የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ሀገሪቷን ለቀጣይ ሶስት ዓመታት እንዲያስተዳድር በተቃዋሚዎች ህብረት እና በመከላከያ መካከል ስምምነት መደረሱን የሱዳን መከላከያ አመራሮች ገለጹ፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ የፖለቲካ ስልጣኑ ለሲቪል አስተዳደር እንደሚተላልፍም አስታውቀዋል፡፡
ቢቢሲ ከካርቱም እንደዘገበው፤ የተቃዋሚዎች ህብረት በሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ሁለት ሶስተኛ መቀመጫ እንደሚኖራቸው የመከላከያ አመራሮች በመግለጫቸው ያሳወቁ ቢሆንም በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው መከላከያና የተቃዋሚዎች ህብረት በህግ አውጪ ምክር ቤት ውስጥ ፍጹም የበላይነት የመያዝ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው እየተነገረ ነው፡፡ ሁለቱ ኃይሎች የህግ አውጪ ወንበር ክፍፍል ዙሪያ እስካሁንም ከስምምነት አልደረሱም፡፡
ሌፍተናንት ጄኔራል ያሴር አል አታ በሰጡት ጋዜጣዊ መ ግ ለ ጫ እንዳብራሩት፤ በ መ ከ ላ ከ ያ ና በተቃዋሚዎች ህብረት መካከል የ ህ ዝ ቡ ን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የስልጣን ክ ፍ ፍ ል ስምምነት በ24 ሰዓታት ውስጥ ይ ፈ ጽ ማ ል ፡ ፡ የተቃዋሚዎች ህ ብ ረ ቱ የሽግግር ህግ አውጪ ምክር ቤት ውስጥ ካለው 300 ወንበሮች ውስጥ ሁለት ሶስተኛ መቀመጫ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን፣ የተቀረውን ወንበር የተቃዋሚዎች ህብረት አባል ላልሆኑ ሀይላት ይከፋፈላል፡፡
የሱዳን የተቃውሞ ንቅናቄ ቃል አቃባይ ታሃ ኦስማን፤ በበኩላቸው የስልጣን መዋቅር፣ በሉዓላዊ ምክር ቤት፣ ካቢኔና የህግ አውጪ መዋቅር ዙሪያ ሁሉም ኃይሎች ከስምምነት መድረሳቸውን አብራርተዋል፡፡ በመዋቅር ዙሪያ ከስምምነት መድረሱ በራሱ ግን ልዩነቶችን መፈታታቸውን አያመላክትም ብለዋል፡፡ በተለይም በህግ አውጭ እና በሽግግር ምክር ቤት የበላይ ምክር ቤት ውስጥ ሁለቱ ኃይሎች በሚኖራቸው መቀመጫ ዙሪያ ብስለት የተሞላበት ድርድር ሊያደርጉ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
አዲስ የሚፈረመው የስልጣን ክፍፍል ስምምነት ዙሪያ ሁሉም ኃይሎች ከስምምነት ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ያብራሩት ደግሞ የተቃዋሚዎች ህብረት አባል የሆኑት ሳቴ አል ሀጂ ናቸው፡፡ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስምምነት ላይ እንድንደርስ ፈጣሪ ይረዳናል›› በማለት ተስፋ መሰነቃቸውን አብራርተዋል፡፡
የተቃዋሚዎች ህብረት አባልና የተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት ሳዲቅ የሱፍ 11 አባላትን የሚያቅፈው የሽግግሩ የበላይ ምክር ቤት አባላት ስብጥር ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ የተቃዋሚዎች ህብረት 11 አባላትን ከሚያቅፈው የበላይ ምክር ቤት ውስጥ ስምንት ወንበር በመያዝ ሶስት ወንበር መከላከያው እንዲይዝ ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ መከላከያ በበኩሉ ከምክር ቤቱ ወንበሮች ውስጥ ሰባቱን በመያዝ አራቱን የተቃዋሚዎች ህብረት አባላት እንዲይዙት ፍላጎት አላቸው›› ብለዋል፡፡
ሀገሪቱን ለሶስት አስርት ዓመታት ያ ስ ተ ዳ ደ ሩ ት ፕሬዚዳንት ኦመር ሀሰን አልበሽር ባለፈው ወር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ የሽግግር መከላከያ ምክር ቤቱ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የቆየ ቢሆንም፤ ሀገሪቱ ውስጥ የነበረው አመጽ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አልበሽርን ያስወገዱት ሱዳናዊያን የሱዳን መንገዶችን በተቃውሞ ሰልፎች ማጨናነቃቸውን ቀጥለዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የመከላከያ ምክር ቤቱ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለሲቪል አስተዳደር ማስተላለፍ አለበት በሚል በተቃውሟቸው የጸኑ ሲሆን፣ የመከላከያ አመራሮች ከተቃዋሚዎች ህብረት ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን መግለጫ ከመስጠታቸው ከሰዓታት ቀደም ብሎም የሀገሪቱ መዲና በሆነችው ካርቱም ሲቪል በሆኑትና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት አምስት የሲቪል የፀጥታ አካላት ለህልፈት መዳረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
መላኩ ኤሮሴ