የስሪ ላንካ መንግሥት ጥሎት የነበረው አገራዊ የሰዓት እላፊ ገደብ ከአገሪቱ ዋና ከተማ ኮሎምቦ በስተሰሜን አቅጣጫ ከምትገኝ ግዛት በስተቀር በሌሎቹ አካባቢዎች ተነስቷል፡፡ የሰዓት እላፊው ገደብ የተጣለው ከሦስት ሳምንታት በፊት በአብያተ ክርስቲያናትና በሆቴሎች ላይ ከተፈፀሙ የቦምብ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በሙስሊሞች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ የአጸፋ ምላሾች በግዛቲቱ የሰላም መደፍረስ እንዲፈጠር በማድረጋቸው ነው ተብሏል፡፡ የሰዓት እላፊው ገደብ ቀደም ሲል በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተጥሎ የነበረ ቢሆንም፤ ሁኔታዎች መሻሻል በማሳየታቸው ተነስቷል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከአገሪቱ ዋና ከተማ ኮሎምቦ በስተሰሜን አቅጣጫ በምትገኘውና በመንጋ ፍርድ አንድ ሙስሊም ሰው በተገደለባት ግዛት ግን ገደቡ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ በበኩሉ በሙስሊሞች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ሁኔታው የማይበርድ ከሆነ ከባድ የኃይል ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ አንድ የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ በሰሜናዊ ምዕራብ ግዛት ያለው ሁኔታ መሻሻል እስከሚያሳይ ድረስ የታወጀው የሰዓት እላፊ ገደብ እንደጸና ይቆያል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው፤ በሙስሊሞች ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት ከሦስት ሳምንታት በፊት የተፈጸመውን ጥቃት ምርመራ የሚያስተጓጉልና ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዳይቀርቡ እድል የሚያመቻችላቸው ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከሶስት ሳምንታት በፊት በአብያተ ክርስቲያናትና በሆቴሎች ላይ የተፈፀሙ የቦምብ ጥቃቶች ክርስቲያን ስሪላንካውያን በሙስሊሞች ላይ የበቀል ርምጃ እንዲወስዱ አነሳስቷቸዋል፡፡ በተለይ በሰሜናዊ ምዕራብ የአገሪቱ ግዛት የተፈጸሙት ጥቃቶች ለሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በጥቃቱም መስጊዶችና ሱቆች ተቃጥለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በስሪ ላንካውያን ሙስሊሞች ላይ ተፈጸሙት ጥቃቶች አስፈሪና አሳዛኝ እንደነበሩ እየገለጹ ነው፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) ባወጣው መግለጫ፤ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ነገር
የበለጠ ቀውስ የሚጋብዝ እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የአገሪቱ መንግሥት ፌስቡክን ጨምሮ ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንንም ዘግቷል፡፡ የአገሪቱ መንግሥት የመረጃ ዘርፍ ዳይሬክተር ናላካ ካሉዌራ ጥቃቶቹ እንዳይባባሱ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በጊዜያዊነት መታገዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በርግጥ ጥቃቱ በተፈጸመ ማግሥትም የስሪላንካ መንግሥት ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያ በጊዜያዊነት ዘግቶ ነበር፡፡
ቡድሂስቶች በሚበዙባት ስሪ ላንካ ሙስሊሞች ከአገሪቱ ሕዝብ 10 በመቶ፤ ክርስቲያኖቹ ደግሞ ከሰባት በመቶ በላይ ቁጥር ይሸፍናሉ፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት በአብያተ ክርስቲያናትና በሆቴሎች ላይ በተፈፀሙ የቦምብ ጥቃቶች እስካሁን ድረስ ከ257 በላይ ሰዎች የተገደሉባትና ከ500 የሚበልጡት ደግሞ የቆሰሉባት የደቡብ ምስራቅ እስያዋ አገር ስሪ ላንካ አሁንም በከባድ የሀዘን ድባብ ተውጣለች፡፡ በጥቃቶቹ ዒላማ የተደረጉት ሦስት አብያተ ክርስቲያናትና አራት ሆቴሎች እንደነበሩና ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኞቹ ስሪ ላንካውያን ቢሆኑም የውጭ አገራት ዜጎችም እንደሚገኙበት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
በርካታ ፖለቲከኞችና ተንታኞች የፕሬዚደንት ማይትሪፓላ ሲሪሴና መንግሥት ጥቃቱን ማክሸፍ አለመቻሉን ኮንነዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንዳሉት፤ የአገሪቱ መንግሥት ከሳምንታት ቀደም ብሎ ስለጉዳዩ መረጃ ቢደርሰውም ችላ በማለቱ አሰቃቂው ጥቃት ሊፈፀም ችሏል፡፡
ከሦስት ሳምንታት በፊት የተፈፀሙት ጥቃቶች በታሚል ተገንጣዮችና በመንግሥት መካከል ለ26 ዓመታት ያህል ሲካሄድ የቆየው ደም አፋሳሹ የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃበት (እ.አ.አ ከ2009) ወዲህ የተፈፀመ የመጀመሪያው አሰቃቂ ጥቃት ነው ተብሏል፡፡ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት መሰል የቦምብ ጥቃቶች የተለመዱና የስሪ ላንካ የየዕለት ገጠመኞች ነበሩ፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት በዚያች አገር የሚገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ቦምቦችንና ጥቃት መፈፀሚያ ሌሎች ጦር መሳሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ እድል እንደሚሰጣቸውም ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
አንተነህ ቸሬ