በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውኃ በሚፈልጉት ደረጃ ማግኘት እየቻሉ እንዳልሆነ ይሰማል፡፡ በተለይም በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍሎች ችግሩ የሰፋና ሥር የሰደደ ነው፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችንና ለጋሽ ድርጅቶችን በማሳተፍ መንግስት በዘርፉ ሰፊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑም ይነሳል፡፡
በኢትዮጵያ ንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦትና አካባቢ ጽዳት (ሳኒቴሽን) ዘርፍ የተቀመጡ ግቦች በሚሊኒየም አፈጻጸም ውስንነት ከታየባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአለም አቀፍ ደረጃ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የአካባቢ ጽዳት (ሳኒቴሽን) ሥራዎች ከዘላቂ ግቦች ጋር ተካትተው እንዲተገበሩ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያም 2021/22 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2030) ድረስ ማሳካት እንዲቻል ታልሞ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና የአካባቢ ጽዳት (ሳኒቴሽን) ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ የሁለተኛውን የለውጥ እቅድ ግቦች፣ የብሔራዊ /ዋሽ/ መሪ እቅድ እና የአገራዊ ስትራቴጂዎች የዘርፉን መዳረሻ ግብ መሰረት በማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ተግባራት ን ለማከናወን ተችሏል፡፡
በዚህ መሰረት የሁለተኛው የለውጥ እቅድ የመጠጥ ውሀ የአካባቢ ጽዳት (ሳኒቴሽን )ግቦች በገጠር አንድ ሰው በቀን 25 ሊትር ውሀ ማግኘት አለበት:: አጠቃላይ የመጠጥ ውሀ ተደራሽነት ሽፋን በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 59 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ታስቦ 79 ነጥብ 1 በመቶ መፈጸም ተችሏል፡፡ 20 በመቶ የገጠር የመጠጥ ውኃ አቅርቦት በቧንቧ መስመር የሚገናኝ መሆን እንዳለበት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የከተማ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ደግሞ እንደ የከተሞቹ ደረጃ ከ40 ሊትር እስከ 100 ሊትር ውሀ በቀን አንድ ሰው ማግኘት እንዲችል ታቅዷል፡፡ 2007 ዓ.ም ከነበረበት 57 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 75 በመቶ ለማድረስ ቢታቀድም መፈጸም የተቻለው 63 ነጥብ 6 በመቶ ነው፡፡ ሁሉም የከተማ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት በቧንቧ መሆን እንዳለበት መዳረሻ ግቦቹን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶክተር ነጋሽ ማብራሪያ፤ የብልሽት ምጣኔውን መቀነስና የሚባክነው የውኃ መጠንም ዝቅተኛ እንዲሆን ታልሞ እየተሰራባቸው ነው፡፡
የብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም (one wash National progeram) ለመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተና ተጠቃሽም ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም የመጀመሪያው የለውጥ እቅድ በቀጣዩ ሰኔ ወር የሚጠናቀቅ ሲሆን የሁለተኛው ዙር ደግሞ ለቀጣዮቹ አምስት አመታት መተግበር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ተሰርተዋል፡፡ 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሥራ ማስኬጃም ከለጋሽ አካላት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን የገጠር ሕዝብ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ተደራሽ ተደርጓል፡፡ አፈጻጸሙም 95 በመቶ ደርሷል ብለዋል ሚኒስተር ዴኤታው፡፡
በከተማ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሕዝብን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን በ9 ወር 500 ሺህ ሕዝብ ተደራሽ ተደርጓል:: ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያቶቹ፤ በስትራቴጂው የተቀመጠው በከተሞች ሙሉ በሙሉ ወጪ ማስመለስ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ውሀ የሚቀርበው፡፡ ከረድኤት ድርጅቶች እና ከአበዳሪ አካላት የሚገኘውን ገንዘብ የክልልና የዞን ከተሞች ውሀ ቢሮዎችና ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ተረክበው ያስተዳድራሉ:: የውሀ ተቋማትንም ይገነባሉ:: ለሕብረተሰባቸውም ተደራሽ ያደርጋሉ፡፡
ከሕብረተሰቡ ከውሀ ቢል በሚሰባሰብ ገንዘብና አነስተኛ ወለድ (ከ3 በመቶ በታች) በማስከፈል ብድሩን በረዥም ጊዜ ለአበዳሪዎች እንዲከፍሉ ይደረጋል:: በዚህ ሂደት ውስጥ የሚገኘውን ገቢ በቁርጠኝነት የመሰብሰብ ውስንነቶች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ተቀናጅተው ማስፈጸም አለመቻል፤ እንዲሁም የከተሞች እድገት በራሱ የሚፈጥራቸው ተጽዕኖዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በገጠር ግን ሀብቱም አቅርቦቱም የመንግስት ነው:: ሥለዚህ የዚህ አይነቱን ብድር የሚሰጡ አበዳሪዎች መስፈርት አላቸው፤ ጊዜም ይወስዳል፡፡ ከጥናትና ዲዛይን ጀምሮ እስከ ግንባታ ድረስ የሚፈጠሩ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የውሀ መገጣጠሚያ እቃዎች (ፓምፖች፣ ጀኔሬተሮች፣) ከውጪ የሚመጡ በመሆናቸው ከምንዛሪ እጥረት በተግዳሮትነት ተነስቷል፡፡ በተለመደው የአሰራር ሂደት የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦትን በገጠር ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል የተናገሩት ዶክተር ነጋሽ፤ የተለያዩ ሥልቶች ተነድፈው በመተግበር ላይ መሆናቸው አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የገጠር የመጠጥ ውሀ አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ ነው፡፡ የአገሪቱን የቆዳ ሥፋት 60 በመቶ የሚሸፍነው ቆላማ አካባቢ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በቀላሉ ውሀ ማግኘት የሚቻልባቸው ምንጮች፣ ጥልቅ ጉድጓዶች ወይም ወንዞች የሉም፡፡ ሥለዚህ በመደበኛው የውሀ ማቅረብ አሰራር መሸፈን የሚቻል ባለመሆኑ በተለየ መንገድ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮግራም ድርቅን በመመከት ለእንስሳትም ጭምር የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ መተግበር የጀመረው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ፕሮግራም ከመንግስትና ከረድኤት ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የ13 ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራ ተሰርቷል፡፡ አንዱ ፕሮጀክትም ከአሥር እስከ አስራ አምስት ቀበሌዎች የንጹህ መጠጥ ውሀን ማቅረብ የሚያሥችል ነው፡፡
የፍሎራይድ ፕሮጀክት ሌላው ተጠቃሽ ሥራ ነው:: በዚህ የተጠቃው የሥምጥ ሸለቆ አካባቢ ነዋሪ ሕዝብ ብዛት 11ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ከጥልቅ ጉድጓዶች በቀላሉ ውኃ መገኘት ይችላል፡፡ ነገር ግን ውኃው ለመጠጥ የሚሆን አይደለም፡፡ የአገሪቱንም ሆነ የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የመጠጥ ውኃ ዝቅተኛ መስፈርት (ሥታንዳርድ) የሚያሟላ አይደለም፡፡ ሥለዚህ በኬሚካል ሊጣራ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፡፡
ኦሮሚያ፣ ደቡብና በተወሰነ ደረጃ የአፋር አካባቢዎች በዚህ የተጠቁ ናቸው፡፡ 8 ትላልቅ የገጠር የንጹህ መጠጥ ውሀ ተቋማት እስከ አሁን ተሰርተዋል:: በመሆኑም 110 ሺህ ነዋሪዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡ 12 የፍሎራይድ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች ደግሞ እየተሰሩ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በጎርፍ፣በመፈናቀል፣በሥደት….ወዘተ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከሥታንዳርዱ እጅግ በጣም ያነሰና ለአንድ ሰው በቀን እስከ 5 ሊትር የሚደርስ ውሀ መሰራጨቱ ነው የተነገረው፡፡
በዘጠኝ ወር ሪፖርቱ እንደተመላከተው፤ የአካባቢ ንጽህና (ሳኒቴሽን) ፕሮጀክት በገጠርና በከተማ የተከፈለ ነው፡፡ ይሄን ማሳካት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ተነድፈው ተተግብረዋል፡፡
የከተሞች የአካባቢ ጽዳት (ሳኒቴሽን) ትኩረቱ በትምህት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ በገበያዎችና በሌሎችም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ንጹህ መጸዳጃዎች መኖር አለባቸው የሚል ነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁን ላይ 60 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ የተቀናጀ ከተማ አቀፍ የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ (ሳኒቴሽን) ሥራ በ23 ከተሞች ላይ ጥናትና ዲዛይን ተሰርቷል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓትን፣ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድና መልሶ መጠቀምን ጭምር ያካተተ ነው፡፡
ከቱቦዎች ጋር አገናኝቶ ፍሳሽ ቆሻሻን ማስወገድ አዳጋች በሆነባቸው አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጥ የተለየ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥልትንም ማካተቱ ተነግሯል:: ይህ ዲዛይን ለ5 ትላልቅ ከተሞች፤ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌና አዳማ ተሰርቷል:: የሌሎች 17 ከተሞች ሥራ በሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የገጠር የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ (ሳኒቴሽን) ፕሮግራም ሁሉም የገጠር አካባቢዎች በቀጣዮቹ 5 አመታት ንጹህ የመጸዳጃ ቤት መጠቀም አለባቸው የሚል አላማን የሰነቀ ነው፡፡ በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 9 ወራት 84 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቦ የመጠጥ ውኃና የሳኒቴሽን አገልግሎት ማድረስ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የሚሰሩና የማይሰሩ የመጠጥ ውሀ ተቋማት ቆጠራም 95 በመቶ ተለይቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
ሙሐመድ ሁሴን