የጀመረ ሰው ሳሙና ከተለቀለቀ በኋላ ቀዝቃዛ ውሃ ሊቋረጥበትም ይችላል። ይህ ገጠመኝ የደረሰበት ደጀኔ ፈጠነ “ፈጣን ሻወር ይሻለኛል ብዬ፣ ገንዘብ በመጨመር ዓባይ ከተባለው ቤተ ወሸባ ብሔድ ወረፋ ሆኖ ጠበቀኝ። ምርጫ ስላልነበረኝ ጠብቄ ገባሁ። ሆኖም እየታጠብኩ፣ ቀዝቃዛ ውሃው ስለጠፋ ቃጠሎው አንገበገበኝ። በሩን እየደበደብኩ ኡ-ኡ ስል አስተናጋጇ ውጣ አለችኝ።
እንዴት ብዬ ልውጣ! … ግድ ነውና የተወሰነ አረፋዬን አደራርቄ በፎጣ ተጠቅልዬ ወጣሁ። ወደ ሌላ ብሎክ ልብሴን አቃቅፌ እየሮጥኩ ሔድኩ፤ አስተናጋጇ እግዜር ይስጣት እየመራች ወሰደችኝ። ቅድም «ውሃ የለም» የተባለበት ቤት ውስጥ ገባሁና ተለቃልቄ ወጣሁ፤ አሁንም እንዳይጠፋ ስለሰጋሁ ቶሎ ብዬ ጨረስኩ” ሲል አጫውቶኛል።
ተደጋጋሚው የውሃ መጥፋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መከሰቱ የድርጅቱ የአስተዳደር ሠራተኞች ይመሠክራሉ። አልፎ አልፎ ይከሰት የነበረው የውሃ መጥፋት አሁን ዘወትር የሚያጋጥም ሆኗል። ችግሩ የፍል ውሃ ድርጅት ሳይሆን የውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤት እንደሆነ ከተራ ሠራተኞች እስከ አስተዳደር ኃላፊዎች ደጋግመው ለማስረዳት ይሞክራሉ።
“ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለድርጅታችን ከሚያስፈልገው የውሃ መጠን ሃምሳ በመቶውን ቀንሷል፤ በዚህም ምክንያት የሌሊት አገልግሎት ተቋርጧል። የቀኑም ቢሆን ሁል ጊዜ ላይኖር ይችላል። ምክንያቱም ዘጠና ዲግሪ የሚሞቀው የተፈጥሮ ፍል ውሃ ካልተበረዘ ሰው ገላ ላይ ቢያርፍ ከባድ ጉዳት ያደርሳል” ሲሉ የገበያ ጥናት ኃላፊው አቶ ከበደ ወርቁ ይገልፃሉ።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ገብረ ፃድቃን ዓባይም “ፍል ውሃው ቢጠፋ ተጠያቂ መሆን እንችላለን፤ አሁን ግን የቸገረው ከውሃና ፍሳሽ የምናገኘው ቀዝቀዘዛ ውሃ ነውና ጥፋቱ የእኛ አይደለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
የውሃው ጨርሶ መጥፋት እንዳለ ሆኖ አንዳንዴ ግን ግራ የሚያጋባ ነገር እንደሚፈጠር ተገልጋዮች ይገልፃሉ። ገንዘብ ተቀባዮች «ውሃ ያለው አንድ ብሎክ ብቻ ነው» ብለው ሁሉንም ተገልጋይ ወደ አንድ ቦታ ይመድቡትና መጨናነቅ ይፈጠራል። አንድ ብሎክ ላይ ከሁለት መቶ በላይ ተጠቃሚዎች ተመድበው ወረፋ የሚጠብቁበት ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜ ተገልጋዩ ማማረር ይጀምራል። መጀመሪያ ላይ ሠራተኞች የደንበኛን ማማረር ችላ
ብለው መደበኛ የመስተንግዶ ሥራቸው ላይ ያተኩራሉ። አስተናጋጆች ምንም ሊያደርጉለት እንደማይችሉ የተረዳው ተገልጋይ ምሬቱን ይዞ ወደ በላይ አካላት ይሔዳል።
የተገልጋይ ቅሬታ መስማት ልምድ የሆነባቸው ሱፐርቫይዘሮች ዘና ብለው «እስኪደርሳችሁ በትዕግስት ጠብቁ፤ ካልፈለጋችሁ ወይም ከቸኮላችሁ ሌላ ጊዜ መምጣት ትችላላችሁ» እያሉ ምሬቱን ወደ ብሶት ካሳደጉት በኋላ ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ሲል «ውሃ የለባቸውም» የተባሉ ብሎኮች እየተከፈቱ እንዲያገለግሉ ያደርጓቸዋል። ወዲያው አንድ ቦታ የተከመረው ሕዝብ ወደ ሌሎች ብሎኮች ይሰራጭና በቅጽበት ወረፋው ይጠፋል። በዚህ ሒደት አንደኛ ማዕረግ ለመታጠብ ከፍ ያለ ገንዘብ ከከፈሉት መካከል ሦስተኛ ማዕረግ የሚገቡ አሉ። ወረፋው ስላማረራቸው የገንዘብ ኪሳራው ብዙም ሲያስጨንቃቸው አይታይም።
የዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መነሻ የቀዝቃዛ ውሃ መጥፋት ነው ያሉት ኃላፊዎች ከሦስት የተለያዩ መስመሮች የሚመጣው ውሃ “ስርጭቱ የተዘበራረቀና መቼ ጠፍቶ መቼ እንደሚመጣ ለመገመት የሚያዳግት ነው፤ አንዱ መስመር ሲቋረጥ በሌሎቹ እንጠቀምና ከዚያ መስመር ውሃ የሚቀበሉትን ብሎኮች እንዘጋቸዋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን ውሃ ያልነበራቸው መስመሮች ድንገት ይመጣላቸዋል። ውሃ የለም ብለን ብዙ ሰው ከመለስን በኋላ ወዲያው የሚመጣበት ጊዜም አለ” ሲሉ የገበያ ጥናት ኃላፊው አቶ ከበደ ወርቁ ይገልፃሉ።
ከፍል ውሃ ድርጅት በዓመት አሥራ ሦስት ሚልዮን ብር የሚቀበለው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ትልቁን ደንበኛውን በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረ ፃድቃን ይገልፃሉ። ከቦርዱ ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ ያደረጉት ጥረትም ስላልተሳካ የቀራቸው ነገር ሌሎች መፍትሔዎችን ማሰስ ሆኗል። “የውሃና ፍሳሽ ባለ ሥልጣን መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ እኛጋ የቦርድ አባል እንዲሆኑ ተደርጎ መፍትሔ ለማምጣት ተሞክሯል፤ ውሃና ፍሳሽ ከድርጅታችን ፍል ውሃ ተቀብሎ በማቀዝቀዝና በማጣራት ቢጠቀምበት እዚህ ያለው የውሃ ሀብት ግማሽ አዲስ አበባን የሚያዳርስ እንደሚሆን ተማምነን የነበረ ቢሆንም ወደ ተግባር ግን አልተገባም” ሲሉ ችግሩን ለመቅረፍ የሔዱበትን ርቀትና የገጠማቸውን ማነቆ ይገልፃሉ።
“የውሃ ሥራዎች ዲዛይን ድርጅት ጋር በመተባበር፣ እንዲሁም ከፍተኛ የጂኦሎጂ ባለሙያ በመቅጠር በአካባቢው የሚገኘውን የውሃ ሀብት አስጠናን። ቀዝቀቃዛ ውሃ የሚባል ነገር በጊቢያችን ውስጥ ሊገኝ አልቻለም። ትንሽ ራቅ ብሎ በአምባሳደር፣ ግዮንና ዘውዲቱ ሆስፒታል አካባቢ ግን ይገኛል። ከዘውዲቱ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት እነሱ ለፊዝዮቴራፒ የሚያስፈልጋቸውን ፍል ውሃ ከእኛ ሊወስዱ፣ እኛም በጊቢያቸው ውስጥ የሚገኘውን፣ የማይጠቀሙበትን የጉድጓድ ውሃ ልንጠቀም ተስማምተን ነበር” ፡፡
ሌላው አማርጭ ደግሞ ያላለቀ ጥናትን ታሳቢ ያደረገው ነው። “ግዮንና ፍል ውሃ ተዋሕደው በአዲስ አበባ መስተዳድር ሥር ይሆናሉ የሚል ያላለቀ ጥናት ስለነበር፤ ከግዮን ሆቴል ተመሳሳይ ልውውጥ ለማድረግም ሌላ አማራጭ በሐሳብ ደረጃ ይዘናል። በግቢያችን ውስጥ መሥራት የምንችለውን የማስፋፊያ ሥራ ሠርተናልና ተጨማሪ ክፍት ቦታ የለንም። ከግቢ ውጭ እንድናስፋፋ ቢፈቀድና አምባሳደር አካባቢን ብንጠቀም መፍትሔ እንደሚኖረን ጥናታችን ጠቁሟል”፡፡
ሥራ አስኪያጁ የተጋረጠባቸውን ተግዳሮት ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ብዙ ቢሆንም፤ ከበላይ አካላት አስፈላጊው ውሣኔ ስላልተሰጠ ጥረታቸው መና እንደሆነ በማማረር ይገልፃሉ። አሁን ያለው የፍል ውሃ አገልግሎት ሲመሠረት የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ሚልዮን የማይሞላ የነበረ ሲሆን የሕዝብ ብዛቱ በብዙ እጥፍ ሲጨምር የሚፈጠረው ክፍተት ከባድ መሆኑ አይቀርም። የማስፋፊያ ሥራዎች ቢከናወኑም ከሕዝብ ቁጥር እድገቱ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን አልቻለም። ከማስፋፊያ ግንባታዎች በተጨማሪ አገልግሎቱን በማዘመን የሰው ኃይል ጭማሪ ተደርጎና ተዛማጅ አገልግሎቶችም ተፈጥረው በተወዳዳሪነት ስኬትን ለመቀዳጀት ጥረት ቢደረግም፤ ይህ ሁሉ ጥረት ዛሬ ላይ የተፈጠረውን ከፍተኛ ፍላጎት የሚያስታግስ አልሆነም። ከሕዝብ ብዛት መጨመር ሌላ የተጠቃሚዎች ፍላጎትም እያደገ ይገኛል። በተለይ በከተማው ውስጥ ውሃ መቆራረጥ እየበዛ ሲመጣ ገላውን እቤቱ መታጠብ ያልቻለው ሕዝብ አማራጩ ወደ ፍል ውሃ መምጣት ነው።
በዚህም የተነሣ የተጠቃሚዎች ቁጥር በቀን እስከ ስምንት ሺ የሚደርስ ሲሆን፤ በበዓላት ቀንም እስከ አሥራ አምስት ሺ ያድጋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ በቀን ይህን ያህል ደንበኞችን በማስተናገድ የፍል ውሃ ድርጅት ግንባር ቀደሙ ነው” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ “አየር መንገድም ሆነ ሌላ ተቋም በየቀኑ ይህን ያህል ሰው አያስተናግድም፤ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ደንበኛ ማስተናገድ ከባድ ስለሆነ አገልግሎታችን ውስጥ አለመናበብና አንዳንድ ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እኛም ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሚቻለንን ከማድረግ አልቦዘንም። በእኛ አቅም ሊፈታ የሚችለውን ብንፈታው ከእኛ ውጭ የሆኑ ችግሮች ግን የበለጠ አልፈን እንዳንራመድ አድርጎናል። በዚህም የተነሣ በየቀኑ እየመጣ የሚያማርርብን ደንበኛ እያሳቀቀን ነው” ብለዋል።
የፍል ውሃ አገልግሎት ተጠሪነቱ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ነው። ተጠሪነታቸው ለዚህ ተቋም የሆኑ ድርጅቶች ነግደው በማትረፍ ለመንግሥት ደህና ገቢ እንዲያስገቡ ይጠበቃል። የፍል ውሃ አገልግሎትም ከዓመታት በፊት ከአንድ ሚልዮን ተሻግሮ የማያውቅ ትርፉን አሳድጎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰላሳ ሚልዮን ማስገባት መቻሉን ሥራ አስኪያጁ በኩራት ይገልፃሉ። እኔ ግን የትርፍ ምጣኔው በቂ አልመሰለኝምና “በቀን በአማካይ እስከ ስምንት ሺ ደምበኛ የሚያስተናግድ የንግድ ተቋም ትርፉ ለምን ሠላሳ ሚልዮን ብቻʔ” ስል ጠይቄአለሁ። የሥራ አስኪያጁ መልስ ወጪው ስለሚበዛ የሚል ነበር። “ወጪው ብዙ ነው፤ ፎጣው፣ ሳሙናው፣ መታሻ ቅባቱ፣ የጥገና ሥራው ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመን ስርቆትም ወጪያችንን አንሮታል። በትንሽ ብር ለመታጠብ የገባ እንግዳ በውድ ዋጋ የሚገዛ የገንዳ ክዳን ደብቆ ይወጣል። የሻወር ወንፊትም ብዙ ጊዜ ከሚሰረቁ ቁሶች አንዱ ነው። ደንበኛ ደግሞ ተገልግሎ ሲወጣ ቦርሳውን እየከፈቱ መፈተሽ ከሆቴል ሥነ ምግባር ውጭ ነው፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ቸግሮናል”
ፍል ውሃ አገልግሎት ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ ድርጅት ነው። አስፈላጊው ማስፋፊያ ቢደረግበት እና ተጨማሪ አገልግሎቶች ቢካተቱበት ገቢውን በብዙ እጥፍ ማሳደግ ይቻላል። ከገንዘባዊ ትርፉ ሌላ የከተማ ንፅህና መስጫ ለአንድ ከተማ ዘመናዊነትና ጤነኝነት ወሳኝ ጉዳይ ነውና ልዩ ትኩረት ይሻል። የፍል ውሃን ነገር ልዩ የሚያደርገው ለራሱ ችግሮች መፍትሔውን በጉያው የያዘ መሆኑ ነው። የከርሰ ምድር ውሃው በተፈጥሮ ፈልቶ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ በዚህ ቀን ሊቋረጥ ይችላል ተብሎ የሚያሰጋ አይደለም። የቀዝቃዛ ውሃ ፍላጎቱም ከግቢው ብዙ ሳይርቅ
ሊገኝ እንደሚችል ድርጅቱ ባስጠናው ጥናት ተረጋግጧል።
ራሱን ፍል ውሃውን አከማችቶ በማቆየት ማቀዝቀዝም አንድ መፍትሔ ስለሆነ ችግሩ የተራቀቀ ሳይንስ የሚሻ አልነበረም። በርግጥ አስተዳደሩ መፍትሔዎቹን በባለሙያ አስጠንቷል፤ ሙከራም አድርጎ ችግሩን በመጠኑ ቀርፏል። ግን የተጠናውንና በባለሙያ የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ችግሩ በዘላቂነት ተቀርፎ ደንበኞችን እፎይ ሊያስብል አልቻለም። ለዚህ ችግርም ጣቱን የሚጠቁመው ወደበላይ አካላት ነው።
በርግጥ በበላይ የመንግሥት አካላት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነውና ጠቀም ያለ ገቢ የሚያስገባው አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት ማግኘት እንዳልቻለ መገንዘብ አያዳግትም። ተገልጋዮች ለከፈልነው ክፍያ አገልግሎት ይሰጠን ሲሉ አስተናጋጆችን ያስጨንቃሉ። አስተናጋጆች ጩኸቱ ከአቅም በላይ ሲሆንባቸው ወደ ሱፐርቫይዘሮች ይጠቁማሉ። ሱፐርቫይዘሮች የበላይ አመራሮችን ያማርራሉ። አመራሩ ደግሞ አንቆ የያዘኝ ችግር ከቦርዱ በላይ ባለ የመንግሥት አካል ሊቀረፍ የሚችል እንጂ እኔ የሚጠበቅብኝን ሠርቻለሁ ይላል።
ውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤት ምን እንደሚል ለመስማት ደወልኩ፡፡ በተለመደው ኃላፊነትን ወደሌላ ቢሮ የመግፋት ልማድ አንዱ የሌላውን ቢሮ ስልክ እየሰጠኝ በመጨረሻ የኮሚውኒኬሽን ኦፊሰር ደረስኩ፡፡ የውሃ እና ፍሳሽ ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር ወይዘሮ ሠርካለም ጌታቸው መጀመሪያ “እኛ ስለፍልውሃ ምን አገባንʔ” ሲሉ ጥያቄውን ወደ እኔ መለሱት፡፡ “ቀዝቃዛ ውሃ የሚያገኙት እኮ ከእናንተ ነው” ስል አስረዳሁ፡፡ “ያው እንደሚታወቀው በከተማው ሁሉ ያለ ችግር ነው” አሉኝ፡፡ “ፍል ውሃ ግን በዓመት አሥራ ሦስት ሚልዮን ብር የሚከፍል ልዩ ደንበኛ ከመሆኑም በላይ ለሕዝብና ከተማ ንፅህና ወሳኝ እኮ ነው” አልኳቸው፡፡ “አዎ ነው፤ ለመሆኑ ከመቼ ጀምሮ ነው ተቋረጠብን ያሉትʔ” ሲሉ ተጠያቂዋ ጠያቂ ሆነው ይመረምሩኝ ጀመር፡፡ “አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ከደረሰ አንድ ዓመት አካባቢ ሆኖታል” ስል መመለሴን ቀጠልኩ፡፡ “እንዴ ምን ማለታቸው ነው! ዓመት ሙሉ አልሠሩምʔ” የደወልኩት እንደጋዜጠኛ ልጠይቅ ይሁን በኮስታራ ኦፊሰር ልመረመር ትንሽ ግር ቢለኝም በትዕግሥት ማስረዳቴን ቀጠልኩ፡፡ “ሙሉ በሙሉ አልተቋረጠም፤ ሆኖም ውሃ የሚጠፋበት ጊዜ እየበዛ ስለተቸገሩ የሌሊት አገልግሎት አቁመዋል” ደግሞ ሌላ ምን ሊጠይቁኝ ይሆን እያልኩ ስጠብቅ “በቃ ጉዳዩን አጣርቼ እደውላለሁ፡፡ ነገሩን ገና አሁን ከአንተ መስማታችን ስለሆነ ለማጣራት ጊዜ ያስፈልገናል” ብለው አሰናበቱኝ፡፡
በነጋታው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ ከመሥሪያ ቤታቸው የአራዳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ጋር በስልክ እንድገናኝ አደረጉ፡፡ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ እጀታ የፍል ውሃ አገልግሎት በሳምንት ሃምሳ ሺህ ኪውቢክ ሜትር ውሃ በመጠቀም ቀዳሚ ደንበኛ መሆኑን አስታውሰው ይህ መጠን ከአንድ ክፍለ ከተማ ጋር የሚቀራረብ ፍጆታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ዘመን ከከተማው ስፋት፣ ከሕዝቡ ብዛት እንዲሁም ከግንባታዎች ብዛት የተነሣ የውሃ አቅርቦትን ማጣጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከሁሉም ደንበኞች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ድርጅቶች ድረስ – ፍጆታ ለመቀነስ እንደተገደዱ አስረድተዋል፡፡
“ካለን ላይ የፍል ውሃ አገልግሎት ብዙ ውሃ የሚፈልግ በመሆኑ በሚቻለን መጠን ትልቁን ድርሻ እንዲወስድ አድርገናል” በማለትም የውሃ አቅርቦቱ መቀነሱን አረጋግጠዋል፡፡ “አሁን ባለው ችግርም ሌላ ተጨማሪ መስጠት አንችልም” በማለት ለመፍትሔው ፍል ውሃ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀም በውይይት የተሰጠውን አቅጣጫ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ከሆነ የውሃው መጠን በቂ እንደማይሆን ከሁለት ዓመት በፊት ታውቆ የፍል ውሃ አስተዳደር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ መላ እንዲፈጥር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ “ስለዚህ ከውሃና ፍሳሽ ባለ ሥልጣን መሥሪያ ቤት ጋር ተነጋግሮ ፈቃድ በመቀበል የራሱ የውሃ ምንጭ መፍጠር አለበት” ሲሉ ከውሃና ፍሳሽ ዋና ባለ ሥልጣን ፍቃድና የቴክኒክ ድጋፍ በመቀበል የራሳቸውን የውሃ ግድብ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ከሁለት ዓመት በፊት ተነጋግረው የደረሱበትን የጋራ ውሣኔ ተግባራዊ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ገልፀዋል።
በኤጀንሲው የሚበዘበዙ የፍል ውሃ ሠራተኞች
በፍል ውሃ አገልግሎት ከሚንገላቱ ተገልጋዮች ባልተናነሰ የሠራተኞች ምሬትም ጎልቶ ይሰማል። ወረፋ በመጠበቅ ላይ ያለ ሰው እግረ መንገዱን ከሠራተኞች ጋር ቢነጋገር ምሬታቸውን አይደብቁትም። በመቅረፀ ድምፅ ለመናገር ግን ይፈራሉ። አስተያየት የሠጡኝ ሠራተኞች መቅረፀ ድምፅ ሲቀርብ ወዲያው ያፈገፍጋሉ። በተለይ የጽዳት ሥራን የሚሠሩት የደሞዛቸው ማነስ የፈጠረባቸውን የሥራ ተነሳሽነት መቀነስ ለመግለፅ አያቅማሙም። የስቃያቸው መንሥኤ የሚያያዘው በመካከላቸው በገባው ቀጣሪ ወኪል ነው።
የለበሱት የሥራ ቱታ “ቤስት የቅጥር ወኪል” የሚል ጽሑፍ ታትሞበታል። ይህ ድርጅት ሠራተኞቹን ቀጥሮ ለፍል ውሃ ድርጅት አቅርቧል። በወኪል የተቀጠሩ ሠራተኞች ማንኛውም ዓይነት የሥራ ግንኙነት የሚፈጽሙት በዚሁ ወኪል በኩል ስለሚሆን ሥራ ከሚሠሩበት ድርጅትጋር ቀጥታ ግንኙነት የላቸውም። የፍል ውሃ አስተዳደርም ደሞዛቸውን የሚልከው በዚሁ ወኪል አማካይነት ነው። ወኪሉ ከትንሽዋ የሠራተኞች ደሞዝ ላይ ሲሦውን አስቀርቶ ቀሪውን ይከፍላቸዋል።
በርግጥ ይህ አሠራር የቅጥር ወኪሎች ጣልቃ በሚገቡባቸው ተቋማት ሁሉ የታወቀና የተለመደ ነው። የፍል ውሃ ድርጅትን የሠራተኛ ቅጥር ልዩ የሚያደርገው ይህን በወኪል የመቅጠር አሠራር የተገበረው በረዳት ሠራተኞች (Supportive stuff) ላይ ሳይሆን በዋና ሠራተኞቹ ላይ (Line stuff) መሆኑ ነው። የጽዳት ሠራተኞች በሌሎች ድርጅቶች ረዳት ሠራተኞች ቢሆኑም ለፍል ውሃ አገልግሎት ግን ዋናውን ሥራ የሚሠሩ በመሆናቸው ድርጅቱ ሊያሰለጥናቸውና የጽዳት አሰጣጡን ሙያዊ በሆነ መልኩ ሊያሳድገው ሲገባ በተቃራኒው ሥራውንም ሆነ ሠራተኞቹን እንደ ትርፍ ቆጥሮ በውክልና ሊያስተዳድራቸው ባልተገባ ነበር።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በምን የተነሣ ይህ ያልተለመደ አሠራር ሊተገበር እንደቻለ ጠየኳቸው። እሳቸውም ሲመልሱ የሠራተኛን አያያዝ አስመልክቶ ትርፍና ኪሣራችንን (ኮስት ቤኔፊት አናሊሲስ) ሠራን። በቀጥታ ቋሚ አድርገን ብንቀጥራቸው ልናወጣ የምንችለው ወጪ በጣም ብዙ ነው። ምግባቸውን፣ ትራንስፖርት፣ የጤና ኢንሹራንስና ሌላም ብዙ ግዴታዎች ይኖራሉ። በቅጥር ወኪል በኩል ሲሆን ግን ይህ ሁሉ አይኖርም። ይህ ታስቦ የሠራተኞቹ ቅጥር በወኪል እንዲሆን ተደረገ የሚል ምክንያት አቅርበዋል።
የሠራተኞችን መብትና ጥቅም በማሟላት የኑሮ ደረጃቸው እንዳይሻሻል የሚያደረግ የአሠራር ሥርዓት በመከተል ሠራተኞችን መበደል ከአንድ ድርጅት እንደማይጠበቅ እሙን ሆኖ ሳለ ይህ ነገር ከመንግሥት ተቋም ለዚያውም ጠቀም ያለ ትርፍ ከሚያገኝ ተቋም ውስጥ መፈፀሙ ግር ይላል። በርግጥ ስህተቱን አስተዳደሩ የተረዳው ይመስላል። ከዚህ በኋላ ከሴቶችና ህፃናት ቢሮ ጋር በመተባበር ሥራ የሌላቸውን ሴቶች ለመቅጠር ማሰባቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። በርግጥ ቅጥሩ በሴቶችና ህፃናት ቢሮ በኩል መሆኑ ተቆራጩን ቢያስቀረውም ድርጅቱ አሁንም በቀጥታ ቀጥሮ ማስተዳደር አለመፈለጉ አሁንም ቅሬታውን የሚያስቀጥል መሆኑ አይቀርም።
የሠራተኞቹ መብት እንዴት ይታያል የሚለውን ለማወቅም ወደ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደወልኩ። መረጃ ለመስጠት የቀረቡት ግለሰብ ነገሩን ከሰሙ በኋላ “እኛን አይመለከትም፤ የአዲስ አበባ አሠሪና ሠራተኛ ኤጀንሲ ነው ኃላፊነቱ›› ብለው የኃላፊውን ስልክ ሰጡኝ። በተደጋጋሚ ሞከርኩ ስልኩ አይሠራም።
የፍል ውሃ አገልግሎት ከጤና፣ ከከተማ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ ከመዝናኛ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እጅግ ወሳኝ አገልግሎት ነው። ከዚሁም ጋር ለመንግሥት የሚያስገባው ገቢ አገልግሎቱን ይበልጥ ወሳኝ ያደርገዋል። ሆኖም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ሠራተኞች አያያዝ ድረስ በችግር ተተብትቧል። የድርጅቱ አቅም ጎልብቶ ሥራው ተፈላጊውን ጥቅም እንዲሰጥ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል። በተለይ ገንዘቡ ሳይጠፋ የላባቸውን ምንዳ በተገቢው መንገድ እንዳያገኙ ተከልክለው በቅጥር ወኪል የድለላ ተግባር የሚበዘበዙ ሠራተኞች ሁኔታ ሊሻሻል ይገባዋል። በገዛ አገራቸው የጤና ኢንሹራንስና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ማጣታቸውም ሆነ የደሞዛቸውን አንድ ሦስተኛ ለአገናኝ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸው የሚማቅቁበት አሠራር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011
በዳዊት አብርሃም