አብሮነት- የጥንካሬ መሠረት

የአብሮነት ቋንቋ መግባቢያው ፍቅር ነው። የጋራ በተባለ ጉዳይ ላይ መረዳት ይኖራል። በመልካምነት ቀለም ይፃፋል። በደግነት ማህተም ይታተማል። በዚህ የሕይወት ጉዞ ብቻነት ብቻውን ነው። ችግር በቤት እስኪደርስ አይጠበቅም። አንዱ ስለሌላው ይታመማል። አብሮ ሲኮን በደስታም በኀዘንም ነው።

አብሮነት ብቸኝነትን ይሽራል። ከእኔነት ለእኛነት ያደላል። ለሰው ልጆች ደስታ ምንጭ ነው። ተጋግዞ ይበረቱበታል። መጽውተው ይጸድቁበታል። ከብዙዎች ተለይቶ ለመልካሞች የተሰጠ ልዩ ፀጋ ነው። ያገሬው ሰው ስለአብሮነት ተረቶች አሉት። ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› ይላል። ደግሞ በሌላ ጊዜ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› ብሏል። ዓለማዊው ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ አስተምህሮዎችም ይደገፋል። ደስታ የሚገኝበት የሕይወት መንገድ ነው።

ኢትዮጵያውያኑ በዚህ አይታሙም። በአብሮነት ታሪክ የድል ጽዋ ተቋድሰዋል። በጋራ በልተዋል ተሳስበዋል፤ ፍቅርን ተጋርተዋል። ከሀገራቸው አልፈው ተጉዘዋል። በዚህ አብሮነት ከግዛታቸው አልፎ ለአፍሪካዊ ተርፈዋል። የአፍሪካውያን ድምጽ በመሆን የብዙዎችን እምባ አብሰዋል። ለዓለምና ሕዝቧም የተረፈ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ሆነዋል። ይህ የአብሮነት ነገር በየወቅቱ መታወስ የሚያስፈልገው ዐቢይ ጉዳይ ነው። ይህንም ብዙዎች ይስማሙበታል።

የሀገር ሽማግሌው አህመድ ዘካሪያ ይናገራሉ። አብሮነት ለእርሳቸው በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው። መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ እርካታው በምንም አይተካም። ለሃይማኖት ተቋማትና ለመልካም አሳቢዎች ብቻ አይተውም። ለተወሰኑ ዜጎች ብቻ የሚተው ኃላፊነት አይደለም። ለሁሉም የተሰጠ ከሁሉም የሚጠበቅ እሴት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ሁሉም ሲተባበር ነገር ይቀላል። በቤተሰብና በጎረቤት መካከል አብሮነት መፍጠር ያሻል። ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህም ሥራን ይጠይቃል። በአብሮነት አለመጓዝ መሪ ሳይጨብጡ መኪና ለማሽከርከር እንደመሞከር ነው። የሀገርን አንድነት ሁለንተናዊ ዕድገት ማጠናከር ላይ አብሮነት ሚናው ከፍ ያለ ነው። ቁልፍ ተግባር መሆኑን በመረዳት መንቀሳቀስ ይገባል ይላሉ።

አብሮነት የሥነ- ልቦና ጫናዎች ለመቀነስ ፋይዳው ጉልህ ነው። የድህነት ችግሮቻችንን ለመቅረፍ መድኃኒቱ አብሮነትና መደጋገፍ ነው ይላሉ። አብሮነት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ጊዜ፣ ቦታ እንዲሁም ካለአስተማሪ የሥነ ልቦና ውቅር መገንባት ይችላል። ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤትም ነው ባይ ናቸው የሀገር ሽማግሌው።

የነበረው የአብሮነት እሴት መጥፋቱን የሀገር ሽማግሌው አንስተዋል። ይህም ማኅበረሰቡ ላይ ማኅበራዊ ጫና እያሳደረ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። ስለአብሮነት አንስቶ ማውራት ብቻ ሳይሆን የመኖር ተግባር ይጠይቃል።

አዲሱ ትውልድ አብሮነትን በሚመለከት የቤት ሥራዎች አሉበት። የሀገሪቷን ትናንት ማጥናት አለበት። በድል ስለተሻገረቻቸው ፈተናዎች መጠየቅ ይኖርበታል። ይህ የጉዞ መንገድ ውጤታማ ነው። አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው። ድህነታችንንም በአብሮነት መቅረፍ እንችላለን ብለዋል የሀገር ሽማግሌው።

ሌላኛው ሀሳብ ሰጪ መሰለ መንግሥቱ ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ለእሳቸው አብሮነት ለሰው ልጆች ምሉዕነት የታደሉት ጸጋ ነው። አዲስ ብያኔም አይፈልግም።

በሰው ልጆች መካከል የኃይል ትስስር አለ። ይህ ትስስር ውጤታማ እንዲሆን ሥራዎች ያሻሉ። ግንኙነቱ ጭቆናና ተጽዕኖ ላይ መመስረት የለበትም። ይህን አብሮነትና መደጋገፍን ማጠናከር ያስፈልጋል።

የሰው ልጅ ብቻውን ይኖር ዘንድ አይቻለውም። ተነጣጥሎ መቆምም የማይችል ነው። በአብሮነት ማኅበራዊ ትስስሩን ማጠናከር ይገባዋል ባይ ናቸው መምህሩ።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You