የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጥ መልኩ እንዲከናወን ተጠየቀ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፡- በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 79ኛው የ.ተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባዔ የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነውና ከ140 በላይ የሀገር መሪዎች የሚሳተፉበት የመጪው ጊዜ ጉባዔ (Summit of the Future) ተከፍቷል።

በዚሁ ጉባዔ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እየተሣተፈ ይገኛል።

በጉባዔው ላይ ክቡር ሚኒስትሩ ባሰሙት ንግግር የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠይቀዋል።

አምባሳደር ታዬ ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካን የውክልና አድማስ ከሁሉም መመዘኛዎች አንጻር ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባው ጠይቀዋል።

ስምምነቱ ሁሉንም ሀገራት በእኩል አይን የሚመለከተው ጊዜ አይሽሬ የሆነው የተመድ መመሥረቻ ቻርተር ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ለማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በመጪው ጊዜ ጉባዔ ላይ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥርዓትን ሪፎርም ለማድረግ በትውልድ የአንድ ጊዜ ዕድል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባዔ ሠነድ ከ143 ሀገራት በላይ ድጋፍ በማግኘት ፀድቋል።

አምባሳደር ታዬ ስምምነቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራት ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት በራሳቸው የፖሊሲ ማዕቀፍ ምርጫ አግባብ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው የፀደቁት ሠነዶች Pact for the Future, Declaration on Future Generations, Global Digital Compact የድርድር ሂደት ላይ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።

የሠነዱ መፅደቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድህነት፣ ረሃብ፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ አደገኛ ግጭቶች፣ ወረርሽኞች እና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች እያደጉ በሚገኙበት ወቅት፣ የጋራ ምላሽ እና መፍትሔ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You