በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል በትኩረት እየተሰራ ነው። የመንገድ ፣የቴሌኮም ፣የሀይል እና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች እየተስፋፋ መምጣትም አንድም ኢንቨስትመንትን መሳብን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የባለሀብቶች መሰረታዊ ችግር የነበረው የቦታ አቅርቦትም በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ዞኖች መመስረት መፍትሄ እያገኘ መጥቷል። ባለሀብቶች አሁን የሚያስፈልጋቸው ማሽኖቻቸውን አምጥተው በመትከል በቀጥታ ወደ ስራ መግባት ብቻ ሆኗል።
ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ከቢሮ ቢሮ ይዞሩ ከነበረበት ሁኔታ ተላቀው በአብዛኛው በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በኢንቨስትመንት ኮሚሽኖች እና ቢሮዎች በተቋቋሙ የአንድ መስኮት አገልግሎቶች መፍትሄ እያገኙ መጥተዋል። ይህ አሰራር በሁሉም ክልል ተግባራዊ ባይደረግም ወደ አገልግሎቱ ለመምጣት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ከክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የእነዚህ አገልግሎቶች እየተሳለጠ መምጣት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ እያደገ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ በ2006 ዓ.ም ከነበረበት 1 ነጥብ 46 ቢሊዮን ዶላር በ2009 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም ይህንኑ ያመለክታል። አለመረጋጋት በነበረበት 2010 ዓ.ም 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱም ቢሆንም ለውጡን ያመለክታል።
ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨትመንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ታዋቂ የሆኑ ባለሀብቶች የተካተቱበትና የኢንቨስትመንቱ ምርቶች የውጭ ምንዛሬ እና ገበያ እንደልብ ማግኘት እንዲችል ያደረገም ነው። ይህም በኢንቨስትመንቱ ላይ በተሰራ ጠንካራ ተግባር የተገኘ ውጤት ነው።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ መንግስት የድጋፍ ፓኬጆችን አዘጋጅቶላቸዋል። ባለሀብቱ ከለመደው በቀላሉ የማትረፍ አባዜ መውጣት ጊዜ ስለሚወስድበት በዚህ አንጻር ያለውን ለውጥ ለመናገር ጊዜው አሁን ባይሆንም አንዳንድ ባለሀብቶች ለብቻቸውና ከውጪዎቹ ጋር ሽርክና እየፈጠሩ እየሰሩ መሆናቸው ግን ሊጠቀስ የሚገባውና መጠናከር ያለበት ተግባር ነው።
ከባለሀብቶች እና ከኢንቨስትመንት ቢሮዎች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በሀገሪቱ የተከሰተው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንቱ ላይ ያስከተለው የጎላ ችግር የለም። ባለሀብቶቹ አለመረጋጋቱን ጊዜያዊና በሁሉም አካባቢ የታየ ሲሉ ገልጸው፣ የጎዳቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን ጠቁመዋል። ሌሎች ባለሀብቶች ዘርፉን ለመቀላቀል እንደሚያማክሯቸውም ነው የገለጹት። በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የሚገኙ ባለሀብቶችም በየእርሻዎቻቸው ውስጥ መሆናቸው ተጠቁሟል። ይህ ትልቅ ዜና ነው። ኢንቨስትመንት ዘላን ነው ፤ ነገሮች ካልተመቹት መጭ ብሎ ይሄዳል›› ከሚለው አንጻር ሲታይም ኢንቨስትመንቱ በጠንካራ መሰረት ላይ መቆሙን ያመለክታል።
ኢንቨስትመንቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አሁንም ብዙ መስራት ያስፈልጋል። ሀገሪቱ ንግድ በቀላሉ የማይጀመርባት ተብላ በዓለም አቀፍ ደረጃ መፈረጇን ማጤንም ይገባል። ይህን ስም ለመቀየር የተጀመሩ ስራዎችን በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ባለሀብቱ ቶሎ ወደ ስራ የሚገባበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
ሀገሪቱ በአብዛኛው በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ታጥራ እንደመቆየቷም ኢኮኖሚው ክፉኛ ተጎድቷል። ለዚህም የውጭ ንግድ መዳከሙ ፣ ሀገሪቱ በዋጋ ንረት እየተቸገረች መሆኗ ማሳያዎች ናቸው። መንግስት አሁን ያለውን ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ በማጠናከር ኢንቨስትመንቱ ይበልጥ የሚነቃቃበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል።
ለዚህም ካለፈው ሳምንት አንስቶ በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማእከል እየተካሄደ ያለው የኢንቨስትመንት ሳምንትና ኢግዚቢሽን ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በኢግዚቢሽኑ ከተሞች ፣ ኢንቨስተሮች ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተሳተፉ ናቸው። ባለሀብቶች እንዳሉትም ኢንቨስትመንቱ ሀገሪቱ ለውጡን ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ሀይሎች በፈጠሩት አለመረጋጋት ብዙም ሳይደናገጥ ቀጥሏል።
በዚህ የኢንቨስትመንት ሳምንት በሚገባ የተሳተፈው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ነው። ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን፣አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጭምር ይዞ ነው በመድረኩ የተገኘው። ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን ይዞ የመጣው በሀዋሳ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታና የኢንቨስትመንት አማራጮች እና መስተንግዶ ከመንግስት ይልቅ ከባለሀብቱ ቢሰሙ ይሻላል በሚል ነው። ይህ ትክክለኛ እርምጃ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ በመድረኩ በዚህ አይነት መልኩ መሳተፉ ሌሎችም በአርአያነት ሊከተሉት የሚገባ ተግባር ነው።
ሀገሪቱ በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮችን በስፋት በማካሄድ ኢንቨስትመንቱ ይበልጥ እንዲነቃቃ ማድረግ ይኖርባታል። የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡት ለባለሀብቶች ነው። ፓርኮቹ በባለሀብቶች እንዲያዙ ደግሞ ተከታታይነት ያለው የኢንቨስትመንት መድረኮችን በማካሄድ ማስተዋወቅ ይገባል።
ሀገሪቱ ያጋጠማትን የዋጋ ግሽበት ለመታደግም አንዱ መሳሪያ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ፣ የስራ እድል መፍጠር ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደመሆኑ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲነቃቃ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011