የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ሚስጥርና ፋይዳ

ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው ዓመታዊ የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት፤ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶችን በአዲስ አባልነት ተቀላቅለዋል። ሀገሪቱ ኅብረቱን መቀላቀሏን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ስብስቡን መቀላቀሏ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ከተመዘገቡ ትላልቅ ዲፕሎማቲክ ድሎች አንደኛውና ዋነኛው ነው ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ወደ ስብስቡ መቀላቀሏ በብዙ ንግግርና ትግል የተገኘ ትልቅ ድል ነው። ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል የተደረገውም በብዙ መመዘኛዎች ሀገሪቷ ብቁ ሆና በመገኘቷ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ስብስቡ መግባት የቻለችው በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በሕዝብ ብዛትና በዓለም በመደመጥ አቅም እንዲሁም ወደፊት ባላት ተስፋ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ተደማጭነት ያላት ሀገር በመሆኗ ነው።

ታሪኳ፣ የሕዝብ ብዛቷ፣ ከፍተኛ ዕድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል መሆኗ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ በግብርና ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት፤ እንዲሁም አጠቃላይ የምርት ዕድገት በስብስቡ አባል ሀገራት ስለታመነበት እንድትካተት ተመርጣለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ኩራትና የዲፕሎማሲ ድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስብስቡ አዲስ ከተካተቱ ስድስት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ መካተቷ ለሀገሪቷ ሁለንተናዊ ድል መሆኑንም አንስተዋል።

ብሪክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ካሉ የስብስብ ኃይሎች መካከል በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ በመደመጥ አቅሙ እያደገ የመጣ ቡድን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ ቤተሰብ አባል መሆን አፍሪካ በዓለም ላይ ላላት ዲፕሎማሲያዊ የመደመጥ አቅም ወሳኝ መሆኑንም ማመናቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በሰላም አስከባሪነት የምትሠራውን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያላት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ፤ ያላት የታሪክ ሀብት እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የሀገራት ግንኙነት ኢትዮጵያ የብሪክስ አንድ አካል ብቻ ሳትሆን የብዝሃነት እና አካታችነት ዋና ቁልፍ ድምፅ ያደርጋታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ለብሪክስ አባልነት ጥያቄ ካቀረቡና ፍላጎት ካሳዩ ከ40 በላይ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር አባል እንድትሆን ፍቃድ ያገኘችበት ሚስጥሩ ምንድን ነው? ኅብረቱን መቀላቀሏስ ምን ፋይዳ አለው? በሚለው ላይ ምሁራን በጥልቀት የሚሉት አላቸው።

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ተንታኝ አቶ አትክልት አጥናፉ እንደሚገልፁት፤ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዓለም የሚመራው በአሜሪካ መሪነት በሚንቀሳቀሰው የምዕራባውያን ርእዮተ ዓለም ነው። ሆኖም ግሎባላይዜሽንና ቴክኖሎጂ እያሳደረ ካለው ተፅኖ አኳያ፤ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት አዲስ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ (global power order) እየፈለገ ነው። ይህን በመረዳት ከደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የተውጣጡ ሀገራት ከዚህ ቀደም ያለውን የዓለም አቀፍ ሥርዓት የሚገዳደር ኅብረት ፈጥረዋል። ስለዚህ ብሪክስ በኢኮኖሚና ወታደራዊ ኃይል እየተደራጁና እያደጉ ያሉ በተለይ ከደቡብ ንፍቀ ክበብ የተውጣጡ ኃያላን ሀገራት ያዋቀሩት ጥምረት ነው። ጥምረቱም የዓለም አቀፍ ሥርዓቱን ሚዛን የሚያስጠብቅ ነው።

ለብሪክስ አባልነት ጥያቄ ካቀረቡና ፍላጎት ካሳዩ ከ40 በላይ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር አባል እንድትሆን ፈቃድ ማግኘቷ ሀገሪቱ የረዥም ጊዜ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ የነበራት ታሪካዊ ሂደቶች፣ ክንዋኔዎች እና ተግባራቶች ጥምር ውጤት እንደሆነ አቶ አትክልት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማህበርን (League of Nations)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመመሥረት ደረጃ፤ አሁን ኃያላን ከሚባሉት ሀገራት እኩል የመሠረተችና ከአፍሪካ የመጀመሪያውና ቀዳሚ ሀገር ናት። እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመመሥረት ቀዳሚ ሀገር ናት። እንዲሁም ቅኝ ግዛት ካለመገዛቷ ባለፈ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ይናገራሉ።

ሌላው የአፍሪካ ቀንድ፤ የኃያላን ሀገራት መራኮቻ ሜዳ ነው። በዚህ ቀጣና ተደማጭናትና ተቀባይነት ያላት ሀገር ናት። ኢትዮጵያን ሳይዙ በቀጣናው ምንም ነገር ማሳካት ከባድ እንደሆነ ያውቃሉ። እንዲሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሀገር በመሆኗ ከኒውዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ የዓለም ትልቋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። ከእነዚህ ምክንያቶች ባሻገር ሊዘነጋ የማይገባው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በተዋረድ የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከሀገሪቱ አልፎ የአህጉሪቱን ድምጽ ለዓለም በማሰማት ረገድ እረፍት የሌለው ጥረት በማድረጋቸው እንዲሁም ተራማጅ የዲፕሎማሲ መርህ በመከተል ዓለም አቀፍ ሥርዓቱ ምን ያህል ተቀያያሪ እንደሆነ በመገንዘብ ዲፕሎማቶች እና መሪዎች ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ባሳዩት ብርቱ ጥረት ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር ብሪክስን ከተቀላቀሉ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ውስጥ አንዷ ለመሆን በቅታለች።

ኢትዮጵያ ስለፈለገች ብቻ ሳይሆን ጥምረቱ አባል እንድትሆን የፈቀደላት መሠረታዊ ምክንያት ስላለው ነው። ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ቁጥር፣ ወሳኝ መልካ ምዕድር አቀማመጥ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማሲ ባላት ሚና እንዲሁም በፈተና ውስጥ ሆኖ እንኳን እድገት እያስመዘገበ ያለ የማይበገር ኢኮኖሚ ያላት የነገ የአፍሪካ ተስፋ ተብለው ከሚታሰቡ ሀገራት አንዷ በመሆኗ እንደሆነ ያስረዳሉ።

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ሀዬሶ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ብሪክስ አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር በሰፊው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የአምስት ሀገራቶች ጥምረት ነው። ጥምረቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ በአምስት አባላቶች የቀጠለ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ያለውን ተጽዕኖ ከፍ ለማድረግ በርከት ያሉ የዓለም ሀገራቶችን አባል ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁና መቀበል መጀመሩ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥምረቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ማስገባቷ ይታወሳል። በቅርቡ በብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ፤ ጥያቄዋ ተቀባይነት አግኝቶ በመጀመሪያው ዙር ኅብረቱን ከተቀላቀሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራቶች በተለየ በመጀመሪያው ዙር ህብረቱን እንድትቀላቀል ይሁንታ ያገኘችበት ፈርጀ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ሀገሪቱ ያለችበት የመልከዓ ምድር አቀማመጥ በአፍሪካ ቀንድ ይሁን በገልፍ ሀገራቶች ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ገዥ የጆግራፊ አቀማመጥ ያላት በመሆኑ ነው። ሌላው የአፍሪካ መዲና ከመሆኗ ባሻገር በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረች ያለች በመሆኗ ሀገሪቱን መያዝ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሰፋ ያለ እድል በመኖሩ ነው። እንዲሁም እያደገ የመጣው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለጥምረቱ አባል ሀገራት ሰፋ ያለ ገበያ ከመፍጠርና ግብዓት ከማቅረብ አኳያ ሰፊ አቅም ያላት በመሆኗ እና በሕዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ከመሆኗ አንጻር ከሌሎች ሀገራቶች ጋር ሲነጻጸር ሀገሪቱ ቅድሚያ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ይላሉ።

አቶ አትክልት ሀገሪቱ ጥምረቱን እንድትቀላቀል እድሉን ማግኘቷ ትልቅ ድል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ አዲስ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ (global power order) ጥምረት የሆነውን ብሪክስን መቀላቀሏ ብዙ አንድምታዎች አሉት ይላሉ።

እርሳቸውም፤ ጥምረቱ በቀጣይ ይበልጥ እየተጠናከረ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ የሚመጡ አጀንዳዎችን (ከስደት፣ ከኒውክሌር ማብላላት፣ የአየር ንብረት ለውጥ … ወዘተ) በበላይነት ውሳኔ የሚሰጥ ተቋም እንደሚሆን ጠቁመው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የአፍሪካን አጀንዳ በዓለም አቀፍ መድረክ ማጉላት የምትችልበት እድሉ ይፈጠርላታል። እንዲሁም በቀጣይ የዓለምን ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሥርዓት በበላይነት ይዘውራሉ ተብለው ከሚገመቱ ኃያላን ሀገራት መካካል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ እንደ ቻይና፣ ራሺያ፣ ህንድ የመሳሰሉ ሀገራት የሚገኙበት ጥምረት ነው። ከእነዚህ ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ በአንድ ጎራ በመሰለፍ በዓለም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ጉዳዮችን የምትመክርበት እድል ማግኘቷ፤ ሀገሪቱ ቀጣዩን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሚቀበሉ ሳይሆን ከሚወስኑ አካላት አንዷ የሚያደርጋት ነው። ስለዚህ ሀገሪቱ ህብረቱን መቀላቀሏ ሁለንተናዊ ፋይዳ አለው።

ከዚህ ባሻገር ብሪክስ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ተደማጭነት የሚያጎላ ድልድይ ነው። በዚህም ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ማንነቶች (የሀገሪቱ ባህል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ ቋንቋ …) የሚጎሉበት እንዲሁም የሌሎች ሃሳብ ተሸካሚ ከመሆን ሃሳብ ወደ መሸጥ የምትሸጋገርበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ያለምንም ልዩነትና የፖለቲካ አመለካከት ሁሉም ዜጋ ሊደሰትበት የሚገባ ድል እንደሆነም ተናግረዋል።

አቶ አትክልት፤ ሀገሪቷ የራሷ የውስጥና የውጭ ፖሊሲዎች አሏት። ይህንን መሠረት በማድረግ ከህብረቱ ሀገራት ጋር በሚኖረው ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የራሷን ፍላጎት መለየት አለባት። እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ተጽኖዎችን ለመመከት የጀመረቻቸውን ልማቶች (አረንጓዴ ዐሻራ፣ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ …ወዘተ) ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በአባል ሀገራቱ ድጋፍ እንዲያገኝ፣ ተቋማዊ እንዲሆን የሰው ኃይል ማፍራት በይበልጥ ህብረቱን ከተቀላቀለች በኋላ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

ከምዕራባውያንና አሜሪካ ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራት የብሪክስ አባልነት ውስጥ እንደተካተቱ አቶ አትክልት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ እንደአንድ ሉዓላዊ ሀገር ጥቅሟን በራሷ መንገድ ለማስጠበቅ ፖሊሲና ፍላጎቷን የሚያሟላላትን የትኛውም ጥምረት ውስጥ የመግባት ሙሉ መብት አላት። ስለዚህ ሀገሪቱ ካላት ፖሊሲ ጋር እያናበበች ከየትኛውም ጥምረት ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላማዊ መንገድ ማስኬድ አለባት። ሆኖም ሀገሪቱ ብሪክስን መቀላቀሏ በምዕራባውያን ሀገራት በዓይነ በቁራኛ የምትታይበት ምንም ምክንያትና ስጋት እንደሌለ ያስረዳሉ።

በአንጻሩ “የብሪክስ አባል በመሆኗ የምታገኘው ጥቅም እንዳለ ሁሉ ስጋቶችም ይኖራሉ” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት፤ ዓለም እየተዘወረች ያለችው በልዕለ ኃያሏ አሜሪካና ምዕራባውያን ሥርዓት ነው። ስለዚህ የአንድ አገር ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚመራው በዚህ ሥርዓት ነው። ይህ ደግሞ አንድ ሀአገር ከምዕራባውያን ጋር የፖሊሲም ይሁን የተለያየ ቅራኔ ውስጥ በምትገባበት ወቅት፤ የሚገጥማትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውሶችን መፍትሄ ለመስጠት ያስቸግራል። ርዳታና ብድር የምታገኝበት መንገድ ይጠባል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከምዕራባውያን ጋር የሚኖራት ግንኙነት በሚሻክርበት ወቅት አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ሁለተኛ ሀገሪቱ ከምዕራባውያን ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ስለዚህ የብሪክስ አባል ሀገራት ሰፊ የንግድ ቀጣና ስለተቆጣጠሩ፤ ሀገሪቱ አማራጭ የንግድ ቀጣና ታገኛለች። በዚህም ምርቷን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ አባል ሀገራቱ በመላክ የኤክስፖርት አቅሟን ይበልጥ ታሳድጋለች። በተዘዋዋሪ ደግሞ በቀላሉ ከውጭ የምታስገባውን ምርት የምታገኝበት እድል ይፈጥራል።

ሶስተኛ የብሪክስ መሥራች ሀገራቶች እስካሁን በተግባር በታየው ልምዳቸው በትብብር ከማልማት ባለፈ በአንድ ሀገር በውስጥ ወይም በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገቡም። ሀገራት የራሳቸውን የፖለቲካ ጉዳይ በራሳቸው መፍታት አለባቸው የሚል የጸና አቋምና እምነት አላቸው። በተለይ ርዳታም ይሁን የንግድ ትስስር በሚፈጠርበት ወቅት የፖሊሲ ነጻነት ይሰጣሉ። ስለዚህ ሀገሪቱ ጥምረቱን መቀላቀሏ አሁን ላይ የያዘችውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በነጻነት እንድትተገብርና የራሷን ዕድል በራሷ የምትወስንበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላት ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ የብሪክስ አባል ሀገራት በኢኪኖሚ እየፈረጠሙ፣ ዓለም ላይ የፖለቲካ ተጽዕኗቸው እያደገ መጥቷል። ሆኖም ፖሊሲያቸውን የሚያስፈጽሙበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠነክሩበት ተቋም እንዳልፈጠሩ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸው፤ የጥምረቱ አባል ሀገራት እየጨመረ ቢሆንም የፖሊሲ ማዕቀፍ በስፋትና በጥራት አዘጋጅቶ አጸድቆ በአባል ሀገራቶች ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም። የአባላቱ ሀገራቶች ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የርዳታ … ወዘተ ግንኙነቱ ተቋማዊ አልተደረገም። ስለዚህ በጥምረቱ ሀገራት መካከል ተቋማዊ ግንኙነት ስላልተፈጠረ ሀገሪቱ ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር ወደፊት የሚኖራት ግንኙነት ዘለቄታዊነቱ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው። ይህ ደግሞ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

በአንጻሩ አሜሪካና ምዕራባዊያን ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበት እንዲሁም ፖሊሲያቸውን የሚያስፈጽሙበት እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አቋቁመዋል። እነዚህ ሀገራቶች የውጭ ግንኙነታቸውና ዓለም ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ውጤታማ የሆነበት ሚስጥሩ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የዓለም ሀገራትን በቁጥጥር ሥር በማድረጋቸው እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ከፖለቲካ አመለካከት አኳያ ሲታይ ነባር ወዳጅ ትቶ ወደ አዲስ ወይም ወደሌላ ወዳጅ በሚኬድበት ወቅት፤ ነባር ወዳጅ ሀገራቶች የሚያደርሷቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጽኖ አሁን ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚም የሆነ የፖለቲካ ድል ላይ አሉታዊ ተጽኖ ሊያሳድር ይችላል ብለዋል።

እንደዚህ አይነት አዲስ ጥምረት ውስጥ በሚገባበት ወቅት ጥቅም እንዳለው ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ በሌላኛው የፖለቲካ አሰላለፍ ጎራ የሚያስፈርጅ እንደሆነ ባለሙያው ጠቅሰው፤ ኃያላን ሀገራት የሚያደርጉት የፖለቲካ ሽኩቻም ይሁን ጦርነት ዳፋው ለሀገራችን እንዳይተርፍ ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሚዛናዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ይዞ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። በተቻለ መጠን ጥቅሙን የሚያሰፋ፣ በተቃራኒው ደግሞ ስጋቶችን የሚቀንስ የግንኙነት መርህ በመከተል ከተቻለ ብሪክስ አዲስ ጥምረት ከመሆኑ አንጻር ሀገሪቱ የምታገኛቸው ጥቅሞች ፈርጀ ብዙ እንደሆኑ ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ይናገራሉ።

እንደምሁራኑ ገለጻ ሀገሪቱ ለየትኛውም ጥምረት ተመራጭ የሚያደርጋት ፈርጀ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከፖሊሲዋ ጋር እያገናዘበች ከየትኛውም ጥምረት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ በማስቀጠል ጥቅሟን ማስከበርና ኢኮኖሚዋን ማሳደግ እንደሚገባ ይመክራሉ።

 ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 23/2015

Recommended For You