ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት

በነሐሴ ጅብማ ሰማይ እና ነፍራቃ ክረምት ላይ ቆሜ ኢትዮጵያዊነትን ከኳሉና ካቆነጁ እውነቶች ውስጥ አንዱን መዘዝኩ..ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት። ጊዜ በተፈጥሮ አስገዳጅ ምህዋር ላይ እየተሽከረከረ ይሄዳል ይመጣል። የሰው ልጅም በዚህ የዘመን እሽክርክሪት ውስጥ መሪ ተዋናይ ሆኖ ይመላለሳል። ከመስከረም እስከ ነሀሴ።

እኛ ግን ከዓለም የተለየን ነን..በዘመን እሽክርክሪት ውስጥ ከሌላው የሰው ልጅ በተለየ መልኩ የምንረግጠው፣ የምንነካው፣ የምንደርስበት ሌላ የዘመን እውነት አለን..ጳጉሜ የሚባል። ጳጉሜ ሲነሳ አብሮ የሚነሳ አንድ ታላቅ ስም አለ እርሱም ኢትዮጵያዊነት ነው። በዚህ አንድ አይነት በሆነ ዓለም ውስጥ ለየት ብለን እንድንቆምና እንድንታይ ካደረጉን ሀገራዊ ትውፊቶቻችን መካከል ጳጉሜ አንዱ ነው።

ጳጉሜ ኢትዮጵያዊነት የፈጠረ የድንቅ እውነት መሰረት ነው። በዚህ ድንቅ እውነት ከዓለም ሁሉ ሌላ ነን። በዚህ ድንቅ እውነት የተለየ ታሪክ ባለታሪክ ነን። በዚህም ብዙዎች አይኖቻቸውን ወደ እኛ እንዲያነሱ፣ ጆሮዎች ለኛ እንዲከፍቱ የሚያደርግ ታሪካዊ እውነት ነው።

እኔና እናንተ የዚህ እውነት ባለቤቶች ነን፣ ዓለም የዚህ ታሪክ ባለቤት አይደለችም፣ እኛም ብንሆን ጳጉሜ እንደሰጠን፣ ከጳጉሜ እንዳገኘነው አይነት የወራት ገፀ በረከት የለንም። አብዛኞቹ በረከቶቻችን ከጳጉሜ ማህጸን ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው። ነሐሴን ተሻግረው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሚጀምሩ ናቸው።

ዓለም እንኳን ሲጠየቅ ‹ኢትዮጵያ እንዴት ሆና ነው አስራ ሶስት የወራት ጸጋዎች ያሏት? በምን አይነት የዘመን አቆጣጠር ህግ ነው አንድ ወር አምስትና ስድስት ቀን ብቻ ሊኖረው የሚችለው? ብሎ ነው። አዎ እውነት ነው ገና ዓለም ስለኢትዮጵያ የሚጠይቀው፣ የሚመራመረው ብዙ እውነት ይኖረዋል። ኢትዮጵያዊነት ያልተደረሰ፣ ያልተነገረ፣ ያልተደረሰበት ሩቅ ማንነት ነው።

በዘመን አቆጣጠር ስርዐታችን ውስጥ እንደ ጳጉሜ አይነት ዘመነ አጭር ግን ደግሞ የታሪክ ሀብታም የለም። እንደ ሀገር ከከበርንባቸው፣ እንድ ህዝብ ከተደነቅንባቸው ወራቶቻችን መካከል ጳጉሜ ፊተኛ ነው። ጳጉሜ የኢትዮጵያ ድንቅና ረቂቅ ባህረ ሀሳብ የፈጠራት የአባቶች የጥበብ ውጤት ናት። ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፣ ጥንታዊው ትውልድ ምን ያክል ከዓለምና ከስልጣኔ እንደቀደመ ጳጉሜን ማሰቡ በቂ ነው።

ዓለም ጊዜንና ዘመንን በአስራ ሁለት ወራት ሲከፍል ኢትዮጵያ አባቶቻችን በአስራ ሶስት ወራት የከፈሉበት ሚስጢር በራሱ ዓለም ያልተረዳው ምስጢር ነው። ያለምንም ጥርጥር ጳጉሜ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ። ጳጉሜ ውስጥ እውቀትና ጥበብ፣ ዘመናዊነትም ነፍስ ዘርተው አሉ።

ጳጉሜ ውስጥ ድሮነት ከነወዙ ተቀምጧል። ጳጉሜ ውስጥ የአባቶቻችን እውነት አለ። ለዚህም ነው ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት ነው ስል የተነሳሁት። ለዚህም ነው የጳጉሜ መባቻ በሆነው የነሐሴ ወር ላይ ቆሜ አጭሯን ወር የማስቃኛችሁ። ይህ ወር ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ፣ ብኩርናዋንም ቀድሞ የተናገረ ወራችን ነው። ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ ዘውድና ጎፈር ናቸው። ከታሪክ አብራክ የበቀሉ የእውነትና የጥበብ ግንድ። ከአባቶች የዘመን ፍሬ ውስጥ የጸደቁ የጥቁርነት ሰምና ወርቅ።

ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት፣ የአበው የሊቃውንት ድጓ ልሳን ናቸው። ከተንስኦ የጣሙ፣ ከታሪክ የላሙ ጸዐዳ ቀለሞች። ቀለማችን ጳጉሜ ነው። ከእውቀትና ከማይመረመው የጥበብ ኩሬ ውስጥ ዓለም ያልተረዳው፣ የሰው ልጅ ያልደረሰበትን የወራት ማለቂያ ፈልጎ ማግኘት አጀብ ብሎ ከማለፍ በቀር ምን ሊባል ይችላል? እንግዲህ ይሄ ነው ታሪካችን..ይሄ ነው ኢትዮጵያዊነት።

ዓለም አስራ ሁለት ወራትን ሲያከብር እኛ ግን በራሳችን እውነት ተረማምደን አስራ ሶስት ወራትን እናከብራለን። ዓለም አስራ ሁለት ወራትን እንደ አንድ ዓመት ሲቆጥር እኛ ግን በራሳችን እውቀትና ጥበብ ተመርተን አስራ ሶስት ወራትን አንድ ዓመት እንላለን።

ዓለም አንድን ወር ሀያ ስምንትና ሀያ ዘጠኝ ቀን ሰላሳም አድርጎ ሲቆጥር እኛ ግን በአባቶቻችን የጥበብ እውነት ልቀንና መጥቀን ጳጉሜን አምስትና ስድስት እንላለን። ታዲያ ልዩዎች አይደለን? ከዚህ በላይ ምን ጥበብ ምን ልቀት ይመጣል? በዘመን አቆጣጠራችን ዓለም ቢቀና ምን ይገርማል? ኢትዮጵያዊነት ያልተደረሰበት ጥበብ፣ ያልተደረሰበት ሚስጢር ነው።

አብዛኛው የዓለም ሀገራት ህይወቱን፣ ዘመኑን የሚቆጥረው በሌላ ሀገር የዘመን መቁጠሪያ ነው። አብዛኛው የዓለም ህዝብ አዲስ ዓመቱን የሚያከብረው በተወራረሰና የራሳቸው ያልሆነን የዘመን መቁጠሪያ ካላንደር በመጠቀም ነው። እኛ ግን በራሳችን ነው ይህ የትናንት አባቶቻችን ሙሉነት መገለጫ ነው።

ጰጉሜ የብዙ ነገር መጀመሪያችን ናት። የብዙ ህልሞች፣ የብዙ ተስፋዎች ማቆጥቆጫ አጸዳችን ናት። ከሰኔ ጉሩምሩምታ ሽረን፣ ከሀምሌ ጭጋግ ወጥተን፣ ከነፍራቃው ከነሀሴ እዬዬ ወደ ብሩህና ለምለሙ መስከረም የምናዘግምበት የንሰሀ ጎዳናችን ናት። የአደይ አበባ መፈጠሪያ፣ በዓመት አንድ ጊዜ የምትወጣው የመስቀል ወፍ ቀጠሮዋ ጳጉሜን ታካ ነው።

አሮጌውን አስተሳሰብና አሮጌውን ዓመት ትተን ወደ ከበረ ሰዋዊ እውነት የምንሳብበት ኃይላችንም ነው። ከፊታችን ላሉት አስራ ሁለት ወራቶች ሞገስ ሆኖን የሚቆም፣ ኢትዮጵያዊነት በተነሳ ቁጥር ከፊት የሚመጣ የወራት ቅንጣቢ ግን ደግሞ የታሪክ ባለጸጋችን ነው..ጳጉሜ።

ዘመን የራሱ የሆነ የታሪክ ገጽ አለው። እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ አንዳንድ ጠቢባኖች በዚህ የዘመን ገጽ ላይ ታሪክ የሚያወሳውን ታሪክ ጽፈዋል። አንዳንዶች ደግሞ ሌሎች በጻፉት ታሪክ ማጌጥን ምርጫ አድርገው ተቀብለዋል። ዓለም በታሪክ ገጹ ላይ ከጻፈው እውነትም ይሁን ጀብድ የሚልቀው የእኛ የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር ነው።

ለዚህ ደግሞ አንድ ጊዜ ዓለምን ማሰብ በቂ ነው። በአንድ አይነት ታሪክ፣ በአንድ አይነት እውነት፣ በአንድ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ናት። ወደ እኛ ስንመጣ ግን ከዓለም ልዩ የሆነ በርካታ ነገሮችን ማየት እንችላለን። የምናነበው፣ የምንጽፈው፣ የምንማረው፣ ከዘመን ዘመን የምንሻገረው አባቶቻችን በዘመን ገጽ ላይ በከተቡት እውነት ነው።

ጳጉሜ ለሁላችንም የለውጥ ሀሁ ናት። ሁሉን ትተን ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ የምናቀናበት የሰላማችን መዳረሻ ናት። ወደ አዲስ እምነት፣ ወደ አዲስ ተፈጥሮ የምናዘግምበት የለውጥ ጅማሬ እንዲህም ናት። እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ለምንም ነገር ጳጉሜን የምንጠብቅ ነን።

የጳጉሜ በረከት ከሌሎች ወራት የላቀ ነው። በመስከረም መንደርደሪያ ጳጉሜ ላይ ቆመን ተስፋ የምንሰንቅ፣ መታደስ የሚጎበኘን፣ አሻግረን ነገን የምንመለከት ብዙ ነን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካና የማህበራዊ ተልዕኮዎች ማስፈፀሚያ እየሆነች የመጣችበት ሁኔታም እያየለ ነው።

መንግስት እንኳን ጳጉሜን ዝም ብሎ ማለፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የጳጉሜን ወር የመልካም ምኞት መሸጋገሪያ፣ የበጎ ተስፋና፣ የበጎ ህልም ጅማሬ በማድረግ እየተጠቀምንበት ይገኛል። ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ እስከ አምስትና ስድስተኛው ቀን ድረስ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እየሰበክን መጥተናል። ይቅርታን፣ መቻቻልን፣ ኢትዮጵያዊነትን እየተናገርንበት መጥተናል።

ዘንድሮም በአዲስ አስተሳሰብ ጳጉሜን እንደምንቀበላት እምነቴ ነው። እናም ጳጉሜ ከወራት ባለፈ የአዲስ ነገር መጀመሪያችን ናት። ከጥበብ፣ ከታሪክ፣ ከስልጣኔ ባለፈ ፍቅርና አንድነትን የምንመሰክርበት፣ ጥላቻና ክፉ ነገርን የምንጸየፍበት፣ ያለፈውን ትተን የኢትዮጵያዊነት ቃል ኪዳን የምናስርበት የወራት ጌጣችን ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከዘመን፣ ከስልጣኔ፣ ከታሪክ፣ ከስርዐት፣ ከህገመንግስት፣ ከሀገር ግንባታ፣ ከመንግስት ምስረታ ከዓለም ቀደምት ማንነት ነው። አሁን ላይ ዓለም እየተለማመደችው ያለው ስልጣኔ፣ ዲሞክራሲ መሰረቱ ኢትዮጵያ ነበር። ኢትዮጵያዊነት ላለፈውም፣ አሁን ላለውም ለሚመጣውም ትውልድ ጥያቄ ነው። ዓለም በአስራ ሁለት ወራት ተኝታ ስትነቃ እኛ ግን በአስራ ሶስት ወራት ተኝተን እንነቃለን።

ታሪኮቻችንና ትውፊቶቻችን እንዳሉ ሆነው የዓለም ቀልብ የሚስቡ፣ ዘመን ሮጦ ያልደረሰበት ብዙ መስህብ ያለን ህዝቦች ነን። በአንድነት መተቃቀፍ ከቻልን ከዚህም በላይ ለዓለም መደነቂያ መሆናችን ይቀጥላል። እንዳንታይ፤ ታሪኮቻችን እንዳይወጡ ያደረገ የጥላቻና የዘረኝነት በሽታ መታከም ከቻለ ከዚህም በላይ የምንደምቅበት ጊዜ ይመጣል።

ጳጉሜን በተመለከተ አንድ ወዳጄ በአንድ ወቅት ያጫወተኝን ላካፍላችሁና ጽሁፌን ላጠናቅ ‹ሁሌ ጳጉሜ ሲመጣ ሌላ ሰው ነኝ። ራሴን ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩና ድንቅ ሆኜ የማገኘው በጳጉሜ ማግስት ላይ ነው። ችግሮቼ ሁሉ መስተካከል የሚጀምሩት የጳጉሜን መምጣት ተከትለው ነው። እያንዳንዱን ቀን እየሳኩ እየተደሰትኩ ነው የማሳልፈው። አናውቀውም እንጂ ወርሀ ጳጉሜ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ይዞልን የሚመጣው የሆነ ጸጋ አለው። ፈጣሪ ራሱ ሳናየውና ሳንሰማው በስውር መጥቶ ምድር ላይ የሚመላለስበት ወርም ይመስለኛል›።

እውነት ነው ጳጉሜ ደስ ትላለች። ብዙዎቻችን እንደምንለው የሚወደድ፣ የሚናፈቅ የሆነ ውብ ገጽ አላት። ከደስታ የዘለለ፣ ከፍሰሀ የተለቀ ጸጋን በጉያዋ ሸጉጣለች እላለው። የአስራ ሁለት ወር ማብቂያ፣ የአስራ ሁለት ወራት መጀመሪያ ስለሆነች የራሷ የሆነ የትዝታ ቀለም አላት።

የብዙ ታሪኮች መጀመሪያ፣ የብዙ ትዝታዎች ፍጻሜ ስለሆነች በመምጣቷ ውስጥ እንኖራለን በመሄዷ ውስጥም እንተክዛለን። ጳጉሜ የትዝታችን መጀመሪያና ማብቂያ ወር ናት። ኢትዮጵያዊነትን በአጭር ቁመት በጠባብ ወርድ ይዛ በእያንዳንዳችን ነፍስና ስጋ ውስጥ የበቀለች የትዝታችን ፈርጥ ናት።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You