ትኩረት የሚሻው የተመጣጠነ ምግብ

ዜና ትንታኔ

እ.ኤ.አ በ2030 የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ከዓለም ለማስወገድ የዘላቂ ልማት ግቦች አካል ተደርጎ እየተሠራ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነታ አሳሳቢና ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ በሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ውስብስብ የጤና ችግር እየጎላ መምጣቱን የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ለመሆኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር መንስኤው ምንድን ነው? የችግሩ ደረጃስ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንዴት ይገለፃል? መፍትሔውስ ምንድነው? ስንል የዘርፉ ምሑራንን አነጋግረን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

የሥርዓተ ምግብ ባለሙያው አቶ ቢራራ መለሰ የተመጣጠኑ ምግቦች የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በውስጣቸው የያዙ፤ ኃይልና ሙቀት የሚሰጡ፣ ሰውነት የሚገነቡና በሽታ የሚከላከሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ የሚገኙት በዋናነት በተለያዩ በምግብ ዓይነቶች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑና እንደየሰው የእድሜ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ ምግቦች እንዳሉ ነው አቶ ቢራራ የሚናገሩት፡፡

እነዚህን በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ የምግብ ምድቦችና አይነቶችን ያሟላና በትክክል የተመገበ ሰው የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያገኝ የሚናገሩት አቶ ቢራራ፤ ከእነዚህ የምግብ አይነቶችና ምድቦች ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ አልያም ከዛም በላይ ሲጓደል ግን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጠመ ሊባል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

ምግቦችን በማቀላቀልና በማሰባጠር እንዲሁም የምግብ ምድቦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመመገብ ሁኔታ ካለ የሚፈልጉትን የምግብ ንጥረ ነገሮች ማግኘት እንደሚቻል ይገልፃሉ፡፡ ይህ በተጓደለ ሁኔታ የመመገብ ሁኔታ ካለ ግን በተቃራኒው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለ የሚያሳይ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡

በሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ የፕሮጀክት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ታመነ ታዬ በበኩላቸው የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ሲያብራሩ ‹‹አንድ ሰው በእድሜውና በተለያየ የሕይወት ዑደቱ ሲያልፍ የሚያስፈልገውን የምግብ ንጥረ ነገር መጠን በሚፈለገው መጠን፣ ጥራቱንና ስብጥሩን ጠብቆ ሳያገኘው ሲቀር የሚፈጠር ችግር ነው›› ይላሉ፡፡

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግር ዋነኛው መንስኤው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻል መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ቢራራ፤ በዚህም በርካቶች ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት ይጋለጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በጊዜው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዋነኛ መንስኤዎችን አውቆ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የተራቡ ሕፃናትን የመመገብና በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት ለከፋ ጉዳት ተዳርገው ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ሕፃናትን በማከምና የተመጣጠነ ምግብ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት ይሠራ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አሁንም የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ችግርን ለመቅረፍ ብዙ ያልተሠሩ ሥራዎች እንዳሉ አቶ ቢራራ ጠቅሰው፤ በተለይ ከምግብ ዋስትና ችግር መውጣት አለመቻልና የተቀመጡ ሰነዶችን ያለመተግበር ከሚጠቀሱ አሁናዊ መንስኤዎች ውስጥ ዋነኞቹ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ አግባብነት ያለው የሥርዓተ ምግብ መዋቅር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ደረጃ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ መዋቅር ደግሞ በዘርፉ በሠለጠኑ ባለሙያዎች ሊደገፍ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ የተዘጋጁ ሰነዶችንም መተርጎምና ሥራ ላይ ማዋል፣ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠትና የአመጋገብ ሥርዓትን መቀየር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ባለፈ አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎችም ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰትና ይበልጥ መባባስ የራሳቸውን አስተዋፅዖ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው አቶ ቢራራ የገለፁት፤ ከዚህ አንፃር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለሚታየው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መዋቅራዊና በሀብት ላይ የተመረኮዘ መፍትሔ እንደሚስፈልግ ያመለክታሉ፡፡

አቶ ታመነ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር በስፋት የሚታይ እንደነበረ አስታውሰው፤ ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤ በቂ የምግብ ምርት ማምረት ካለመቻል ጋር ተያይዞ የምግብ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን፣ ጥራትና ስብጥር አለመኖር እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ እነዚህ መንስኤዎች ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በፊት የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በግምባር ቀደምትነት ሲንቀሳቀስ የነበረው የጤና ዘርፍ ብቻ እንደነበር አቶ ታመነ አስረድተው፤ ይህ ደግሞ ዘላቂ በሆነ መንገድ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግሩን እንዳልፈታው ያስረዳሉ፡፡

የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም በወቅቱ ትኩረቱ ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንጂ የምግብ ጥራትና ስብጥር ላይ እንዳልነበር የተናገሩት አቶ ታመነ፤ ለአብነትም የእንስሳት፣ የወተትና የዶሮ ተዋፅዖ በሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ልክ ተለክቶ ሲመረት አልነበረም፡፡ ከዚህ አኳያም አቅርቦቱ ውስን እንደነበር ይናገራሉ፡፡

አሁን ላይ ደግሞ ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት ዋነኛ መንስኤዎች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የግንዛቤ እጥረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የተሰባጠረ የአመራረት ሥርዓት እንዲኖር በቂ የሆነ የዘር አቅርቦት አለመኖርም ሌላኛው መንስኤ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የምግብ ጥራትና ደኅንነት እንዲሁም ድህረ ምርት ብክነትም ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት መፈጠር አንዱ አሁናዊ መንስኤ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መንግሥት የሚመለከታቸውን ሴክተር መሥሪያ ቤቶችንና አጋር አካላትን በማስተባበር ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ታመነ ይገልፃሉ፡፡ ለአብነትም በሀገሪቱ የተስተካከለ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲኖር የምግብና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ ተቀርፆ ይፋ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ተቀርፆ እያንዳንዱ ሴክተር መሥሪያ ቤት ምን መሥራት እንዳለበት የትኩረት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንና ወደ ሥራ መገባቱን ይጠቁማሉ፡፡ የምርምር ተቋማትን በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችን በሀገራዊ የሥርዓተ ምግብ ግብረ ኃይል ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ በምርምር ሥራዎች እንዲያግዙ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የሚጠቁሙት፡፡

የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አሁናዊ መንስዔዎችን ማወቅ ከተቻለና በዚሁ ልክ በመፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆነ በርካታ ለውጦች ሊመጡ እንደሚችሉ ነው አቶ ቢራራ ሀሳባቸውን የሚያስቀምጡት፡፡ ለአብነት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ከኢትዮጵያ ተወገደ ማለት በአጭር ጊዜ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት እንደማይኖሩ ይጠቁማሉ፡፡

ከሚፈለገው የክብደት መጠን በታች የሆኑና የቀነጨሩ ሕፃናት እንደማይኖሩም ይጠቅሳሉ፡፡ ጥሩ አመጋገብ ያላቸው ሕፃናት ደግሞ በቀላሉ በበሽታ እንደማይጠቁ፤ በትምህርታቸውም ውጤታማና በቀጣይም አምራች ዜጋ እንደሚሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አሁናዊ መንስዔዎችን አውቆ በመፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ሥራዎች የማይሠሩ ከሆነ ግን የቀነጨሩ፣ የቀጨጩ፣ ከሚጠበቀው ክብደት በታች የሆኑ፣ የንጥረ ምግብ እጥረት ያጠቃቸው፣ የፎሊክ፣ ዚንክ፣ ካልሺየምና፣ ቫይታሚን እጥረት ያጋጠማቸው ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ነው አቶ ቢራራ ያላቸው ስጋት የሚገልፁት፡፡

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጠመ ማለት ደግሞ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ይናገራሉ። ጤናውን ለማከም የሚወጣው ወጪ ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይጠቁማሉ። ከዚህ ውጪ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት የተጠቁ ሕፃናት በትምህርታቸውም ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። ይህም ሀገሪቱ የምትጠብቀውን የተማረና አምራች የሰው ኃይል እንደሚያሳጣትና የምትፈልገውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልታሳካ እንደማትችል ነው ያብራሩት፡፡

አቶ ታመነ በበኩላቸው በተመጣጠነ የምግብ እጥረት መፍትሔዎች ላይ ሥራዎች በተሠሩ ቁጥር አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በጤና፣ በምርታማነት፣ በአዕምሮ ልኅቀት የዳበረ በመሆን የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ነው የሚገልፁት፡፡

ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የወጣውን ጥናት መነሻ በማድረግ በጊዜው ኢትዮጵያ ዓመታዊ የተጣራ ምርቷን 16 ነጥብ 5 ከመቶ ያህሉን በመቀንጨር ምክንያት እያጣች መሆኑን ያወሳሉ፡፡ በጤናው፣ በኢኮኖሚው፣ በትምህርት፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች ላይ በከፍተኛ መጠን ወደኋላ እንደሚጎትትም ነው አቶ ታመነ የሚጠቁሙት፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You