በሰውነታችን የተለያዩ እጢዎች ይገኛሉ። እነዚህ እጢዎች የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በማምረት በሰውነታችን ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።ከእነዚህ እጢዎች መካከል፡- ታይሮይድ የሚባለው አንደኛው ነው። ከእነዚህ እጢዎች የሚመረተው ንጥረ ነገር በሚበዛበት ወይንም በሚያንስበት ጊዜ ሰውነታችን የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። የምልክቱ ክብደት እና ዓይነት እንደሚመረተው የንጥረ ነገር መጠን የሚወሰን ነው። ለዛሬ ታይሮይድ የሚባለውን በሰውነት የሚገኘውን እጢ እና እሱ የሚያመነጨውን ንጥረ ነገር በመብዛት የሚከሰተውን የህመም አይነት (Hyperthyroidism) ወይም እንቅርት ተብሎ የሚጠራውን የህመም አይነት እንመለከታለን።
የታይሮይድ እጢ በፊት ለፊተኛው የአንገታችን ክፍል ውስጥ የሚገኝ አካል ነው። ቅርፁም የቢራ ቢሮ ዓይነት ቅርፅ ያለው ነው። ይህ እጢ የተለያዩ ሆርሞኖች (ንጥረ ነገሮችን) የሚያመርት ሲሆን በዋናነት T3 እና T4 የተባሉ ኬሚካሎችን ያመርታል።እነዚህ ኬሚካሎች የሰውነታችን ሥርዓት (ዑደት) የሚቆጣጠሩ ናቸው። ለምሳሌ ያክል፤የልብ ምትን፤የሰውነት ሙቀት፤ የእንቅልፍ ስርዓትን፤ የካርቦ ሐይድሬት (ስኳር) እና የፕሮቲን ምርት እና አጠቃቀምን፤በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ባህሪያችንን የሚቆጣጠሩ ኬሚካሎች ናቸው።
እንግዲህ ይህ እጢ (ታይሮይድ) ከመጠን ያለፈ T3 እና T4 የተባለውን በሚያመርትበት ወቅት ከላይ የጠቀስናቸውን የሰውነት ሥርዓትን ያውካል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከመጠን በላይ በሚመረቱ የሚኖረው ምልክት የተጋነነ ይሆናል።ይህ ማለት ከላይ ለአብነት የተጠቀሱት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ እና ሰውነት ከሚፈልገው በላይ ይሆናል።
ምልክቶቹ
የእንቅርት በሽታ (Hyperthyroidism) ምልክቶች በጣም ሰፊ እና ከሰውነት ሰውነት ክፍል የሚለያይ ነው። እንዲሁም በሚመነጨው መጠንም የሚወሰን ነው። በአብዛኛው የእንቅርት በሽታ እንደሚታወቀው በፊት ለፊት ከሚታየው እብጠት ውጪ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምልክቶች የሚያሳይ ይሆናል።
- የላብ ስሜት (ከፍተኛ የሆነ የላብ ስሜት)
- ሙቀትን ወይንም ቅዝቃዜን አለመቋቋም
- የልብ ምት መጨመር እንዲሁም መዘበራረቅ (እየቆየ ሲሄድ ደም ግፊት ማምጣት)
- የምግብ ፍላጎት መጨመር ነገር ግን እንደ አበላላችን ሳይሆን፤ክብደት መቀነስ
- እንቅልፍ ማጣት
- የፀባይ (ባህሪ) መቀያየር (የቁጡነት እና የተነጫናጭነት ባህሪ) ማሳየት
- ከእብጠቱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶች/ማለትም እብጠቱ እየጨመረ ሲመጣ ትንፋሽ ማጠር፤ድምፅ መቀየር የመሳሰሉት ይገኙበታል።
መምጫ ምክንያቶች
እንቅርት መምጫ ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም በዋናነት የሚጠቀሰው የአዮዲን (Iodine) እጥረት ነው።ሌሎች እንደ ካንሰር፤ የታይሮይድ እጢ መቆጣት ወይም ኢንፌክሽን የሚያመጡ ቢሆንም፤ የመከሰት ዕድላቸው ግን በጣም አናሳ ነው።በተጨማሪም በተፈጥሮ የሚከሰቱ (በአፈጣጠር ችግር ) የሚከሰቱ የእንቅርት (Hyperthyroidism) ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
እንደ እርግዝና እና በአፍላ የዕድሜ ክልል መሆን ለህመሙ መምጫ ሆነውም ይጠቀሳሉ።
ምርመራው እና ህክምናው
ልክ እንደማንኛውም ህመም የእንቅርት በሽታን ለማወቅ (ለመመርመር) የበሽታው ምልክቶችን በአግባቡ መጠየቅ ያስፈልጋል። ከላይ የተጠቀሱትን የበሽታ ምልክቶች ከአካላዊ እና ላብራቶሪ ምርመራዎች ጋር በማያያዝ ህመሙን ማገናኘት ይቻላል። ከሚደረጉ ምርመራዎች ውስጥ የ T3 እና T4 መጠንን በደም ውስጥ መለካት እንዲሁም እነዚህን እንዲመረቱ የሚያደርግ ሆርሞንን (TSH) መጠኑን በደም ውስጥ መለካት ዋነኛዎቹ ናቸው። በመቀጠል እንደ አልትራሳውንድ፤ ሲቲእስካን፤ የመሳሰሉት የምስል ምርመራዎች ደጋፊ ይሆናል።
ሌሎች ምርመራዎች ከበሽታው ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች የሚደረጉ ምርመራዎች ናቸው ለምሳሌ የልብ ምርመራ፤ የዓይን ምርመራ፤ ወ.ዘ.ተ ናቸው።
የእንቅርት ህመም ህክምናውን እንደ ላብራቶሪ ውጤት እና እንደ በሽተኛው የሚያሳየው ምልክት የሚወሰን ይሆናል። የህክምናው አማራጮች ውስጥ የሚዋጥ መድኃኒት አንስቶ እስከ ቀዶ ጥገና ድረስ የሚሄድ ይሆናል። የእነዚህ የህክምና አማራጮች የሚወሰነው በሐኪምዎ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011