ዛሬ መሃል አዲስ አበባ እንሁን፤ በነገራችን ላይ በአንድ ሰፈር ውስጥ ብቻ ብዙ ትንንሽ ሰፈሮች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ በተለይም አንዳንድ ሰፈሮች ሰፊ ስለሚሆኑ በውስጣቸው ንዑስ ሰፈሮችን የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ እስኪ ካዛንቺስ አካባቢ እንቆይ፡፡ መቼም ካዛንቺስን የማያውቅ ማግኘት ከባድ ነው፤ ቢያንስ ቢያንስ በስም ያልሰማ አይኖርም፡፡ ካዛንቺስ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከአራት ኪሎ በስተደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ካዛንቺስ ለምን ተባለ?
ሁሉንም የሚያስማማው ቃሉ ጣሊያንኛ መሆኑ ነው፤ በትክክል ምን ማለት ነው የሚለውን ግን ሰዎች የተለያየ መልስ ቢሰጡበትም ግን የተጠጋጋ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ‹‹ካዛ›› የሚባል የጣሊያን አስተዳዳሪ ይኖርበት ስለነበር በዚያ የተሰየመ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ካዛንቺስ ማለት በጣሊያንኛ ቤቶች፣ መንደሮች እንደማለት ነው ይላሉ፡፡ ሁለቱም ትርጉም ተቀራራቢ ነው፡፡ በሰውየው ስም ከተሰየመ የካዛ ሰፈር፣ የካዛ ቤት፣ የካዛ መንደር እንደማለት ነው፡፡
መናኻሪያ
እዚሁ ካዛንቺስ አካባቢ መናኻሪያ የሚባል ሰፈር አለ፡፡ከቤተ መንግሥትና ገብርኤል ከሚባለው ሰፈር ትንሽ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡
መናኻሪያ ለምን ተባለ?
አጠገቡ መናኻሪያ የተባለ ሆቴል ነበር አሉ፤ በዚያ ሆቴል ምክንያት ነው ስያሜውን ያገኘው፡፡ አሁን ግን ሆቴሉ የለም፤ አጠገቡ ‹‹መናኻሪያ ፎቶ ቤት›› የሚባል ነው ያለው፡፡
ፈልጌ አስፈልጌ
ይሄ የሰፈር ስም አይደለም፤ ካዛንቺስ ውስጥ የሚገኝ ይልቁንም ባርና ሬስቶራንት ነው፡፡ ዳሩ ግን ከሰፈር ያላነሰ ታዋቂ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎች ለመገናኘት እንደምልክት የሚጠቀሙት ይህን ባርና ሬስቶራንት ነው፡፡
ይልቅ የሚገርመውን ነገር ልንገራችሁ፤ በዚህ ፈልጌ አስፈልጌ ባርና ሬስቶራንት ሥር ካለፋችሁ ‹‹ፈልጌ አስፈልጌ›› የሚለውን የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን በተደጋጋሚ ትሰሙታላችሁ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011