ለመጀመሪያ ጊዜ የአድዋ ድል በዓል የተከበረው ድሉ በተገኘ በሰባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም ነበር። በዚያን በዓል ራሳቸው የድሉ ተዋንያን ዐፄ ምኒልክ እና በርካታ የጦር መሪዎችም ስለነበሩ የጦርነቱን መራራ ተጋድሎ እና በጦርነቱ የተሰው ኢትዮጵያውያንን በማሰብ ጭምር ነበር።
ሰባተኛ ዓመት የተመረጠበት መነሻም ኃይማኖታዊ ነበር፤ እቴጌዪቱም ሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ ለዘማቾቹ ቃል በገቡት መሠረት በጦር ሜዳ ተጋድሎ የተሰውትን ሁሉ ቁርባናቸውን ለማውጣት ፍትሐታቸውን እንዲፈፀም ለማድረግ ነበር። ይህ በሰባተኛ ዓመትም የማድረግ ልማድ ስላለ ያነን መነሻ ያደረገ ነበር።
ንጉሡ ግን የሀገር አንድነትን ማጠናከሪያ አንድ አጋጣሚ ለማድረግ ጥረውበታል። ስለዚህ በደማቅ ወታደራዊ ሰልፍ እንዲከበር ወሰኑ።
በዓሉ እንዲከበር የተወሰነበት ቀን የካቲት 23 ነበር። የዚህም ምክንያቱ ድሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት ጭምር የተገኘ ነው የሚል እምነት በመላው ተዋጊዎች ዘንድ ተይዞ ስለነበር ነው። አስቀድመው ንጉሡ ለበዓሉ ዝግጅት ለማድረግ እንዲቻል አዲስ አበባ ላሉት፣ በየአውራጃው ለሚገኙት መኳንቶቻቸው መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በመልዕክታቸውም በዓሉ የሚከበርበትን ዓላማ ለመኳንቶቻቻው ግልጽ ለማድረግ ሞክረዋል።
‹‹ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና እኔም ይሄንን በዓል እንዲህ አድርጌ ማክበሬ፣ እናንተንም ማድከሜ እግዚአብሔር በቸርነቱ ሰባት ዓመት ሙሉ በዕረፍት እና በጤና ስላኖረን ስለዚህ ነገር ማክብር ይገባናል ብዬ ነው እንጂ ለጥጋብ እና ለትዕቢት ሠራዊት በዛ፣ ነፍጥ በረከተ ለማለት አይደለም። ነገር ግን በዚህ በየስራው ነገር በእንጨት በድንጋይ የማደክማችሁን አትመልከቱ … ይልቁንም እኔን ስታጡ /ስሞት/ ብርቱ ኃዘን ያገኛችኋል። አሁንም ወንድሞቼ ወዳጆቼ የማናውቀው መከራ እንዳይመጣብን በዚህ ነገር ደስ ይበላችሁ። …. እግዚአብሔር እንዳይለየን አብሮ እንዲያስበን እኔም አዝናለሁ፤ እናንተም እዘኑ። ››
በዓሉ የተከበረበት ዋነኛው ሥነ ሥርዓት የወታደራዊ ሰልፍ ትርዒት በማሳየት ነበር። በዚያም መሠረት 270 ሺህ የሚደርሱ በየሀገረ ገዥዎቹ የሚመራ ሠራዊት በበዓል አከባበሩ ሰልፍ አሳይቷል። ከቦታው ርቀት የተነሳ የሐረር እና ውጋዴን፣ ከጨጭሆ በላይ የባብሎስ ወፍላ፣ የትግራይ፣ የጎጃም ሀገረ ገዥዎች ያዘጋጁአቸው ወታደሮች አልተገኙም ነበር።
በዓሉ እጅግ በድምቀት የተከበረ ነበር። ሰልፉ ዛሬ የምኒልክ ሐውልት በቆመበት አካባቢ ከቤተክርስቲያኑ ፊት ለፊት ነበር። በዚያም ንጉሡን ጨምሮ መላው የክብር እንግዶች ሁሉ የሚቀመጡበት የክብር ስፍራ ተደልድሎ፣ በልዩ ልዩ ሥጋጃ እና ምንጣፍ ሲለብስ ሰነበተ። ይሄ ለመኳንንቱ መቀመጫ ለባለሟሎች መቆሚያ የተዘጋጀው ሥፍራ ርዝመቱ ሁለት መቶ ክንድ ስፋቱ መቶ ሃምሳ ክንድ እንደነበር የንጉሡ ጸሐፌ ትእዛዝ በንጉሡ ዜና መዋዕል ከትበዋል።
አለቃ ገብረሥላሴ በዚያም የክብር ስፍራ ንጉሡ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ካባ ላንቃ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ በዙፋን ተቀምጠው ነበር። እቴጌ ጣዪቱ፣ ግብጻዊው አቡነ ማቴዎስ፣ እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች እና መኳንንቱ በክብር ስፍራቸው ተቀምጠው ነበር።
ከዚያም የታየው የሰልፍ ትርዒት እጅግ ደማቅ ነበር። በዚያም የመድፉ፣ የጠመንጃው ተኩስ፣ የፈረሱ ኮቴ፣ ጎራዴና ሰይፉን ይዞ በፉከራ እየፎከረ በንጉሡ ፊት የሚያልፈው የወታደሩ እርምጃ ያስነሣው አቧራ ፀሐይዋ ጋርዷት እንደነበር የንጉሡ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ያብራራሉ።
የንጉሡም ጠባቂ (ዘበኛ ሠራዊትም የራሱን የሰልፍ ትርዒት አቅርቧል። የዘበኞች የመድፍ እና ነፍጥ ተኩስ ትርዒት በሚያስፈራ አኳኋን ሲያሳዩ ሠራዊቱ ሁሉ ይደነቅ ነበር። የንጉሡ ጦር ያንን ያደረገው ‹‹የሚመጣባችሁን ጠላት እንዲህ አድርጌ አግዤ እከላከልላችኋለሁ›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ዜና መዋዕል ጸሐፊው ጠቀስ አድርገዋል።
የተፈሪ ዘመን
በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ስላለው የበዓል አከባበር ጉልህ ማስረጃ ማግኘት ባይቻልም ንግሥቲቱ ለአባታቸው ለምኒልክ እና ለእቴጌ ጣይቱ መታሰቢያዎችን ለመሥራት ጥረት ያደርጉ ነበር።
በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በዓሉ የሚከበርብትን ዐውድ ስናይም ኃይማኖታዊ የሆነው ሥነ-ሥርዓት መንግሥታዊ ከሆነው ሥነ-ሥርዓት ጋር ተዋህዶ የሚፈፀም ነበር።
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በተጀመረበት አግባብ በዓሉ የካቲት 23 ሲከበር በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከጠዋቱ በአስራ ሁለት ሰዓት 21 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል። ያንን የመድፍ ድምፅ ሰምቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወደ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን (አራዳ) ይጎርፋል።
በቤተክርስቲያኑም ንጉሡን ጨምሮ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ክቡራን ሚኒስትሮች ይገኛሉ። የክብር ዘቡም የሚሰለፈው በቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ነበር። ንጉሡ በዚያ የሰልፍ ሥነ-ሥርዓት ውስጥ አልፈው በቤተክርስቲያኑ በመገኘት በዓሉን ምክንያት አድርገው ለዚያ አባቶቻቸውን ለድል ያበቃ አምላክ የሚያመሰግኑበት ፀሎት ያደርጋሉ። በዕለቱ የጊዮርጊስ ታቦት ወጥቶ ይነግሣል፤ በዕለቱ እጨጌው (ሊቀ ጳጳሱ) ፓትርያርኩ መግለጫ እና ቃለ ቡራኬ ይሰጣሉ። ታቦቱ ዑደት ካደረገ በኋላ የበዓሉ ፍፃሜ ይሆናል።
የአድዋ ድል በዓል በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ደማቅ ነበር ለማለት ግን ያስቸግራል። የዚህ ምክንያት ተደርገው ሊታሰቡ የሚችሉት ኢጣሊያ ዳግም ወረራ እስከተፈፀመበት ዓመት ድረስ በአመዛኙ ከምኒልክም ጋር ዘምተው የነበሩ፣ ራሳቸውን የድሉ ባለቤት አድርገው የሚያስቡ መኳንንት፣ የዳግማዊ ምኒልክ አፍቃሪዎች የልጅ ኢያሱ ደጋፊዎችም ስለነበሩ፣ በንጉሡም አድሃሪያን ተደርገው ስለሚታሰቡ በዓሉን አድምቆ ማክበር የምኒልክን ስም የሚያደምቅ ስለሚመስላቸው ኃይለ ሥላሴ እና ተራማጅ የሚባሉት የእርሳቸው ዘመንኛዎች ከመሳተፍ ባለፈ በዓሉን በማድመቁ ሂደት ውስጥ የጎላ ሚናቸው አይታይም። ይልቁንም የጥቅምት 23 ዘውድ በዓል ደምቆ እንዲከበር ይተጉ ነበር። ሌላው ቀርቶ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ያሠሩት በአደባባዩ የሚገኘው ሐውልት ተሠርቶ የተመረቀው በንጉሥ ተፈሪ የበዓለ ንግሥ ዋዜማ ጥቅምት 22 /1923 ነበር።
ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ደግሞ የካቲት 12 የሰማዕታቱ ቀን እና ሚያዝያ 27 የነፃነት ቀን እጅግ በደመቀ ሁኔታ ይከበር ነበር። በተለይ ሚያዝያ 27 በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም በፀሎት እና በምስጋና፣ በኦሜድላ አደባባይ በጦር ኃይሎች አስተባባሪነት በአርበኞች ሰልፍ፣ በንጉሡ ቀስቃሽ ንግግር፣ በኢዩቤልዩ ቤተ መንግሥት በግብዣ፤ በማግስቱ በእስታዴየም በትምህርት እና ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተማሪዎች ሰልፍ፣ በኋላም በልዑላን የራት ግብዣ፣ በሦስተኛውም ቀን በስፓርት እና በጃንሆይ ሜዳ በሚደረግ የወታደራዊ ሰልፍ ትርዒት ሞቆ ይከበር ስለነበር ለዚህ በዓል በየዓመቱ የሚደረገው ሰፊ ዝግጅት አድዋን ለመሰሉ በዓላት መጋረድ ምክንያት ነበር።
ዘመነ ደርግ
ደርግ የበዓሉን አከባባር ከኃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ተነጥሎ እንዲከበር ያደረገው ወዲያው ወደ ሥልጣን እንደመጣ ነበር። ደርግ የበዓሉን አከባበር ብርቱ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲኖረውም ማድረግ የጀመረው ወዲያውኑ ነው። ለዚህም በልዩ ሁኔታ በዓሉ እንዲከበር የተደረገባቸውን አጋጣሚዎች ማስታወስ ይበጃል።
የመጀመሪያው ልዩ ተብሎ የሚታሰበው በ1967 የተከበረበት ዐውድ ነው። ፡ በጊዜው የንጉሡ ሥርዓት የተገረሰሰበት ዓመት ስለነበር ከፍተኛ የአቢዮተኞች ሰልፍ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ምኒልክ አደባባይ ድረስ ተደርጓል። የምኒልክ አደባባይ በሚያገናኙ የመንገድ አቅጣጫዎች ሁሉ ትርዒት የሚያቀርቡ ስልፈኞች የተሞሉ ነበሩ። ከልዩ ልዩ ተቋማት በጥሪ እና በትእዛዝ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ዜጎች በርካታ ነበሩ። ገና በሽብር መደፍረስ ያልጀመረ የአቢዮቱ ትኩስ ወራት ስለነበር ሁሉም ፊውዳሊዝምን እያበሸቀ ሀገራዊ ስሜትን ደግሞ በአድዋ ድል እያደመቀ ለመሄድ የተጣጣረበት ጊዜ ነበር።
ሁለተኛው ደግሞ ከ1969-1970 የተከበረው በዓል ልዩ ነበር። የሶማሊያ ወረራ፣ የኤርትራ ተገንጣይ ኃይሎች እና ኢሕአፓ እና ኢዲዩን የመሳሰሉ ጠላቶች የተነሡበት ደርግ በሊቀ መንበሩ በመንግሥቱ ኃይለማርያም በኩል ቀስቃሽ ንግግር አሰምቷል። የዚያን ጊዜው በዓል አከባበር ደርግ ጠላቶቼ በሚላቸው ኃይሎች ላይ ሕዝቡ እንዲነሣሣ ለማነቃቃት የተደረገ የበዓል አከባበር ይዘት ነበረው።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በ1970ው በዓል ላይ በንግግራቸው
‹‹ሀገራችን የዛሬ 81 ዓመት እንደገጠማት ሁሉ ዛሬም የመጨረሻውን ተጋድሎ በሚጠይቅ ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። ያን ጊዜ ጀግኖች አባቶቻችን በተስፋ ብቻ ለሚያውቋ ትና ጥቂቶች ብቻ ለሚዘባነኑባት ኢትዮጵያ ወድቀዋል፤ የዛሬው ሰፊው ሕዘብ የሚወድቀው ደግሞ የራሱ ለሆነችው፣ የራሱን የመኖር ዋስትና በማረጋገጥ ላይ ላለችው አቢዮታዊት ኢትዮጵያ ነው። ፍትህ እኩልነት እና ሰላሟ ለሰፈነበት የሶሻሊስት ሥርዓት ነው። ስለዚህ ከአባቶች በበለጠ ዳር
ድንበሩን በመጠበቅ እናት ሀገሩን በአድሃርያን እንዳትደማ መከላከል፣ የተያዘብንን መሬት በአስቸኳይ በማስለቀቅ በቆራጥነት በመዋደቅ ላይ ይገናል። ›› ብለው ነበር።
ሊቀ መንበሩ በንግግራቸው በጊዜው በነበሩ ጠላቶች ላይ ለማነሣሣት ጥረት ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን በዓሉ በጊዜው አቢዮተኞች የመደብ ጭቆና ትርክት ውስጥ የሚፈጥረውን ተቃርኖ ለማቻቻል የሞከሩበትም ነበር። ጥቂቶች የሚዘባነኑባት ኢትዮጵያ በማለት በጊዜው የነበረውን ፊውዳላዊ ሥሪት ኮንነው ሲያበቁ መልሰው ንጉሡን ጨምሮ በጦር ሜዳ ተጋድሏቸው የከበረ ዝናና ስም የነበራቸውን ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንንት ጀግኖች አባቶቻችን በማለት ያወድሳሉ። ያለፈውን ዘመን ጅግንነት ለጥቂቶች ጥቅም፣ የአሁኑን የእርሳቸውን ዘመን ጀግንነት ለብዙኃን ጥቅም እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ።
በዓሉ የሚከበርበት ዓላማ ይለይ እንጂ የበዓል አከባበሩ ቅርፅ በአመዛኙ ነባሩን ባህል የጠበቀ ነበር። በዓሉን በዋናናት ትኩረት ሰጥተው የሚያከብሩት የጦር ኃይል መምሪያዎች ነበሩ። በዓሉ በዚያው በምኒልክ አደባባይ ይከበር ነበር። በንጉሡ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ጠዋት በአስራ ሁለት ሰዓት 21 ጊዜ መድፍ ይተኮስ ነበር። ከዚያም በአዲስ አበባ ከንቲባና የጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አስተባባሪነት በአደባባዩ የክብር ዘብ ሰልፍ ይደረጋል። ልዩ ልዩ የሙዚቃ ቡድኖችም ለበዓሉ ድምቀት ጣዕም ያላቸው የሀገር ፍቅር ቀስቃሽ ዜማዎችን ያሰማሉ።
ፕሬዚዳንት መንግሥቱ በሞተረኞች ታጅበው ሞቅ ባለ አቀባባል በስፍራው ይደርሳሉ። ከእርሳቸው ጋር የደርጉ ከፍተኛ ሹማምንት አብረዋቸው ይገኙ ነበር። ለአከባበሩም ራሳቸው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በስፍራው ተገኝተው በምኒልክ ሐውልት ግርጌ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ። የተሰበሰበው ሰልፈኛ እና በዓሉን ለማክበር የታደመው ሕዝብ ሁሉ የወቅቱን የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር አድምቆ ይዘምራል።
ደርግ ከሻቢያ እና ከወያኔ ጋር የገባበት ጦርነት እጅግ እየሰፋ በመምጣቱ፤ የቅስቀሳ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውም ተጠናክሮ ስለነበር አድዋን ለዚህ ዓላማ ማሞቅ እና ማድመቅ አስፈላጊ ሆኖ ነበር። ስለዚህም ከ1980 ጀምሮ በዋዜማው የማርሽ የሙዚቃ ቃና የሚያሰሙ ሰልፈኞች ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምረው በዋና ዋና የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በዓሉን አስመልክተው ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም በምድር ጦር እና በባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያዎች በየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ተቋም የጥናት ጉባኤ እና የውይይት መድረኮች ይዘጋጁ ነበር። በዚህም የታሪክ ምሁራን እየተገኙ የአድዋን ጦርነት ድል በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት የአባቶቻችንን ጀግንነት ይዘክሩ ነበር።
በ1983ደርግ የመጨረሻውን አድዋ በዓሉን ሲያከብር እጅግ ትኩረት የተሰጠው በዓል አከባበር አባት አርበኞች በመላው ሀገሪቱ ጦርነት በሚካሄድባቸው ዐውደ ውጊያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው፣ ህዝቡን በየአዳራሹ ሰብስበው ለውጊያ እንዲያነሳሱ በማድረግ ነበር።
ዘመነ ኢህአዴግ
በዘመነ ኢህአዴግ የበዓሉ ቅርፅ ከደርግ አከባበር ብዙ ባይለይም በዓሉን ለማክበር የሚገኙ ባለሥልጣናት ማንነት ግን ለበዓሉ የሚሰጠውን ክብር ያሳነሰ አስመስሎታል። ሕገ መንግሥቱ እስኪፀድቅ ድረስ በአብዛኛው ለማክበር ይገኙ የነበሩት የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ነበሩ። ቀድሞ ቁልፍ የመወሰን ሥልጣን የነበራቸው ንጉሡ እና የደርጉ ሊቀመንበር ከመላ ቁልፍ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ተገኝተው ያከብሩበት የነበረው ዐውድ በመጠኑም ቢሆን በኢህአዴግ የአክባሪ ባለሥልጣነት አሰያየም ተሳትፎ መልዕክት ነበረው።
የዚያም ምክንያት የደርግ አብዮተኞች የገጠማቸው የጨቋኝ ተጨቋኝ መደብ ትርክት ውስጥ የተፈጠረባቸው አጣብቂኝ አሁን ደግሞ ከፍቶ በመጣው በኢህአዴግ አብዮተኞች የብሔር ጭቆና ትርክት ውስጥም አጣብቂኝ ሆኖ መቀጠሉ ነው። ስለዚህ የቁልፍ ባለሥልጣናት ለበዓሉ ትኩረት መንፈግ በዓሉን በማክበር ሂደት ሳይነሱ የማይታለፉት ዳግማዊ ምኒልክ ኢህአዴግ ፖለቲካውን እየሠራ ለነበረበት የብሔር ጭቆና ትርክት ዒላማ ስለነበሩ የተፈጠረውን አጣብቂኝ ለማለፍ የተሄደበት መንገድ ስለመሆኑ መገመት ይቻላል።
በኢህአዴግ ዘመን የተሻለ የአከባበር ሥነ-ሥርዓት የታየው ከ1988 ዓ.ም ላይ ሲሆን፤ ያም የበዓሉ 100ኛ ዓመት በመሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ከሚጠብቁት አንፃር አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ስለነበር ነው። በዓሉ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ድሉ በተከናወነበት ስፍራ እንዲከበር በመወሰን፣ በአሥመራ መንገድ አንድ አደባባይን በአድዋ ድል ለመሰየም በመወሰን፣ የአድዋ መታሰቢያ ሐውልት ለመሥራት የመሰረት ድንጋይ በመጣልም፣ በመስቀል አደባባይም ችቦ በመለኮስ እንዲከበር፣ በስብሰባ ማዕከል የኪነት ዝግጅት እንዲደረግ በመወሰን፣ በዋዜማው አንድ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም እንዲዘጋጅ በማድረግ፣ ጠዋት በማለዳው አዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት የደወል ድምፅ እንዲያሰሙ፣ 21 ጊዜ መድፍም እንዲተኮስ በማድረግ ለማክብር ጥረት ተደርጓል።
በአድዋ ከተማም አብያተክርስቲያናት የደወል ድምፅ እንዲያሰሙ፣ መድፍም እንዲተኮስ፣ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የቅዳሴው ሥርዓት እንዲከናወን፣ ከዚያም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲካሄድ ተደርጎ ተከብሯል። የአውሮፕላን ትርዒትም ታይቷል። የባህል
ትርዒቶችም ቀርበዋል። ለአንድ ላልታዋቀ ጀግናም አንድ ሐውልት እንዲቆምለት በማድረግ እንዲከበር ሆኗል። ታሪካዊ ሙዚየም በአድዋ እንዲሠራ ለማድረግ፣ አንድ መናፈሻ በድሉ ለመሰየም በመወሰን ተክብሯል። በዓሉ ካለፉት ጊዜያት በተሻለም ፕሬዚዳንት ነጋሦ ጊዳዳ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ንቁ ተሳታፊ የሆኑበት ስለነበር የተሻለ ነበር።
በበዓሉ አከባበር በፖለቲከኞች አካባቢ የነበረው ጭንቅ የብሔር ጭቆና የመኖሩ መነሻ እና መሰረት አድርገው ሲተነትኑት ከነበረው የዳግማዊ ምኒልክን የመስፋፋት (ሀገር የማቅናት) ፖሊሲ ጋር እንዴት ተለይቶ ለአክባሪው እንደሚነገረው የነበረው አጣብቂኝ ነበር። በአንድ በኩል በንጉሡ አመራር የተገኘው ድል በዓለም ካገኘው ክብር እና ሞገስ አንፃር ክብር አለመስጠት እንደማይቻል ተገንዝበው ሲያበቁ የነበረውን የፖለቲካ ትንታኔ ጫና እንዳያሳድርበት በተገኙ ሲምፖዚየሞች የውይይት መድረኮች ሚዛን ማስጠበቅ እንደሚቻል የተደረገው ጥረት ነበር። ይሄንን በጊዜው ፕሬዚዳንት ነጋሦ ጊዳዳ ንግግር ውስጥም እንዲህ ልናገኘው እንችላላን።
‹‹ዐፄ ምኒልክ በውስጣችን ያካሄዱት የመስፋፋት ወረራ ለብዙ ህዝቦች መጨፍጨፍ ማለቅ ምክንያት መሆኑ፤ ብሔራዊ ጭቆናና ውርደት እንዲስፋፋ ማድረጉ የዳግማዊ ምኒልክን አገዛዝ ዓይነተኛ ባህርይ የሚያመለክት ቢሆንም፤ ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለመመከት ሕዝቡን በማስተባበር እና በማዋጋት የተጫወቱት ሚና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ከእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት በመነሳት ህዝብን የማስተባበር እና የማዋጋት ሚና የተጫወቱት በርካታ የጦር መሪዎች እና ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በታሪካችን ውስጥ ተገቢውን ሚዛናዊ ቦታ ሊያገኝ ይገባዋል›› ብለው ነበር።
በፕሬዚዳንቱ ንግግር በንጉሡ ደረሰ የሚባለው ግፍ ደረጃው ሕዝቡን አስተባብረው የየአካባቢውን ገዥዎች አሳምነው በቆራጥነት ተዋግተው ለድል በቁ ከሚለው ትረካ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የጊዜው ንግግራቸው ይዘት አንቀፅ በአንቀፅ ቢታይ ንጉሡን ያከበሩበት ሳይሆን የወረፉበት መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ በኢህአዴግ ዘመን የዚህ የድል በዓል ደመቅ ብሎ የተከበረበት ሌላው ጊዜ በ1991 ዓ.ም ነበር። በዚያን ጊዜ የተከበረው 103ኛው የአድዋ ድል በዓል ልዩ የሆነው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት ትኩስ ጊዜ ስለነበር ነው። በዚያው ወር ውስጥ በኤርትራ ‹‹የባድመ ጦርነት ፀሐይ ግባት በተባለው ዘመቻ ስያሜ የኢትዮጵያ ጦር በኤርትራ ላይ ድል ያገኘበት ስለነበር ድርብ የድል በዓል ተደርጎ ተወስዶ ነበር። መንግሥትም ሕዝቡን በኤርትራ ላይ የተወሰደውን የጦርነት እርምጃ አምኖበት የበለጠ እንዲደግፍ ‹‹የአድዋ ድላችን በባድመም ተደገመ›› የሚል መፈክር ተይዞ ቅስቀሳ የተደረገበት እና በበዓሉ ዕለትም በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ የተደረገበት ነበር። በዚያም መሠረት በዓሉ በምኒልክ አደባባይ ብቻ ሳይሆን በመስቀል አደባባይም ደምቆ ተክበሮ ነበር።
በኢህአዴግ ዘመን የበዓሉ አከባበር የደመቀበት ሌላው አጋጣሚ ኢትዮጵያ አዲሱን ሚሊኒየም ለመቀበል በዓል አድርጋ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ እንዲከበር ከተደረገበት ዕቅድ ክንውን ጋር በመግጠሙ ነው። በዓሉ በዋናነት ደምቆ የተከበረው ድሉ በተመዘገበበት ሥፍራ በአድዋ ሲሆን፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ የፌዴራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል ሹማምንት ተሳትፈውበታል። በ100ኛ ዓመት ቃል የተገባለት በአድዋ ሙዚየም የማቋቋም እና ድሉን በዓለም ቅርስነት የማስመዝገብ ዕቅድ እንዳለም ይፋ የሆነው የዚያን ጊዜ ነበር። በዚህ ወቅትም ቢሆን ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ እንደቀጠለ ስለነበር በጊዜው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፀጋዬ በርሄ በበዓሉ ላይ ሕዝቡን ለማነቃቃት መልዕክት ለማስተላለፍ የሞከሩበት ነበር። ከዚያ ባለፈ ግን በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ከተሞች በህዝባዊ የውይይት መድረኮች፣ በጥናት ጉባኤዎች ለማክበር ጥረት የተደረገበት ነበር።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የአድዋን ድል በዓል ለማክብር ከመንግሥታዊ ጥረቶች ባሻገር የወጣቶች ተነሳሽነትም እየጨመረ ነው። በዚህም መሠረት እስከ አድዋ ተራሮች በሚደረግ የእግር ጉዞ በዓሉን ለማክበር “ጉዞ አድዋ” የሚባል ኅብረት ተቋቁሟል። ዘንድሮም ለ6ኛ ጊዜ ወጣቶች ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡
ማጠቃለያ
የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በዳግማዊ ምኒልክ አመራር ስር ተደምረው ያስመዘገቡት ድል ነው። ተደምሮ የተገኘን ድል ደግሞ ተደምሮ ማክበር የሚገባ ነው።
የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል ተደርጎ በመላው ዓለም ተወስዷል፤ ድሉ መላው የኢትዮጵያን ህዝብ በተለያዩ መንገዶች ተሳትፎ ባደረጉበት ተጋድሎ የተገኘ ድል ነው። በሁሉም አቅጣጫ ከነበረው የንጉሡ ግዛት ጥሪያቸውን በመቀበል ያለልዩነት በአድዋ ተራሮች ላይ ደሙን ያፈሰሰበት፣ ህይወቱንም የገበረበት ድል ነው። ያለልዩነት የተገኘው ይህ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊው የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ለአንድ ሀገር ምስረታ ጥረቱ ቁልፍ አስተዋጽኦም ነበረው።
በየዘመኑ የሚመጡ መንግሥታት በተቻለ መጠን ድሉን የማክበር ሥነ ሥርዓቱን እስከ አሁን ዘመን ማቆየታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ያም ሆኖ ከየመንግሥታቱ ፖለቲካዊ ዓላማ አንፃር ሲሞቅና ሲበርድ፣ ለድሉም ያለውን የህዝብ አተያይ አንዴ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቀኝ ወደ ግራ በማንሸዋረር አልፎ አልፎ ያሳዩት የነበረው ድካም ካለፈው መልካሙን ገፅታ በማወደስ የወደፊቱን መልካሙን ለመሥራት ቃል በመግባት መንፈስ እየታረመ አከባበሩ ቢደምቅ ኢትዮጵያንም ያደምቁታል እንላላን።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011
በማለደ ዋስይሁን