አገራቸው ኢትዮጵያን ልክ እንደ ነብሳቸው እንደሚወዷት ይናገራሉ። እረ እንደውም ከነብሳቸው በላይ እንደሆነ ነው የሚገልጹት። ለሀገራቸው ከቴሌኮሙኒኬሽን ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ባለሙያነት ሰርተዋል። በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የዘለቀ ልምድ ያላቸው አንጋፋ ባለሙያ ናቸው። የታሪክ ተቆርቋሪነት እና የቱሪዝም ሥራን አጣጥሞ ያስኬደ የኢንቨስትመንት ሥራ በማከናወን ይበል የሚያሰኝ ተግባርንም ፈጽመዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከደብረብርሃን ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው በሚያገኟት ቀዝቃዛማዋ አንኮበር አካባቢ ከተራራው በላይ የተቀመጠ ታሪካዊ ሎጅ ገንብተው አገራቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ።
ኢንጂነር ተረፈ የተወለዱት በ1928 ዓ.ም በታሪካዊቷ አንኮበር አፈር ባይኔ የተባለው ገዳም አካባቢ ነው። የትምህርት ጊዜያቸው ያለፈው ግን አዲስ አበባ ላይ ነው። ይህን ሁሉ እንዲሆን ደግሞ የወራሪው ጣሊያን አስተዋጽኦ ነበረበት። ምክንያቱም ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ወርሮ አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት አባታቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ግዕዝ እና አማርኛ ቋንቋን ያስተምሩ ነበር። ጣሊያን ሲገባ ግን ወላጃቸው ቤተሰባቸውን ጠቅልለው ወደ አንኮበር ገቡ። በዚህ ወቅት ነበር ኢንጂነር ተረፈ የተወለዱት።
ይሁንና ጣሊያን በአርበኞች እና እንግሊዝ ጦር ትግል ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ የኢንጂነር ተረፈ ቤተሰቦችም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ይወስናሉ። በመሆኑም የዛሬው ኢንጂነር የያኔው ድንቡሽቡሽ ህጻን ተረፈ ገና በአምስት ዓመታቸው ወደ መዲናዋ የመምጣት ዕድሉ ተመቻችቶ ቀረበላቸው። በመዲናዋ የትምህርት ጊዜያቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለው የመጀመሪያ ደረጃ ብሎም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲጠናቀቅ ጥሩ ውጤት በመያዛቸው ደግሞ በቀጥታ ያመሩት ወደ ቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነበር። በዚያም ምህንድስናን ለሦስት ዓመታት የሙጥኝ ብለው ተማሩ። የአፄ ኃይለስላሴ መንግሥት በወቅቱ ለተማሪዎች የውጭ አገራት ነፃ የትምህርት ዕድል ይሰጥ ነበርና ወደ አሜሪካ መላካቸው አልቀረም። በዚያም በኒውዮርክ ትሮይካ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪክ ምህንድስናን ትምህርት ለሁለት ዓመታት ተከታተሉ። ቀድሞም አገራቸውን ማገልገል ነበርና አላማቸው ወደሀገራቸው ተመልሰው ለመስራት ወሰኑ።
ኢንጂነር ተረፈ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማት ውስጥ ለመቀጠር ይጠይቃሉ። አየር መንገዱ ተስማምቶ ነገር ግን አዲስ ለሚገዙት ጀት አውሮፕላን የሚሆን ቴክኒክ አሰራር እንዲማሩ አሜሪካን እንደሚልካቸው ይነግራቸዋል። በዚህ ያልተስማሙት ኢንጂነር ተረፈ አየር መንገዱን ሳይቀላቀሉ ቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱን ተቀላቀሉ። በዚያም በ450 ብር የወር ደመወዝ በ1952 ዓ.ም አሀዱ ብለው ሥራ ጀመሩ። ለሥራ የሚሆናቸውም ቮልስ ዋገን መኪና ተመድቦላቸው የቴክኒክ ክፍሉን ማለትም የስልክ እና ቴሌግራም ቁጥጥር ቴክኒክ ሥራውን መምራት ጀመሩ።
በቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ የአማርኛ ጽሁፎችን የሚተይብ የቴሌግራም መሳሪያ ባለመኖሩ አንድ ቀን መፍትሄ ለማበጀት ይነሳሳሉ። ውጥናቸው ተሳክቶ የመጀመሪያውን የአማርኛ መተየቢያ ቴሌግራም መሳሪያ ማዘጋጀት ቻሉ። ይህን ያየው ዓለም አቀፉ የሲመንስ ኩባንያ የአዕምሯዊ ንብረትነቱ የኢንጂነር ተረፈ የሆነውን ማሽን በማምረት በእያንዳንዱ ሽያጭ ክፍያ መፈጸም ጀመረ። ለኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ሽያጭ ሲፈጸም ከመሳሪያው አምስት በመቶ እና ለሌሎች ተቋማት ሲሸጥ ደግሞ አስር በመቶ የመሳሪያውን ዋጋ እየቆረጠ መክፈሉንም ቀጠለ። ኢንጂነር ተረፈ በውጤቱ እና በገቢው ደስተኛ ሆነዋል።
አስር ዓመት በቴሌኮሙኒኬሽን እንደሰሩ
ግን አንድ የሥራ ውድድር መጣ። ጄኔቫ የሚገኘው የዓለም አቀፉ ቴሌኮሙኒኬሽን ማህበር የአፍሪካ አገራት ኃላፊነት መደብ ሥራ ለመወዳደር መስሪያ ቤታቸውን ጠይቀው ተፈቀደላቸው። ውድድሩንም አሸንፈው የዓለም አቀፉ ቴሌኮሙኒኬሽን ማህበርን ተቀላቀሉ።
በዚያም የአፍሪካ ክፍል ዋና ኃላፊ፣ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ልዩ አማካሪ እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ለ30 ዓመታት በማገልገል የካበተ ልምድ ይዘዋል። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ደግሞ የአፍሪካ አገራት በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲገናኙ በሚደረገው ጥረት ዋነኛ ተዋናይ ነበሩና በየጊዜው ለሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ መምጣታቸው አልቀረም።
በመቀጠል ደግሞ ለንደን የሚገኘው ወርልድ ቴል የተባለ ኩባንያ ሲቋቋም ወደዚያም አምርተው ለአሥር ዓመታት አገልግለዋል። ለግማሽ ምዕተ ዓመት ከዘለቀው የቴሌኮሙኒኬሽን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በኋላ ግን ወደ ትውልድ አገራቸው ጠቅልለው በመግባት በኢንቨስትመንቱ መሰማራትን ነው የመረጡት።
አዲስ አበባ ቢያርፉም ልባቸው ግን ወደ አንኮበር መሸፈቱ አልቀረም። ወደ ትውልድ መንደራቸው አንኮበር በማቅናት ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ያጠኑ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚያም የአብነት ትምህርት ቤት አቋቁመው ካደጉበት አካባቢ ህብረተሰብ ጎን መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል።
በወቅቱ ግን በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የአስተዳደር ማዕከል የነበረው የምኒልክ ቤተመንግሥት ደብዛው ጠፍቶ ቢያዩት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ልባቸው ነገራቸው። ጣሊያን ዳግም ኢትዮጵያን በወረረ ወቅት በእሳት አጋይቶት የጠፋው ቤተመንግሥት ዳግም ሰርተው ሎጅ ማድረግ ወስነዋል።
ቤተመንግሥቱ በአማረ ሁኔታ ተገንብቶ በሎጅ መልክ አገልግሎት ቢሰጥበት ከቦታው መልክዓምድር ውበት እና ከታሪኩ ጋር ተቆራኝቶ በርካታ ጎብኚዎችን ሊስብ እንደሚችል ገምተዋል። እናም ቦታው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሲጠይቁ ከቅርስ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ማስፈቀድ እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። በጊዜው ጉዳዩን አስረድተው በፍጥነት ሊፈቀድላቸው ባለመቻሉ ያለመታከት ለሦስት ዓመታት ያህል እንደተመላለሱ ያስታውሳሉ።
ከብዙ ማሳመን እና ጉትጎታ በኋላ ግን ኢንቨስትመንቱ በታሪካዊው ቦታ ላይ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ከባለስልጣኑ ፍቃድ ያገኛሉ። በቀጣይ ደግሞ ወደ አማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም መሄድ አለባቸውና እዚያም ጉዳዩን አስረድተው ፈቃዱ ተሰጣቸው። ዝግጅቱን ከጨረሱ በኋላ በሊዝ ዋጋ ለ50 ዓመታት ቦታውን የተቀበሉት ኢንጂነሩ አንኮበር ቤተመንግሥትን ሊያስውቡ ተነሱ።
በዓለም አቀፍ ተቋማት ሲሰሩ ያገኙትን ገንዘብ አሰባስበው ታሪካዊው የትውልዳቸው ቦታ ላይ ቤተመንግሥቱን ማስገንባት ጀመሩ። የስነ-ጥበብ ይዘቱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ሁነኛ ባለሙያ ከጎናቸው አድርገው በቂ ውሃ እንኳን በሌለበት ግንባታውን ማፋጠን ተያያዙት። ጥንታዊ ይዘት ያላቸውን የአንኮበር ቤተመንግሥት የግንብ አሰራር ዲዛይን እንዲመስል ለሥራው የመረጡት የአካባቢውን ህብረተሰብ ነው። ነዋሪውን በማሰልጠን በሥራው ላይ አሰማርተዋል። እንዲህ እንዲህ እያሉ በሚሊዮኖች የወጣበት ታሪካዊ ሎጅ በሦስት ዓመታት ውስጥ አስገንብተው አጠናቀቁ።
አንኮበር ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኗ እና ከደብረብርሃን 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ በመሆኑ የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ነበር ህልማቸው። የገነቡት ሎጅ በዓመት እስከ 500 የውጭ አገር ዜጎች ይስተናገዱበታል። ለአንድ ቀን አዳር 65 ዶላር ለውጭ አገር ዜጎች የሚያስከፍለው ሎጁ ጎብኚዎችን እንዲሁም የምግብ እና መጠጥ ተጠቃሚዎችን የማስተናገድ አቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም ገቢው ግን እንደታሰበው እንዳልሆነ ኢንጂነር ተረፈ ይናገራሉ።
ይሁንና ታሪካዊ ቦታው እንዲታወቅ እና ቅርስነቱ እንዲጠበቅ በማድረጋቸው በኢንቨስትመንት ሥራቸው አይቆጩም። ይልቅንም ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ እና ገቢ ማስገኛ በማኖራቸው ደስተኛ ናቸው።
የኢንጂነር ተረፈ አንኮበር ሎጅ በአሁኑ ወቅት ለ40 ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል እና በየጊዜው ደግሞ ለ50 ሠራተኞች ጊዜያዊ ዕድል ፈጥሯል። በሎጁ ከሚሰጡ ዋነኛ አገልግሎቶች መካከል ደግሞ ወደፊት ተስፋ የተጣለበት የባህላዊ ሰርግ ክንውኑ ነው። ኢንጂነር ተረፈ እንደሚናገሩት ባህላዊ ሰርግ በአንኮበር የሚያደርግ ሰው ነጋሪት ተጎስሞለት በፈረስ ታጅቦ እና እንቢልታ እየተነፋለት ነው።
አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ በተጋቡበት ባህላዊ አዳራሽ ተድሮ ሲወጣም ልክ እንደንጉሳዊ ቤተሰብ ነው መስተንግዶ የሚደረግለት። በመሆኑም የሎጁ የቱሪዝም ገቢ መፍጠሪያነት በቀጣይ ጊዜያትም እንዲጨምር በየጊዜው ሥራዎች ይሰራሉ።
ኢንጂነር ተረፈ ከሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፉ በተጨማሪ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉም ገበያ ፈጥረው መስራት ጀምረዋል። ከልጃቸው ኢዛና ተረፈ ጋር ባቋቋሙት ኢሊቲ ኢንፎ ሰርቪስ በተባለ ኩባንያ አማካኝነት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስኩም ተሰማርተዋል። ድርጅቱ በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ አገራት የድረገጽ ግንባታ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ እና ማማከር እንዲሁም ተያያዥ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
«ያለኝ ሃብት እና ያወጣሁት ገንዘብ ተመጣጣኝ ባይሆንም ለታሪክ እና ለሀገር ያበረከትኩትን ሥራ ነው የማስበው» የሚሉት ኢንጂነር ተረፈ አሁን ላይ መንግሥትን በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ እያማከሩ ለሀገራቸው ማገልገል እንደሚፈልጉ ነው የሚገልጹት።
ማንም ሰው ከሰራ እና በሀቀኛ መንገድ ከተንቀሳቀሰ መጨረሻው ማማሩ አይቀርም የሚሉት ኢንቨስተሩ፣ ታሪክ እና ቅርስን ያማከለ ገበያ መፍጠር ደግሞ ከሁሉም በላይ ሊታሰብበት ይገባል ባይ ናቸው። «እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የአገሩን ጥቅም ባስከበረ ሁኔታ ሰርቶ ለመለወጥ አላማ ካለው እና ስርቆት ውስጥ ካልገባ ያደገች እና ለዜጎቿ የተመቸች አገር ትኖረናለች፤ እናም እውነተኛ የሥራ መንገድን ተከትሎ በመሄድ ማደግ ይቻላል» የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ጌትነት ተስፋማርያም