እንዴት ?
ከአመት በፊት “በጥቂቱ በጥቂቱ ይሞላል ልቃቂቱ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር። የጽሁፌ መልዕክትም የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሰነጣጠቅ ወጥተው ወደ አንድነት እንዲመጡ የሚመክር ነበር። ወትሮም ቢሆን በግለሰቦች አለመግባባት እንጂ በፖለቲካ አይዲዎሎጂ ፓርቲዎች አሁን ያለውን ያህል ቁጥር ላይ እንዳልደረሱ ጥሩ ማሳያው ቀጥሎ የቀረበውና ለትውስታ ከቀደመው ጽሁፌ የቀነጨብኩት (የተወሰነ ማስተካከያ አድርጌበታለሁ) ታሪክ ነው።
ታሪኩ እንዲህ ይተረካል… እንዴቱም ይሄውልዎ!
እዚሁ በአገራችን ከአመታት በፊት መአሕድ የሚባል አንድ ፓርቲ ነበር። በዚህ ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ተፋቅረውና ተሳስበው ሲኖሩ፣ ሲኖሩ ከእለታት አንድ ቀን ከአመራሩ ጋር ተጋጩ። ግቢም አትግቡ ተባሉ። በጣም ተናደዱ። በእልህ ተነሳስተውም የራሳቸውን ሰው አሰባሰቡና “ኢዴፓ” የተባለ ፓርቲን መሠረቱ። ኢዴፓዎችም አንድ ላይ መኖር ቀጠሉ። አሁንም ሲኖሩ፣ሲኖሩ በፓርቲያቸው ኢዴፓ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ። አለመግባባቱም ቀጠለና መለያየታቸው የግድ ሆነ። ተለያዩም። የተወሰኑትም “ማን ከማን ያንሳል” ብለው “መኢዴፓ” የተባለ ፓርቲን መሰረቱ።
እናት ፓርቲው “መአሕድ”ም አሰላለፉን ቀየረና ከብሄር ፖለቲካ ፓርቲነት ወጣ ብሎ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እራሱን ለወጠ። አንባቢ ሆይ ከፈለጉ አሳደገም ብለው መረዳት ይችላሉ። ለእኔ ግን አዘለም አቀፍም ያው ተሸከመ ነው። እናም በዚህ ፓርቲ ስር መቀጠል የፈለጉ ሁሉ ቀጠሉ። ድሮም ውስጣቸው ቁርሾ የነበረባቸው ግለሰቦች ግን ጊዜ ጠብቀው ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ፓርቲውን እሰጥ አገባ ውስጥ ከተቱት። በመጨረሻም ያው እንደተለመደው የተወሰነው ቡድን ከፓርቲው ወጣና ሌላ አዲስ ፓርቲ መሰረተ። የፓርቲውንም ስም “ብርሃን” ሲል ሰየመው። (ግን ይሄ ፓርቲ የት ደረሰ? ካለስ ምን እየሰራ ይሆን?)።
ያ የ1997ቱ ምርጫ ብዙ ታሪክ ያየንበት፤ በተለይ ደግሞ ድህረ ምርጫው ላይ የነበረው ቀውስና እልቂት ዳግም እንዳይመጣብኝ የምመኘው፤ ብዙዎችንም “ድሮስ ፖለቲካ” አስብሎ ያራቀብን ስለነበረ ጭምር በግሌ ስለ እሱ ማሰብ አልፈልግም። በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንደርም ቢሆን ብዙ ታሪኮችን አሳይቶናል። ከዚህ መካከልም በአግባቡ ሳይቀናጅ ቅንጅት ተብሎ የብዙዎቻችንን ልብ አስኮብልሎ የነበረው ፓርቲ ዛሬም ድረስ እንዳይቀናጅ ሆኖ ተፈረካከሰ። (በነገራችን ላይ ሳይቀናጅ ያልኩት እኔ አይደለሁም። ራሳቸው የፓርቲው ሰዎች ሲበታተኑ በጻፏቸው የግል ታሪኮቻቸው ላይ የገለጹት ጉዳይ ነው)። በክፍፍሉ መሰረትም አሁን ያለው ቅንጅት በአቶ አየለ ጫሚሶ ስር ሆኖ ሲቀጥል፤ መኢአድና ኢዴፓ ወደ ነባር ስማቸው ተመለሱ። ሌሎች ደግሞ ሰብሰብ ብለው አንድነትን መሠረቱ።
ፓርቲዎቻችን እንደ አሜባ እየተከፋፈሉ መራባት እጣ ፋንታቸው የሆነ ይመስል አንድነት የተባለው የቅንጅት ክፋይ ፓርቲም፤ በተራው ሰላም ርቆት ችግር ውስጥ ገባ። ችግር ውስጥ የገቡት የፓርቲው ሰዎችም እንደተለመደው ገንጠል አሉና “ለምን የራሳችንን ፓርቲ አንመሰረትም?” ብለው መከሩ። አደረጉትም። ሰማያዊ የተባለ አዲስ ፓርቲም መስርተው ወደ ሜዳው ተቀላቀሉ።
የአገሪቷ የፖለቲካ ሜዳም አርበ ሰፊ ነውና ሳያቅማማ ተቀበላቸው። እነርሱ ግን መታመስ ሲጀምሩ የአንድ ምርጫ እድሜን እንኳን አላስቆጠሩም ነበር። በፓርቲው ውስጥ ባለው እሰጥ አገባ ምክንያት ከዛሬ ነገ ሁለት ሆኑ እየተባለ በሽምግልና ሳይቀር እየተደገፉ ቆዩ። ነገሩ ስር ሰዶ የተወሰኑ ግለሰቦች ከሰማያዊ ፓርቲ ወጥተው የራሳቸውን ፓርቲ ወለዱ
ስሙንም “ኢአአን” (የኢትዮጰያዊያን አገር አቀፍ ንቅናቄ) አሉት። ይሄ ፓርቲም ገና ብዙም ወደ ትግሉ ያልገባ፤ ብዙም ያልታወቀ ስለሆነ እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም አንድ ሆኖ ይቀጥላል? ወይንስ እንደ አያቶቹ ይሰነጠቃል? የሚሉት ጥያቄዎች ጊዜ የሚመልሳቸው ይሆናሉ። በግሌ ግን አመራሮቹ ከድሮው አስተሳሰብ ካልተላቀቁ በስተቀር ፓርቲው መሰንጠቁ አይቀርም ባይ ነኝ።
ከዚህ የብዜት ታሪክ መለስ ስል…
አዎን መለስ ስል፤ ከላይ ለመጠቃቀስ የሞከርኩት አንደኛው የፓርቲዎች የብዜት ታሪክ እንጂ ብቸኛው እንዳልሆነ ልብ በሉልኝና ልቀጥል። በውጭ አገራት ያሉት ፓርቲዎችም ቢሆኑ የአመሰራረትና ብዜት ታሪካቸው ከዚህ የተለየ የሆኑት ኢምንት ናቸው። ግለሰቦች ሲዋደዱ አንድ ላይ ይሆኑና አንድ ፓርቲ ይመሰርታሉ። ሲጣሉ ደግሞ ጥሉ ፓርቲ እስከ መሰንጠቅ ይደርስና የየግላቸውን ፓርቲ ይመሰርታሉ። የፓርቲዎቻችን ቁጥርም 70 እና 80 መድረስ አብይ ምክንያት ይሄው ነው። (መቶም ደርሰው እንደነበር ልብ ይሏል)
በአማራጭ ፕሮግራም ቀርቶ በስም እንኳን የማናውቃቸው ፓርቲዎች እንደ አሸን መብዛት፤ ምንም ሳንደባብቅ የልብ የልባችንን የምናወራ ከሆነ የጠቀመው ኢህአዴግን ነው። ምክንያቱም የምርጫው ድምጽ በተበታተነ መልኩ ለሁሉም ፓርቲዎች ስለሚሰጥ አብላጫውን ድምጽ ያገኝ የነበረው የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግም ይህችን አሳምሮ ስለሚያውቅና ፓርቲዎች ተቀናጅተው ከመጡ እንደማይችላቸው ከ1997ቱ ቅንጅትም ስለተረዳ ጭምር መብዛታቸው ደስታው ነው። እንዲያውም አንድም በግልጽ (ህገ መንግስቱ ስለሚያስገድደው) አንድም በህቡዕ ያበረታታ እንደነበር አሁን ላይ የሚወጡ አንድ አንድ መረጃዎች አሳይተዋል። (ስም መጥቀሱ አይጠቅምምና “ሆድ ሲያውቅ..” ብዬ አልፌዋለሁ)።
እነሆ ዛሬ ግን ኢህአዴግ ነገሩ ትክክል እንዳልሆነ የተረዳ ይመስላል። ሰሞኑን በሊቀመንበሩና በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አንደበት “ሰብሰብ በሉ” የሚል ምከረ ሀሳብ ለፓርቲዎች ተለግሷል። ይሄ ከኢህአዴግ ይመጣል ብሎ መገመት ዛሬ ላይ ቀላል ቢመስልም ብዙም ሳይሆን ጥቂት አመታት መለስ ብለን ከተመለከትን ግን የማይታመን ነው። በእርግጥ እየሆነ ያለው ሁሉ ህልም እንጂ እውን አይመስልም። ኢህአዴግ በመንግስትነት መንበሩ ሲያሳድዳቸውና አሸባሪ ብሎ ፈርጆ ሲያውግዛቸው የነበሩ ፓርቲዎችን ያሉበት ድረስ ሄዶ አግባብቶ፣ እጁን ዘርግቶ መንገድም ዘግቶ በእቅፍ አበባ ተቀብሏቸዋል። ይሄ ከግማሽ ርቀትም በላይ ይመስለኛል።
ይሄም ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልበሙሉነትና ላቅ ያለ የሞራል ልዕልናን በሚያሳይ መልኩ “ሰብሰብ በሉና ሞግቱን” ሲሉ ተናግረዋል። ይሄ ሊመጣ ላለው ጥላ ስለሆነ በግሌ ቀጣዩን ምክርቤት እንድናፍቅ አድርጎኛል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለው አስበው ከሆነ ተሳስተዋል። ጊዜ የለም፤ ጊዜው አሁን ነው። ስለሆነም ሰብሰብ ብለው ባለአራት ግንባሩን ኢህአዴግ እንዲሞግቱልን እንፈልጋለን። ይሄንን አለማድረግ አሁንም እንደድሮው ዋጋ የሚያስከፍለው ራሳቸው ተፎካካሪዎችን እንደሆነ ማወቅ አለባቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰብ ፋይዳው እልፍ ነው። በተለይም ምክንያት እየፈለገ ጸብ ውስጥ እየገባ ያለውን አዲሱን ትውልድ አስተሳሰብ በመቅረጽ ወደ አንድነት ለማምጣት የሚኖረው አስተዋጾ ቀላል አይሆንም። ለአንድ ክልል ህዝብ እንቆረቆራለን፤ አንድ አይነት አላማ አለን የሚሉ ነገር ግን አንድ ያልሆኑ ፓርቲዎች ብዛት ከጣት ቁጥር በላይ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ እውነት ለመናገር በፕሮግራምና በአይዲዎሎጂ ደረጃ ልዩነት የላቸውም። ልዩነቱ ያለው ፓርቲው ላይ ሳይሆን ፓርቲውን በሚመሩት ግለሰቦች ዘንድ ነው። ግለሰቦች ደግሞ አላፊ ናቸው። ስለሆነም ይሄንን መረዳትና ከፋፍለው የኖሩትን ህዝብ ወደ አንድ ለማምጣት ጊዜው አሁን ነው የሚለውን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ወቅቱን የተረዱ ፓርቲዎች መለያየቱ ይበቃናል እያሉ መዋሀድ ጀምረዋል። በሚገርም ሁኔታ ውህደቱ ከገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ጋር ጭምር ሆኗል። ይሄንን ስንመለከት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድም በአገራዊ ለውጡ ላይ እምነት እንዳደረባቸው፤ አንድም የአይጥና የድመት ፖለቲካ ማብቂያው ዘመን ይሄ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል።
ይሄንን ለማለት የግድ ነብይ መሆን አይጠይቅም። ምክንያቱም አዴፓ/ብአዴን (የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ከአዴሀን (አማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ንቅናቄ) ጋር፤ ኦዴፓ/ኦህዴድ (ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ደግሞ ከኦዴግ (ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ጋር ተዋህደው ሲታዩ የተቀሩት ወደዚህ የማይመጡበት ምክንያት ግለሰባዊ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልምና ነው። ለምን ቢሉ፤ አዴፓ እና ኦዴፓ ገዥ ፓርቲዎች ሆነው ተፎካካሪዎቻቸውን ካቀፉ ተፎካካሪዎች እርስ በእርስ ለመዋሀድ እስከፈለጉ ድረስ የሚገድባቸው አንዳች ነገር የለም።
በተፎካካሪ ፓርቲዎች ጎራም እርስ በእርስ የመዋሀድ ጅምሮች መታየት ጀምረዋል። በአቶ ተሻለ ሰብሮ የሚመራው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ከሰባት ድርጅቶች ጋር ለመዋሃድ መስማማቱን ይፋ አድርጓል። ሌሎችም ከሚመስላቸውና ይመጥነናል ብለው ካመኑት ጋር ለመዋሀድ ንግግር ጀምረዋል። ይሄ ለአገራችን ትልቅ ብስራት ነው። የመለያየቱ ዘመን ይበቃናል። በአገር ጉዳይ አንድ ሆነን አንዷን አገራችንን ልንጠብቅና ወደበለጸጉት አገራት ዴሞክራሲ ልንደራደር ይገባናል።
አሁን ሁሉም ነገር ያለው እንደ ወትሮው በኢህአዴግ እጅ ብቻ አይደለም። ያ ዘመን አብቅቷል። ኢህአዴግ ተጸጽቶ በገሀድ ንስሀ ገብቷል። ይቅርታም ጠይቋል። ይቅርታም ብቻ ሳይሆን የአሸባሪነት ፍረጃ ያለባቸውን ድርጅቶች ሳይቀር ፍረጃውን አንስቶላቸው ወደሰላማዊው ትግል ቀላቅሏቸዋል። እናም ኳሷ ያለችው በራሳቸው በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጅ ነው። ጥሩ ተጫዋች ሆኖ ጥሩ ነጥብ ማግኘት አሁንም የራሳቸው የፓርቲዎች ጉዳይ ይሆናል። ጥሩ ነጥብ የሚገኘው ደግሞ በቡድን ሰብሰብ ብሎ መጫወት ሲቻል ብቻ ነው። ስለሆነም “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ..” ነውና ተረቱ ፓርቲዎች ሆይ የረባ ያልረባ ሰበባሰበቡን ተዉትና ሰብሰብ በሉማ። ይሄንን ማድረግ ካልቻላችሁ ሌላ የብዜት ታሪክ ማስቆጠር ትቀጥላላችሁ። በታሪክም ከመወቀስ አትድኑም።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
አርአያ ጌታቸው