የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጆኦሎጂካል ሰርቬይ የፋይናንስ አጠቃቀም ዙሪያ ኦዲት አድርጓል። በተደረገው ኦዲትም ያልተወራረደ ብር አምስት ሚሊዮን 648 ሺህ 757፤ ለአምስት ዓመት ያህል ያለተከፈለ 50 ሺህ 867 እዳ፤ እንዲሁም አላግባብ የተከፈለ ሁለት ሚሊዮን 398 ሺህ 457 ብር ጉድለት አግኝቷል።
በሌላ በኩል፤ ለጫማ ግዥ ወጪ የተደረገ 97 ሺህ 19 ብር በገቢ ተተክሎ መገኘቱ እና ተቋሙን ለለቀቁ ስራተኞች ብር ዘጠኝ ሺህ 133 ክፍያ መፈጸሙም በኦዲቱ ተረጋግጧል። በበጀት ዓመቱ የመደበኛ፤ የውስጥ ገቢ እና የካፒታል፤ በድምሩ 42 ሚሊዮን 887 ሺህ 793 ብር ስራ ላይ ለማዋል የተያዘው ገንዘብ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ሌላው የተረጋገጠ ግኝት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፤ በተቋሙ ንብረት አስተዳደር ላይ በተደረገው ኦዲት አገልግሎት የሚሰጡና የማይሰጡ ዕቃዎች ተደባልቀው ተከማችተዋል። አገልግሎት የሚሰጡ ዕቃዎችም ለስምንት ዓመት ያለ ጥቅም በግምጃ ቤት ተቀምጠው ተገኝተዋል። መወገድ ያለባቸው ያረጁ አስር መኪኖች ደግሞ ሳይወገዱ መገኘታቸውን ዋና ኦዲተር በግኝቱ አረጋግጦ ነበር።
ባለፈው ዓመት የሁሉንም የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ ይህ ጆኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት የኦዲት ግኝትም ተካትቶ ቀርቧል። ምክር ቤቱም ለዋና ኦዲተር መርሀ ግብር በመላክ የኢትዮጵያ ጆኦሎጂካል ሰርቬይን ጨምሮ ሁሉም ተቋማት የኦዲቱን ህጸፅ እንዲያርሙ ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ መሰረት በማድረግ የኦዲት ማስተካካያው ተግባራዊ መሆኑን ይገመግማል። ባለፈው ሳምንትም ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ጆኦሎጂካል ሰርቬይ የኦዲት ግኝት መስተካከሉን ዋና ኦዲተርና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በተገኙበት ገምግሟል።
ቋሚ ኮሚቴው ለኢትዮጵያ ጆኦሎጂካል ሰርቬይ የስራ ኃላፊዎች፤ ያልተወራረደ፤ አላግባብ የተከፈለ፤ ተቋሙ መክፈል ሲገባው ያልከፈለው፤ ወጪ ተደርጎ በገቢ ተመዝግቦ ስለተገኘው ገንዘብ መጓደል፤ ለለቀቁ ሰራተኞች አላግባብ የተከፈለው ገንዘብ መመለሱን፤ የተመደበው በጀት ጥቅም ላይ እያዋለ መሆኑን፤ ንብረቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን፤ መወገድ የሚገባቸው ንብረቶች ስለመወገዳቸው፤ በአጠቃላይ በኦዲት ግኝቱ የተመላከቱ ህጸፆች ስለመታረማቸው ማብራሪያ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ጆሎጂካል ሰርቬይ የግዢና ፋይናንስ ተወካይ አቶ ዘውዱ ንጉሴ፤ በሰጡት ማብራሪያ ካልተወራረደው አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ውስጥ አምስት ሚሊዮን ብር ተወራርዷል። ቀሪው 500 ሺህ ብር በህግ ተይዟል። ለረጅም ዓመታት ተንጠልጥለው የነበሩ ተከፋይ ሒሳቦች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተዋል። ከሒሳብ አመዘጋገብ ጋር የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የሙያ ድግፍ በመጠየቅ በዘንድሮ በጀት ዓመት መጨረሻ እልባት ለመስጠት እየተሰራ ነው። ስራ ከለቀቁ በኋላ ደመወዝ ከተከፈላቸው ሰራተኞች የሁለቱ ሁለት ሺህ 119 ብር የተመለሰ ሲሆን፤ የቀሪ ሶስት ሠራተኞች ጉዳይ ደግሞ በህግ ተይዟል። መስሪያ ቤታችን ለረጅም ዓመታት የነበረበትን የበጀት አጠቃቀም ችግር ለመፍታት በ2011 ዓ.ም ማሻሻያ አድርጎ እየሠራ ነው። ሲሉ አብራርተዋል።
በተቋሙ የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሁንዴ መልካ በበኩላቸው፤ ንብረቶችን ለማስወገድ ፈጥኖ ማከናወን ባይቻልም ኮሚቴ በማቋቋም አብዛኞቹ ተወጋጅ ንብረቶች ተወግደዋል። ተሽከርካሪዎች ከመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር ተነጋግረን በመወገድ ላይ ናቸው።
በአጠቃላይ በኦዲት ግኝቱ የተመላከቱትን ችግሮች ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ፤ በህግ አግባብ የሚፈቱት በህግ ተይዘው እየታዩ ስለመሆናቸው፤ የንብረት አያያዝ የአቅም ውስንነት ቢኖርም ክፍተቱን ለመሙላት ማሻሻያዎችን በመውሰድ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ ስለመሆኑ የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት፤ መስሪያ ቤቱ በኦዲት ግኝት ላይ የወሰዳቸው ማስተካከያዎች የሚያስመሰግን ነው። በቀጣይም የተጀመሩና የቀሩ የኦዲት ግኝት ማስተካከያዎች ላይ አጥናክሮ መቀጠል ይገባል። የንብረት አወጋገድና አያያዝ ላይ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት፤ በጀትን በአግባቡ ማቀድና ተፈፃሚነቱን ማረጋጋጥ፤ ሠራተኞች ከተቋሙ ሲለቅቁ ለፋይናንስ የሥራ ክፍል በወቅቱ ማሳወቅ፤ ያላሳወቁ ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባና ቀሪ ያልተስተካከሉ ግኝቶችን በድርጊት መርሃ ግብሩ መሰረት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዋና ዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ ሁንዴ፤ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የመጡ የኦዲት ህጸፆች እንደነበሩ አንስተው፤ የተለያዩ የማስተካካያ ርምጃዎች ተወስደዋል። ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታትም እየተሰራ ነው። ቀሪ የኦዲት ጉድለቶችን ለማስተካከል ከዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር እየሰራን ነው። አንዳንዶቹም በህግ ተይዘው በተቀመጠው መርሃ ግብር ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም መፍትሄ ለማምጣት እየሰራን ነው። በግዥና ፋይናንስ ዘርፍ ላይ ግን የአቅም ውስንነት አለብን።
ንብረት በማስወገድ ረገድ በቀጣይ ማስተካካያ እናደርጋለን። የበጀት አጠቃቀምንም በሂደት እናስተካክላለን። በፋይናንስ በኩል ያለውን ችግር እየፈታን ነው። ዋና ኦዲተርም የሚያደርግልን ድጋፍ ጥሩ ስለሆነ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት እንሰራለን። ሌሎች ተቋማትም የሚያደርጉልን ድጋፍ እያጠናከርን በመሄድ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራንም ነው፤ ብለዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ፤ ተቋሙ ለኦዲት ግኝት የሰጠው ትኩረት አበረታች ነው። በዘህም በኦዲቱ በታዩ ግኝቶች ላይ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅተው የማስተካከያ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ከማስተካከያዎቹ መካከል ተሰብሳቢው አምስት ሚሊዮኑ ብር ተሰብስቧል። የተከፋይ ሂሳብ ሙሉ በሙሉ ተስተካክሏል። የ2009 በጀት ዓመት የሂሳብ አያያዝ ችግርም ተስተካክሏል።
ተቋሙ የሚያበረታቱ እርምጃዎችን ቢወስድም በ2010 በጀት ተመሳሳይ የሂሳብ አያያዝ ችግር ገጥሞታል። ለጫማ ግዥ በወጪ የተመዘገበውና በገቢ የተመዘገበው ገንዘብ መጠን አልተስተካከለም። ለለቀቁ ሰራተኞች የተከፈለ ገንዘብ የተወሰነው ቢመለስም አሁንም ያልተመለሰ አለ። ከበጀት አጠቀቃም ጋር በተያያዝ በ2010 በጀት ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል። መስሪያ ቤቱ ከንብረት አጠቃቀም ጋር መልካም ስራ ቢጀምርም አሁንም ተጨማሪ ስራዎች ይቀራሉ። በመሆኑም እነዚህን ጉድለቶች ሙሉ ለሙሉ ማረም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ የሱፍ መሐመድ፤ ተቋሙ የወሰዳቸው የማስተካካያ ርምጃዎች የሚያስመሰግኑ ናቸው። ተቋሙ በኦዲት መውጫ ስብሰባ ከዋና ኦዲተር ጋር ስምምነት አድርጎ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ወደ ስራ ገብቷል። በተቀመጠው መርሃ ግብር መሰረት የማስተካከያ ርምጃ ወስዷል። ይህ ተቋሙ ለኦዲት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠ የሚያሳይ ነው። ይህ ተግባር በኦዲት ማስተካካያ ሂደት ተቋሙን በአስተማሪነት የሚያስወስድ ነው። ዘንድሮ ከገመገምናቸው ተቋማት ይህ የተሻለ ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በማስተካከያው መርሃ ግብር መሰረት ያልተስተካከሉትን የኦዲት ግኝቶች በቀጣይም ማጠናቀቅ ይገባል። ተጣርተው መወሰድ የሚገባቸውን ርምጃች መውሰድ አስፈላጊ ነው። ከዋና ኦዲተር ጋር ተናብቦ በመስራት የተጀመረው መልካም ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የንብረት አያያዝና አመዘጋገብ በህጉና በአሰራሩ መሰረት መከናወን ይገባዋል። የውስጥ ኢዲትን በማጠናከር የተቋሙን አሰራር ማጠናከርና ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ ነው። ይህ ከተደረገ ተቋሙ ምሳሌ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ