አዲሱ ዓመት በመልካም ተግባር ለሚገለጽ ዐሻራ የምንተጋበት ይሁን

 ዘመን ዘመንን ሲተካ፣ ዓመት በዓመት ሲለወጥ፣ ሁሌም አዲስ ብለን የተቀበልነውን አሮጌ ማለት፤ ሌላ አሮጌ የሚሆን አዲስ ዓመት መቀበል የተለመደ ነው። ለዚህም ነው መስከረም ላይ አዲስ ብለን በአበባ አንቆጥቁጠን የተቀበልነውን የ2015 ዓ.ም አሁን ነሐሴ 30 ላይ ሆነን ጷጉሜን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅመን አሮጌ ብለን ልንሸኘው፤ በምትኩም 2016 ዓ.ም ን አዲስ ብለን ልንቀበለው ሽር ጉድ እያልን ያለነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሁሌም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ለአዲስ ነገር ራሳችንን የምናዘጋጅ ስለመሆኑ እንናገራለን። በዓዲስ ዓመት በርካታ አዳዲስ ሕልሞች ይኖሩናል። ሁሌም ከችግር ባሻገር ያሉ መልካም ነገሮች ይታዩናል። ከፀብ ይልቅ እርቅ፤ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላም፤ ከመገፋፋት ይልቅ መተባበር፤ ከመነጣጠል ይልቅ አብሮነት፤… በብዙ መልኩ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን አብዝተን የምንመኛቸው ጉዳዮች ናቸው።

ባለፈው መስከረም ላይ አዲስ ብለን የተቀበልነው 2015 ዓ.ም በብዙ መልኩ በሕልምና ምኞቶቻችን ልክ፤ በብዙም መልኩ ደግሞ ከምኞትና ሕልሞቻችን ተቃርኖ እየተጓዘ እነሆ አሮጌ ብለን ልንሸኘው የመሸጋገሪያዋ ጷጉሜን ስድስት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ዓመቱ በብዙ ስኬቶች የሚገለጽባቸው ሁነቶች ነበሩት።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከጦርነት የመውጣት ሕልማችን እውን ሆነ። በልማቱም በኩል፣ ስንዴን ከራስ አልፎ ለውጪ ገበያ ማቅረብ የተቻለበት ከፍ ያለ ስራ የተከናወነበትም ነበር። በኢንዱስትሪውም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ ታምርት ብለን ከፍ ያለ ውጤት አስመዝግበንበታል።

በዲፕሎማሲው ዘርፍም ቢሆን፣ ከፍ ያሉ ዓለማቀፍ ጫናዎችን መሻገር የተቻለባቸው ሥራዎች፤ አያሌ የባለ ብዙ እና የሁለትዮሽ የትብብር ተግባራትም ነበሩበት። አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ሁነቶች በስኬት የተከናወኑበት፤ የኢትዮጵያን ብሩህ ነገ በግልጽ ያሳየው የብሪክስ አባልነት ጥያቄዋም መልስ አግኝቶ በአባልነት የታቀፈችበትን ሁነት ያስተናገደ በዚህ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ነው።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከጦርነት የተላቀቅንበት የሰላም ስምምነት በተፈረመ ማግስት፣ በሌላ መልክ የተገለጸ ጦርነት ውስጥ መግባታችን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሰላምና ፀጥታ ችግሮች መበራከት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለዜጎች ምሬት ምክንያት መሆን፤ ያልተገባ የዋጋ ንረትና ከፍ ያለ የኑሮ ውድነት፤ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች፤ ስደትና መፈናቀሎችን የመሳሰሉ በብዙ መልኩ የሚገለጹ ፈታኝ ሁኔታዎች የተገለጡበትም ዓመት ነበር።

እነዚህ ሁሉ ሁነቶች (በመልካምም፣ በችግርም የሚነሱት) ታዲያ ዓመቱ በራሱ የፈጠራቸው ሳይሆኑ፤ መልካሙ ነገር የመልካም ተግባራችን ውጤት፤ ችግር ሆኖ የተገለጠውም የክፉ ምግባራችን ፍሬ ናቸው። እኛ መልካም ስንሰራ በተሰጠን ጊዜ ውስጥ መልካም ዐሻራን አሳርፈን እንሻገራለን፤ ግብራችን ክፉ ከሆነም በተሰጠን ጊዜ ውስጥ በክፋታችን ልክ የሚያስገልጸን የተበላሸ ታሪክን አኑረን እናልፋለን።

አሁንም ከስድስት ቀናት በኋላ አዲስ ብለን የምንቀበለው ዓመትም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገለጥ ነው። ዓመቱን አንድ ብለን ስንጀምረው ቀኖቹ ሁሉ በእኛ ምግባር ልክ የሚገለጡ፤ በእኛው የእጅ ስራ ውጤት በመልካምም በችግርም ልንለካቸው የተዘጋጁ ናቸው።

በብዙ ተስፋ የምንጠብቅው አዲሱ ዓመት፤ አንድ 365 ገጽ ንጹህ ሉክ እንዳሉት ደብተር ነው። እያንዳንዱ የዓመቱ ቀን ላይ የሚኖረን ምግባር፤ በእያንዳንዷ የደብተሩ ገጽ ላይ በፊደል ታግዘን እንደምንኖረው ሃሳብ ነው። ይሄን ደብተር ጥሩ እንዲሆንና ሰውም ሊወድደውና ሊያነብበው ከፈለግን፣ በእያንዳንዷ ቃል የምንወክለው ሃሳብ፤ በእያንዳንዷ ገጽ የምናሰፍረው መልዕክት በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል።

ይህም ማድረግ ዝግጁነት አሁን ላይ ከሌለን፤ ደብተሩ ከተራ የፊደላት ክምችት አውድነት አይዘልም። ዓመቱም እንዲሁ ነው። ዓመቱን በመልካም ለመግለጽ ከፈለግን፤ በእያንዳንዷ ሰዓትና እለት የሚኖረን ተግባርና እንቅስቃሴ በወጉ ሊጤን፤ በኃላፊነትም ሊሆን የተገባ ነው።

አዲስ ዓመት መልካም ነገርን ከመመኘት ያለፈ የሚጨበጥ መልካም ነገርን የምናይበትና የምናገኝበት እንዲሆን ከክፋት መልካምነትን፤ ከጠብ ተነጋግሮ መግባባትን፤ ከቂምና በቀል ይቅርታና እርቅን፤ ከክፋት ደግነትን፤ ከመግፋት መደገፍን፤ ከመለያየት አብሮነትን፤ … ልናስቀድም ይገባል።

ከራስ ይልቅ ለሌሎች ማሰብን፤ ከግል ይልቅ ለሕዝብ፣ ከቡድን ይልቅ ለሀገር ቅድሚያ መስጠትን መላበስ፤ ሕዝብ ማገልገልን፤ ከሕዝብ አለመስረቅን፤ ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ በሕዝብ ላይ የኑሮ ጫና አለመፍጠርን፤ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ በንጹሃን ደም የራስን ኑሮ አለማደላደልን የሰብዕናችን ልኬት ማድረግ ይኖርብናል።

ለዚህ ደግሞ ራስን ማዘጋጀት፤ ቀጣይ የጷጉሜን ስድስት ቀናት ይሄንኑ ልዕልና ለሚያጎናጽፉን እሴቶቻችን ህይወት በመስጠት የራሳችን ሃብት ለማድረግ እንትጋ። ይሄን ስናደርግ አዲሱ ዓመት ለመልካም ነገር የምንተጋበት፤ እንደ ሕልማችን የአዳዲስ መልካም ነገሮች ምንጭ በመሆን በታሪክ የሚታወስ ሰናይ ዐሻራችንን የምናኖርበት ይሆናል።

 አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You