ታሪክ በአንድም በሌላም መንገድ ይሰራል፤ ይመዘገባል። አገራችን በታሪኳ አንገት አስደፊም አቅኝም ታሪኮችን አሳልፋለች። ከቅኝ ግዛት ነጻ አገርና ህዝብ መሆናችን የራሳችን በርካታ ማንነቶች እንዲኖሩን ያደረገን ስለሆነ ኩራታችን የትየለሌ ነው። በአንጻሩ የድህነት ታሪካችን አንገት አስደፊ የረሀብና የስደት ታሪክ ባለቤቶች አድርጎናልና እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የረሀብ ምሳሌ ሆነን ኖረናል። በዚህም አዝነናል፤ ተዋርደናልም።
“ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም” እንዲል ብሂሉ፤ ያለፈውን ውድቀታችንን እያነሳን መብሰልሰሉ ቁልቁል ቢያዘመን እንጂ ሽቅብ አያዘምነንም። እርባና ቢስነትም ነው። ስለሆነም ላለንበት ዘመን የሚመጥን ታሪክ ሰርተን በመጪው ትውልድ በታሪክ ለመዘከር መትጋት ጊዜ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።
ከዚህ አንጻር “ያለንበት ጊዜ የለውጥ ነው” ብለን አምነን ለዚህ የሚሆን ተግባር ለመፈጸም እድሉ ከፊታችን ነው። ለውጡ የተለወጠ አስተሳሰብና የተለወጠ ትግበራ ይፈልጋል። እውነቱ ይሄ ነው። በዚህ ልክ መራመድ አንድም ልክ፤ አንድም ግድ ነው።
ታሪክ እንሰራ ዘንድ ለውጡ ከፊታችን ካኖረልን የታሪክ አጋጣሚ መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻ መናፈሻ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ እስከ 29 ቢሊዮን ብር የሚፈልገው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ሊተገበር ጫፍ ላይ ደርሷል። በዚህ ፕሮጀክት ላይ አሻራን ማሳረፍ አገራዊ ኃላፊነት ነው ብለን እናምናለን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ብዙ መጣራቸው የእስካሁኑ ውጤት ያሳያል። በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ በስራ አጋጣሚ ያገኟቸውን መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች አግባብተው ለሸገር ራት እስካሁን 250 እንግዶችን ቃል አስገብተዋል። ይህንን ቁጥር በአንድ ገበታ አምስት ሚሊዮን ብር ሂሳብ ሲሰላ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው። (ለአንድ ገበታ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የከፈሉ እንዳሉም ሳይዘነጋ ማለት ነው) በዚህ ተግባራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ይገባቸዋል። ከምስጋና መልስ ሌሎች ሚኒስትሮችና አምባሳደሮቻችንስ በዚህ ዙሪያ ምን ሰሩ፤ ምን አመጡ፤ ማን ከማን የተሻለ አፈጻጸም አለው፤ ይህ የታሪክ ምዕራፍ በስኬት ይዘጋ ዘንድ ማን ደከመ? ማን ለገመ? በሚል ሊጠየቁ ይገባል።
የሸገር እራት ነገ ነው። ነገ ሌላም መርሀ ግብር አለን፤ ከተሞቻችንን ማጽዳት። የጸዳ ከተማ እና የጸዳ የወንዝ ዳር መናፈሻ በብዙ ምክንያት ይመጥነናልና ይገባናል። ከቆሻሻ ጋር ተለማምደንና ተስማምተን መኖራችን ይብቃን። ይበቃናል ካልን ደግሞ እነዚህን መርሀ ግብሮች መሬት ማስያዝ በመሬት ከመባላት በብዙ እጥፍ የተሻለ ታሪክ ነውና ሁሉም ወገን በየፊናው ይትጋ።
ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ይሳተፍ፣ እውቀት ያለው እወቀቱን ያፍስስ፣ ጉልበት ያለው ለጉልበቱ አይሰስት። ገንዘብን፣ እውቀትን አሊያም ጉልበትን መንፈግ መብት ቢሆንም፤ ትክክል ነው ግን ሊባል አይችልም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የዚህ አይነት ወገኖች ከቀና አስተሳሰባቸው ይልቅ ነቀፌታቸው የወፈረ ነውና ቢያንስ ዝም ይበሉ።
ግብጽ ሰሞኑን በናይል ወንዝ ላይ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ተንጠልጣይ ድልድይ በካይሮ መሀል ሰርታ አስመርቃለች። ይህ ቁጭት ሊያሳድርብን ካልቻለና የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ልማት ዳር ማድረስ ካልቻልን እውነትም ታሪክ አውሪ እንጂ ታሪክ ሰሪ መሆናችን ከሽፏል። አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ማድረግ አለብን ካልን በህልም ወይንም በምኞት ብቻ አይሳካም። በዚህ አይነት ግዙፍ ወገብ አጉባጭ ፕሮጀክቶችም ጭምር እንጂ። ስለሆነም ይህንን ፕሮጀክት ከዳር ማድረስ ኩራትም ራትም ነው ብለን እንነሳ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011