አበበች ጎበና- የበጎነት አርአያ

በኢትዮጵያውያኑ ልብ ውስጥ በደማቁ ተፅፈዋል።በዘመናት የማይነዋወጥ የክብር ስፍራ አላቸው።ማኅፀናቸው ዘር ባያፈራም ልባቸው እናት ለመሆን አልቦዘነም። በወለዷቸው ለተጣሉ ነፍሶች ታዛ ሆነዋል።ልጅ በማኅጸን ብቻ ሳይሆን በልብም ተምጦ እንደሚወለድ እማኝ ናቸው።ለሚያሳድጓቸው ልጆች ሲባል እልፍ ሆነዋል።ለእነሱ በእርሳቸው ያልተሆነ ነገር የለም።ከጠላ መጥመቅ እስከ ቆሎ ሻጭነት ድረስ።የሃያ ዓመታት ትዳራቸውንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትነዋል።የኢትዮጵያውያን እናት በመባል የሚታወቁት አበበች ጎበና።

ልጆቻቸው “አዳዬ” እያሉ ነው የሚጠሯቸው።በጎነት ሰው ቢሆን የእሳቸውን ስጋ ለባሽ ነበር።የሰውነት ውሃ ልክ የቅንነት መሠረት ሆነዋል።የጥሩ መሆን መለኪያ ናቸው፤ ጥሩነት እሳቸውን ተጠቅሞ ይለካል።ስለ በጎ ተግባር ያልሆኑት መሆን የለም። በትናንት መልካምነት ነገን ይሻገራሉ።ላልወለዱት ልጅ ከእናት ይልቅ ይሳሳሉ።ስለ በጎነታቸው ጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።

ሸበል በተሰኘ ስፍራ ከመኖር ጋር ትውውቅ ፈጠሩ። የልጅነት ወዘናቸው ሳይጠፋ ነበር ዓለም ክፉ መልኳን ያስጎበኘቻቸው። አባታቸውን እድሜያቸው በቅጡ ሳይነጋ ተሰናበቱ፤ በጣሊያን የጦርነት ዘመን።አባታቸው መገደላቸውን ተከትሎ በአያቶቻቸው እጅ አደጉ።

እድሜያቸው አሥርን እንደተሻገረ ነገር መጣ።ተገደው ሊዳሩ ሆነ።ይህን ችግር ማለፊያ መላ ዘየዱ።ከነበሩበት ፊቼ ወደ አዲስ አበባ ኮበለሉ።አስኳላ ገቡ።መሠረታዊ ትምህርትም ቀሰሙ። በአንድ የቡናና ሰብል ድርጅት ውስጥ የጥራት ተቆጣጣሪ በመሆን ሠርተዋል።

እዳዬ ሃይማኖታቸውን አጥባቂ ናቸው።ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ነበር ወሎ ላይ የተገኙት።ግሸን ደብረ ከርቤ ሊሳለሙ። እዚያው በሄዱበት የበጎነት ሥራቸው አልፋ ተባለ። ወቅቱ ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰኔና ሰኞ ሆኖ ነበር። ወሎ በከባድ ድርቅ ተመታች።በርሀቡ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስክሬን እዚህም እዚያም ይታያል።አሞራ የሰውን ስጋ ይበላል።

ዓይናቸው የሞተ እናትን ጡት ከምትጠባ ልጅ ጋር ተገጣጠመ።ልባቸው አልችል አለና ልጅቷን በእቅፋቸው አስገቡ።እዛው ባሉበት ሌላ ጎልማሳ ልጁን በእቅፉ እንደያዘ ሊሞት ሲያጣጥር ተመለከቱ።በእጃቸው የነበረውን ምግብ ቢያቀምሱትም ሊያተርፉት ግን አልቻሉም። ምንም ማድረግ ባይችሉም ልጁን ግን ወደቤታቸው ይዘው ሄዱ።

የቀራቸውን ምግብ ላሉት ችግረኞች ሰጥተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።በዓመቱ ሌሎች 19 ልጆችን ጨምረው በቤታቸው 21 ልጆችን ማሳደግ ጀመሩ።ልጆቹን በማሳደግ ሂደት በብዙ ተፈትነዋል።የሚያበሏቸው አጥተው እነሱን ለማሳደግ ያልሰሩት ሥራ የለም።በሁለት ልጆች ማሳደግ የተጀመረው የበጎነት ጉዞ ለብዙዎች ደረሰ።በሂደት እናትነት ከማኅፀን ልጅ ማውጣት ብቻ አለመሆኑን አስመሰከሩ። ስለመልካምነት ዘመሩ።ጥሩነትን በመኖር አሳዩ።

የዛሬ ሦስት ዓመት ዓለምን ያስጨነቀው ወረርሽኝ እሳቸውምጋ ደረሰ።በኮቪድ 19 ምክንያት በ85 ዓመታቸው ይህችን ምድር ተሰናበቱ።እሳቸው በስጋ ቢለዩም ድርጅታቸው ግን ለሰዎች የመድረስ ተግባሩን አላቋረጠም።

ድርጅታችን እርሳቸው ካለፉ በኋላ የጀመሯቸው ተግባራት ምን ላይ እንዳሉ ጠየቀ።እሸቱ አረጋ ይባላሉ።የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።በአበበች ስም የተመሰረተው የበጎ አድራጎት ድርጅት በርካታ ተግባራትን እየከወነ ስለመሆኑ መስክረዋል።ወላጅ አልባዎችን ወላጅ ሆኖ እያሳደገ መሆኑን ጠቅሰዋል።ለሚያስፈልጋቸው የኪስ ገንዘብ ይሰጣል።

አበበች በሕይወት ሳሉ የጣሉት መሠረት ዛሬም እያገለገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።ዓላማውን ለማሳካት ደፋ ቀና በማለት ይሠራል።ስማቸውን በሚመጥን መልኩ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።እንጀራዎችን በመጋገር በውጭ ሀገራት ሁሉ ያደርሳል።በዚህም ገቢ ያገኛል።

ሌላኛው መስካሪ ይትባረክ ተካልኝ ይባላል፤ የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው።አበበች ለሱ ቃል ያሳጡታል፤ ሰው እንዴት በዚህ ልክ ለመልካምነት ይሰጣል ባይ ነው።በእናታቸው የተጣሉ እልፎችን አንስተው እናት ሆነዋል።ከእናት በላይ እናት መሆን መቻላቸው ይደንቀኛል ሲል መሰከረ።በእርሳቸው ፋንታ ሙት ቢባል ሳያንገራግር እንደሚያደርገውም ተናግሯል።

መልካም ስለሆኑ ጠይቀው አያጡም።ግንባራቸው ጥሩ ነው፤ የለመኑት ሁሉ ይሰጣቸዋል ይላል።ከሞቱ በኋላ አበበች ጎበና በጎ አድራጎት ድርጅታቸው እንዲንቀሳቀስ እየሠሩ ስለመሆናቸውም ገልጿል።

“ድርጅቱ አሁንም ሥራ ላይ ነው።ሕፃናት ላይ ትኩረት ያደርጋል።ከቅርብ ዘመድ ጋር በማቀላቀልም ይረዳል።የምግብ ችግር ያለባቸውንም ይመግባል።ጤና አጠባበቅ ላይ ይሠራል።የሕፃናትን ችግር ለማቆም ሴቶች ላይ መሥራት ወሳኝነቱን ያምናል።ከዐረብ ሀገራት ተመላሽ ሴቶችን ያሠለጥናል።የሥራ እድል ያመቻቻል። የራሱ ገቢ መሰብሰቢያ ዘዴዎችም አሉት።ሆስፒታል ገንብቷል።እንጀራ እየጋገረ ይሸጣል።የሸማ ሥራዎችንም ይሠራል” ሲል ተናግሯል።

ዳግማዊት ግርማ

 አዲስ ዘመን ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You