ዘመን በሚሉት የጊዜ ሽክርክሪት አሮጌውን ሸኝተን አዲሱ ላይ ከተምን፡፡ ከሰኔ ገመገም፣ ከነሐሴ ዋይ ዋይ ወደሚደነቅ ብራ መስከረም ዘመን ይሉትን የተስፋ ሸማ ለብሰን ለእንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽ በቃን። ዘመን ሾሮ ባደራው የሰው መሆን ጸጋ ትውፊት በገጻችን ላይ ሳቅን ኩሎ የሀዘናችንን ወዛም ጥላ ከለለ..ስለዚህም አሜን አልን፡፡ ዘመን የጌታ የቸርነቱ ዋጋ ነው.. ለሰው ልጅ ሁሉ የተገለጠ..እናም ስለተሰጠን አዲስ ዘመንና ቀን አፋችንን ለምስጋና አሞጠሞጥን፡፡
መስከረም መግቢያ ደጅ ላይ የጳጉሜን አፋፍ ተንተርሶ የሚነገር አንድ ሀገርኛ አባባል አለ ‹ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት› የሚል፡፡ የዶሮው ያስማማናል..መዐልተ ሌሊት ክንፉን ያማታ ኮከናም ዶሮ አኩኩሉ ባለ ቅጽበት ሲዳራው ካመሸ ጽልመተ ጠፍ ይኳረፋል..ያን ማግስት ለሰው ልጅ ሁሉ የመንጋት ተስፋ በምስራቅ አውድ ስር ይፈነጥቃል፡፡ የቡሄ ጅራፍም የተስፋ መለከት ድምጽ ነው..የአዲስ ዘመን የናስ ቃጭል፡፡ ትላንትን ከአሁን አኳርፎ፣ አሮጌውን በአዲስ ቀይሮ ለአዲስ ነገ የሚዳርግ፡፡
ንጋት የመኖር ስም ነው፡፡ ሕይወት በዚህ ጋሚያ የብርሃን ባተቶ ስር እትብቷን ሰውራለች፡፡ ማለዳ የከንፈር ወዳጁን እንደሚከጅል ሳዱላ የነፍስ የተስፋ አጥቢያ መፈንጫ ነው..ነገን ማያ የወዛም ሳቅ ሽንቁር። ጎህ ከጀምበር በተወለደ በላመ የብርሃን ቀለም ወዝቶ በልብ ምስራቅ ላይ የሚያቅላላ የተስፋ፣ የስኬት፣ የመንቃት፣ የመብሰል እለት ነው፡፡ ማለዳ ትንሳኤያችን ነው..ከዛሬ ወደነገ ስንተላለፍ ለአዲስ ጀብድ እየተሰናዳን ነው፡፡
የመጣው የአዲስ ዓመት ተስፋችን የኢትዮጵያን ችግሮች ቀርፎና አሽሮ ዘላለማዊ እንዲሆን 2017 ዓ.ም አዲሱ ዓመት እንደ ሀገር የብዙ ነገር መጀመሪያችን ነው፡፡ እንዳለፈው ጊዜ በምኞት ተቀብለነው የሚያልፍ ሳይሆን የነበሩብን ችግሮች እንዳይቀጥሉ፣ መጪውን ጊዜ ካለፈው ነጥሎ ተስፋና ኢትዮጵያዊነት የጎመራበት እንዲሁን የእርቅና የፍቅር፣ የሰላምና የተግባቦት ዋጋ የምንከፍልበት ነው፡፡ ሀገራችን በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ያሉባት ናት፡፡ ሰላም ተኮር በሆኑ ጥያቄዎች ስር ከወደቀችም ሰንበትበት ብላለች። እርቅና ውይይት የሚያስፈልጋቸው፣ አንድነትና ይቅርታ ሀገራዊ ምክክር እየተደረገባቸው ያሉ ጉዳዮችም አሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ አጀንዳዎች የሰከነና የረጋ፣ በሃሳብ የበላይነት ስር የወደቀ አድማጭና አሰላሳይ ዜጋ ይፈልጋሉ፡፡ አዲሱ ዓመት እንደ አዲስ መንፈስ በዚህም የመንፈስ ከፍታ ዳብረን ከችግሮቻችን ነፃ የምንወጣበትን አጋጣሚ እንደሚሰጠን በማመን ራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ራሳችንን ለለውጥና ለተሃድሶ ካላዘጋጀን ዘመን በራሱ የሚሰጠን ምንም የለውም፡፡ የዘመን ዋጋ በእኛ ዋጋ፣ በእኛ ብርታት የሚሰላ ነው፡፡
የሀገር የእድገት ልኬት ሚዛኑ ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ ስንል እንቶፈንቶ ሳይሆን ወደ ነገ የሚያይ፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚያስተውል፣ ስለትውልድ፣ ስለወገን የሚዳዳው ማለቴ ነው፡፡ ሃሳብ ስል የጦርነትን የበላይነት የሻረ፣ የአብሮነትን መንፈስ ያሰረጸ፣ በእርቅና በይቅር ባይነት ለእግዜር የዳበረ፣ በደም ሳይሆን በምክር ሀገር ለማጽናት የታጠቀ ማለቴ ነው፡፡ ሃሳብ ስል እልህና ማን አለብኝነት የሌለው፣ ጀግንነትን በጦር ሜዳ ሳይሆን በሰላም ወዳድነት ውስጥ የቀመረ፣ ለጋራ ባሕልና እሴት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከዘር ተኮር ፖለቲካ፣ ከማንነት አቀንቃኝነት ወጥቶ ለሰብዓዊነት ጋሻ ጃግሬ የሆነ እሱ ነው፡፡
ሃሳብ ስል ፍቅር ሰባኪ፣ እውነት ዘካሪ፣ ስለዘሩ ሳይሆን ስለሀገሩ የሚሟገት፣ በበሰለና በብልህ እይታ ከችግር ፈጣሪነት ወደመፍትሔ አመንጪነት ያጋደለ ሀገር ወዳዱን ማንነት ማለቴ ነው፡፡ ነባርና ወቅታዊ ችግሮቻችንን በዚህ የመፍትሔ አቅጣጫ ካልቃኘናቸው አባባሽ እንጂ አለዛቢ አይኖረንም። ያጣነው መድረክ ሳይሆን ለመድረኩ የሚመጥን አንቂ ሃሳብ ነው፡፡ ያጣነው ትውልድ ሳይሆን፣ በጎ ትርክት ሳይሆን አንደበታችንን ከዝምታ አላቀን ስለአብሮነት መነጋገር ነው፡፡ ያጣነው ታሪክ ሳይሆን ታሪክ ሳያዛንፉ እውነት የሚነግሩንን ፖለቲከኞችን ነው፡፡
በእልህና በይዋጣልን ያባባስናቸው እንጂ መፍትሔ የሰጠናቸው ችግሮች እምብዛም ናቸው፡፡ በችግር ላይ ችግር ስንደርብ እንጂ መፍትሔ አፍልቀን እፎይ ስንል አንታይም፡፡ ጦርነቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የዘር ሽኩቻው፣ የፖለቲካው ትኩሳት እንዳለ ነው።የሀሰት ትርክቱ፣ የበሬ ወለደ አሉባልታው፣ የእርስ በርስ ጥላቻው እንደለ ነው፡፡ ያለፈውን ዓመት በበጎ ምኞት ተቀብለነው ምኞታችንን ቀርጥፎ በልቶ ዛሬ ላይ ጥሎናል፡፡ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር እንመኛለን እናቅዳለን ምኞትና እቅዶቻችን ግን ዋጋ ለብሰው ነፃ ሲያወጡን አይታይም፡፡ ለምን ካልን ልባችን ጨልሞ አፋችን ስለሚናገር ነው፡፡
በጨለመ ልብ ውስጥ ደግሞ ብርሃን የለም። ብርሃናችን ገሀድ እንዲወጣ በእልህና በዘረኝነት የጨለመ ልባችንን በኢትዮጵያዊነት ብርሃን ልንዘራበት ግድ ይላል፡፡ በጦርነትና በጥላቻ ያደፈ ውስጣችንን በፍቅርና በወንድማማችነት ልናጠራው ይገባል፡፡ እንደ ሀገር ደስ በማይልና ለመጣንበት የአብሮነት ዳና በማይመጥን የዘረኝነትና የጦርነት ጨለማ ውስጥ ነን፡፡ አዲሱ ዓመት ታድሰንና ተለውጠን ለሀገራችን ሰላም በኩር የምንሆንበት እንዲሆን መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ‹በልባችሁ ተሃድሶ ተለወጡ እንጂ ይሄን ዓለም አትምሰሉ ይለናል›፡፡ ታላላቅ ህልሞቻችን በልባችን ተሃድሶ ስር ያደፈጡ ናቸው። ልባችን ካልታደስን የትኛውም ዘመን፣ የትኛውም አዲስ ዓመት ተሃድሶን አይሰጠንም፡፡ አንደበታችን ስለሰላም እያወራ ልባችን ግን ጦርነት ላይ ነው። ፍቅር ይሻለናል፣ ወንድማማችነት ይበልጥብናል እያልን በጎን ግን ወንድማማችነትን የሚያጠፋ እኩይ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ይሄ በልባችን ያለመታደሳችን ማሳያ ነው፡፡
ብዙዎቻችን በአንደበታችን የታደስን ነን፡፡ እንደ እኛ ኢትዮጵያን በአፉ ያንቆለጳጰሰ፣ በአንደበቱ ያላሞካሸ የለም፡፡ ነገር ግን አፍና ተግባራችን ለየቅል ነው፡፡ ስለዚህም የእጃችንን እያገኘን ነው፡፡ እውነት አፍ ላይ የለም ስፍራው በልብ ነው፡፡ ከአንደበት ወደልብ እስካልመጣን ድረስ ሀገራችንን መታደግ አንችልም፡፡ ፍቅራችን፣ መከባበራችን ከአንጀት ቢሆን ኖሮ የክፉ ሰዎች አፍ ባልጣለን ነበር፡፡ በአፋችን እየሸነገልን በልባችን ግን እናሴራለን፡፡ አሁን ባለው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ እንደ ትልቅ ችግር ሊነሳ የሚችለው አፋዊ ማስመሰላችን ነው፡፡ የምንናገረውን መኖር በጀመርን እለት ብዙ ችግሮቻችን ተቀርፈው በአሸናፊነት መቆም እንጀምራለን፡፡ ከሁሉ በፊት የምንናገረውን እንኑር፡፡
የአንደበቱን የሚኖር ፖለቲከኛ ያስፈልገናል። አንደበታችን እውነታችን ሆኖ ሀገራችንን ገላጭ፣ ትውልዱን ገሪ እንዲሆን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። ከልባችን ርቃ ድምጽ ማጉያ ስንይዝ ብቻ ትዝ የምትለን ኢትዮጵያ አትበጀንም፡፡ አዲሱን ዓመት ለተሃድሶና ለዘላቂ ለውጥ ተጠቅመነው ከአንደበት ወደልብ የምንሸጋገርበት እንዲሆን ምኞት አለኝ፡፡ በእውነቱ የአንደበታችንን የምንኖር ቢሆን በዓለም ላይ ሰላማዊ ሀገር በሆንን ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት ከማስመሰል ወጥተን በእውነት ሀገራችንን የምናገለግልበት እንዲሆን ሰፊ እድል ይዞልን መጥቷል በእድሉ ተጠቅመን ፍሬ ማውራት የትውልዱ ግዴታ ነው፡፡
‹አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የሕይወት መውጫ እርሱ ነውና› የሚል ለመነሻ ሃሳቤ የሚበጅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ አውቃለሁ፡፡ ይሄም ሆነ ከላይ የገለጽኩት የሃይማኖት አስተምህሮዎች የሚነግሩን ለውጥና ተሃድሶ ከዘመን ሳይሆን ከልብ የሚመነጭ እንደሆነ ነው፡፡ ያለፈውን ረስተን ወደተሻለ ነገ ለመሄድ የታደሰ ፖለቲካ፣ የተለወጠ አእምሮ ወሳኝነት አላቸው፡፡ በአብሮነት ስሜት ቀዳዳዎቻችንን መድፈን ከቻልን ለጦርነትና ላላስፈላጊ ንትርክ የጣሉን እሰጥ አገባዎች መለዘብ ይጀምራሉ፡፡
ከእኛ በስተቀር ሁሉም ነገር በተለወጠና በታደሰ ተፈጥሮ ስር ነው፡፡ መስከረም ብራ ደረቱን ገልብጧል፣ አደይና ጸደይ ተሳስመው ደጃፋችን ላይ አሸብርቀዋል፣ ተናፋቂዋ የመስቀል ወፍም በአፏ የብስራት ነጋሪ ይዛ አድማሱን በመዞር ላይ ትገኛለች። ቀዬው አረንጓዴ ለብሷል፣ አእዋፍት በዓመት አንድ ጊዜ በሚሰማ የክት ዜማቸው ታድመዋል..እጽዋቶች በአዲስ ዓመት ሙቀት እስክስታ ላይ ናቸው.. ሁሉም አዲስና ልዩ ነው.. እኛስ ለምን አዲስና ልዩ መሆን አቃተን? በትላንት ትርክት ዛሬን ዋጋ መክፈል፣ ጥቅም የሌለው የአሉባልታ ተረት ለምን ተመቸን? እስኪ ሀገር እንፍጠር.. እስኪ ትውልድ እንስራ፡፡
በእውነተኛ ተሃድሶ ሀገራችንን በልባችን ለመፍጠር ጥሩ ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ከሞገደኝነት ወደለዘበ የወንድማማችነት ተጋድሎ የምንሸጋገርበት የአዲስ ዓመት ሰማይ ስር ነን፡፡ በሃሳብ በልጽገን፣ በኢትዮጵያዊነት አምረን ልዩነቶቻችንን በምክክር ፈትተን ለሁላችንም ወደሚበጅ የከፍታ ማማ እናንጋጥ፡፡ አዲስ ዓመትን በተመለከተ ማህበራዊ ልምምዶቻችን አልተቀየሩም፡፡ አበባዬ ሆይ እንላለን፣ በሆታና በእልልታ እንቀበለዋለን፣ እንበላለን እንጠጣለን ከዚህ ባለፈ የመንፈስ ተሃድሶ የለንም፡፡
እድሜ ለሰጠው ሰው አዲስ ዓመት የራሱ ውበት አለው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በብዙ ባሕልና እሴት ላጌጡ ሕዝቦች ሲሆን ደግሞ ትርጉሙ ለየት ይላል። ለእሴቶቻችን ዋጋ ከሰጠን አስታራቂዎቻችንና አግባቢዎቻችን ይሆናሉ፡፡ አብረን በልተንና አብረን ጠጥተን በአንድ ስም ተጠርተን የመጣን ነን መለያየት አያምርብንም፡፡ መስከረም እንደስሙ አስተቃቃፊና አጠያያቂ ወር ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ የተሰራ የመለያየት መርገምት የሚሰበርበት፣ ሕዝቦቿ ወደአንድነት የሚመጡበት እንዲሆን በልባችን መታደስ እንቀበለው፡፡
መነሻ ሃሳቤ አዲስ ዓመት የአዲስ ሀገር አዲስ ብስራት የሚል ነው፡፡ በዚህ ርእስ ተመርኩዤ ምን አጥተን እንደተራራቅን፣ በብዙሀነት ውስጥ በቅለን ብቻነትን ስለምን እንደሻትን አሰብኩ..መድረሻዬ የብኩርና ግፊያ የሚል ሆኖ ተገኘ፡፡ እናንተዬ..ያራራቀን፣ ወንድማማችነታችንን ጥላሸት የቀባው በሀሰት ትርክት የተፈጠሩ እውነት መሳይ ውሸቶች ናቸው፡፡ እናም በአዲስ ዓመት ለአዲስ ሀገር አዲስ አስተሳሰብን ማዋጣት የመከራችን መፍትሔ ሆኖ ተገልጦልኛል፡፡
2017 ዓ.ም መሳሪያ ጥለን በፍቅር የምንሸናነፍበት፣ በወንድማማችነት ትግል ውስጥ አሸናፊ እንደሌለ የምንረዳበት፣ በሞትንና በገደልን ቁጥር ሀገራችንን እያደከምናት እንደሆነ የምናውቅበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ መከራ የሚበቃን፣ ሞትና እሮሮ የሚርቀን፣ በእርቅና በምክክር ካለ አፈሙዝ የምንግባባበት እንዲሆን፣ ሰርተን የምንከብርበት፣ አቅደን የምናሳካበት ከምንም በላይ የእርስ በርስ ጉርብትናችን ዋጋ የሚያገኝበት እንዲሆን ምኞቴ የላቀ ነው፡፡ ረግተንና ሰክነን ትላንት ለእኛ ምን ዓይነት ጊዜ እንደነበር የምናስተውልበት፣ ዛሬን እንደትላንት ላለማድረግ ቁርጠኞች የምንሆንበት ታጋሽና አሰላሳይ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ በብራ ሰማይ ስር የአዲስ ዓመትን አዲስ መንፈስ እየካደምን፣ እንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽ ስንል አበባ ተሰጣጥተን ፍቅራችን ሳይነጥፍ የምንቀጥልበት እንዲሆን እሻለሁ፡፡
ዘመን ከለውጥ ጋር አንገትና ዶቃ ነው። ለመለወጥ በወሰነው ውሳኔ ልክ ይከፍለናል። ስለሆነም አዲሱ ዓመት በበርካታ ውሳኔ ትርፍ የምናገኘበት እንዲሆን ከወዲሁ ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የዘመን ታሪክ ውስጥ አዲስ ዓመት የተለየ ዋጋ ያለው ነው። ሁሉም ሃይማኖትና ብሔረሰቦች በእኩል ስሜት የሚያከብሩት በዓላችን ነው፡፡ በተለይ የይቅርታና የተሃድሶ፣ የእርቅና የመተሳሰብ በዓል መሆኑ ብዙዎች ከችግሮቻችን ተምረን መጪውን ጊዜ በተስፋና በትብብር እንድንቀበለው ማድረግ መቻሉም ልዩ ያደርገዋል፡፡
ዘመን የሰው ልጅ ባሪያ እንደሆነ የማልቀይረው መረዳት አለኝ፡፡ ራሳችንን ለለውጥና ለሀገራዊ ጸጋ ከተጠቀምንበት በርግጥም አዲሱ ዓመት የሚሰጠን በርካታ በረከቶች ይኖሩታል፡፡ ከተለማመድናቸው ትርፍ የለሽ ልምምዶች ካልወጣን ግን እንዳለፈው ጊዜ ከምኞት ባለፈ ፋይዳ ቢስ ሆኖ መጥቶ የሚያልፍ ነው፡፡ ሀገራዊና ግለሰባዊ ምኞቶቻችን ተግባር ለብሰው ሀገርን ከድህነት፣ ማህበረሰቡን ከእርስ በርስ ግፊያ እንዲታደጉ አእምሯዊ ተሃድሶ ወሳኝ ነው፡፡
መልካም ዘመን፡፡
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም