በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ 1እና2 የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንደሚያደራጅና ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ በአንቀጽ 82 ላይም ጉባዔው 11 አባላት እንዳሉት ያመለክታል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የጉባዔው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ መሆናቸውንም ደንግጓል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ በሙያ ብቃታቸውና በስነምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የህግ ባለሙያዎችንም ለጉባዔ አባልነት ያካትታሉ፡፡ ጉባዔው ከፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሶስት አባላት ይኖሩታል፡፡ ጉባዔው የስራ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መዋቅርም እንደሚዘረጋ ህገ መንግስቱ ይደነግጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 84 ጉባዔው በፌዴራልም ሆነ በክልል ህግ አውጭ ከህገ መንግስቱ ይቃረናል የሚል ጥያቄ በፍርድ ቤቶች እና በባለጉዳይ አቤቱታ ሲቀርብለት መርምሮ የህገ መንግስት ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች የመጨረሻ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡ በጉባዔው ውሳኔ ቅር የተሰኘ አቤቱታ አቅራቢ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ህገ መንግስቱ ያመላክታል፡፡ በአንቀጽ 83 ደግሞ በጉባዔው የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡
በህገ መንግስቱ የተደነገገው የህገ መንግስቱ የአተረጓጎም ስርዓት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የህገ መንግስት የአተረጓጎም ስልት ተግባራዊ ቢሆንም በተርጓሚውም ሆነ በአፈጻጸሙ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ይነሳሉ፡፡ በተለይም የዩኒቨርሲቲ የህግ ልሂቃን በተርጓሚ አካል ላይ በተደጋጋሚ የተገቢነት ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ በምርምሮቻቸውና የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማነጻጸርም ህገ መንግስቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መተርጎም የለበትም የሚል አቋም ያንጸባርቃሉ፡፡ ምንም እንኳ ምክራቸው ጆሮ ባያገኝም፤ ምርምሮቻቸው ከመደርደሪያ ባይወርዱም፡፡
አዲሶቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በቅርቡ ከጉባዔው አባላት ጋር ትውውቅ ባደረጉበት መድረክ ላይ ስለህገ መንግስት አተረጓጎም ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህገ መንግስት መምህሩ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ፤ ህገ መንግስት በብዙ አገራት በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች እንደሚተረጉሙ አመላክተዋል፡፡ ምንም እንኳ የብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ልሂቃን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስቱን መተርጎም የለበትም የሚል አቋም ባያንጸባርቁም ህገ መንግስቱን ማን ይተርጉመው የሚለው ጥናት ቢደረግበት መልካም መሆኑን መክረዋል፡፡
የህገ መንግስቱ ተርጓሚ ላይ በምሁራን ከሚነሳው የተገቢነት ጥያቄ በተጨማሪ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስቱን ለመተርጎም የተዘረጋው ስርዓት ላይ የአፈፃፀም ችግር እንዳለበትም ተነስቷል፡፡
የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ እንዳሉት፤ ጉባዔው ከ1992 እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም ከቀረቡለት 3ሺ724 አቤቱታዎች ውሳኔ የተሰጣቸው 2ሺ40ዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 65 ብቻ የህገ መንግስት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው ተወስኖ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ የተቀሩት 1ሺ619 ግን የጉባዔውን የውሳኔ ሀሳብ እየጠበቁ ነው፡፡
እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ከቀረበባቸው 65 ጉዳዮች የግለሰብና የቡድን መብቶችን የሚመለከቱ፤ መሬት የህዝብ ከመሆን ጋር የተገናኙ፣ የአርሶ አደሮች ከመሬት ያለመፈናቀል መብት፤ ከሴቶችና ህጻናት ጋር የተያያዙና ሌሎች ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ ከቀረቡት አቤቱታዎች አብዛኞቹ በግለሰቦች የቀረቡ ናቸው፡፡
ለጽህፈት ቤቱ ከ1992 እስከ 2000 ዓ.ም የቀረቡት አቤቱታዎች ከአራት የማይበልጡ ነበሩ፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት ግን የአቤቱታ አቅራቢዎች ቁጥር በየዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ አቤቱታ የመብዛቱን ያህል ግን የጽህፈት ቤቱ አደረጃጀት ያለውን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ አልተደራጀም፡፡ ለስራው ምቹና በቂ ቢሮ እንዲሁም የመሰብሰቢያ አዳራሽ የለውም፡፡ ጥያቄውን መመለስ የሚችል የሰው ኃይል እና ሀብት በበቂ ሁኔታ አልተሟላም፡፡ መደበኛ ስብሰባ በየወሩ ቢሆንም ካለው ችግር አንፃር ጉባዔው በየሳምንቱ ረቡዕ እንደሚገናኙም አመላክተዋል፡፡
ለጉባኤው የሚቀርቡ አቤቱታዎች መብዛት ዜጎች ስለህገ መንግስቱ ግንዛቤያቸው እየጨመረ መምጣቱን እንዲሁም የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመጓደሉ አለመርካታቸውን ያሳያል የሚል አመለካከት ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡
የአቤቱታ መብዛት እንደየምክንያቱ መጥፎም ጥሩም ጎን ሊኖረው እንደሚችል የሚያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ ጉባዔው አሁን ባለው አሰራርና አደረጃጀት አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት አዳጋች እንደሆነበትና በዚህም ዜጎች አቤቱታ አቅርበው ምላሽ እስኪሰጣቸው እየተጉላሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም አቤቱታ አቅራቢዎች ከአቤቱታቸው ጋር የእግድ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ እግዱ ሲፈቀድ የመደበኛውን ፍርድ ቤት አሰራር ስለሚያግድ የፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ላይ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እግድ ይፈቀድ ወይስ አይፈቀድ የሚለው በአዋጁ ጉባዔው እንዲወስን ስልጣን ሰጥቶታል፡፡ ሆኖም አስቸጋሪ በመሆኑ አዋጁ ተጥሶ በጽህፈት ቤት ኃላፊው ፊርማ እግድ ይፈቀድ ወይስ አይፈቀድ እየወጣ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አባል አቶ ክፍለጽዮን ማሞ፤ ጉባዔው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቶሎ ውሳኔ አይሰጥም፡፡ ውሳኔዎች ሲሰጡ ክርክሩ ህዝብ እንዲማርበት በመገናኛ ብዙሃን አይተላለፍም፡፡ ጉባዔው አንድ መሰብሰቢያ ቦታ እንጂ ህገ መንግስትን እንደሚተረጉም ደምና አጥነት እንዳለው ተቋም አይቆጠርም፡፡ ይህ አስተሳሰብ የሚጎላው በከፍተኛ አመራሩ ነው ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው፤ ማብራሪያ ምንም እንኳን ለህገ መንግስት ተርጓሚ በተቋማትና በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ባይሰጥም በርካታ የውሳኔ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎች በርካታ ቦታ ከረገጡ በኋላ ወደ ጉባዔው በመምጣት ተስተናግደዋል፡፡ ህገ መንግስቱን በተገቢ አስተምህሮት የማክበርና የመጠበቅ ችግር ይታያል፡፡ ተራው ህዝብ ባይፈረድበትም በህግ ሙያተኞች ዘንድ ትላልቅ ጉዳዮች ከፖለቲካው ውሳኔ ይልቅ ለህገ መንግስት ተርጓሚ በማቅረብ የማስፈታት ችግር አለ፡፡ ሌላው ብዙ ጊዜ ውሳኔዎች ተግባራዊ ስለማይሆኑ ተስፋ በመቁረጥ ለጉባዔውና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ብናቀርብ ምን ያደርግልናል የሚል አስተሳሰብም ይታያል፡፡ ምክንያቱም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማስፈጸም አቅም የለውም፡፡
አቶ ክፍለጽዮን አንደሚሉት፤ ህገ መንግስት ተጥሶ ወደ ጉባዔው የሚመጣ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይህ የእውቀት ችግር ነው ማለት አይቻልም፡፡ ብዙ ጊዜ የሚመጡት ጉዳዮች የግለሰቦች ናችው፡፡ የፍትህ ትንሽ ባይኖረውም ትላልቅ የፍትህ ጉዳዮች ግን እየታዩ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጉባዔው በአዲስ አበባ ብቻ ስለሆነ ያለው የተደራሽነትም ችግር አለበት፡፡ የክልሎችን የህገ መንግስት ኮሚሽኖችን በማጠናከርና ምን አይነት ስልጣን ይኑራቸው የሚለውን በመወሰን ችግሮችን ማቃለል እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አባል አቶ ሚሊዮን አሰፋ በበኩላቸው በህገ መንግስት ትርጉም ዙሪያ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ይታያሉ፡፡ የፖለቲካ ኃላፊነት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህን እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም፡፡ ከመደበኛው ስራቸው ወጥተው ይህን እንዲያዩ ዕድል መስጠት ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱን የቱንም ያህል አሳምረን ብንጽፈው በተግባር ማዋል ካልቻልን ዋጋ የለውም ይላሉ፡፡ የህገ መንግስትን አዳጊ ባህሪ አካቶ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግስቱ በብዙ መልኩ ይጣሳል፡፡ ህገ መንግስቱ የሚተረጎመው ሲጸድቅ በነበረው ነው ወይስ አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ የሚለው በተግባራም በጽንሰ ሀሳብም አከራካሪ ነው ይላሉ፡፡
ለጉባዔው በርካታ አቤቱታዎች እንደሚቀርቡ የሚያነሱት አቶ ሚሊዮን፤ የፍርድ ቤቶች የፍርድ አሰጣጥ ችግር እንዳለበት ይተቻሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ፍትህ ሲሰጡ አሞራውን ጅግራ ይላሉ፡፡ አሞራውን ጅግራ ብለው የሚሰጡ ከሆነ ደግሞ የማይበላው አሞራ ይበላል ማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ስራቸውን በአግባቡ ስለማይሰሩ ወደ ጉባዔው በርካታ የአሞራና የጅግራ ታሪክ ያላቸው አቤቱታ አቅራቢዎች ይመጣሉ፡፡ ጉባዔውም በዚህ ላይ ክርክር ሳያደርግ የውሳኔ ሀሳብ ስለሚያሳልፍ በአተረጓጎም ላይ ውስንነት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ሌላኛው የጉባዔው አባል ዶክተር ፋሲል ናሆም፤ የህብረተሰቡ አንገብጋቢ ጥያቄ ፍትህ እንጂ የህግ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ ባለሙያው የሚሰራው ወቅታዊ ሁኔታዎችን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ የህግ ሊህቃን ግን በህግ ወደ ፍትህ የሚያስኬድ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡
የፍትህ አሰጣጡ በጣም የተንዛዛ ነው፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ከማህበራዊ ፍርድ ቤት ተነስተው የክልል ፍርድ ቤቶችን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን፣ የሰበርን ችሎትን አልፈው ወደ ጉባዔው ፍትህን ፍለጋ ይመጣሉ፡፡ ጉባዔውም ጋር ከደረሰ በኋላ ሁለትና ሶስት ዓመትን ለውሳኔ ይቆያል፡፡ ይህን አይነት የተንዛዛ የፍትህ አሰጣጥ የግድ መስተካከል አለበት፡፡ ህግ በሁሉም ደረጃ ለፍትህ መሆን አለበት፡፡ ከአንድ ደረጃ ወደሌላ እንዴት እንደሚሸጋገር መፃፉ ሳይሆን የህብረተሰቡ ፍትህ የማግኘት ጉዳይ መረጋገጥ አለበት ሲሉ ዶክተር ፋሲል አስረድተዋል፡፡
ሌላው ዶክተሩ የሚያነሱት ጉዳይ በአገሪቱ በህገ መንግስት ትርጓሚ መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚችሉ ትላልቅ ጉዳዮች ወደ ጉባዔው አለመምጣቸውን ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአገሪቱ ከፖለቲካ ይልቅ ህግ መፍትሄ የሚሰጣቸው እንደመፈናቀል ያሉ ጉዳዮች ወደ ጉባዔው አይመጡም፡፡ በአገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ቢፈናቀልም ወደ ጉባዔው አይደርስም፡፡ አንድ ሰው ድንበሬ ተገፋብኝ ብሎ ግን ወደ ጉባዔው ይመጣል፡፡ በመሆኑም ህግን የችግሮች መፍቻ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ህገ መንግስትን ማን መተርጎም አለበት የሚለው በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ የህገ መንግስትን የበላይነት ለማስከበር በየትኛው መንገድ ቢኬድ ያዋጣል የሚለውን ማየትና ማጥናት ያስፈልጋል የሚሉት ሌላኛው የጉባዔው አባል አቶ መለስ ዓለም ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ህገ መንግስቱን ማን ይተርጉመው ከሚለው ሀሳብ በተጨማሪ አሁን ያለው አደረጃጀት የሚቀርቡትን ጉዳዮች ለመመለስ የሚያስችል ባለመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን አደረጃጀቱን በማስተካከል የተከመሩ የህዝብ አቤቱታዎች ውሳኔ ማግኘት አለባቸው፡፡ ህዝቡ ለጉባዔው በርካታ አቤቱታዎችን ይዞ እንዲመጣ ገፊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚለውን በማጥናት መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጉባዔው ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ለመለየትም ግልጽ የመለኪያ ስርዓት መዘርጋትም እንደሚገባው ያመላክታሉ፡፡
ሌላኛው የጉባዔው አባል ወይዘሮ ደስታ ገብሩ፤ በህብረተሰቡ ላይ በደላሎችና በአስፈጻሚው በርካታ በደሎች ይደርሳሉ፡፡ ማስረጃዎች ይሳሳታሉ፡፡ ለአንድ መሬት በርካታ ማረጋገጫዎች ይሰጣሉ፡፡ ሌሎችም በርካታ ወንጀሎች በዜጎች ላይ ይሰራሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ተፈጥረው ዜጎች ወደ ፍርድ ቤቶች ሲሄዱ ዳኞች እስከታች ወርደው በማየት ትክክለኛ ፍትህ መስጠት አልቻሉም፡፡ በዚህም ፍትህ ለማግኘት ተስፋ ባለመቁረጥ ጉባዔው ጋር መምጣት የማይገባቸው ጉዳዮች እየመጡ ነው፡፡ ይህም ጉባዔው በፍርድ ቤቶች መስራት የሚገባቸውን ጉዳዮች እያጨናነቁት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ጌታቸው አሰፋ፤ አጣሪ ጉባዔው ዋና ዓላማው ህገ መንግስቱን ማስከበር ነው፡፡ የሞራልና የፖለቲካ ማራመጃ መሆን የለበትም፡፡ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተመሳስሎ መሄድ ሳይሆን የህገ መንግስቱን ኃላፊነት በትክክል በመተርጎም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ በሙያ መመራትም ይገባዋል፡፡ ከጉባዔው በሚቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌዴራሽን ምክር ቤት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎቸ ይግባኝ ስለሌላቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸውም ያመላክታሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የህግ የበላይነትን ማክበር፤ ዴሞክራሲን መሰረት አድርጎ መስራት፤ የግለሰቦችን መብት ማክበርና ማስከበር እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ጉባኤው በዋናነት ትላልቅ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ የንብረት፣ የቤተሰብ፣ የንግድና ሌሎች መደበኛ ጉዳዮች ላይም አያተኩርም፡፡ እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት መታየት አለባቸው ይላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ጉባዔው እያያቸው ያሉት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ሊታዩ የሚገባቸው ከግለሰቦች መብት መጣስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ አቅጣጫ ተቀምጦ መፈታት አለበት፡፡ ምንም እንኳን የግለሰብ ጉዳዮች ወደ ጉባዔው አይምጡ ባይባልም በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት ስራዎችን ለመስራት መፈተሽ የሚገባቸውን ጉዳዮች መስተካከል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ ከጉባዔው አባላትም ሆነ ከሌሎች ባለሙያዎች በቀረበላቸው ሀሳብ ብዙ መረጃ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተው ያሉትን የአሰራር ክፍተቶች ለማሻሻል ከህግ ልሂቃን፣ ከመንግስትና ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ለማስተካከል እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ከፍርድ ቤቶች አሰራር ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጉዳይ ከፍርድ ቤት ዳኞች፤ ጠበቆችና ከሌሎች ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት በመሆን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የፍትህ ተቋማት በህዝብ ዕምነት የተጣለባቸው እንዲሆኑ ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡ በዘርፉ ማሻሻያ በማድረግ ተቋማት ለፍትህ አሰጣጣቸው ጥርስ እያወጡ እንዲሄዱ ለማድረግም እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አረዳም፤ ወደ ሙሉ ስራ ከመግባታችን በፊት የጋራ ግንዛቤ መያዝ አለብን፡፡ በችግሮቹ ላይ ብቻ ከመቆዘም ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም በጋራ መስራት አለበት በማለት፤ ይህ እንዲሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
አጎናፍር ገዛህኝ