የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ (General Assembly) እ.አ.አ በ2017 ባሳለፈው ውሳኔ (የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 72/130) ግንቦት 8 ቀን (May 16) “ዓለም አቀፍ በሰላም አብሮ የመኖር ቀን” (International Day of Living Together in Peace) ሆኖ እንዲከበር ወስኗል፡፡ ድርጅቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላምን፤ መቻቻልን፤ አብሮነትን፤ አካታችነትንና መግባባትን ለማስፈን የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማገዝና እነዚህ እሴቶች የኅብረተሰቡ ገዢ መርሆች ሆነው እንዲጎለብቱ ለማድረግ ነው፡፡ ቀኑ ሰላምና ወንድማማችነት የነገሰባትን ዓለም ለመገንባት በአብሮነት መቆምንና በልዩነት ውስጥ ኅብረት መፍጠርን ዓላማው አድርጎ ይከበራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “ዓለም አቀፍ በሰላም አብሮ የመኖር ቀን” አገራት ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት መሪዎች፤ ከማኅበረሰብ ተወካዮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመቻቻልን መርህ እንዲከተሉና የይቅርታ ባሕልን እንዲያዳብሩ ይጠይቃል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ስለሰላም አስፈላጊነትና ቀጣዩ ትውልድ ከጦርነት ስጋት ነፃ መሆን እንዳለበት ያብራራል፡፡ ይሁን እንጂ፤ የመንግሥታቱ ድርጅት “ዓለም አቀፍ በሰላም አብሮ የመኖር ቀን” እንዲከበርና ቡድኖች፤ እንዲሁም አገራት በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን ከሚያዳክሙ ድርጊቶችና አስተሳሰቦች ርቀው ዓለም ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን ቢሰብክም ጦርነት፤ መፈናቀልና ግድያ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ ድርጅቱም ቀኑ እንዲከበር በጠቅላላ ጉባዔው የወሰነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የዓለም የሰላም እጦት አሳስቦት ነው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ አገራት፤ በአፍጋኒስታን እንዲሁም በሌሎች የዓለም አገራት ለበርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት፤ መፈናቀልና ሞት መንስዔ የሆኑ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሳያባሩ እስከዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ እነዚህ ግጭቶች ጥለዋቸው ከሚያልፉት ጠባሳዎች መካከል
አንዱ በሰላም አብሮ የመኖር እሴት እንዲሸረሸር ማድረጋቸው ነው፡፡ በተለይም በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ዘዋሪነት የሚቀሰቀሱና የዘር መልክ ይዘው አድማሳቸውን የሚያሰፉ ግጭቶች የማኅበረሰቦችን በሰላም አብሮ የመኖር የቆየ መልካም ታሪክ ላይ አስከፊ ጠባሳ ጥለው ያልፋሉ፡፡ ይህም ቀጣዮቹ ትውልዶች በበቀልና ግጭቶቹ በወለዷቸው ቀውሶች ምክንያት ሰላሙ አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህም በተከታታይ ትውልዶች ላይ ዘላቂ ቀውስ በመፍጠር ጠንካራ ስነ-ልቡናዊ አቋም ያለው ትውልድ እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ግጭቶች ሲፈጠሩ ሰላም አስከባሪ ኃይል እየላከ ግጭቶቹን ማረጋጋቱ ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል የሚገልፁ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰላም አብሮ የመኖርን ጥቅም በማስተማርና የሰው ልጅ በሰላም አብሮ መኖር ባለመቻሉ የደረሱበትን መከራዎች እንደማስተማሪያ በማሳየት ግጭቶችን ከምንጫቸው ማድረቅ እንደሚገባ ይገልፃሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰላምና መግባባት ዓለምን በብዙ መልኩ ርቀዋታል፡፡ በየቀኑ የሚሰማው ግጭት፤ መፈናቀልና ሞትም የዚሁ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ፍልሰት (Internal Displacement) ላይ አተኩሮ የሚሰራ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በግጭቶች ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥራቸው በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀ ዓለም ዐይታው ወደማታውቀው ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
አንተነህ ቸሬ