ለፈተናዎች የማይንበረከክ ኢኮኖሚ የመገንባቱ ሂደት

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የዓለም ኢኮኖሚ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየወደቀ ይገኛል። ይህ ቀውስ ከስምንት ቢሊዮን እየተሻገረ ላለው የዓለም ሕዝብ ውስብስብ ፈተናዎችን እየደቀነ ነው። በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ብቻ ወስደን ለመመልከት ብንሞክር፤ የሁለቱ ታላላቅ ሀገራት ፍጥጫ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን እንረዳለን።

ይህ ጦርነት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አፈናቅሎ ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲሹ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ግጭቱ ዓለም አቀፋዊ ጫና የፈጠረም ሲሆን፤ የበርካታ ሀገራትን ኢኮኖሚም እያመሳቀለ ይገኛል።

ጦርነቱ የሸቀጣሸቀጦችን ገበያ ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ዘርፎችን ክፉኛ እየጎዳ ይገኛል። የንግድ ግንኙነት መበጠስ፣ የገንዘብ ፍሰት መቋረጥ፣ የተፈናቀሉ ሰዎች መብዛት እና የገበያ እምነት መጥፋት ጦርነቱ በጥቅሉ በዓለማችን ላይ የፈጠራቸው መጠነ ሰፊ ቀውሶች ማሳያዎች ናቸው።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኃይል ዘርፍ፣ በስንዴ ምርት፣ በአፈር ማዳበሪያ እና መሰል አቅርቦቶች ላይ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ጫና የፈጠረና እየፈጠረ የሚገኝ ነው። የምግብ ዋስትና እጦት እና እያሻቀበ ያለው የዋጋ ግሽበትም ከዚሁ ጋር የሚያያዙ ተጨማሪ ማሳያዎቹ ናቸው።

የፋይናንስ ገበያዎች ላይ እርግጠኛ አለመሆን እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረትም የዚህ አስከፊ ጦርነት ውጤቶች ናቸው። ከዚህ በተጓዳኝ የምግብ እና የኢነርጂ ዋጋ መናር ድህነትን እያባባሰ ነው። ጦርነቱ ከዚህ በኋላ በአጠረ ጊዜ የሚቋጭ ቢሆን እንኳን ድባቴ ውስጥ የገባው ኢኮኖሚ በቶሎ ያገግማል የሚል እምነት የለም።

ይህ የሚያመለክተው ውጤቱ ሳይተነተን እና «በግፋበለው» የሚደረግ ጦርነት ሂደት ውስጥ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያስከትል ነው። ምክንያቱም ጦርነቱ የሁለቱ ሀገራት ይሁን እንጂ የችግሩ ገፈት ቀማሾች በርካቶች ናቸው። ለምሳሌ፣ በዚህ ጫና ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተጎጂ ሆነዋል። የሀገራችን ገበሬዎች ክረምቱን ማሳቸውን ሰብል ለመሸፈን የአፈር ማዳበሪያ መቸገራቸውን፤ እንዲሁም የዋጋው የመናር አንደኛው ምክንያት ይሄ ዓለም አቀፍ ጫና ነው።

ሌላው ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው ዓለምን በከባድ የኢኮኖሚ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ውስጥ በመክተት ጠባሳውን ጥሎ ያለፈው ክስተት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነው። የቅርብ ጊዜ ትዝታችን የሆነውና አሁንም ድረስ ዐሻራው የሚታየው ይህ ወረርሽኝ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ከማስከተሉም በላይ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጓጎል አስከፊ ነው።

ምክንያቱም ሚሊዮኖች ወደ አስከፊ ድህነት የመውደቃቸው ምክንያት ነበር። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ወደ 690 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲገጥማቸው ከማድረጉም በዘለለ፤ ይህ ችግር ተጨማሪ 132 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለተመሳሳይ አደጋ ማጋለጡን ይፋ አድርጎ ነበር።

ወረርሽኙ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢንተርፕራይዞችን የህልውና ስጋት በመፈታተን የኢኮኖሚ አውታሮችን አነቃንቆና ስጋት ውስጥ ጥሎ ያለፈ ነው። ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን አምራች የዓለም ሕዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የኑሮ መሠረታቸውን የማጣት ስጋት የተደቀነባቸው በዚሁ የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ነበር። በተለይም መደበኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ገቢ ያላቸውና የዕለት ተለት ገቢን የሚያገኙ ሠራተኞች ለችግር የተጋለጡበት ሆኖ አልፏል።

ከላይ ያነሳኋቸው ሁለት ማሳያዎች አሁን ዓለማችን የተደቀኑባት ፈተናዎች ማሳያ ናቸው። በዚህ ፈተና ከሚታመሙ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትገኝበታለች። በእነዚህ ታላላቅ ወቅታዊ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ የኢኮኖሚውን መሠረት ለመናድ የሚገዳደሩ ሌሎች ተጨማሪ የውስጥ ችግሮችንም እያስተናገደች ነው። አንደኛው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሲደረግ የቆየው ግጭትና ጦርነት ሲሆን፤ ይሄም ግዙፍ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሎት ነው ያለፈው።

ይህ ጦርነት ለብዙኃን መፈናቀል፣ ለመሠረተ ልማት ውድመት፣ ለንግድና ለልዩ ልዩ የኢኮኖሚ መሠረቶች ውድቀት ቀጥተኛ ተፅእኖ የነበረው ነው። ይህ የውስጥ ችግር ከላይ ካነሳናቸው ዓለም አቀፍ ጫናዎች ጋር ተደምሮ አሁንም ድረስ ተጠግኖ ማለቅ ያልቻለ የኢኮኖሚ ፈተና መፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ለመልሶ ግንባታ፣ የተረጋጋ የገበያ ሥርዓትና የፋይናንስ ፍሰት አመኔታን ለመፍጠር ሰፊ ጊዜንና ጥረትን የሚጠይቅ ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ «ኮሽ ሲል» በግጭት ውስጥ ማትረፍ የሚሹ የግጭት ነጋዴዎች ማኅበረሰቡ ላይ ሌላ እንቅፋት ናቸው። ምርቶችን በመሸሸግ፣ ከትርፍ ህዳጉ በላይ በመጠየቅ በቋፍ ላይ ያለውን ችግር ለማባባስ ከላይ እታች ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላል።

«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ የሰሜኑ ጦርነትን ጨምሮ ከላይ ለማንሳት የሞከርኳቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ከፈጠሩት የኢኮኖሚ ቀውስ ማኅበረሰቡ ሳያገግም በሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ነገሩን በይበልጥ እያባባሱት ይገኛሉ። ሰላም ሲኖር ሰዎች ያሻቸውን ይሸምታሉ፣ የንግድ ልውውጡ የተረጋጋ ይሆናል።

መንግሥትም ጤናማ የግብይት ሥርዓት ዘርግቶ ሕግን ማስከበር ይችላል። ሰላም በሌለበት፣ እዚህም እዚያም ጦርነትና አለመረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ግን ከግጭት የሚያተርፉ አካላት ካልሆኑ በስተቀር ዜጎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱ አይቀሬ ነው።

በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደነበር፣ ለዓመታት የገነቡት ሀብት መውደሙን፣ የንግድና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መቋረጡ በተጨባጭ ማስረጃ ተመልክተናል። ኪሳራ እንጂ ትርፍ ካልነበረው ጦርነት «አፍስሰን ከመልቀም» ውጪ አንዳች ጠብ አላለልንም።

ግጭቱ ከአንድ ወገን አሸናፊነት ይልቅ የኢትዮጵያን አሸናፊነት አብስሮ ቢደመደም እንኳን በገንዘብ የማይተመን የሰው ሕይወት መጥፋት ከማስከተልም አልፎ ታላቅ ድባቴ ውስጥ የሚከትት የኢኮኖሚ ስብራት ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው በቅርብ ጊዜያት ከደረሱብን ዓለምአቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ ችግሮች ትምህርት ልንወስድ የሚገባው።

ሕዝብ ለሕዝብ እንዲጋጭና ሀገር ትርምስ ውስጥ እንድትገባ የተዛቡ መረጃዎችን መስጠት፣ ችግሮች ላይ ጋዝ ማርከፍከፍ በቂ ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ሰዓት ይህንን የሚያደርጉ አካላት አሉ። ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው ከወዲያኛው ጫፍ የግጭት አታሞ ሲመቱና ነገሮችን በቀላሉ ሲያጋግሉ እየተመለከትን ነው።

አለመግባባትን በሽምግልና፣ በውይይት እና በሰከነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ የሚጥሩት ደግሞ ወደዳር ተገፍተው ጩኸታቸው ሰሚ እያጣ ነው። ሀገራችን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት «ግፋ በለው» በሚል ነጋሪት ሲጎስሙ የነበሩ አካላት ጆሮ በማግኘታቸው ምክንያት ከጠፋውም የሰው ሕይወት በላይ ዛሬም ድረስ በደረሰባቸው የኢኮኖሚ ጫና በሁለት እግራቸው መቆም ያቃታቸው መቶ ሺዎች ተፈጥረዋል። እንደ ሀገርም ጦርነቱ ቢቆምም የኢኮኖሚ ስብራቱ ግን እስካሁን ድረስ ሊሽር አልቻለም።

ጥያቄው የሚሆነውም «ዛሬስ?» የሚል ነው። ምክንያቱም ዛሬም ከትናንት ለመማር የፈቀድን አንመስልም። ማሳችንን ጦም አሳድረን፣ የንግድ ሱቆቻችንን ሸጉረን ለግጭት አደባባይ እንድንወጣ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ብዙ «ግፋ» ባዮች ተፈጥረዋል። እነዚህ የግጭት ወቅት ነጋዴዎች ችግሮቻችን በውይይት፣ በቀላል ኪሳራ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊፈቱ እንደሚችሉ ሊነግሩን ፍላጎት የላቸውም። ይልቁኑም ጠብ-መንጃዎቻችንን ወልውለን ደም እንድንፋሰስ መንገድ እየጠረጉልን ነው።

ወቅቱ ክረምት ነው። አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ሲዘጋጅበት የከረመውን የሰብል ማምረት ሥራ የሚያከናውንበት ጊዜ ይሄ ነው። በዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት የመሬት ማለስለሻ ማዳበሪያ ተቸግሮ መፍትሄ እየፈለገ ያለን አርሶ አደር ሌላ ችግር ፈጥሮ ወደ ጫካ እንዲገባ መቀስቀስ ዳግም በሁለት እግሩ እንዳይቆም፣ የሀገርም ኢኮኖሚ ላያንሰራራ እንዲሽመደመድ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም።

ስለዚህ ከግጭት የዘለለ መፍትሄ ማፈላለግ የግድ ይለናል። ጦርነት እንደማያዋጣን፣ ግጭት እንደማያዛልቀን አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጊዜ እያየነው ነው። አይደለም በራሳችን ሀገር ውስጥ የምንፈጥረው ትርምስ፣ በሩቁም ያለው የኃያላኑ ሽኩቻ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ከገባበት ፈተና ውስጥ እንዳያገግም እያሽመደመደው ነው።

ሌላኛዋ የቅርብ ምሳሌ የምትሆነን ጎረቤት ሀገራችን ሱዳን ነች። በሁለት የተከፈለው የሱዳን መንግሥትና ቡድን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመምጣት ፍላጎት ባለማሳየቱ ለዜጎቹ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ረሀብና የኢኮኖሚ መሽመድመድ ምክንያት እየሆነ ነው። ለዚህ መረጃ ለማግኘት ሩቅ መሄድ አይጠበቅብንም።

በሱዳን በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት መሸሸጊያ ፍለጋ በአማራ ክልል ጎንደር የተጠለሉ የሱዳን ዜጎችን መመልከት በቂ ነው። ጦርነት ሰብአዊውን የሰው ልጅ ሕይወት ከመንጠቅ ባለፈ የድህነት ማቅ ውስጥ የሚዘፍቅ፣ ክብርንም የሚያዋርድ ነው። ይህንን ተገንዝበን ለጥያቄዎቻችን የተሻለ ሰላማዊ መንገድ ልንፈልግላቸው ይገባል።

መንግሥትም ዓለም አቀፍ ጫና የፈጠረውን የኢኮኖሚ ድቀት ለመቅረፍ ከሚያደርገው ርብርብ፣ እየወሰደ ካለው አማራጭ መፍትሄዎች ባሻገር መሽቶ ሲነጋ የሚፈለፈሉ ተደራራቢ ችግሮችን እንደየመልካቸው ማስተናድ የሚችል ቁመናን መገንባት ይኖርበታል።

በሕዝቦች መካከል ተደጋግመው የሚነሱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ሳይውሉና ሳያድሩ ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን መዘርጋት ይጠበቅበታል። ከዚህ መካከል ሀገራዊ መግባባትና ምክክር ለማድረግ የተጀመረው ሂደት በፍጥነት ሊጀመር ይገባል። ለፖለቲካዊ ልዩነቶችና ጥያቄዎች እንደየፈርጃቸው መፍትሄ ማፈላለጉ ላይ ቸል ማለት አያስፈልግም።

ጦርነት ኃያላን ሀገራት ላይ ጉዳት ቢያስከትልም እንደ እኛ ግን የከፋ እንደማይሆን እርግጥ ነው። ዩክሬንና ሩሲያ በገቡበት እሰጥ እገባ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የገባነው እኛው ነን። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በራስ አቅም አለመሸፈናችን ለሰፊ ችግር አጋልጦናል።

በልዩ ልዩ ምክንያት በውስጥ ግጭቶች መጠመዳችን ደግሞ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መሻሻል እንዳናመጣ ጋሬጣ ሆኖብናል። የእኛ ባልሆነ ዓለም አቀፍ ጫና መወጠራችን ሳያንስ እራሳችን በምንጠምቃቸው ግጭቶች «ከድጡ ወደ ማጡ» እየገባን እንገኛለን። ዝቅተኛ የኑሮ ገቢ ያላቸው፣ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ደፋ ቀና የሚሉ ሚሊዮኖች የተረጋጋ መስመር ላይ እንዲገቡ ሀገራዊ እቅድ ነድፎ ከመሥራት ይልቅ በጊዜያዊ ግጭት እየባከንን እንገኛለን።

ከገባንበት ጦርነት በሰላም ስምምነት ብንወጣም ዳግም መሰል ግጭት ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች ዛሬም ድረስ እያስተዋልን ነው። ይህ አደገኛ አካሄድ በሰሜኑ ጦርነት፣ በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በኃያላኑ ፍጥጫ ምክንያት ለተጎዳው ኢኮኖሚና እያደገ ለመጣው ግሽበት ተጨማሪ ፈተና እንዳይሆን ያሰጋል። ስለዚህ «ሳይቃጠል በቅጠል ብለን ከድሮ ሳይሆን ከቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን እንማር» የሚለው የዛሬው መልዕክት ነው።

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *