አብዱልሚኒየም አልሀጂ እና ጓደኞቹ ጠቅላላ የህብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ ሥራ ቦታ የደረስኩት ጠዋት ነበር። በሥራ ሰዓት አይከፍቱ ይሆን የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ ። እንደገመትኩት ሳይሆን በሥራ ሰዓት ነው በሥራ ቦታቸው ተገኝተዋል። ብዙዎቻችን ‹የግል ሥራ በኖረን› ብለን የምንመኘው በፈለግነው ሰዓት ለመግባትና ለመውጣት ነው። እነርሱ ግን ከዚህ አስተሳሰብ ውጭ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። በልቤ አድናቆቴን ለገስኳቸው።
በቅድሚያ የኢንተርፕራይዙ መስራችና ኃላፊ ሆኖ ከሚሰራው ወጣት አብዱልሚኒየም አልሀጂ ጋር ነበር ስለኢንተርፕራይዛቸው አመሰራረት የተጨዋወትነው። ወጣት አብዱልሚኒየም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርቱን የተከታተለው ተወልዶ ባደገበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው። በትውልድ አካባቢው የሥራ ዕድል በመፍጠር መንቀሳቀሱ ሥራ በአካባቢያቸው እያለ ርቀው ከሚሄዱ ለአንዳንድ ወጣቶች አርአያ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
ወጣት አብዱልሚኒየም ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በርቀት ትምህርቱን በመከታተል ደግሞ በዚህ አመት ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር ‹ቢዝነስ ኤንድ ማኔጅመንት› በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። ትምህርቱ ይቀጥላል ሲልም አጫውቶኛል።
በነበረን ቆይታ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያለ ነበር የሥራ እቅዱን የነደፈው። በሚማርበት አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማህበር ተደራጅተው ግንባታና የተለያየ ሥራ ሲሰሩ ከነበሩ ወጣቶች ብዙ ነገር ቀስሟል። ብዙዎቹም የገንዘብ አቅም ፈጥረው ለሌላም የሥራ ዕድል በመፍጠር ውጤታማ ሆነው ኑሮአቸውን መለወጥ መቻላቸው የእነርሱን ፈለግ እንዲከተል መንገድ ከፍቶለታል። ብርታትንም ጭምር ነበር ከተሞክሮአቸው የቀሰመው።
ትምህርቱን ጨርሶ ከተመረቀ በኋላ ሥራ ፈጥሮ ለመጀመር አልተቸገረም። መንግሥት ለወጣቶች የመደበው ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ የተለቀቀበት እና በማህበር ተደራጅተው ሥራ ለመጀመር ለሚፈልጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ስለነበር የሥራ ፍላጎትና ድጋፍ በመጣጣሙ አሁን ከሌሎች ጋር በጋራ ባቋቋመው ጠቅላላ የህትመት ሥራ ውስጥ ለመሰማራት አልተቸገሩም። ኢንተርፕራይዙ የተቋቋመው ከዩኒቨርሲቲ በተመረቀበት ዓመት 2009 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነበር።
በማህበር ተደራጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት አምስት ሰዎች ወይም አባላት ያስፈልጉ ስለነበር የአባላት ቁጥር በማሟላትና የሚሰሩትንም የሥራ ዘርፍ በጥናት በተደገፈ ዕቅድ ወይም ፕሮፖዛል አቅርበው ነው ሥራ የጀመሩት። በወቅቱም ለሥራ መጀመሪያ ያገኙት ብድር 270ሺ ብር ነበር።በተለያዩ የሕትመት ስራዎች ማለትም ልደት ካርድ ዝግጅት እና ሌሎች ተያያዥ የህትመት ስራዎችን በስፋት እየሰሩ ተጉዘዋል። በወሰዱት ብድር ሰርተው ውጤታማ በመሆናቸው ወደ መካከለኛ ደረጃ ለመሸጋገር ችለዋል። የተበደሩትንም መልሰዋል።
ስለ ውጤታማነታቸውም ወጣት አብዱልሚኒየም እንደገለጸው፣ አባላቱ ሰርቶ ለመለወጥ ፍላጎት የነበራቸው ስለነበሩ ሁሉም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሰጥተው ነበር የሚሰሩት። ሁሉም የነገ ውጤታማነታቸውን ዓላማ በማድረግ እንጂ ለኪስ የሚሆን ገንዘብ እንኳን አልነበራቸውም። ለሥራ የወሰዱት ብድር መመለሳቸው ታይቶ እንዲሁም ትጋታቸውና ጥረታቸው በከተማው የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ተገምግሞ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለመሸጋገር ችለዋል።
ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ሲሸጋገሩ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸዋል።ያገኙትንም የመስሪያ ቦታ ሰፊ ሥራ ለመስራት እንዲያስችላቸው ከፍተኛ ወጭ በማውጣት የእድሳት ሥራ አከናውነዋል። የህትመትና ኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠትም ከሌሎች ባልተናነሰ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም ከነንብረቱ ካፒታላቸው ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር ደርሷል።
የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ችግር የገጠማቸው የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ነው። እነርሱ እያሉ የህትመት ሥራዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይላካሉ።ይህ መሆን አልነበረበትም።እነርሱ ሥራ ላይ ሆነው ከእነርሱ አልፎ ያውም ከከተማ ውጭ ሥራው መሰጠቱ ቅሬታ ፈጥሮበታል።ሥራቸውን የበለጠ ለማሻሻል ገቢ ማግኘት አለባቸው። የህትመት ማሽን መግዛት ይፈልጋሉ። ማሽኑን በራሳቸው ቢገዙ ብድር ከመጠየቅና ለብድር ወለድ ከመክፈል ይድናሉ።
አጠቃላይ በሥራ ላይ ስለሚያጋጥማቸው ችግር ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከክልሉ መንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለያየ ጊዜ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ችግሩ እንደሚፈታ በተደጋጋሚ ተነግሯቸዋል። ነገር ግን አይተገበርም። እንዲህ ያለው ነገር መደጋገሙ መሰላቸት ፈጥሮባቸዋል። እነርሱ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ለተሻለ ስኬት እንቅስቃሴአቸውን አጠናክረዋል።
ወጣት አብዱልሚኒየም ከእርሱ ተሞክሮ የአካባቢው ወጣቶች ምን መማር እንደሚችሉ ላቀረብኩለት ጥያቄ ወጣቶች ከእኔ የሚያገኙትን ተሞክሮ በሁለት መልኩ ነው የማየው። ወጣቱ ሥራ ስላልሰራ ጥፋተኛ ሆኖ መታየት የለበትም። ይሄን የምልሽ አካባቢዬን መሰረት አድርጌ ነው።ወጣቱ እራሱን ባያስተካክል የክልሉ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በወጣቱ አዕምሮ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል። ወጣቶችም የተገኘውን ሁሉ አጋጣሚ መጠቀም ነበረባቸው።ተዘዋዋሪ የብድር ፈንዱን ማለቴ ነው። ብዙ ማህበራት መጠቀም እየቻሉ ግን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።
‹‹ማህበራቸውንም አፍርሰዋል።እንዲህ ያለው ነገር ለተተኪ ወጣቶች እንቅፋት ስለሚሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩ ደስ ይለኛል። በተለይ ተደራጅተው የሚሰሩትን በመደገፍ ማብቃት ቢቻል ለተተኪዎች ተስፋ ይሆናል።መነቃቃትንም ይፈጥራል።›› በማለት ሀሳቡን አጋርቶኛል።
የእነርሱን እንቅስቃሴ ለሌሎች ሞዴል ለማድረግ ጥረት ቢደረግም በቂ እንዳልሆነ ወጣት አብዱልሚኒየም ይገልጻል። በክልሉ የተለያየ ሀብት ቢኖርም ወጣቶችን አደራጅቶ ከሀብቱ ተጠቃሚ በማድረግ በኩልም እንቅስቃሴው ደካማ እንደሆነ ይናገራል። ሀብቱን መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ በማስፋፋት በኩልም እንቅስቃሴ አለመኖሩን በመጠቆም ይሄን መስራት ባለመቻሉ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ትምህርታቸውን በማይመጥን ሥራና ደመወዝ የሚሰሩና ሥራ የሌላቸውም መኖራቸውን ያስረዳል።
ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ያለውን ሀብት ለመጠቀም ጥረት ቢደረግ ብዙዎችን ተጠቃሚ በማድረግ አልባሌ ቦታ የሚውሉትንና ለደባል ሱስ ተገዥ የሆኑትን ወጣቶች መታደግ እንደሚቻል እምነቱ ነው። እርሱ እንደሚያስተውለው በጫት ሱስ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ጥቂትም ቢሆኑም እንደርሱ ከደባል ሱስ ነጻ ሆነው ለሌሎችም አርአያ መሆን የሚችሉ ወጣቶች መኖራቸውንም ተናግሯል።
ተደራጅተው በሚሰሩ መካከል ስለሚፈጠሩ አለመግባባቶች በተመለከተ ተሞክሮውን እንዲያካፍለኝ ላቀረብኩለት ጥያቄም ወጣት አብዱልሚኒየም በሰጠኝ ምላሽ አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ባህል ስላላቸው ሥራቸውን የሚያደናቅፍ ችግር አላጋጠማቸውም። በዚሁ በመቀጠል ውጤታማነታቸውን ለማሳደግ ነው ፍላጎቱ። የኢንተርፕራይዝ ሽግግሩ እስከ ከፍተኛ ባለሀብት የሚደርስ በመሆኑ እዚህኛው እርከን ላይ ለመውጣት ነው የሚሰሩት። በግሉም በተሰማራበት ዘርፍ አንቱ መባልን ስለሚፈልግ ጠንክሮ ለመስራት ጥረት ያደርጋል።
በሂሳብ መዝገብ አያያዝ ‹አካውንቲንግ› የትምህርት ዘርፍ እጩ ተመራቂ የሆነችው ሌላዋ የኢንተርፕራይዙ አባል ወጣት መካ ኢብራሂም ናት። መካ ኢንተርፕራይዙ ሲቋቋም በወቅቱ ሥራ አልነበራትም። ከሌሎች አባላት ጋር ትተዋወቅ ስለነበር አባል ለመሆን አልተቸገረችም። በመደራጀትዋ ደስተኛ ናት። ከህትመት ውጤቶቹ የሚገኘው ገቢ ኑሮዋን በሚለውጥ ደረጃ ላይ ባይደርስም ሥራ መሥራትዋ የአዕምሮ እረፍት እንደሰጣት ተናግራለች።
መኪያ እንዳለችው ሰው ያለሥራ ሲቀመጥ አእምሮው ጥሩ ነገር አያስብም። ቤተሰብም ይጨነቃል። ስለምትገኝበት የሥራ መስክ ግንዛቤው አልነበራትም። አሁን ግን የህትመት ሥራውን ብቻ ሳይሆን፣ የህትመት ውጤቶቹ ለምን ጥቅም እንደሚውሉም ለማወቅ ችላለች። ይህንንም እንደጥቅም ነው የምታየው። ወደፊት የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡም ተስፋ አላት። በተለይ የመጽሐፍት ማተሚያ ማሽን ቢኖራቸው ተጠቃሚነታቸው ከፍ ስለሚል ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል ቢኖር ደስተኛ ናት።
ባለፈው አመት በጽህፈት ትምህርት ከግል ኮሌጅ የተመረቀችውና ኢንተርፕራይዙ በተመሰረተ በአመቱ በአባልነት የተቀላቀለችው ወጣት በላይነሽ ፋንታሁን በተማረችው የጽህፈት ሥራ በማገልገል በህትመት ሥራው ላይም እንደምትሳተፍ ነው የነገረችኝ።
እርሷም እንደ መካ ሁሉ ስለህትመት ሥራ ትምህርት አግኝታበታለች። በወር የምታገኘው ክፍያ አነስተኛ ቢሆንም የኢንተርፕራይዙ ገቢ ሲያድግ ተጠቃሚ እንደምትሆን ተስፋ አድርጋለች። በሥራ ጥራትም ሆነ በገቢ በልጠው ለመገኘት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ሥለስራቸው ዋና አጀንዳ አድርገው እንደሚነጋገሩ ገልጻለች። እርሷም እንደሌሎች የኢንተርፕራይዙ አባላት ሁሉ በጨረታ ሥራ እንዲሰጣቸውና የህትመት ማሽን ድጋፍ የሚያደርጋላቸው ቢኖር ትፈልጋለች።
የኢንተርፕራይዙ አባላት ቋንቋቸው አንድ ነው። ሥራ መስራት፣ ማደግና መለወጥ ስለሆነ፣ ክልሉ እንደነርሱ ለሥራ የተነሳሳውን ወጣት በመደገፍ ለውጤት ማብቃት ይጠበቅበታል። ከከተማው ኢንቨስትመንት ቢሮ ባገኘሁት መረጃ በክልሉ በተለያየ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት መሬት ወስደው ወደ ሥራ ካልገቡ ባለሀብቶች መሬት በማስመለስ ወጣቶች ተደራጅተው በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል።
ሥራ ኑሮን ለመለወጥና ተሽሎ ለመገኘት ብቻ ሳይሆን፣ ሰው ያለሥራ መኖር እንደሌለበት ብዙዎች ይስማማሉ። ሥራ እንዴት ይገኛል? የሚለው ግን በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱትም ሆኑ የትምህርት ቤት ደጃፍ የረገጡትም እኩል ጥያቄ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። ሥራ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የማይገኝ የሚመስላቸውም ጥቂት አይደሉም። በመሆኑም ሥራ ፍለጋ የትውልድ አካባቢያቸውን ብቻ ሳይሆን ሀገራቸውንም ለቀው ሊያውም በህገወጥ የሚሰደዱም እንዲሁ ብዙ የሚባሉ ናቸው።
ሥራን በአካባቢ መፍጠር አይቻልም፣ ሥራ አይገኝም በሚለው ላይ የተለያየ ሀሳብ ቢንጸባረቅም ሥራ ፈላጊውም የግል ጥረት ማድረግ እንዳለበት የሚስማሙም ጥቂት አይደሉም። ለዚህም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ በትምህርትም በሥራም እራሳቸውን በማብቃት ለስኬት የበቁ እና ራዕያቸው ትልቅ የሆኑትን አብዱልሚኒየም አልሀጂ እና ጓደኞቹን ጠቅላላ የህትመት ሥራ ኢንተርፕራይዝ አባላትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተለያየ ዘርፍ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ውጤታማ ኢንተርፕራይዞች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑም ከሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አረጋግጫለሁ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣በተፈጥሮ የታደለ፣የወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናት መገኛ ነው። ለእርሻ የሚውልም ሰፋፊ መሬት አለው። የተጀመረው እርምጃ ከተጠናከረና ወጣቱ ተደራጅቶ ሥራ እንዲሰራ ቅድመ ሁኔታዎች ከተመቻቸ በስኬት ጎዳና ላይ እንደሚገኙት እንደ አብዱልሚኒየም አልሀጂ እና ጓደኞቹ ጠቅላላ የህትመት ሥራ ኢንተርፕራይዝ አባላት ውጤታማ መሆን ይቻላል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
ለምለም መንግሥቱ