የተወለዱትና ያደጉት በቀድሞ አጠራር ወለጋ ክፍለ አገር በነቀምት አውራጃ ጉደያ ቢላ በሚባል አካባቢ ነው ። 1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት እዛው አካባቢ በሚገኝ ሲቡሲሬ በሚባል ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በነቀምት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከዚያም የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ 18ኛ ካዲት ኮርስ ገብተው በፖሊስ ሳይንስ ተመርቀዋል። ከፖሊስ ኮሌጁ እንደወጡም በትግራይ፣ በጎጃም፣ በሃረርጌ፣ በኡጋዴንና በሌሎችም ክፍለ አገሮች ላይ እየተዘዋወሩ ለአሥር ዓመታት በፖሊስ ኦፊሰርነት አገልግለዋል። በመቀጠልም ወቅቱ አገሪቱ የምትመራው በሶሻሊዝም መንግሥት በመሆኑም ሶቭየት ህብረት ተልከው ወታደራዊና ፖለቲካል ስልጠና እንዲወስዱ ተደርገዋል። ከስልጠናውም መልስ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በፖሊስ መርማሪነት፣ በህዝብ ግንኙነት፣ የፓርቲ ጸሐፊነት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊነት፣ በመምሪያ በኃላፊነትና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተመድበው አገልግለዋል።
ኢህአዴግ በ1983ዓ.ም አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን የፓርቲውንም ሆነ በሰለጠኑበት የፖሊስ ሳይንስ ዘርፍ ሥራ መስራት የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ክፍል አቀኑ ።እዛም ከ20 ዓመት አገልግሎት በኋላ በመደበኛው የትምህርት መርሐግብር ገብተው በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል ። ከዚያ እንደወጡም በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን የህግ ክፍል ውስጥ አማካሪ ሆነው ለአራት ዓመት ሰሩ ። እንደገና አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙና በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕላን የሪሰርችና የጥናት መምሪያ ኃላፊ በመሆን ለአንድ ዓመት አገለገሉ። ኒው ጀኔሬሽን፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ በአምቦ፣ በአዳማና ሱማሌ ላንድ የሚገኘው ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ካስተማሩባቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ናቸው። ከእኚህ የፖለቲካ ምሁር ጋር አዲስ ዘመን ቅዳሜ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ካለዎት የሥራ ልምድና ትምህርት አኳያ አሁን ያለው የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል? በተለይ ከሰላምና ህግ ማስከበር አኳያ?
ረ/ ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- በዚህ የለውጥ ጉዳይ ላይ መነሻ ማድረግ የሚገባን የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊመጡ ግድ የሆነበት ሁኔታ ነው ። እውነት ነው ለውጥ አለ፤ በዚህ ላይ አንካካድም። መዋቅራዊ ለውጥም ተጀምሯል ። ግን ደግሞ ይሄ ለውጥ እንዴት ነው የመጣው የሚለው ጉዳይ አሁን ላሉት ተግዳሮቶች ምክንያት ነው ብዬ ነው የማምነው። እንደ አጠቃላይ ግን የሚታይ ለውጥ አለ፤ ግን ለውጡ የመጣው በከፊል ግብታዊ በመሆን ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ ።
አዲስ ዘመን፡- ግብታዊ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ረ/ ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- ግብታዊ ስል ማህበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ማሟላት ይገባል። ከዚህ አንፃር የህዝቡ ሚና ትልቅ እንደነበር እሙን ነው ። ህዝቡ የኢህአዴግ አገዛዝ ባለበት ሁኔታ፣ በተለመደው መልኩ እንዲቀጥል ፈቃደኛ አልነበረም። ይህንንም ጉዳይ በንቃት ነበር ሲከታተል የነበረው ። ይህም ህሊናዊ ሁኔታዎች መሟላቱን የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት አድጓል ።ዴሞክራሲን ለድርድር በማይቀርብ ሁኔታ ፈልጓል። ነባራዊ ሁኔታ ሲባልም በአንድ አገርን ሲመራ መንግሥታዊ ሥርዓት ከለመደው ውጪ ሌላ ለውጥ ለማምጣት አለመፈለግ ነው። እዚህ ላይ ነው ለውጡ የተሟላ ነው ለማለት የሚከብደን።
ለውጡ መጥቷል በምንበት ወቅት ኢህአዴግ ራሱ በሁለት ተከፍሎ ነው የሚገኘው። በአንድ ወገን ለውጡ በተጨባጭ እንዲመጣ የሚፈልግ ቡድን በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ለውጥ ሳይመጣ ሥርዓቱን ማስቀጠል የሚፈልግ ቡድን አለ ። በሁለቱ መካከል ልዩነት ተፈጠረና ይሄ ነባራዊ ሁኔታ ስላልተሟላ ማህበራዊ አብዮት ሊመጣ አልቻለም ። ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች በሙሉ በነበረው ስርዓት ነው መቀጠል ያለብኝ ቢል ኖሮ ወደ ማህበራዊ አብዬት እንዲሁም ትርምስና ነውጥ ነበር የምንገባው ። በሌሎች አገራት እንደሚታየው ሁሉ ማለት ነው።
ይሄ የለውጥ ኃይል ተብሎ የሚጠራው በድርጅቱ ውስጥ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት ፈቃደኛ ሆኖ ስለተነሳ ማህበራዊ አብዮት ሊመጣ አልቻለም። ግልፅ ነው። አሁን ይሄ ማህበራዊ ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ ጥገናዊ ለውጡ መዋቅሩን እንዳለ ይዞ ነው ጥገና እያደረገ ያለው። መዋቅሩን ይዞ አባላቱን ይዞ ነው ወደ ጥገና መሄድ የፈለገው። እንዲህ ሲሆን አንድም ወደ ጦርነትና ብጥብጥ እንዳንሄድ አድርጎናል። ወደ መተላለቅ አልሄድንም ። ወደ አገር መፈራረስ አልሄድንም። ይህ አንድ በጎ ጎኑ
ነው። ጉዳትም ደግሞ አለው። ጉዳቱ የነበረውን ያረጀ ያፈጀ መዋቅር ይዞ መሄዱ ነው። ይህ ደግሞ ጉዞውን አዝጋሚ ነው የሚያደርገው። የሚታሰበውንም ያህል እምርታ አያመጣም። ስለዚህ በዝውውር፤በሹመት ወዲያ ወዲህ ልናቀያይረው እንችላለን እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ስርነቀል የሆነ ለውጥ አልመጣም እያሉኝ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- ይህ እኮ ግልፅ ነው፤ እምርታዊ ለውጥ አልመጣም። በእኔ እምነት በዚህ ምክንያት አንዳንድ ተግዳሮቶች ይፈጠራሉ። አንደኛ የለውጡ አራማጅ የሚፈልገውን ፍጥነት፣ አስተሳሰብ፣ የሚፈልገውን ድጋፍ፣ ሩጫ የነበረው ያረጀ ያፈጀ መዋቅር አብሮት ሊራመድ ይቸግራል። ይሄ በራሱ ተግዳሮት ነው። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ቅራኔዎች ይኖራሉ። በለውጥ ፍላጎትና ለውጡን ለማራመድ ፅኑ ፍላጎት ባላቸውና ባረጀው መዋቅር መካከል ፍጭት አለ። ባረጀውና በአዲሱ ኃይል መጓተት መኖሩ ደግሞ ለውጡ ላይ ተግዳሮት መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ሌላው ተግዳሮት ነው ብዬ የማስበው ኋላቀር የሆኑና አስተሳሰብ ያለቀባቸው ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ መኖራቸው ነው። ምክንያቱም ሁልጊዜ የፖለቲካ ሥራ አሰልቺ ነው። እነዚህ ሰዎች የሰለቹ ናቸው። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡም የሰለቻቸው ናቸው። አንድ መልክ፣ አንድ ገፅታና አንድ አንደበት ያላቸውን ሰዎች በራሱ ተሸክሞ ለውጥ ማካሄድ ከባድ ነው። ስለዚህ ይሄ አንዱ ተግዳሮት ነው ብዬ አምናለሁ። ራሱ ኢህአዴግ በቅራኔ ውስጥ ነው ያለው፤ ለውጥ ማምጣት ይፈልጋል ሌላው ጉዳይ ነው። ስለዚህ በዚህ ውስጥ ሁልጊዜ ተቃርኖዎች መኖራቸው የግድ ነው። ስለዚህ እነዚህ ከዚህ የመነጩ ናቸው።
ሌላው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጥምረት እና አንፃራዊው ውህደት በራሱ አንዱ ተግዳሮት ነው። ኢህአዴግ ስንጥቃት ላይ ያለ ድርጅት ነው። የተሟላና የበቃ ድርጅት ነው ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህ በአንድ በኩል ድርጅቱ የስንጥቃት አደጋ ላይ ሆኖ ስንጥቃቱን እያከመ ለመቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ አገርና ለውጥ ነው የሚመራው። ይህም ተቃርኖ ትልቁ ፈተና ነው። ከባድ ነው። እንዳውም ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለዚያ ነው የሚል እምነት አለኝ። በመሆኑም በመጀመሪያ ስንጥቃቱን ማዳኑ ላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስንጥቃቱን እያከመ መኖር አይችልም እያሉኝ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- ይችላል። ግን ከባድ ነው። እንዳውም ቅድሚያ መስጠት ያለበት ማከሙ ላይ ነው። ምክንያቱም አንድ ውስጠ ደንብ ያለው የፖለቲካ ግንባር ውስጣዊ አንድነትና ውህደት የመስመርና የፖሊሲ አንድነት ሳይፈጥር አገር መምራት ከባድ ነው። ስለዚህ የውስጥ ችግሩን ማስወገድ ነው በመጀመሪያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው። ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ አለን ቢሉም፤ ለውጥ እያካሄዱ ያሉትም ይህንን ስያሜ ባይቀይሩም ግን በመካከላቸው ስንጥቃት ስለመኖሩ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለዚህ ይሄ ስንጥቃት ወይም መዳን አለበት ወይም ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊኖር ይገባል። በዚህ መልክ ግን መቀጠል ለአገሪቱም ለድርጅቱም አደጋ ነው የሚታየኝ ።ድርጅቱ ነው አገር እየመራ ያለው። ይሄ ድርጅት የውስጠ ፓርቲ ችግሩን ባልፈታበት ሁኔታ ይህችን አገር፣ የተለያዩ ፓርቲዎችን አቅፋ፣ አመራሩን ዴሞክራሲያዊ አድርጎ፣ የአገሪቱን አንድነት ህልውና አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ መቀጠል ያስቸግረዋል ባይ ነኝ። ስለዚህ በመጀመሪያ ስንጥቃቱ መዳን አለበት። እንደ ሰለጠነ የፖለቲካ ድርጅት ልዩነቶችን ወደ መድረክ አምጥተው በመወያየት መፍታት አለባቸው። ስለዚህ ይሄ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም፤ የአገር ጉዳይ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው። ህወሓትም ቢሆን ከጀርባው ይብዛም ይነስም ህዝብ አለ። ህዝቡም ደግሞ ለውጥ ይፈልጋል። ከሌላው ህዝብ የተለየ አይደለም። ስለዚህ የለውጡ ተቋዳሽ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ችግሮቹን ከሌሎቹ ጋር ቁጭ ብሎ መፍታት ይገባዋል የሚል ጠንካራ አቋም ነው ያለኝ ።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ሰሞኑን በተከታታይ ስብሰባ አድርጓል፤ በወቅቱ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በመፍታት አገራዊ አንድነት የሚያመጣ መፍትሄ ይዘው አለመምጣታቸው በራሱ ሌላ ፖለቲካዊ ቀውስ አያስከትልም ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- አለ እንጂ፤ የሚፈለገው እውነተኛ የሆነ ዴሞክራሲ ነው። የግለሰቦች ፍላጎትም ሆነ ድርጅታዊ ኡደት ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት። ብዙውን ጊዜ በየትኛውም የአፍሪካ አገር እንደሚታየው ፓርቲዎች በጥቂት ግለሰቦች ማነቆ ውስጥ ይገባሉ። የተወሰኑ ሰዎች ለዴሞክራሲ የተቋቋመን ፓርቲ አምባገነን ያደርጉታል። ስለዚህ ይሄ አዝማሚያ መቀየር አለበት ብዬ ነው የማምነው። ዞሮ ዞሮ የህዝብ ውክልና ያለው ድርጅት ነው ወደ ስልጣን የሚመጣው። ይሄ የዴሞክራሲ መርሆ ነው። የዓለምም ሆነ የአገራችን ህዝብ የተሰዋለት ጉዳይ ነው። ይሄ መርሆ ደግሞ በምንም ምክንያት ለድርድር የሚቀርብ ሊሆን አይገባም። በትግራይም ውስጥ ይሁን በሌላም የኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ውክልና ያለው፤ የህዝብ እምነት ያለው፤ የህዝብ ፍላጎት የሚገለፅበት የፖለቲካ ድርጅት ነው ወደ መድረክ መምጣት ያለበት። ይሄ በማፈንም፤ በመደፍጠጥም የሚደረጉ ሙከራዎች የትም የሚደርሱ አይደሉም። ደግሞም ዞሮ ዞሮ ህዝብን ነው የሚጎዳው፤ ዴሞክራሲን ነው የሚያፍነው፣ እድገትን ነው የሚያቀጭጨው።
በመሆኑም በትግራይ ውስጥም ያለው ህውሓትም ይሁን ህዝቡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጅ፤ አብሮ ለመኖር ተቻችሎ ለማደግ የሚያስችለውን መስመር ነው መምረጥ ያለበት። ከዚያ ውጭ የፖለቲካ ገመድ ጉትቻው ማንንም አይጠቅምም። ምክንያቱም በዚህ መልክ ያደገና የዘለቀ አገር የለም። መጨረሻቸው ውድቀት ነው። ይህ ካልሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። ህዝብን ለእልቂት ያስከትላል። ኢኮኖሚውና ማህበራዊ
እሴትን መናድ ነው። የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱን የሚለውም ጭምር ለዴሞክራሲ መስራት አለባቸው። እውነተኛ የህዝብ ፍቅርንና የኢትዮጵያን አንድነት ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሥራ ነው መስራት ያለባቸው።
እኔ እንደማየው ይህንን መጓተት እያመጡ ያሉት በአፍሪካ ውስጥ የፖለቲካ ስልጣን አያያዝና አለቃቀቅ ችግር ነው። በፖለቲካ ስልጣን ላይ ሲቆዩ እነዚህ ሰዎች በስልጣን ይባልጋሉ ።ሙስና ውስጥ ይገባሉ። ዝርፊያ ውስጥ ይገባሉ፤ የነፍስ ግድያ ውስጥ ይገባሉ፣ ወንጀል ውስጥ ይገባሉ ። ወንበርን የመጨረሻ ግብ አድርገው ስለሚያዩት ነው። ነገር ግን ወንበር የመጨረሻ ግብ ሆኖ አያውቅም። ለውጥ ይዘገያል እንጂ መምጣቱ አይቀርም። ስለዚህ በዚህ መልክ የሚቆዩ ኃላፊዎች በቀጣዩ የመኖር ዋስትና ያጣሉ። ለዚህ ነው ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ወንበር ላይ የሚሞቱት። ስለዚህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዚች አገር መለመድ ያለበት ነው ። አንዱ ስልጣን ይይዛል፤ በደል ይፈፅማል፤ በተራው መቀመቅ ይወርዳል፤ ይታሰራል፤ ይገደላል፤ ሌላውም በተመሳሳይ መንገድ ይመጣል። የተለመደ ነገር ነው። ይህንን ሰብረን መውጣት የምንችልበት ሁኔታ ነው መቅረፅ ያለብን። እንዴት ነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚደረገው? እንዴት ነው ዴሞክራሲያዊ የምንሆነው? ዋስትና እየተሰማው ከስልጣኑ ወርዶ በነፃነት አገር ውስጥ መኖር የሚችለው? እሱን መፍጠር መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ሽግግሩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው የተካሄደው፤ ይህ ከተለመደው ሁኔታ ተወጥቷል ለማለት አይቻለም?
ረ/ ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- በሰላምም ቢሆን ሽግግሩ ጥገናዊ ነው። ስርነቀል አይደለም። እኔ እንደሚገባኝ ይህንን ቢያውቁት ኖሮ ለእነሱ እድል ነው። ጥገናዊ ለውጡ አብዮትን ነው ያስቀረው እኮ። አመፅን ነው ያስቀረው። ስለዚህ ፓርቲውን የማዳን፣ ራሱን እንዲፈትሽና እንዲጠናከር ብሎም
እንዲቀጥል የሚችልበት አንድ አጋጣሚ ነው። ግን በዚህ መልክ እንዲቀጥል አይደለም ፍላጎቱ። ህዝቡ የፈለገውና መስዋዕት ሲከፍልበት የቆየበት ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ ነበር የፈለገው። ግን ያ አልሆነም። ሌላው ይቅርና በመካከላቸው እንኳ መተማመን የለም።
አዲስ ዘመን፡- በስልጣን የባለጉ የቀድሞ አመራሮችን ለህግ አሳልፎ ለመስጠት ያለመፈለግ ጉዳይ በምን መልኩ ነው መቋጫ ሊያገኝ ይችላል ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እኛ ባንልም ይሄ ጉዳይ የህዝብ ጥያቄ ነው። ወደ ዓለም አቀፍ ወንጀል ውስጥም የሚያስጠይቅ ነው። በዓለም አቀፍ ህጎችና ቻርተሮች ስምምነቶች ስር ያለ ድንጋጌ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም የተቀበለውና ብዙ አገሮች ፈርመው የሚመሩበት አሰራር ነው። ጉዳዩ የህግ የበላይነት የማስከበር ጉዳይ ብቻ አይደለም። አሁን ብዙ ሰው የሚያተኩረው እዚህ ላይ ነው። ለምሳሌ በግልፅ የመዳኘት መብት ፣ ክስን አውቆ በባለሙያ የመከራከር መብት፣ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውሳኔ የማግኘት መብት፣ በተወሰነበት ውሳኔ ላይ ይግባኝ የማለት መብት እነዚህ ነገሮች መሰረታዊና አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ይሄ ከሌለ መንግሥት አለ ለማለት አይቻልም።
ሌላው የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው። ወፍራም ቀጭን፤ ጥቁር ነጭ፤ ረጅም አጭር ሳይል ማንም ዜጋ በህግ ፊት እኩል ነው። እከሌ ወይም እከሊት ስለሆነች የሚለወጥ ነገር አይኖርም። የዚህ ክልል ሰው በመሆናችን ህግ የሚለወጥበት ሁኔታ አይኖርም። ለእኔ የዚህ ክልል ሰው ስለሆነ ተብሎ በህግ እንዳይጠየቅ የሚደረግ ከለላ በጣም ኋላቀርነት ነው።
ይህ ሁኔታ ህግ አልባ ወደሆነ ስርዓት ውስጥ ነው የሚከተን። ከዚህ በኋላ የሚመጡት አመራሮች ምንድን ነው ሊማሩ የሚችሉት? እንዴት ነው መልካም አስተዳደርን ሊያመጡ የሚችሉት? ስልጣን እስከ ዘላለም እኔ ብቻ ልያዝ
የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም። ህግና ስርዓት ሊከበር ይገባል። የትም የሚያደርሰን ጉዳይ አይደለም። ይሄ ግለሰብ የኔ ክልል ሰው ስለሆነ መጠየቅ የለበትም የሚለው ነገር ከብሄር ውጭ ለህግ የሚቀርብና በህግ የሚዳኝ ሰው የለም ማለት ነው። ይሄ ተገቢም አይደለም። በጣም ኋላቀርነት ነው። በሌላ በኩል በእነዚህ ሰዎች የተበደለው ሰው ቁስል በደል ግፍ እንዴት ነው ሊረሳ የሚችለው? ህግ ጣልቃ ገብቶ እልባት ካልሰጠና ፍትህ ካልታየ እንዴት ነው ያንን የጥላቻ ሰንሰለት መበጣጠስ የምንችለው? ይህም ሌላው በግድ አስፈላጊ የሚያደርገው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች የዶክተር አብይ መንግሥት በተለይም ከዚህ ቀደም ስልጣን ላይ የነበሩትን ሰዎች በአፋጣኝ ለህግ አለማቅረቡ በድክመት እየተቹት ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር የመንግሥት ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እውነት ነው፤ ሁልጊዜ በግጭት ማኔጅመንት ላይ ከሚታዩ ንድፈ ሃሳባዊ ትምህርቶች አንዱ ይሄ ነው። የግጭት መንስኤዎች ተብለው ከሚታዩት መዋቅራዊ መንስኤዎች መካከል ይሄ አንዱ ሲሆን አግላይ የፖለቲካ መዋቅር ነው የሚባለው። ይህ ሲሆንም ጨቋኝ የፖለቲካ መዋቅር፣ በጠላትነት ላይ የተቃኘ ውስጣዊ ግንኙነት ነው የሚኖረው። እነዚህ ደግሞ ሁልጊዜ የራሳቸውን ግጭት እያመጡ ይችላሉ። አሁን ደግሞ በፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ የምናየው ህጋዊ ውክልና የጎደለው መዋቅር አንዱ ምክንያት ነው። ይህም አንድ መንግሥትን ደካማ ሊያሰኘው የሚችለው ዋነኛው ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁልጊዜም ከጀርባ የፖለቲካ ምሁራን ስላሉ የራሳቸውን ቡድን መስርተው ግጭቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ልናየው የሚገባው ህጋዊ ውክልና የጎደለው መዋቅር አንዱ ምክንያት ነው። ቀጥሎ ያለው ደካማ መንግሥት ነው። ደካማ መዋቅር የሚፈጥረው ተፅዕኖ አንደኛ የውስጥ ተቃዋሚና ተፎካካሪ ድርጅቶች ያንን በመሙላት ለስልጣን እንዲቋምጡ ያደርጋል። ያነሳሳቸዋል። በአጠቃላይ በራሱ በስልጣን ላይ መተራመስን የሚጋብዝ ይሆናል። ሁለተኛው በጎረቤት ያሉ የዚህችን አገር ብሄራዊ ጥቅም የሚፈልጉ አገራት እጃቸውን እንዲሰነዝሩ ይጋብዛል፣ አና አርኪዝም ይፈጠራል።
ስለዚህ በመርህም ደረጃ ደካማ መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖረው ነውጥና አለመረጋጋት ትልቅ ዕድል ይከፍታል። ስለዚህ መንግሥት እንደ አንድ ሉዓላዊ ኃይል ጠንካራ መሆን አለበት። ጠንካራ መሆን አለበት ስንል ግን ከህግና ከስርዓት ውጪ ራሱ እንደፈለገው መጋለብ አለበት ማለት አይደለም። ሦስቱ የመንግሥት አካላት በየራሳቸው ኃላፊነትና ተግባር መስራት አለባቸው። ተነጣጥለው ማለት ነው። ይህ የተነጠጣለ ኃላፊነት ደግሞ መልሱ አንዱ አንዱን መቆጣጠር መቻል አለበት። በተለይም ህግ አስፈፃሚው አካል ከተሰመረለት ቀይ መስመር አልፎ በህግ አውጪውም ሆነ በህግ ተርጓሚው ሜዳ ውስጥ መጋለብ የለበትም። ይሄ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን መንግሥት እንደ መንግሥት ጠንካራ መሆን አለበት። ህግ ማስከበር አለበት። አንድ የሚቸገሩበት ጉዳይ አፈጣጠራቸው ነው። ለውጡ የመጣበት መንገድ በራሱ እንደ ፈለገው እንዳይሰራ፣ ወደ ኃይል እንዳይሄድ ተግዳሮት ነው። ምክንያቱም ፓርቲው ራሱን ችሎ አንድ ሆኖ አገርን በጋራ ወደ መምራት እየሄደ ባለ መሆኑ ማለት ነው።
ሌላው ጽንፍ ወጥተው መሳሪያ ተማዘው ሲዋጉ የነበሩ ድርጅቶች ተጋብዘው በአገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል ። ስለዚህ መንግሥት ወደ ኃይል ልግባ ቢል በዚህ የሽግግር ወቅት ምንድን ነው የሚያስከትለው? ይህች አገር ወደ ምን ቀውስ ነው የምትገባው? የሚለውን በእርጋታ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ህግና ስርዓትን ማስከበር ሰው መግደል ማለት ብቻ አይደለም። አብዛኛው ሰው አሁን ወደ እዛ ነው
ትርጉሙን እየወሰደው ያለው። የሚሰጠውም ምክረ ሃሳብ ከዚያ ጋር የተያያዘ ነው። የበለጠ ወደ ችግር ነው አገራችንን እየከተተ ያለው። ስለዚህ ተረጋግቶ በጋራ ቁጭ ብሎ በማህበራዊ የውይይት መድረክ ስር ችግርን መፍታት ይገባል። እነዚህ ተቃዋሚና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና መንግሥት ቁጭ ብለው የአገሪቱን ፍኖተ ካርታ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል። ይሄ በአንድ ቀን በሁለት ቀን ስብሰባ ለመድረክ ግብዓት ተብሎ አይደለም መዘጋጀት ያለበት። ወርም ሁለት ወር ይፍጅ በመድረክ ላይ ቢያስፈልግ ዝግ ስብሰባ አድርገው ተፋጭተው የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ማስቀመጥ መቻል አለባቸው። ይሄ እስካሁን የተደረገ አይመስለኝም። አሁንም የተናጠላዊነት ስሜት በእያንዳንዳቸው ውስጥ አለ። ይሄ ደግሞ ወደ ህዝቡ ይወርዳል። እንዲህ አይነት ስሜት ወደ ህዝብ ይወርዳል። ስለዚህ የፈለገውን ያህል ጊዜ ይፍጅ በእኔ እምነት ቁጭ ብለው በር ዘግተው አገርን ማዳን አለባቸው። ዞሮ ዞሮ ይህች አገር ከሌሎች የትኛውም ፓርቲ ሊኖር ስለማይችል ማለት ነው። ስለዚህ ይህችን አገር እንደ አገር ማስቀጠል በሚችሉበት መግባባትና መቻቻል በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ጊዜ ፈጅተው መፍትሄ መፍጠር መቻል አለባቸው። በተናጠል ሊሆን አይገባም። በተናጠልማ ድሮም ያደርጋሉ። እሱን አይደለም አሁን አገሪቱ የምትፈልገው፤ ልዩነቶቻቸውን አስታርቀው ለአገር ሰላምና መረጋጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይሄ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው ነገር አይደለም የሚል የራሴ ምልከታ አለኝ ።
አዲስ ዘመን፡- በአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ላይ ክልሎች እርስ በርስ መተማመን ያለመቻላቸው ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መፍትሄ ይኖር ይሆን?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- አስቀድሜ እንዳ ልኩት ለዚህም ጉዳይ መፍትሄ ለማበጀት መሰባሰብ ይፈልጋል። ፓርቲዎች ተሰባስበው ወደ መፍትሄ መምጣት አለባቸው። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ፖለቲካ የሚመራው በፖለቲካ ሊሂቃን በመሆኑ ነው። ፖለቲከኛው የተደራጀ እስከሆነ ድረስ ተሰባስቦ መስራት አለበት ። ህዝብ ሲኖር ነው ፓርቲው የሚኖረው ። ደግሞም ግዴታቸውም ነው። ህዝቡ በራሱ ምንም የፈጠረው ችግርም የለም፤ የሚያመጣውም መፍትሄ የለም። ብዙውን ጊዜ የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነት ልዩነቶች በሰለጠነ መንገድ፤ በህብረት፣ በማቻቻል፣ በአገር ግንባታ ተቃኝቶ ነው የሚፈታው።
ለዚህ ደግሞ የህዝቡን የአዕምሮ አንድነት ማምጣት ይፈልጋል። የወንድማማችነት ስሜቱን ማምጣት ይጠበቃል። ቤተሰባዊ አገራዊነቱን ማምጣት ይፈልጋል። አገር በአንድ ወቅት ሊመሰረት ይችላል። በጦርነት ሊመሰረት ይችላል። የተመሰረተው አገር ግን እንደ አገር ሲቀጥል እዛ ውስጥ ያለው ልዩነት ወደ ቤተሰባዊነት እንዲመጣ ማድረግ፣ ፍቅር ማምጣት ይጠበቃል። ይህንን ካላመጣን ወደ ፊትም ችግሩ እንዲቀጥል እናደርገዋለን። እንደአጠቃላይ አገር ግንባታ ላይ በስፋት አልተሰራም። ብዙ ሰው እንደሚናገርው የፌዴራል ስርዓቱ ነው ይህንን ችግር ያመጣው ይላሉ።
እንዳውም ትዝ የሚለኝ ኢህአዴግ እንደገባ ወደ 40 የሚደርሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ተሰባስበው ቻርተሩን አርቅቀው የተፈራረሙት። እነዚህ 40 ድርጅቶች በመሳሪያ ሲዋጉ የነበሩ ናቸው። ሁሉም የራሱን ማንነት ይዞ ነበር ሲዋጋና ነፃ አውጪ ግንባር የነበረው። ስለዚህ ይህንን ማስታመም የሚቻለው የፌዴራል ስርዓት ስንከተል ነው። በዚያ ጊዜ ሌላ መንገድስ ነበረው ወይ? እያንዳንዱን 40 ድርጅት ታጣቂ ይዞ 40 ኢትዮጵያን ሊፈጥር በሚታገልበት ጊዜ ሌላ መንገድ ነበረ ለማለት ያስቸግረኛል። በዚያ ላይ የሁሉም ተሳትፎ ነበረበት። ወደ እዚያ ውስጥ የተገባው በግድ ነው፤ ነገር ግን እንደ አገር ግንባታ ላይ በወጉ አልተሰራም። ከዚያ ይልቅ ሁሉም የራሱን ማንነት ላይ አጠንክሮ ሰርቷል። ያ ደግሞ አንድነቱን እንዲያጣና ልል እንዲሆን አድርጎታል። ስለዚህ አሁን አድነታችንን የሚያጠናክር ሥራ ነው መስራት ያለብን።
አዲስ ዘመን፡- በማንነት ላይ ያጠነጠነ ስርዓት ሳይነሳ የአገር አንድነት ሊመጣ አይችልም የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በሌላ በኩል በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝም ከቀረ አሃዳዊ ስርዓት ይመጣብናል ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ። እነዚህን ጉዳዮች በምን መልኩ ማስታረቅ ይቻላል?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እኔ በዓለም ላይ ሊታረቁ ያልቻሉ ሁለት ንድፈ ሃሳቦች እንደሆኑ ነው የማምነው። የማንነት ፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ማንነት አለ ለዚህም መገለጫዎች ቋንቋ፣ ባህል፣ የደም ትስስር፣ የቤተሰብ ትስስር በዚህ መልክ ያለ ነው። ስለዚህ የለም ብንል፣ዝም ብሎ አየር ላይ ያለ ነገር ነው ብንል አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ይህንን እውቅና ሰጥተን ነው መሄድ አለብን የሚል አቋም ነው ያላቸው። ምንድን ነው ሰው ሲፈጠር ቋንቋ የለውም፤ አዎ የለውም፤ ግን በተፈጠረበት ቦታ አይደለም ያለው። አሁን ያለው እውነታ ነው ማየት ያለብን የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ይህም ሲባል በኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞ አለ? የለም? በጣም ግልፅ ነው። አለ። አማራ አለ። ጉራጌም አለ። ሌሎች ከ80 የሚበልጡ ብሄር ብሄረሰቦች አሉ። እነዚህ የተጨበጡ ነገሮች ናቸው። ማንነት ይቀየራል የሚል እምነት ቢኖራቸውም ይህ የሚሆንበት አጋጣሚ በጣም ውስን ነው።
እኔ አሁን ከዚህ ተነስቼ ኤርትራ ሄጄ ብኖር ከኤርትራ ህዝብ ጋር ተዋህጄ ልኖር እችላለሁ። ግን ማንነቴን እስከመርሳት ሊያደርሰኝ አይችልም። ይህ የግለሰብ ጉዳይ ነው። አሁን ጥያቄው ሊሆን የሚገባው እንደ ቡድን አለ/ የለም የሚለው ጉዳይ ነው። ቡድኑስ ይፈልገዋል ወይ? ስለዚህ ይህንን አይነት አስተሳሰብ የሚከተሉት ወገኖች አለ ብለን እውቅና ሰጥተን እንነሳ የሚል አቋም ነው ያላቸው። በተቃራኒው በኩል ደግሞ ማንነት የለም። በተደጋጋሚ የሚቀያየር ነው፤ ሰው ከማንነት ጋር አልተወለደም። ሰው ሰው ነው። በሰውነቱ ብቻ ነው እኛ ማክበር ያለብን ብለው ነው የሚያምኑት። መብቱን ካከበርን የቡድን መብት እዛ ውስጥ አብሮ ይከበራል ብለው ነው የሚያምኑት። ስለዚህ ለቡድን እውቅና መስጠት ለግለሰብ መብት ፀር ነው የሚሆነው የሚል እሳቤም አላቸው። እነዚህ ሁለቱም አስተሳሰቦች የየራሳቸው መሰረታዊ መርሆዎች አሉዋቸው። ነገር ግን ሊታረቁ የሚችሉ አይደሉም። ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄረሰብ ባለበት አገር ሁለቱንም በጋራ መጠቀም ነው ጠቃሚው።
አዲስ ዘመን፡- ሊታረቁ ካልቻሉ ግን እንዴት አብረው ሊሄዱ ይችላሉ?
ረ/ ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- ፍልስፍናዎቹ ናቸው እኮ፤ እነዚህን ጉዳዮች እንዳይታረቁ አድርገው የቀረፁት። ይህንን ፅንፍ የያዙት እነሱ ናቸው። እኛ ግን ይህንን ልንከተል ይገባል ብዬ አላምንም። አንደኛ ማንነትን እውቅና መስጠት እንዳለ ሆኖ የግለሰብን መብት እንዲሁ በህገመንግሥት ማረጋገጥ ይገባል። ሁለቱን ጎን ለጎን አስታሞ መራመድ የማይቻልበት ምክንያት የለም።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ አሁን ያለው ህገ መንግሥት ለዚያ ዕድል ይሰጣል ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- በነገራችን ላይ አሁን ያለነው ሽግግር ላይ ነው። ህገመንግሥት ላይ የሚነሱ ክርክሮች ያለ ወቅቱ የሚነሱ ናቸው። አሁን አገሪቱ ችግር ላይ ነው ያለችው። ለውጡም ሽግግርን ለማመቻቸት ነው። በሽግግር ወቅት ማነውስ ህገመንግስትን ማርቀቅ የሚችለው? አሁን ገና የህዝብ ውክልና የያዘ መንግሥትና መዋቅር ባልተዘረጋበት ቀድመን የሃሳብ ትርምስ ማንሳትም ተገቢ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም አዋህዶ ለመቀጠል ህጋዊ መሰረት ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ከምርጫ በኋላ ብቻ ነው እያሉኝ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- አይደለም፤ አሁንም ቢሆን እኮ አገሪቱ አለች። ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ለመሸጋገር ልታልፋቸው የሚገቡ ብዙ መንገዶች አሉ። አንዱ የህዝብ መተማመን ያገኘ ህገመንግሥትን ማደራጀት ነው። ስለዚህ ሊፈፀም የሚችለው የህዝብ ውክልና ባገኘና ህዝቡ በመረጠው መሆን አለበት ነው። ቅደም ተከተል ነው ሰጥተን መሄድ ያለብን። ፌዴራል ስርዓት ውስጥ መቆየት አገሪቱ መበተን አለበት የሚለውን አያመጣም። ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። የፌዴራል ሥርዓቱ ግን ፍትሃዊና ህዝባዊ መሆን አለበት። ከአሻጥርና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን አለበት። ህዝቡን የሚያስማማ ዓይነት መዋቅር ሊኖር ይገባል ። ይሄ ሊሰራ የሚችል ነው። ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለሰላም መስራት መቻል አለባቸው። ስለዚህ ሰላምን ማምጣት ይቻላል። የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰብስበው ሰላም ሊመጣ የሚችልበትን መንገድ መቀየስ አለባቸው። ይህ መሆን ከቻለ ወደ ዴሞክራሲ ግንባታ እንሄዳለን። እንጂ ፌዴራሊዝም ስላለ አገር አትኖርም የሚባል ነገር የለም። ታላላቅ የሚባሉ አገሮች ጭምር በፌዴራሊዝም ስርዓት እየተመሩ ነው የሚገኙት። ቀደም ብዬ እንዳልኩት ሁልጊዜ ከማንነት ፖለቲካ ጀርባ የፖለቲካ ሊሂቃን እጅ አለ። ይህን የግለኝነት አካሄድ ማስቀረት ከቻልን በጋራ መቀጠል የማንችልበት ዕድል አይጠፋም። ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች አገርን ወደ ማዳን ውይይት መምጣት አለባቸው። ረጅም ጊዜ ወስደው ሊፈቱት የሚገባ ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በተለይ በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ አልቻለም፤ ወገንተኛ የሚል ቅሬታ በተለያዩ አካላት ይሰማል። ከዚህ አንፃር ምን መታዘብ ችለዋል?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እኔ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አይመቸኝም። ምክንያቱም ድሞክራሲ ነው። ዴሞክራሲን እየነቀሱ እየለዩ አንዱ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ሌላው የሚከላከልበት ሁኔታ አይበጅም። አንድና አንድ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የሚሄድ የፖለቲካ ስርዓት አገርም የለም። የሰው ልጅ ጉንዳን አይደለም፤ አንድ መስመር ይዞ አይሄድም። የአተያይ ልዩነት አለ። የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አለ። የስርዓት ልዩነት አለ። የአስተዳደግ ልዩነት አለ። ምክንያቱም አገር ብዙ ልዩነቶችን ይዞ ነው የሚመራው። ልዩነት እኮ የእድገት ምክንያትም የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ሁልጊዜ ልዩነትን ጎጆ አድርገን ማየትም የለብንም። የተለየ ሃሳብ አማራጭ ያስፈልጋል። በሃሳብ መለያየት ዜግነትን አይከለክልም። ስለዚህ ማነው ይሄኛው ፓርቲ ብቻ የዜጋ ድርጅት ነው፤ ይሄኛው አይደለም ለማለት ስልጣን ያለው? እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከመነሻው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ላቋርጦትና ጥያቄውን ግልፅ ለማድረግ ያህል ዶክተር አብይ የሚመሩት መንግሥት ወገንተኛ ነው፤ በተለይም ደግሞ በኦነግ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ኃይሎች የሚፈጥሩትን መተራመስ በቁርጠኝነት ማስቆም አልቻለም የሚል ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እሱን ለማለት ምንም የተጨበጠ ማስረጃ የለንም። እኔ እስከማውቀው ድረስ የኦነግ ሰዎች በመንግሥት ሥራ ላይ ጣልቃ ይገባሉ ብዬ አላምንም ።የምቀበለው ነገርም አይደለም። እንዳውም ተቃራኒ ነው። ኦነግ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚሉት መንግሥት እያቀረብን አይደለም የሚል ነው። አሁን ኦነግ ራሱ የሚባለው ድርጅት ብዙ የተከፋፈለ አንጃ ያለው ድርጅት ነው። ስለዚህ የቱ ነው የአገር ሰላም እየበጠበጠ ያለው፤ በመንግሥት ሥራ ጣልቃ እየገባ ያለው የሚለው ጉዳይ መለየት አንችልም ።አገርን በማተራመስ አጀንዳ ይዞ ከዶክተር አብይ ጋር የሚሰራ ድርጅት የለም። ይህንን የሚፈቅድ መዋቅርም የለም። ምንአልባት ሰዎች ሊጠራጠሩ ይችላሉ። ምክንያቱም ፖለቲካ በራሱ ከአስተሳሰብ ነፃ ባለመሆኑ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላለው አለመረጋጋት የፖለቲካ ሊሂቃን እጅ እንዳለበት በተደጋጋሚ አንስተዋል። ምንአልባት ለእነዚህ አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖር ይሆን?
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- ልክ ነሽ፤ አሁን ያለው ቴክኖሎጂ ጠቅሟቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ግን ደግሞ ለግንባታ ለልማት ሊውል የሚል ነገር ነበር። ያንን አሁን ያለአግባብ እየተጠቀመበት ነው ያለው። ምሁር የሚባለውም ሆነ አክቲቪስቱ። ለነገሩ በትክክል የፖለቲካ ሊሂቃን ናቸው የሚለው ጉዳይም ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው። በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ሳይንሳዊ ድጋፍ የሌለው አስተያየት ነው ሲሰጥ የሚታየው። ይህንን በምንም መልኩ ልናስቀረው አንችልም። ግን አንባቢው ማመዛዘን የሚችለው ጉዳይ ነው። እነዚህን አካላት ተከትሎ የሚጎርፍ ትውልድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ ህሊናን ማዳበር የሚያስፈልግ ነገር ነው። በምክንያታዊነትና በስነ አመክኒዮ ማሰብ፣ በተጨባጭ መሬት ላይ ባለው እውነታ ማሰብ ይፈልጋል። እዛ ላይ ሰዎች ለምን ይፅፋሉ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሰው የሚናገረው በአዕምሮው ያሰበውን ነው። ይህንን እንደምክንያት ወስደን አብረን ከምንጋጋ ምንድን ነው የተፃፈው ብሎ ደጋግሞ ማሰብ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ሌላው የወጣቱ አስተምህሮ መጠናከር አለበት። ትልቁ የሰላም አስተምህሮ ከሃይማኖት ነው የሚመነጨው። የትኛውም ሃይማኖት ሰላምን ነው የሚያስተምረው። የውጭ ሰላምን አብሮ መኖርን ነው የሚሰብከወ ።እዛ ላይ ክፍተት የተፈጠረ ይመስለኛል። በሃይማኖት በኩል የሚሰጠው የሰላምና የፍቅር አስተምህሮ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ምክንያቱም የሰው ልጅን አእምሮ ከታች ጀምሮ የሚቀርፅ በመሆኑ። ሁለተኛው ባህላችን እንዳይሸረሸር ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የራሱ መዋቅር ያለው በመሆኑ መዋቅሩ ከተዳከመ ወጣቱ ትውልድ የራሱ ባህል ገዳይ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ይገባናል። ይህ ሲሆን ነው አገራችን ሰላም ሆና የምትቀጥለው።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ በማድረግዎ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ረ/ፕሮፌሰር ብዙነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ማህሌት አብዱል