ብዙዎች እንደሚሉት አሁን በአገር አቀፍም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚው እድገት መስክ ለውጥ አለ፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል በመሆኗም በተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ላይ በመሳተፍ ከአገር ገጽታ ጀምሮ የውጭ ኢንቨስትመንት እስከመሳብ ስለመብቃቷ ምሁራን ይመሰክሩላታል፡፡ የአገሪቷን የኢኮኖሚ ዋልታ በተስፋ መስመር ላይ ካስጓዙትና ብዙ በሮች እንዲከፈቱ ካስቻሉት ውስጥ ደግሞ አዲስ ቻምበር አንዱ ነው፡፡
ከአስር አገራት በላይ የተወጣጡ በምግብ፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በህክምና ቁሳቁስ ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ 35 የውጭ ኩባንያዎች እንዲሁም ወደ 90 የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳተፉበት አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተካሂዷል፡፡
ዘንድሮ 12ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የግብርናና የምግብ ንግድ ትርዒትና የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሜዲካል ንግድ ትርዒቱ የንግድና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበትን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ ተዘጋጅቷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ እንደሚሉት፤ አዲስ ቻምበር የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ የንግድ ክንውኖችን እየሰራ ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እያደረገ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አማካኝነት በየጊዜው የሚካሄደው የንግድ ትርዒት ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትን ያማከለ በመሆኑ የቢዝነስ አማራጮችን ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው፡፡ በተለይ ተቋማት ያላቸውን ምርትና የአገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ለሌሎች ከማካፈላቸውም ባሻገር ተጨማሪ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። በአገር ቤት ኩባንያዎችና ከውጭ በሚመጡ ኩባንያዎች መካከል ያለውን የቴክኖሎጂ እድገት በማየትም ልምድ ለመቅሰም ያስችላቸዋል፡፡
የንግድ ትርኢቱ የልምድ ልውውጥና የንግድ ለንግድ ግንኙነትን ከመፍጠር ባሻገር በተለይ አነስተኛና ጥቃቅን ልማት ላይ የተሰማሩ ኩባንያች በቀላሉ ሊያመርቷቸው የሚችሉ፣ በገበያውም ተመጣጣኝ የሆኑ የቴክኖሎጂ ምርቶች የሚቀርቡበት መሆኑን አቶ ጌታቸው ያብራራሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የግብርናና የምግብ ነክ እንዲሁም የህክምና ቁሳቁስ ምርቶች በንግድ ትርዒቱ መቅረባቸው ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የገበያ ውድድርን ከፍ የማድረግም ጠቀሜታ አላቸው፡፡ የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የግብርናና ምግብ ንግድ ትርዒት ሥራውን ከጀመረ 12ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያደርገው ጉዞ በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን አስገኝቷል፡፡ የስኬቱ ማሳያዎች ከሆኑት ውስጥ ደግሞ በዘንድሮው ዓመት ለየት ባለ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ‹‹የሜዲካል ንግድ ትርዒት›› ማቅረብ መቻሉ ነው፡፡ በዚህም የግል ኩባንያዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ትኩረት በተሰጠውና እንደ አገር በስትራቴጂክ መልኩ የተያዘውን የህክምና ጉዳይ ጥራት ባለው መንገድ ለማስጓዝ ይጠቀሙበታል፡፡ ለአገሪቱ የሚመጥኑ ተወዳዳሪ የህክምና ሴክተሮችን ለመፍጠርም ሚናው የጎላ ነው፡፡
‹‹እንዲህ አይነቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገራት ተገበያዮች እንዲሁም ለጎብኚዎች ስለ ግብርናውና ህክምናው ቢዝነስ ለመወያየት በር ይከፍትላቸዋል፡፡
በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ላይ ከ125 ኩባያዎች በላይ ተሳታፊ መሆናቸው የቢዝነስ ትስስርን ለመፍጠር አማራጭ እድል እንደሚሰጥና የገበያ መረጃን ለማግኘት እንዲሁም የቢዝነስ አጋርነትን ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአነስተኛ የግብርና ስራ የሚተዳደሩ ከ90 በመቶ በላይ ሴክተሮች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያ ምርትን ለማቅረብና የገበያ መረጃዎችን ለማግኘት ስለሚሹ በዚህ ትርዒት ላይ መሳተፋቸው በመጻኢው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል›› በማለት አቶ ጌታቸው የንግድ ትርዒቱን ሁለንተናዊ ፋይዳ ያስረዳሉ፡፡
የግብርናው መስክ አሁንም በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ የንግድ ትርዒቱ ከኋላ ቀር የግብርና ስራ ወደ ዘመናዊ የግብርና ስራ ለመሸጋገር እንዲሁም የአግሮ ኢንዱስትሪውን ክፍተቶች ለመሙላት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል። የተዳከመውን የአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ለማቅለል፣ የግብርናውን ጥራት ለማስጠበቅ፣ በጥሬ መሳሪያዎች የሚገጥመውን የማምረት ችግር ለመቅረፍ፣ የግል ሴክተሮችን በአግሮ ኢንዱስትሪ የበለጠ ለማሳተፍ፣ ተያያዥ የኢንቨስትመንት ሀሳቦችን ለማፍለቅ አዲስ ቻምበር እያስገኘ ካለው ጠቀሜታዎች ውስጥ ከፊሎቹ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በተለይ በ12ኛው የንግድ ትርዒት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና አገልግሎቶች መቅረባቸው ከዓለም አቀፍ የህክምና ሴክተሮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚረዳና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት፣ የዘርፉን ባለሙያዎች ለማብቃትና የአቅም ግንባታ ለማድረግ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ቻምበሩ መሰል አዳዲስ የንግድ ትርዒቶችን የማካሄድ ሂደቱም ቀጣይነት አለው፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የግብርና ሚኒስቴር፤ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ የግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እድገት ዋነኛው ሞተር መሆኑን በመናገር፤ የአገሪቷ የግብርና ፖሊሲ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት በተለይም የግሉን ዘርፍ ሚናን አካታች በሆነ መንገድ የተቀረጸ በመሆኑ በእንዲህ አይነት የንግድ ትርዒት ላይ መሳተፍ የኢኮኖሚ አቅምን መፍጠሪያ አንዱ መድረክ ነው ይላሉ፡፡ ጠንካራ የአገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲኖርና በኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ሊያድግ እንደሚገባና ይህን ማድረግ ከታቸለም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ከባድ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ አይናለም፤ በግብርናው ንግድ ውስጥ ዋነኛ ባለድርሻ የሚባሉትን አምራች ኢንዱስትሪዎችንና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንጻር አዲስ ቻምበር የሚሰጠው ጠቀሜታ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ንግድ ትርኢቱ ኩባንያዎች የግብርና ምርትና አገልግሎታቸውን ለሚፈልጉ ደንበኞች በማስተዋወቅ ዘላቂነት ያለው የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ኩባንያዎች በማስተዋወቅ አገር በቀል ምርቶች እንዲሸጡና ተቀባይነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡
የኢኮኖሚ እድገቱ ከሚዳስሳቸው ሴክተሮች ውስጥ የህክምናው ዘርፍ አንዱ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እንደ ግብርናው ሁሉ የጤና ሴክተሩም በቢዝነስ ረገድ ፈጣን የሆነ ለውጥን ማሳየት እንዳለበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲያስችለው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እያከናወነ ያለውን ሁሉን አቀፍ የንግድ ትርዒት ተግባራት እንደ ስትራቴጂ አጋር አካል እንደሚመለከተው ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባለፈው አስር ዓመት የአባላቱን አቅም ከመገንባት ጀምሮ ኢንቨስትመንት በአገሪቱ ላይ እንዲስፋፋ እስከማድረግ ያካነወናቸው ተግባራት በቀጣይ ከዚህም በላይ በመስራት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚችልም አንስተዋል፡፡ በንግድ ሂደቱም ላይ መንግስት ከምክር ቤቱ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አሳውቀዋል::
የንግድ ትርዒቱ ከውጭ ለሚመጡ ኩባንያዎች አገሪቱን በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለአገር ገፅታ ግንባታ ካለው አስተዋፅኦ በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የንግዱን ኅብረተሰብ መብት ለማስጠበቅና የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየውን የንግድ ሥርዓት ለማዘመን ቻምበሩ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦም አድንቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው