የኮሚሽኑ አበረታች ውጤቶችና ቀሪ የቤት ሥራዎች
ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የምጣኔ ሃብት፣ የሥራ እድልና የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋነኛ ተልዕኮ ነው :: ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንግስት ባስቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት ስልታዊና ዓመታዊ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ::
በዚህም በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በመለየት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን በተያዘው የበጀት ዓመትም ዕቅዱን ወደ ሚዛናዊ ውጤት ተኮር ዕቅድ በመቀየር የስትራቴጂክ ጉዳዮችን አፈጻጸም ደረጃ መምራትና መለካት የሚያስችል የውጤት ተኮር ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል ::
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብና መደገፍ፣ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋትና ተገቢውን የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን መስራት፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በጥናት ላይ የተመሠረቱ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ ዋነኞቹ የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ::
በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ በዕቅድ ከተቀመጡ ስትራቴጂክ ግቦች አኳያ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ገምግሞ ከሰሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አድርጓል :: እኛም በአፈጻጸሙ ወቅት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎቹን እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ልናስቃኛችሁ ወደድን ::
ውጤታማ ዘርፎች
የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ዕድገት፡- ኮሚሽኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ካከናወናቸውና አመርቂ ውጤት አስመዘገብኩባቸው ካላቸው አንኳር ስራዎች መካከል ሃገሪቱ ያላትን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ዕድሎችን በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማሳደግ ረገድ የተከናወነው ቀዳሚው ነው :: ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጭና እድሎች የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል :: በዚህም መሰረት በቻይና ፣ ሆንግ ኮንግ-ቻይና፣ በፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ፣ ቱኒዝያ እና ሞሮኮ ሃገራት በተካሄዱ ልዩ ልዩ መድረኮችና በቻይና አፍሪካ ኮርዲኔሽን ፎረሞች ላይ በመሳተፍ አቅም ያላቸው ባለሃብቶችን የመመልመልና የመሳብ ስራ ተከናውኗል ::
በዚህም መንግስት ልዩ ትኩረት በሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ በ27 መድረኮች ላይ በመሳተፍ ኢንቨስተሮችን ለመመልመል ታቅዶ በሰላሳ ስድስት መድረኮች ላይ በመሳተፍ ከእቅዱ በላይ በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን የማግባባትና የመመልመል ሥራ ተከናውኗል :: በመሆኑም በመቶኛ ሲሰላ የዕቅዱን 133 በመቶ የሆነ ከፍተኛ አፈጻጸም ተመዝግቧል ::
ስለሆነም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የለገሐር የተቀናጀ የልማት እና የሁለገብ መንደር ኘሮጀክትን የያዘውን ግዙፉን የኢግል ሂልስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጨምሮ በኢንቨስትመንት አቅማቸው በግዙፍነታቸው ከሚታወቁ የመኪና አምራች ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቮልስዋገን እና ሲመንስ የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው በጉልህ የሚታይ ኢንቨስተሮችን መሳብና መፈራረም ተችሏል :: እንደዚሁም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወነውን ሰፊ የመሳብ ስራዎች ተከትሎ 16 የውጭ ድርጅቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ተደርጎ ስራ ጀምሯል ::
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዕድገት
– ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ፍላጎት አሳይተው ከተመለመሉ የውጭ ባለሃብቶች ውስጥ እና 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበውን የኢግል ሂልስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጨምሮ 225 ፕሮጀክቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ በመደረጉ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል :: ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ዕድገት አሳይቷል :: እንዲሁም 227 የሀገር ውስጥ ፕሮጀክቶች አዲስ ፈቃድ እንዲያወጡ በማድረግ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ለማድረግ በዕቅድ ደረጃ እንዲመዘገብ መደረጉና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውጭ ቀጥተኛ ንግድ 103 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል ::
የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች፡- ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያ በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተወሰዱ ሪፎርሞችን ቀጣይነትና ውጤታማነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑና ውጤት ካስመዘገቡ ተግባራት ውስጥ ዋና ተጠቃሽ ነው ::
በዚህም እየተካሄደ ካለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር በተጣጣመ አኳኋን ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ እና የቢዝነስ ሁኔታን ምቹነት መፍጠር ያለመ የኢንቨስትመንት ህግ ማዕቀፍ የሚያሻሽል የህግ ካውንስል በማቋቋም የህግ ማሻሻል ጥናት የተከናወነ ሲሆን የጥናቱን ውጤት በቀጣይ ወር የውይይት መድረክ በማዘጋጀት በረቂቅ ሰነዱ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚካሄድ ይሆናል ::
የኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያግዙ የተለያዩ ሴክተሮች ጥናት የማከናወን ስራ ተሰርቷል:: በዚሁ መሰረት የህትመት ኢንዱስትሪ እና የሎጂስቲክስ ጥናቶች ተጠናቆ ለፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ለኢንቨስትመንት ቦርድ ቀርቦ በማፀደቅ በስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ::
ከዚህ አኳያ የተጀመረውን ሃገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማገዝ እና ኮሚሽኑ የተሰጠውን አዲስ ተልዕኮ መወጣት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ከልሶ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል :: ስለሆነም የሁለት ተጠሪ ተቋማት አደረጃጀት ማለትም ሆርቲካልቸርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አደረጃጀት በኮሚሽኑ ሥር እንዲሆኑ በአዲስ መልክ ማዘጋጀትና አጸድቆ ወደ ስራ ለማስገባት በታቀደው መሰረት ለኮሚሽኑ የተሰጡ አዲስ ተልዕኮዎችን ተከትሎ የተቋሙን አደረጃጀት በመከለስ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲጸድቅ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል :: በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ኮሚሽኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የማስተባበርና የማገዝ ስራ ተከናውኗል ::
ያጋጠሙ ችግሮች
በሃገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ፕሮጀክቶች ስራቸውን ለመስራት መቸገር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የፕሮጀክቶች የመብራት አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ጊዜ መውሰድ፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ለመወሰን የክልል ካቢኔ ስብሰባዎች ረጅም ጊዜ ሳይሰበሰቡ እና ውሳኔ ሳያስተላልፉ መቆየት በአፈጻጸም ወቅት የታዩ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ::
ከዓለም ባንክ ሲ.አር.ኤም እና የ ቲ.ቲ.ኤፍ ፕሮጀክት መጓተትና በተያዘለት ጊዜ አለመከናወን፣ ከክልል የሚመጡ መረጃዎች በወቅቱ ያለመምጣትና ወቅታዊ አለመሆንም ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው :: በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢም ኮሚሽኑ በአፈጻጸሙ ወቅት ያጋጠሙትን ችግሮች መኖራቸውን ገልጿል:: ይኸውም በተደጋጋሚ ጊዜ የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ፣ ሰራተኞች ከድርጅቶች ጋር መጋጨት፣ድርጅቶቹ በሚፈለገው መጠን ምርቱን ለውጭ ገበያ እንዳያቀርብ አድርጎታል::
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የውሃና የኃይል አቅርቦት እጥረት፣ ተደጋጋሚ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥና የመሬት አቅርቦት ችግሮችም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈለገውን ማምረት እንዳይችሉ ዋና ማነቆ ሆነው መቀጠላቸውን አመላክቶ ችግሮችን ለመፍታት ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲያደርግ አጽንኦት ሰጥቶ ጠይቋል ::
የትኩረት አቅጣጫዎች
በጥናት ላይ የሚገኘውን የኢንቨስትመንት ህግ መሰረታዊ በሆነ መንገድ በማሻሻል አጠናቆ በማጸደቅ ተግባራዊ ማድረግ፣ የኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል የሃገሪቱን ምቹነት ደረጃ ማሳደግ፣ መንግስት ባዋቀረው አዲስ የመንግስት አደረጃጀት መሰረት ለተቋሙ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በሚገባ መወጣት ኮሚሽኑ በቀጣይ ሥራው ትኩረት የሚያደርግባቸው መስኮች ናቸው :: ለኮሚሽኑ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ ተቀምጧል ::
የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ዕድሎችን የማስተዋወቅ ስራዎችም የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግም ኮሚሽኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል ::
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ከመንግስት ጋር በመተባባር መፍታትና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ባሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሚከናወኑ ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መስራት፣ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መደገፍም ኮሚሽኑ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራበት ቀሪ የቤት ሥራዎች ናቸው ::
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
ይበል ካሳ