
በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ አንድ የማይረሳ ስም አለ። ቢኒያም አድማሱ የሚባል። በዘመናት መካከል ላይረሳ ተከትቧል። ቢንያም እስከ ሞት የመታመን ምልክት ነው። የምድር ቆይታው 33 ዓመታት ብቻ ነው። በጅምር የቀረው የዕድሜው ዘመን በከንቱ ያለቀ አልነበረም። ከዚህች ጥቂት ዓመት ውስጥ ረጅሙን ዓመት ፓርኩን በማገልገል ያለፈ ነው። ይህ ሰው ብሔራዊ ጀግና ነው። ስለ ጀግንነቱም ሐውልት ተቀርፆለታል።
የመንዝ ጓሳን ፓርክ ከአቋቋሙት መካከል ነው። የአካባቢ ተቆርቋሪ ነበር፤ የኢኮ ቱሪዝም ባለሙያም ጭምር። የፓርክ ሥራው በባሌው ፓርክ ብቻ አልተገደበም። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንም ያስተዋውቅ ነበር። በፍራንክፈርት የእንስሳት ጥናት ማኅበር ውስጥ ሠርቷል።
ቢንያም ለተፈጥሮ እጅ የሰጠ ባለ ብዙ ተስፋ ወጣት ነበር። ወጣቱ ለቀይ ቀበሮ የነበረው ፍቅር ይታወቃል። ይኸው ፍቅሩ እስከ ሞት አድርሶታል። ስሙ አካባቢውን የሚያፈቅር ወጣት ስም ነው። ባለ ስሙ በሞቱ እናቱን ያስከተለ ለቤቱ ያጎደለ ነው። ወላጅ እናቱ መሠረት ስሜ ይባላሉ። ሀዘኑን መቋቋም አቅቷቸው በሞተ በዓመቱ ተከትለውት ወደማይቀርበት ሄደዋል። እሱ የተመጠነ ግን በአግባቡ የተኖረ እድሜ ባለቤት ነው።
ሰው ተማክሮ ሀገር ለማፍረስ በሚጥርበት ዘመን ተፈጠረ። እሱ ግን ላመነው ተፈጥሮ ተሰዋ። ስለ ታማኝነት በዘላለም ህያውነት ይመሰክራል። ከተፈጥሮ እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ፍቅር ሲያዙ እንደ ቢንያም ነው። ቢንያም በ2007 ከመኖር የተቋረጠ ነው። በፓርኩ በተነሳው እሳት ነፍሱ ከስጋው ተለይቷል። ቀይ ቀበሮ ከሚቃጠል መሞትን ምርጫው አደረገ። ለሞት የዳረገው የሚያጠፋው እሳት ነፋስ አቅጣጫ መቀየሩ ነበር። እሱ ሕይወቱ ባለፈበት እሳት ጓደኞቹም ተጎድተዋል። ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባቸው በሕይወት መትረፍ ችለዋል። ቢኒያም ግን መስዋዕት ሆነ።
ሕይወቱ ቢያልፍም ታሪክ በመልካም ከትቦ ሲያወሳው ይኖራል። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እስካለ ድረስ ቢንያምም አለ። ባለፈው ሰኞ ደግሞ ይህ ፓርክ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። እንደዚህ ባለ የድል ቀን ደግሞ ቢንያምን አለማስታወስ ከባድ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ይህን ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ ሲል ወዳጅ ዘመዶቹን ጠየቀ።
እዮኤል አድማሱ ይባላል። የቢንያም የአስር ዓመታት ታናሽ ነው። ስለ ወንድሙ ይናገራል። ቢንያም እንደ አባት ያስተማረው ወላጁም ጭምር ነው። ከተፈጥሮ ፍቅር የያዘው ሰው መሆኑን መስክሯል። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መመዝገብ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፈጥሮበታል። በፓርኩ መመዝገብ ሲደሰት ለሂደቱ ሲጥር ለኖረው ወንድሙ በሕይወት አለመኖር አስቦ ተክዟል። የቢንያም አይነቱ የአካባቢ ፍቅር በትምህርት አይመጣም። ከተፈጥሮ ጋር በመግባባት እንጂ ይላል። የሱ ተፅእኖ ቤተሰቡን ለተፈጥሮ እጅ እንዲሰጥ አስገድዷል። ጓደኛና የሥራ ባልደረቦቹ ላይ ጭምር ተፅዕኖው አለ። በአካባቢ ላይ ያለውን አመለካከት መቀየር ችሏል።
እንደ ቤተሰብ መሞቱ ማጉደሉ በወንድሙ ተነግሯል። እሱን ተከትሎ የእናታቸው ሞት ለቤተሰቡ ከባድ ጊዜ ሰጥቷል። እንደ ቢንያም ያለ እስከ ሞት የታመነ ወንድም ነበረው። ይህ በራሱ ለእዩኤል ትልቅ ክብር ነው። ወንድም መሆን የሚሰጠው ክብር ሕይወቱ ካለፈም በኋላ አላሳጣውም። ይህን የቢንያምን አስተዋፅኦ በማሰብ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ቤተሰቡን ሸልሟል። የሕይወት ዘመን የቱሪዝም ስኬት ሽልማት። ወጣት እዮኤልም ቤተሰቡን ወክሎ የክብር ሽልማቱን ተቀብሏል።
ሌላኛው የቢንያም መስካሪ ምስክርነቱን ቀጥሏል። በፓርኩ የቱሪዝም ክፍል ተወካይ ነው። የቢንያም ወዳጅም ጭምር። ሽመልስ ወንድሙ ይባላል። ለሱ የቢንያምና የተፈጥሮ ቁርኝት በግርምት ይታያል። ከወዳጅ ዘመድ ጓደኛ ጎረቤት ሁሉ ጋር ወሬው አይቀያየርም። ስለ ተፈጥሮ ብቻ ነው። እንዴት አድርገን ተፈጥሮን እንጠብቅ የሚል ለሀገሩ ተቆርቋሪ ነው።
በተለያዩ ጊዜ በውጭ ሀገራት ተጉዟል። ለምን ተመለስክ ሲባል መልሱ ሁሉንም ሰው ያስገርማል። ያለ ቀይ ቀበሮ መኖር አልችልም ይል እንደነበር ሽመልስ ይናገራል። ተፈጥሮ የስጋ መንፈሱ እረፍት ናት። አምኖ ለወደዳት ተፈጥሮ ተሰዋ። የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የቢንያም የምንጊዜም ምኞት መሆኑንም ሽመልስ ገልጿል። ቢንያም ስጋው ቢያርፍም ስሙ በሁሉም የሚወሳ እንደሆነ በወዳጁ ተመስክሮለታል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም