የትምህርት ዘርፉን ተግባራት ለማሳለጥ የሚረዳ ዲጂታል የተማሪዎች መለያ ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፦ በ2016 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች የአሠራር ድግግሞሽን ለመቀነስ እና በተማሪዎች የትምህርት ሰነዶች መካከል አንድነትና ቅንጅትን ለማጠናከር ዲጂታል የተማሪዎች መለያ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚያደርግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ የትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በትምህርት ተቋማት መደበኛ የተማሪዎች መለያ አድርጎ ለመተግበር ወስኗል ብለዋል።

ይህ ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግ እና ለማዘመን በምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ በመዋሉ ከሚገኙት ጥቅሞች መካከል ፈርቀዳጅ የሆነው የተማሪዎችን ማንነት በወጥነት መለየት የሚያስችል ሥርዓት ማቋቋም ነው ብለዋል።

ይህም ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም የትምህርት ተቋማት አበይት የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችል እንዲሁም የአሠራር ድግግሞሽን በመቀነስ እና በተማሪዎች የትምህርት ሰነዶች መካከል አንድነት እና ቅንጅትን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ በላቀ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የግል መረጃን የማስቀመጥ እና የመጠቀም ደህንነትን በእጅጉ ይጨምራል፤ ማንኛውም ዓይነት ጥሰቶችን ይቀንሳል። በተጨማሪም ቅንጅቱ ከፍተኛ የአሠራር ቅልጥፍና እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ መርሃ ግብር ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ የብሔራዊ መታወቂያ መርሐ ግብር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋራ ባደረገው ስምምነት እስከ አሁን 640 ሺህ ተማሪዎች ብሔራዊ መለያ ቁጥር ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ይህም የተማሪ ቅበላ፣ ፈተና እና የማህደር አስተዳደር የመሳሰሉት ሥራዎች የተሳለጠ አካሄድ እንዲከተሉ ያስችላል ያሉት አቶ ዮዳሄ፤ የሥርዓቱ ቅልጥፍና ዲጂታል ውህደትን ያረጋግጣል፣ ይህም ተማሪዎች የኦንላይን ግብዓቶችን፣ የኤሌክትሮኒክ መማሪያ መድረኮችን እና ዲጂታል የትምህርት አገልግሎቶችን በፍጥነት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባን ለመጀመር ሁለቱም ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የተቀናጁ ተግባራትን ያከናውናሉ። ተቋማቱ ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን የሙከራ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደት በቀልጣፋነት እና በውጤታማነት ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕግሮራም የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ከፍተኛ የለውጥ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ይህንን ሽግግር ተቀብለው እንዲተገብሩት አሳስቧል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You