የቻይናው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቢዋይዲ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ከፍተኛ ሽያጭ በማድረግ ከኢላን መስክ ድርጅት ጋር እየተገዳደረ መሆኑ ተገለጸ። ድርጅቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ ወር ብቻ 207 ሺህ 734 የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ሸጧል። ይህ ጠቅላላ ዓመታዊ ሽያጩን ወደ አንድ ነጥብ 76 ሚሊዮን ከፍ አድርጎታል።
ድጎማዎች እና ቅናሾች ደንበኞች ቢዋይዲ መኪናዎች እንዲገዙ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል። ቴስላ ሰሞኑን የሩብ ዓመት ሽያጩ ምን ያክል እንደሆነ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የዩኤስ ኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ባለፈው ሩብ ዓመት ከቢዋይዲ ሲነፃፀር አነስተኛ ብልጫ ቢያሳይም መቀመጫውን ሼንዜን ያደረገው የቻይናው ድርጅት ልዩነቱን አጥብቦታል።
ቢዋይዲ ዓመታዊ ሽያጩ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 41 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ጭማሪ የመጣው የሀይብሪድ መኪናዎች ሽያጭ ከፍ በማለቱ ነው ተብሏል። የቻይናው ኩባንያ ሽያጩ እንዲጨምር ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ በሀገር ቤት ያለው የመኪና ገበያው ፉክክር ዋጋው ዝቅ እንዲል ማድረጉ እንዲሁም መንግሥት ዜጎች የቆዩ መኪናዎቻቸውን በኤሌክትሪክ መኪና እንዲተኩ ድጎማ ማድረጉ እንደሆነ ተገልጿል።
ቢዋይዲ 90 በመቶ መኪናዎቹን የሚሸጠው ቻይና ውስጥ ነው። እንደ ቶዮታ እና ቮክስቫገን ያሉ የውጭ ሀገራት መኪና አምራቾች ቢዋይዲን መቋቋም አልቻሉም። የቢዋይዲ እና ሌሎች የቻይና የኤሌክትሪክ መኪና አምራቾች በቻይና ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ዓለምም ሌሎች ጉምቱ መኪና አምራቾችን እየተገዳደሩ ይገኛሉ ተብሏል።
ከቻይና የመኪና አምራቾች ጫና የበረታባቸው የጃፓኖቹ ሆንዳ እና ኒሳን ለመጣመር ምክክር እያደረጉ እንደሆነ ባለፈው ወር ማሳወቃቸው አይዘነጋም። በታኅሣሥ ወር ደግሞ የጀርመኑ ኩባንያ ቮክስቫገን አይጂ ሜታል ከተባለው ድርጅት ጋር ስምምነት መድረሱን አስታውቋል። ኩባንያው ወጪውን ለመቀነስ አንዳንድ ፋብሪካዎቹ ሊዘጋ እንደሚችል ጠቁሞ ነበር።
ጂፕ፣ ፊያት፣ ፔዦ እና ክራይስለር የተባሉትን መኪናዎችን የሚያመርተው ስቴላንቲስ ኃላፊ የሆኑት ካርሎስ ታቫሬዝ በያዝነው ወር መባቻ ሥልጣናቸውን ለቀዋል። ግለሰቡ ከሥልጣን የለቀቁት ኩባንያው ትርፋማ አለመሆኑን ካሳወቀ በኋላ ነው። ቢዋይዲ በ2024 ሦስተኛ ሩብ ዓመት ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ገቢውን ከፍ ማለቱን ያስታወቀ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በገቢ ቴስላን መብለጥ ችሏል።
ኩባንያው እኤአ ከሐምሌ-መስከረም 2024 ባለው ጊዜ 28 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማስገባቱን አስታውቋል። በተመሳሳይ ሩብ ዓመት የኢላን መስክ ኩባንያ ያስገባው 25 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው። ነገር ግን ቴስላ ከቢዋይዲ የበለጠ የኤሌክትሪክ መኪና ሽያጭ አድርጓል።
የቻይና የመኪና አምራቾች ከሀገር ቤት ውጭ ባሉ ገበያዎች መኪና ለመሸጥ የሚያደርጉት ጥረት እክል እየገጠመው ነው። ባለፈው ጥቅምት የአውሮፓ ኅብረት ከቻይና የሚመጡ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ 45 ነጥብ 3 በመቶ ታሪፍ ጭኗል። ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ከቻይና የሚመጡ ኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ 100 በመቶ ታሪፍ ጭናለች። ቢዋይዲ እያደጉ ነው ወደሚባሉ ሀገራት ምርቶቹን ይዞ እግሩን እያስገባ እንደሚገኝ የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ታህሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም