አዲስ አበባ፡- የውጭ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በጋራ የቤቶች ልማት ግንባታ መሳተፍ አለመቻላቸው ተገለጸ፡፡ በቀጣይ የሪል እስቴት አልሚዎች ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በቤት ልማት ግንባታው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢትዮጵያ በደቻ፣ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ የውጭ አገር ኩባንያዎችን በአገር ውስጥ ለማሳተፍ መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡
እንደእሳቸው ገለጻ በ2005 ዓ.ም ብቻ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ዘጠኝ መቶ ሺ ቤት ፈላጊ ዜጎች ተመዝግበዋል፡፡ ተመዝጋቢዎቹ በአዲስ መልክ በተደራጀው የ10/90 የ20/80 እና የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም እንደ አቅማቸው ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ይህን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በአገር ውስጥ ተቋራጭ ብቻ ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም፡፡
የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት እንደ አማራጭ የውጭ አገር ኩባንያዎችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ለማሳተፍ መንግሥትም ሆነ የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው ያሉት ኃላፊው፣ሆኖም ግን በየጊዜው ባህሪውን የሚቀያይረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙና ምንዛሪውም በሚፈለገው መጠን ባለመገኘቱ እንደታሰበው የውጭ አገር ኩባንያዎችን በአገር ውስጥ የቤት ልማት ፕሮግራም ማሳተፍ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
አቶ ኢትዮጵያ እንዳመለከቱት፣ ችግሩን ለመፍታት የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት የሚል ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ በፕሮግራሙ መሰረትም በቀጣይ የሪል እስቴት አልሚዎች ከመንግሥት ጋር በማቀናጀት በቤት ልማት ግንባታው ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
በዚህ ፕሮግራም በዋናነት መንግሥት መሬት ያዘጋጃል የግሉ ዘርፍ ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዘርፉ ላይ ይሰማራል፡፡ ይህ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ አጋርነት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ ይህም ተራርቆ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይገመታል የሚሉት ኃላፊው፣ እስካሁን ከተገነቡት 308 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 280 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መተላለፋ ቸውን አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በፍሬህይወት አወቀ