‹‹አሳዳጊ የበደለው›› ትል ነበር አያቴ ሕጻን ልጅ የሆነ ነውር ነገር ሲሰራ ካየች ፡፡ የምትሳደበውም ልጁን ሳይሆን አሳዳጊዎቹን ነው ፡፡ ምክንያቱም ልጁ ምንም አያውቅም ፡፡ ህጻናት የወላጆች የአስተዳደግ ውጤት ናቸው፡፡
‹‹አሳዳጊ የበደለው›› ማለቷ ደግሞ ወላጆቹ ልጁን በድለውታል ማለት ነው ፡፡ ባደገ ጊዜ ራሱን ችሎ ስለሚኖር በዚያ መጥፎ ነገሩ ይወቀስበታል፤ ይሰደብበታል ማለት ነው፤ ስለዚህ በትክክልም አሳዳጊዎቹ በድለውታል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ነው ፡፡ የተከራየሁበት ግቢ ውስጥ ልብስ እያጠብኩ ነበር ፡፡ በግንቦት ልደታ በዓል ምክንያት ይሁን ሌላ ተደራቢ ጉዳይ ኖሮ ባላውቅም፤ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ‹‹ግንቦት ልደታ›› ተብሎ በሚከበረው ግንቦት 1 ቀን የተከራየሁበት ግቢ ውስጥ እንግዶች መጥተዋል ፡፡ ሐሙስ የመጡ እስከ ቅዳሜም ነበሩ (ሌላ ጉዳይ ተጨምሮ ሳይሆን አይቀርም)፡፡
ቅዳሜ ጠዋት ልብስ እያጠብኩ ነው ፡፡ የአከራዬ ልጅ ግቢ ውስጥ ካየኝ ሁሌም ይመጣል፤ አብሮኝም ከቤት ይገባል ፡፡ እናም ልብስ ሳጥብ አየኝና አጠገቤ መጣ ፡፡ ዛሬ ግን ብቻውን አልነበረም፤ አንዲት የስድስት ዓመት (እሷው እንደነገረችኝ) ልጅ አብራው መጣች ፡፡ ማነው ስምሽ? ስንት ዓመትሽ ነው? እያልኩ ስጠይቅ አትረዳኝም ፡፡ አፏን በአማርኛ ሳይሆን በሌላ ቋንቋ የፈታች ሆኖ ነው ብዬ ትኩረትም አልሰጠሁትም ፡፡ በኋላ በእንግሊዝኛ ታዋራኝ ጀመር ፡፡ እኔም What is Your Name? How old are You? Your Mother, Father… እያልኩ ቀላል ቀላል እንግሊዝኛዎች ጠየቅኳት ፡፡ የምትመልስልኝ መልስ ግን ረጃጅም የእንግሊዝኛ ወሬ ነው ፡፡ በእንግሊዝኛ ማዋራት ስጀምር ያቺ ጸጥ ብላ የቆየች ልጅ አዥጎደጎደችው ፡፡ ዕቃዎችን ሁሉ እያነሳች በእንግሊዝኛ ታወራኛለች ፡፡
አሁንም ብዙም አልገረመኝም ነበር፤ ያንኑም የተገረምኩት በእንግሊዝኛ ችሎታዋ ብቻ ነበር ፡፡ ችሎታዋን እያደነቅኩ ልጆቹ እየተጫወቱ ከአጠገቤ ሄዱ፤ እኔም ጨርሼ ሄድኩ ፡፡
ማታ አካባቢ ወደቤት ስገባ ግቢ ውስጥ ተሰባስበው ያወራሉ (እናቶች) ፡፡ ከጎረቤት የመጡት ሰዎች በእንግድነት ከሌላ ቦታ ከመጡት ጋር ይተዋወቃሉ መሰለኝ አጥብቀው እየተጠያየቁ ነው ፡፡ በዚህ መሃል የልጅቷን እናት የተጠየቀች አንድ ጥያቄ ቀልቤን ሳበችው፡፡ ‹‹ልጆችሽ አማርኛ መናገር ቻሉ?›› ስትል አንደኛዋ ጠየቀች፡፡ ጠዋት የልጅቱን እንግሊዝኛ ሳደንቅ የነበርኩት ሰው ወዲያውኑ በማያገባኝ ነገር ብስጭት ወረረኝ ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል›› የሚባለውን አላምንም ነበር፤ ብዙ የአዲስ አበባ ወላጆች ልጆቻቸው ከእንግሊዝኛ ውጭ እንዳይናገሩ ያደርጋሉ ሲባል ነገሩን ለማጋነን የሚጠቀሙት እየመሰለኝ ሙሉውን አምኜ አልቀበለውም ነበር ፡፡
ወዲያውኑ ቀልቤን ወደ እነዚያ እናቶች አደረኩ ፡፡ እናትየዋም አሁን አሁን ትንሽ ትንሽ እየሞከሩ እንደሆነ ተናገረችና ይችኛዋ ልጅ ግን (እኔ ጋ የመጣችዋ ማለት ነው) አማርኛ እንደማትሞክር ኩራት በሚመስል ቅላጼ ተናገረች፡፡
ጠዋት ልጅቷን ምናልባት በኦሮምኛ ወይም በትግርኛ ወይም በሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ አፏን የፈታች ትሆናለች ብዬ ያሰብኩት ግምት አሁንም ትዝ አለኝ ፡፡ እነዚያ እናቶች ከሐሙስ ጀምሮ ከአማርኛ ውጭ ምንም አይነት ቋንቋ ሲናገሩ አልሰማሁም ፡ ፡ የአነጋገር ቅላጼያቸውም ሆነ ባህላቸው ሁሉ የአማርኛ ተናጋሪ እንደሆኑ ያስታውቃል ፡፡ የአማርኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን ሳውቅ ነገሩ የበለጠ አናደደኝ፤ ልናገራቸው አሰብኩና ግን ደግሞ ምን ያገባሃል ይሉኛል ብዬ ተውኩት፡፡
ልጆቻቸውን ከእንግሊዝኛ ውጭ ሌላ ቋንቋ እንዳይናገሩ የሚያደርጉ ወላጆች ለእኔ ምንም ማንበብና መጻፍ ከማይችል ሰው በምንም አይለዩም፤ እንዲያውም መጻፍና ማንበብ የማይችል የምሁር አስተሳሰብ ያለው ብዙ አለ ፡፡ የእንዲህ ዓይነት ወላጆች አስተሳሰብ ግን መሃይምነት ነው ፡፡ የበታችነት ነው ፡፡ እንግሊዝኛን የበላይ አድርጎ ማሰብ የበታችነት ስሜት ነው ፡፡
አምናለሁ እንግሊዝኛ መቻል በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንግሊዝኛ መቻል መብት ሳይሆን ግዴታ ነው ብንል ማገነን አይሆንም ፡፡ በተለይም በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የእንግሊዝኛ አስፈላጊነት አያከራክርም ፡፡ የእኔ ቅሬታ ለምን እንግሊዝኛ ቻሉ? አይደለም፤ ለምን ሌላውን ቋንቋ እንዳይችሉ ተደረገ የሚል እንጂ ፡፡
ብናምንም ባናምንም አንድ ነገር እውነት ነው ፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፤ ቋንቋ መግባቢያ ነው፤ መግባቢያ ደግሞ በቃ መግባቢያ ነው ፡፡ ሌላ ትርጓሜ የለውም፡፡
‹‹አንድ የትምህርት ዓይነት ከሌላው የትምህርት ዓይነት አይበልጥም›› የሚለውን ለጊዜው እንተወው (ለዚህ ጽሑፍ እንተወው) ፡፡ የትኛዋም አገር በቋንቋ አይደለም የበለጸገች፤ በሳይንስ ነው ፡፡ አገራት የሥልጣኔ ደረጃ የወጣላቸው በቋንቋ አይደለም፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ነው ፡፡ እነዚህ የምናመልካቸው አገሮች የበለጸጉት በሳይንስ ምርምር መሆኑን አለማወቃችን ነው እንግሊዝኛን እንድናመልክ ያደረገን ፡፡ ይቺ ብድር የምትሰርዝልን አገረ ቻይና እንግሊዝኛ ስለማይችሉ በአስተርጓሚ የሚያወሩ ዜጎች አሏት ፡፡ ሀብታም ለጉብኝት፣ ድሃ ለስደት የሚመኛት የበለጸገችዋ ሳውዲ መሪዎቿ ሳይቀር እንግሊዝኛ ጭንቃቸው አይደለም ፡፡
በነገራችን ላይ የግል ትምህርት ቤት ትልቁ ብቃት እንግሊዝኛ መናገር ነው ፡፡ ይሄን ነገር መስማት ከጀመርን ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ግን እስካሁን አንድም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝት አልሰማንም ፡፡ ከመንግሥት ትምህርት ቤት አለ ማለቴ አይደለም፤ ዳሩ ግን የብቃት ጣሪያ ተደርገው የሚታዩት የግል ትምህርት ቤቶች ስለሆኑ ነው ፡፡ ‹‹አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል›› እንደማለታቸው ቢሆን ኖሮ እኮ እስከዛሬ ከጨረቃ ላይ ኤሌክትሪክ የሚጠልፉ ሳይንቲስቶች እናፈራ ነበር ፡፡ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሳይንስ ትምህርት እንጂ በቋንቋ አይደለም ፡፡
ያቺ ከእንግሊዝኛ ውጭ የአገር ውስጥ ቋንቋ እንዳትናገር የተደረገች ልጅ እኮ ይህኔ አራቱን የሒሳብ ስሌቶች አታውቅ ይሆናል ፡፡ ሌላ ቋንቋ እንዳይናገር የከለከሉ እናትና አባት ልጁ ኬሚስትሪና ፊዚክስ በሄደበት የማይሄድ ይሆናል፤ ይሄ ነው ጠቅላላ ውድቀት!
እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸውን ዕጣ ፋንታ እያበላሹ ነው፤ ለእንግሊዝኛ የሰጡትን ትኩረት ለሳይንስ ቢሰጡ ልጆቹ እንኳን ለራሳቸው ለአገርም የሚጠቅሙ ይሆኑ ነበር ፡፡ የእነዚህ ልጆች የእንግሊዝኛ ብቃት የትም አያደርስም፤ እንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፤ የኬንያ ገበሬ አቀላጥፎ የሚናገረው ነው ፡፡
ልጆቹም ልጅ ናቸውና ወላጆች በዚህ ብቻ ካደነቋቸው ትኩረታቸው ሁሉ እንግሊዝኛ ላይ ብቻ ይሆናል ፡፡ ይሄ ማለት የሳይንስ ተመራማሪ ይሆን የነበረ ልጅ ተገለለ ማለት ነው ፡፡ የአገሩን ነባራዊ ሁኔታ እንዳያውቅ ተደረገ ማለት ነው ፡፡ በአገሩ ቋንቋ የተጻፉ ነገሮችን አያነብም ማለት ነው ፡፡ አካባቢያዊ ነገሮችን አያውቅም ማለት ነው ፡፡ አንድ ሕጻን ማወቅ የሚጀምረው ከአካባቢው ነበር ፡፡
እንዲህ ሆኖ ነው እንግዲህ አገር ተረካቢ የሚገኘው? አገሩን እንዳያውቅ ተደርጎ ያደገ ልጅ ምን አይነት አገር ተረካቢ ይሆንልን ይሆን? ኧረ ከጠቅላላ ውድቀት እንውጣ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ዋለልኝ አየለ