ክረምት ማለፉን ተከትሎ ደማቁ ፀሐይ ምድሪቷን እያሞቀ፤ የግሮሰሪውን ሥራም እያደመቀው ነው፡፡ ከተገናኙ የከራረሙት ተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማርያም ዛሬ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ደግ ደጉን መነጋገር ጀምረዋል። ተሰማ ፊቱ ሞላ ብሎ ወፍሯል፡፡ ገብረየስም ፊቱ ላይ የነበረው ማድያት ጠፍቷል፡፡ ዘውዴ ግን አልተመቸውም፤ ሰውነቱ ቀንሷል፡፡ ድሮም ያልነበረች ቦርጭ አሁን ጭራሽ ጠፍታለች፡፡
ገብረየስ ‹‹ትርጉም የማይሠጥ ትግል ከማበሳጨት አልፎ አንዳንዴ ፈገግ ያሰኛል፡፡ በንግግርም ሆነ መሣሪያ በመምዘዝ የሚካሔድ ትግል መጨረሻው ሲታይ፤ እንደሰከረ ሰው በማያስደስት እና ሊያስለቀስ በሚገባ ጉዳይ ለመሳቅ ያስገድዳል፡፡ ጊዜው በሆነ አጥር ውስጥ ገብቶ የሆነ ትግል ውስጥ ለመገኘት ደንዘዝ ማለትን ይጠይቃል፡፡ መደንዘዝ ደግሞ ራስን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን አልፎ ተርፎ ብዙ ሰዎችን እና ሀገርን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በመልካም ንግግር መድመቅ ይሻላል፡፡ በመልካም ንግግር መድመቅ ካልቻልን ቢያንስ ከንግግር ይልቅ ዝምታን የመረጥነው ለእዚሁ ነው፡፡ ያምራል ብሎ ከመናገር ይከፋል ብሎ መተው ይሻላል ይባል አይደል? የማይጠቅም ነገር ከመናገር መቆጠብ ይሻላል፡፡›› አለ፡፡
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ልፋ ያለው ግድግዳ ሲገፋ ያድራል እንዲሉ፤ ልፉ ያለን ግድግዳ ስንገፋ እንውላለን፡፡ ከተገነባው ግድግዳ በላይ ግንብ ገንብተን ራሳችንን በከፍታ ላይ ማስቀመጥ ስንችል፤ ጊዜያችንን ግድግዳ በመግፋት እናባክናለን፡፡ ቃል በማውጣት ብቻ ሳይሆን፤ መሣሪያ እየመዘዝን ተራራ እና ሸንተረሩን እየሮጥን ከላብ አልፈን ደም እናፈሳለን፤ ተኩሰን እየጣልን፤ ተተኩሶብን እየወደቅን እንሰዋለን፡፡
የፈሰሰ ደም ላይመለስ አፈር ውስጥ እየሰረገ ሲደርቅ ዓይናችንን እያጭበረበረ ማንፀባረቁ ቢያውከንም፤ ክርፋቱ አፍንጫችንን ለመቁረጥ ጫፍ ቢደርስም፤ ‹ተጨቁነናል› በሚል፤ ጨቋኙ ማን እንደሆነ በደንብ በውል ሳንለይ፤ ተገቢውን ውጤት ላናገኝ ላባችንን እና ደማችንን ከማፍሰስ ወደ ኋላ ብለን አናውቅም፡፡
በንግግር እና በመተባበር ሠላም ለማምጣት ከመጣር ይልቅ፤ ከፋፋይ በሆኑ ሃሳቦች ተጠምደን መደገፍ ያለብንን ሳይቀር እየተቃወምን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ሀብታችንን እና ሙሉ ማንነታችንን እንቀብራለን፡፡ የአዋቂ ሴት ቤት አለው ውበት ይባላል፡፡ አዋቂ ሴት ቤቷን በሥነሥርዓት ይዛ ታሳምራለች፡፡ እኛ ግን ቤቷን ያሳመረች ባለሞያ ሴትን ስናይ ከማድነቅ ይልቅ እንሳለቃለን፡፡ የሠራችውን እናጣጥላለን፤ ለሠላም ከመረባረብ ይልቅ በምላሳችን መርዝ እንረጫለን፡፡ ቤት ለማፍረስ የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።›› ሲል መረር ብሎ ተናገረ፡፡
ዘውዴ እንደሌላ ቀን ለመከራከር አልሞከረም፤ ደክሞታል፡፡ ሕልም በመሰለ ዓለም ውስጥ እንደሚኖር ሰው ዓይንኑን ቡዝዝ አድርጎ በውል ምን እያሰበ እንደሆነ ለመገመት በሚያስቸግር መልኩ ፈዝዞ ቀረ፡፡ ሁለቱም ልብ አላሉትም፡፡
ገብረየስ ቀጠለ፤ ‹‹በውል ማንነቱን ያልለየነውን ምናልባትም ጨቋኝ ያልሆነውን እናገኛለን ብለን፤ የማይፈርስ ግድግዳ ለመጣል በምናደርገው ትግል ዋጋ የሌለው መስዋትነት እንከፍላለን። አልገፋ ብሎ እንደግድግዳ ተገትሮ የጋረደንን ግንብ ስንገፋ እንደማይወድቅ መገንዘብ የተሳነን ከመሆናችን ባሻገር፤ ተሳክቶልን ቢወድቅ እንኳ፤ ከእርሱ መውደቅ ቀጥሎ ምን እንደምናደርግ ለይተን አናውቅም፡፡ ጥለን እንደምንነሳ እና እንደምንደሰት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ግድገዳ እንደማንገፋ እርግጠኞች አይደለንም፡፡
በተደጋጋሚ ለመጣል ከመታገል አልፈን በመውደቁ ተጎጂ የምንሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አንገምትም፡፡ በጭራሽ ስለራሳችን ጥሎ መነሳት እና በትግላችን ሒደትም ሊመጣብን የሚችለውን ጉዳት አናስብም፡፡ የቀን እና የሌሊት ህልማችን እልሃችንን የምንወጣበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡
ግንቡ መኖሩ ምናልባትም ተንሻፎ ከሚዘንብ የዝናብ ውሽንፍር የሚያድነን ይሆናል፡፡ ነገር ግን አዕምሯችንን ለዚህ አላዘጋጀነውም፡፡ ግንቡ ያለውን ጠቀሜታ ለመገንዘብ አንፈልግም። ተደጋጋሚ ሃሳባችን የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ እንደሚባለው ግንቡ ከክፉ ነገር ሳይሆን ከደግ ነገር ከልሎናል የሚል ብቻ ነው፡፡ ከክፉም ከደጉም የከለለንን ግንብ አፍርሰነው ለመበስበስ እንሯሯጣለን፡፡
የዘነበ ዝናብ አበስብሶ አጥንታችን እየተሰነጠቀ መሆኑ እየተሰማን በጥፋታችን ከመፀፀት ይልቅ፤ በራሳችን የጀመርነው የማያዋጣ ግድግዳ የመግፋት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። የታገልነው የገፋነው ግንብ ቢወድቅ እንኳ፤ በእርሱ መውደቅ እኛ ካልወደቅን ደግሞ ሌላ የሚፈርስ ግድግዳ እንፈልጋለን፡፡ መለስ ብለን አስበን የሚያዋጣንን ፈልገን፤ የማያዋጣንን ትተን ከመጓዝ እና የራሳችንን ወደ ከፍታ የሚያደርሰንን ግንብ እንገንባ የሚል ሃሳብ በፍፁም ብልጭ አይልልንም፡፡›› ሲል ገብረየስ የውስጡን ተናገረ፡፡
ተሰማ የገብረየስን ሃሳብ በመደገፍ እርሱም በበኩሉ፤ ‹‹ትክክል ብለሃል በተደጋጋሚ ሃሳባችን ገፍትሮ መጣል፤ ታግሎ ማፍረስ ላይ የተጠመደ ነው፡፡ ለራሳችን የሚያዋጣንን መንገድ አስበን ለመለየት እንቸገራለን፡፡ ግማሹ ምን ቢደረግለት ወይም ምን ቢያገኝ ትግሉን እንደሚያቆም እንኳ አያውቅም፡፡ የኋላ ታሪክ ላይ ተቸንክረን እየታገልን ግፍ ተፈፀመብን እያልን ስንማረር፤ ያለፈ ድርጊት ለመበቀል የማይደረስበትን ሰማይ ለመቧጠጥ መጣጣርን እንደልማድ ቆጥረነዋል፡፡
በተለይ ተበድለናል ብለን ስናስብ፤ እውነት ሆኖ የተፈፀመ ግፍ ቢኖር እና ተጨባጭ መረጃ ብናገኝ እንኳ፤ ስለተፈፀመው ግፍ በምን መንገድ ማን ካሳ መክፈል ወይም ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት በእርግጠኝነት ለይተን አናስቀምጥም። ጭራሽ ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ሳናውቅ የገዛ ቤታችንን ጓዳችንን እያመስን የጠላት መደሰቻ እንሆናለን፡፡›› ሲል፤ ዘውዴ በበኩሉ ለካ በዝምታ ሲያዳምጣቸው ቆይቷል፤ እንደመባነን ብሎ እርሱም የሚያምንበትን መናገር ጀመረ፡፡
‹‹ግራ የሚጋቡን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዚያ ላይ ግራ የሚያጋባን ነገር ግልፅ እንዲሆን በግልፅ፣ በትህትና እና አንዱ ሌላውን ባከበረ መልኩ የተነጋገርንበት ሁኔታ የለም፡፡ በእርግጥ ትግል ሁሉ መጥፎ አይደለም፡፡ የነፃነት ትግል ሲካሔድ ባርነትን ምረጡ ከትግል ወደ ኋላ በሉ ማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ላለመገዛት የተካሔደው እልህ አስጨራሽ ትግል ተገቢ እና ትክክለኛ ነው፡፡
ቅኝ ገዢ ግንብም ሆነ ተራራ በትግል ተገርስሷል፡፡ የእዚህ ትግል መነሻ እና መድረሻ ማንኛውም ታጋይ በደንብ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ከፋሽስት ጋር ታግለን ነፃነታችንን ማረጋገጣችን፤ ለጥቁር አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በቅኝ እየተገዙ ለነበሩ ሁሉ ብርሃን ማሳየታችንን የምትዘነጉት አይመስለኝም፡፡›› በማለት የትግልን አስፈላጊነት ሲያብራራ ተሰማ አቋረጠው፡፡
ተሰማ ፤‹‹የውጭ ጠላትን ለማባረር የሚደረግ ትግል ተገቢ እና ትክክለኛ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ወንድም በወንድሙ ላይ እየተነሳ የሚካሔድ ትግል ግን ትርፍ ሲያስገኝ አላየንም፡፡ አንዳንዱ ታጋይ ነኝ ባይ ‹ የምታገለው ቡድኔን፣ ጎሳዬን፣ ብሔሬን ነፃ ላወጣ ነው፤› ወይም ‹ይሔንን ነገር የእኔ ወይም የዚህ ቡድን፣ የዚህ ጎሳ፣ የእዚህ ብሔር ለማድረግ ነው፡፡› ይላል፡፡ ነገር ግን የትኛው ቡድን የየትኛውን ቡድን፣ ጎሳ ወይም ብሔር ነፃነት ገፈፈ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልስ ለማግኘት ማዳገቱ አይቀርም፡፡
እንፋለምለታለን የሚባለው ነገር በፍፁም የአንድ ሰው የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ብሔር መሆን የለበትም፡፡ ምንም ሆነ ምን አንድ የጋራ የሁሉም መሆን ያለበትን ጉዳይ ምንም እንኳ አንዱ ተነስቶ የእኔ ቡድን፣ ጎሳ ወይም ብሔር መሆን አለበት ብሎ ወስጃለሁ ለማለት ቢሞክርም፤ በፍፁም ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ሌላውም ጉዳዩ የእኔ ነው ብሎ ብዙ መስዋትነት ቢከፍልም፤ የእርሱ ብቻ መሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የሁሉም ነው፡፡ በተለይ በሕፃናት ጨዋታ ላይ እንደሚገለፀው ሀገራዊ ጉዳይ ከተነሳ ሀገር የጋራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ውሃውም፣ ማዕድኑም፣ አፈሩም ሆነ አጠቃላይ ምድሩ የመላው ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይህ አሁንም ሆነ ወደ ፊት የሆነ እና መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ የትግላችን ሥሩ ዋነኛው ምክንያት በውል ሳይታወቅ፤ ግማሹ እከሌ ስለታገለ እኔም እታገላለሁ ሲል፤ ገሚሱ ደግሞ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቦ መታለፍ ያለበትን ጉዳይ የሙጥኝ ብሎ ሕይወቱን መስዋት ለማድረግ ሲሰናዳ እየተመለከትን አብረን ለትግል መነሳታችን በእርግጥም ከማሳዘን፣ ከማበሳጨት አልፎ ፈገግ ያሰኛል፡፡ ትናንትን እያሰቡ ዛሬን ማበላሸት ባለማወቅ የሚሠራ ሥራ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ ›› ሲል ሃሳቡን ደመደመ፡፡
ገብረየስ ግን ሃሳቡን አልቋጨምና እምነቴ ያለውን ለመግለፅ ወደደ፡፡ ‹‹መታወቅ ያለበት አንድ ሰው በወንድሙ ላይ ሲነሳ፤ መጨረሻው መጥፎ ነው፡፡ ትግሉ አንዱ ሌላውን ለመጣል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለመጣል ሲታሰብ መውደቅ ያጋጥማል፡፡ አንድ ወንድም ከወንድሙ ጋር ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት ሲቻል፤ ሰበብ እየፈለጉ እጅ እየጨበጡ በወንድም ላይ ቡጢ እየሰነዘሩ መታገል በተደጋጋሚ አይተነዋል፤ አድርገነዋል፤ ነገር ግን አዋጪነት የሌለው መሆኑን ከእኛ ውጪ ምስክር አይገኝም፡፡ እየተጋጩ ከገዛ የእናት ልጅ ጋር እየተቦጫጨሩ፤ እየተላላጡ ከመቁሰል እና ኃይል ከመጨረስ ይልቅ፤ ዕድል ሲያጋጥም ልክ እንደማንኛውም ጓደኛ ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት ይሻላል፡፡›› አለ፡፡
ተሰማ ሃሳቡን ቢጨርስም የገብሬ ሃሳብ አነሳስቶት፤ ለመናገር ፈለገና ቀጠለ፤ ‹‹ምንም እንኳ አንዱ ከሌላው በሀብትም ሆነ በጉልበት በልጦ ማሸነፍ ቢችልም፤ የእናት ልጅን ማርኮ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይልቁኑ ያለው ይበቃናል ብሎ ተስማምቶ መኖር ይበጃል፡፡ ተስማምቶ እና ተባብሮ በመኖር ማጣት ሳይሆን ማግኘት ያይላል፡፡ ግድግዳ ለመግፋት የሚውለውም ኃይል ሥራ ላይ ውሎ ሀገር ይቀየራል፡፡ ነፃነት ገፋፊ ባልተለየበት መልኩ መታገልም ሆነ፤ የመላ ቤተሰቡን ሀብት ‹‹የኔ ነው፤ ያንተ ነው›› ብሎ እየተስገበገቡ መናቆር ውጤት አያመጣም። በተቃራኒው ካልተገባ ትግል ይልቅ የቤተሰብን ሀብት የበለጠ ለማሳደግ አቅዶ መሥራት እና ጉልበትን ሕዝብን በሚጠቅሙ ሁኔታዎች ላይ ማዋል የተሻለ ነው፡፡
በእርግጥም እኔም እንደማምነው የተበላሸውን ማስተካከል ቀላል አይሆንም፡፡ ተደጋጋሚ ትግል ያስፈልጋል፡፡ የጠገበን ማረቅ የግድ ነው፡፡ በደም ፍላት ሳይሆን በብልሃት መሥራት ይገባል፡፡›› አለ።
ገብረየስ የሕይወት ተሞክሮውን በማንሳት ጓደኞቹን ለመምከር አሰበ፡፡ ‹‹ምንጊዜም ቢሆን ሁለታችሁም መጠንቀቅ አለባችሁ፡፡ ከላይም ሆነ ከታች በደም ፍላት የሚንቀሳቀሱትን መደገፍ የለባችሁም፡፡ ሳያስቡት በደም ፍላት የሚፋለሙ ብዙ ጊዜ መጨረሻ ላይ አይሳካላቸውም፡፡ ጊዜያዊ ድል ቢያስመዘግቡም ድሉ እና ደስታቸው ከእጃቸው መውጣቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በደም ፍላት የሚፈፀሙ ድርጊቶች የሚመጣውን ጣጣ ግምት ውስጥ የማያስገቡ በመሆናቸው፤ በአብዛኛው ጎጂ ናቸው፡፡ በሕይወታችሁ ግጭት እና ጦርነትን ከማሰብ ይልቅ መልካሙን ነገር ደጋግማችሁ አስቡ፡፡ በጎ በጎውን ተናገሩ፡፡ ማር ሲሰፍሩ ማር ይናገሩ እንደሚባለው ማር ማር የሚል ነገርን ለመሥራት ሞክሩ፡፡ አንድ አስደሳች ሥራ ሲሠራ ሥራው እንዲሳካ እና ትልቅ ውጤት እንዲገኝ ከሕዝብ የሚጠበቀው ጥሩ መናገር ነው። ጥሩ ሲናገሩ ጥሩ ሲሠሩ ጥሩ ውጤት ይገኛል፡፡
ስለሠላም እና ስለሀገራችን እድገት እንሥራ፤ እናውራ፡፡ ስለጦርነት መሥራት እና ማውራት እናቁም፡፡ ስለበጎ ነገር ማሰብ፣ ስለበጎ ነገር መድከም እና መሥራት መልካም ነገርን ያመጣል። ለመልካም ነገር የሚተጉ፤ ከአፋቸው መልካም ቃልን የሚያወጡ ብዙ ባይጠቀሙም፤ አይጎዱም። መልካም ሠሪ እና መልካም ተናጋሪ እንዲሁም መልካም አድራጊ ሲበዛ ሀገራችን ታድጋለችና በበጎ ነገር እንተባበር፡፡›› ሲል የዕለቱን ሃሳቡን ቋጨ እና የጠጡበትን ለመክፈል ኪሱን መዳበስ ጀመረ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም