ኢኮኖሚዋንም ሆነ የምግብ ፍጆታዋን በግብርናው ላይ የመሰረተችው ኢትዮጵያ፣ አብዛኛውን ምርት ከምታግኝባቸው አካባቢዎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ካለው የቆዳ ስፋትም ሆነ እምቅ ከሆነው የግብርና ሀብት አኳያ በሀገሪቱ የግብርና ስራ ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ይሄን ሚናውን በአግባቡ ለመወጣትም ሆነ የክልሉን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ በርካታ ተግባራትን ሲያከናወኑ ቆይቷል፡፡ እያከናወነም ይገኛል፡፡
ክልሉ፣በዝናብ ብቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ያሉበት እንደመሆኑም፤ እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታዎች ይሄን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ነው ከቢሮው የተገኙ መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በ2011/12 የምርት ዘመን በክልሉ በተለይም የበልግ የዘር ስራ እና የመኸር እርሻ ዝግጅት ላይ ያለውን ሂደት አስመልክቶ ዝግጅት ክፍላችን ላቀረበው ጥያቄ በኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በየነ ማሞ የሰጡንን መረጃ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
የበልግ ዘር ስራ
የበልግ ወቅት የሰብል ልማት ክንውንን በተመለከተ፣ በክልሉ ሊታረስና በዘር ሊሸፈን የታቀደው መሬት 910ሺ 550 ሄክታር ሲሆን፤ 13 ሚሊዬን 302ሺ 875 ኩንታል የተለያዩ ሰብሎችን ለማምረትም ነው እቅድ የተያዘው፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግም ለበልግ ወቅት የታቀደው እርሻ ሙሉ በሙሉ ታርሶ ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮም የዘር ስራም ተጀምሮ ነበር፡፡ ለዚህ ወቅት የሚሆን የግብዓት አቅርቦት በቢሮው አቅም በተለይም ማዳበሪያ በተጠየቀው መሰረት አገር ውስጥ በመግባቱ በዩኒዬኖችና በገበሬ ማህበራት አማካኝነት ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በዚህ በኩል በመጓጓዝ ሂደት የተፈጠረ መዘግየት ካልሆነ በስተቀር ከእጥረት አንጻር ያጋጠመ ነገር የለም፡፡
ዘርን በተመለከተ ግን በተለይ በበቆሎ ዘር በተፈለገው ልክ የሚፈለጉ ዝርያዎች ማግኘትና ማድረስ አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ዝርያዎችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፡፡ የዘር አቅርቦት እጥረቱ በአገር ደረጃም፣ በክልሉም ያጋጠመ ቢሆንም፤ ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ ዝርያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም በዝናብ እጥረትና መቆራረጥ ምክንያት የዘር ስራው መቀዛቀዝ ስለታየበት በተፈለገው ልክ እንዳይጓዝ አድርጎታል፡፡
በሚያዝያ ወር ላይ ግን እንደገና ዝናብ በመምጣቱ የዘር ስራውን በማከናወን በአሁኑ ወቅት የእቅዱን 45 በመቶ በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡ ሆኖም ይህ አፈጻጸም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አኳያ ሲታይ ዝቅተኛም ሲሆን፤ የበልግ ወቅት ስራ እየተገባደደ እንደመሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የዘር ስራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሆኖም የዝናቡ ሁኔታ በተለይ በክልሉ ምዕራባዊ ክፍል ላይ በእርሻ ዝግጅቱም ሆነ የረዥም ጊዜ ሰብሎችን በወቅቱ ከመዝራት አኳያ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
የመኸር እርሻ ዝግጅት
የመኸር እርሻን በተመለከተ በክልሉ ስድስት ሚሊዬን 64ሺ 875 ሄክታር መሬት አርሶ በዘር ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን፤ ከዚህም 186 ሚሊዬን 349ሺ 438 ኩንታል በላይ የተለያዩ ሰብሎች ምርት ይጠበቃል፡፡ ይሄን ለማድረግም የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፤ ያለውን የዝናብ ሁኔታ በመጠቀም እስካሁን ድረስ የታቀደው 19 በመቶ መታረሱን የእርሻ ክትትል መረጃ ያሳያል፡፡ የመኸር እርሻ ዝግጅቱን በተመለከተ የዘንድሮው እርሻ ከዚህ በፊቱ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ እንደ ቀድሞው ሁሉ ከዝናብና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ችግር እያጋጠመ ያለበትም ነው፡፡
መልካምና ፈታኝ ሁኔታዎች
የበልግ ዘር ክንውንም ሆነ የመኸር እርሻ ዝግጅት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የተከናወነ ከመሆኑ ባለፈ፤ የሚሰሩ ስራዎች እውቀት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማስቻል ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ስልጠናውም እንደየአካባቢው የአየር ፀባይና መልከዓ ምድራዊ ሁኔታ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜና ረዥም ጊዜ ሰብሎች በምን መልኩ በጥንቃቄ መሰራት እንዳለባቸው የሚያስችል ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ነው፡፡ በዚህም ከክልል ጀምሮ እስከ አርሶአደሩ ድረስ በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ስልጠናውን በጊዜ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የዚህ ስልጠና ተደራሽነትም ወደ ታች ሲወርድ የመቀነስ አዝማሚያ ያሳየ ቢሆንም፤ በዞን ደረጃ ከ95 በመቶ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ ከ90 በላይ ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት ስልጠናዎች ጋር ሲነጻጸር ግን የዚህ ዓመት ስልጠና በቁሳቁስ ታግዞና በእውቀት ላይ ተመስርቶ እርሻን ለማከናወን የተደረገው ጥረት አበረታች ነው፡፡
ከስልጠናው ባለፈ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን፤ ይህም በዞን፣ በወረዳ ብሎም በቀበሌ ያለውን ችግር በቅርበት ተረድቶ ተገቢው ምላሽና መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል እድልም እየፈጠረ ያለ ነው፡፡ የግብዓት አቅርቦቱን በተለይም የማዳበሪያ አቅርቦቱ በወቅቱ ተጠይቆ መቅረቡንና በአርሶ አደሩ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሌላው መልካም ነገር ሲሆን፤ በዚህ መልኩ የባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱና የአመራሩም ክትትልና ድጋፍ መኖሩ ለሚከናወነው ስራ ውጤታማነት እንደ መልካም እድል የሚወሰድ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የዝናብ መዛባት፣ የግብዓት አቅርቦት በማጓጓዝ ሂደት በተወሰነ መልኩ መጓተትና መዛባት፣ እንዲሁም የዘር አቅርቦት እጥረት በእነዚህ ወቅቶች ላይ እየተከናወነ ላለው የሰብል ልማት ስራ ፈታኝ ችግሮች ነበሩ፡፡
ቀጣይ ስራዎች
በክልሉ የተቀመጠውን የምርት መጠን ለማግኘት አሁን ላይ ያለው የበልግና የመኸር ግብርና ስራ በተጠናከረ መልኩ መከናወን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች የተጠናከረና ያላሰለሰ ርብርብ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም የተገኘውን የዝናብ ውሃ በማቆርና ሌሎች የውሃ ማቆያ ዘዴዎችን በመጠቀም የቀረውን የዘር ወቅት በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል እንዲሰራ እየተደረገና እየተሰራም ነው፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ መጀመሪያውንም ይሄ እንደሚገጥም ታሳቢ ተደርጎ ስለነበር እንደየአካባቢው የአየር ፀባይና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ እርጥበትን የማቆያ ዘዴዎች እንዴት እንደሚሰሩና በዘመናዊ መልክም እንዴት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚቻል ስልጠና ተሰጥቶ ስለነበረ፤ ይሄንኑ እየተጠቀሙ በቀጣይም አጠናክረው እንዲገፉበት የማበረታታት ስራ ተከናውኗል፡፡ እየተከናወነም ይገኛል፡፡
በሜቲዎሮሎጂ ትንበያ መሰረትም በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት ውስጥ ቀጣይነት ያለው ዝናብ ይኖራል ተብሎ ስለሚገመት፤ አጋጣሚው ከተገኘና ዝናቡም ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ ጊዜ ሳያባክኑ የዘር ስራውን እንዲቀጥሉና የታረሰው በዘር እንዲሸፈን ሰፊ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
መልዕክት
በእነዚህ የሰብል ወቅቶች የሚፈለገውን ስራ ሰርቶ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከአቅርቦት፣ ስልጠና፣ ክትትልና ድጋፍ ጋር በተያያዘም በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህ መልኩ እስከ አርሶ አደሩ ለማውረድ የተደረገው ትጋትና መፍጨርጨር መልካም እርምጃ ነው፡፡ ሆኖም አሁንም አርሶ አደሩም ሆነ ባለሙያው ተገንዝቦ ሊሰራቸው የሚገቡ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል፣ የሚገኘውን የዝናብ ውሃ በመከተርና የማቆር ስራን በሰፊው ሊሰሩ፤ ለእርሻ ስራው እርጥበትን ሊያስገኙ የሚችሉ የመስኖ ስራዎችን በሙሉ ጥቅም ላይ ሊያውሉ፤ በአፈር ውስጥ ያለው እርጥበት እንዳይጠፋ የተለያዩ እርጥበትን መያዣ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ፤ በመስኖ አጠቃቀም ሂደትም የውሃ ብክነት እንዳይከተል ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ከዚህ በዘለለ የተዘራውንም ቢሆን የተለያዩ የእርጥበት መጠበቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለምርት እንዲበቃ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዝናብ ሲዘንብም በተቻለ መጠን በዘመናዊ መንገድ በመሰብሰብና በማቆየት በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡ ዘርን በተመለከተም አርሶ ደሩ በጠየቀው ልክ መቅረብ ባለመቻሉ አርሶ አደሩ ይሄንን መጠበቅ ሳይኖርበት፤ የተገኘውን በአግባቡ በመጠቀም በጎደለ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ ትውልድ የሚባለውን ወይም ድቅል ዝርያዎችን አበጥሮና አዝርቶ በአማራጭነት ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡
በመሆኑም አርሶ አደሩ እነዚህንና መሰል አጋዥ እርምጃዎችን በመውሰድ፤ ያለውን መልካም አጋጣሚና ችግሮችም በመረዳት አጋጣሚዎችን በአግባቡ በመጠቀም በክልሉ የተቀመጠውን የምርታማነት ግብ ለማሳካት የበኩላቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ወንድወሰን ሽመልስ