ታሪካዊ ጠላትነት ለግብጽ የአርባ ቀን እጣ ፈንታ አይደለም

በፖለቲካው ዓለም ያለውና ሲደጋገምም የምንሰማው አገላለፅ “በፖለቲካ ታሪካዊ ወደጅነትም ሆነ ታሪካዊ ጠላትነት የለም” የሚል ነው። ጉዳዩን ሁሉም ይስማሙበት ወይም አይስማሙበት ለጊዜው ባይታወቅም ፖለቲከኛ መሆንም አለመሆንም እኩል በሆኑበት ደረጃ ሁሉም “በፖለቲካ ታሪካዊ ወደጅነትም ሆነ ታሪካዊ ጠላትነት የለም” የሚለውን አገላለፅ ሲጠቀሙበት ይሰማል።

ይህ ከላይ ያስቀመጥነው አገላለፅ ለፖለቲካው ዓለም ሰዎች ለእርስ በርስ መወነባበጃ አገልግሎት ሲባል ወደ ሥራው ዓለም የገባ ፖለቲካዊ አገላለፅ ሊሆን ይችላል፤ ወደ እውነታው፣ ወደ መሬት ወርደን ስንመለከተው ግን በፖለቲካው ዓለም “የለም” የተባለው “ታሪካዊ ጠላት” ነት ግዘፍ ነስቶ በአካል እናገኘዋለን።

ሰሞኑን፣ ልክ እንደ 1960ዎቹ መጨረሻና 1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ፣ “ታሪካዊ ጠላት” የሚለው ነገር አየር ላይ በብዛት እየዋለ ይገኛል። በተለይ በከፍተኛ አመራር አካላት ደረጃ ቁርጥ ባለ መልኩ ሲነገር እንደሚሰማው “ታሪካዊ ጠላቶቻችን እያስቸገሩን ይገኛሉ።”

ሰሞኑን በስፋትና በብዛት አየር ላይ እየዋሉ ካሉትና አገራችንን ከተመለከቱ ነጥቦች መካከል፡-

  • ጀግና ታሪካዊ ጠላቱን ይፋለማል እንጅ አያወራም!
  • ሰልፋችንም ሰይፋችንም ወደ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ብቻ!!
  • ከኢትዮጵያ መፍረስ አትራፊ የሚሆኑት ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንጂ ኢትዮጵያውያን ፈጽሞ ልንሆን ከቶም አንችልም።
  • የውስጥ ባንዳዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተቀናጅተው የከፈቱብንን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ሁሉም ዜጋ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መመከት አለበት!!!
  • የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።

 

ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ (ተፈጥሮ አብዝታ በሰጠቻት ፀጋዎቿ ምክንያት መሆኑ እርግጥ ነው) ታሪካዊ ጠላት አጥታ አታውቅም። አለማጣት ብቻ ሳይሆን ምን ጊዜም የሚጎመዥዋት፣ ሊውጧት የሚያሰፈስፉ፤ አሊያም ሊያፈርሷት የሚረባረቡ አካላትን አጥታ አታውቅም። ለዚሁ ሲባልም ካንዴም ሁለቴ፣ ሶስትና አራቴም፤ ከዛም በላይ እየደጋገሙ፣ 40 እና በላይ ዓመታትን በመዘጋጀት እየተመላለሱ ሊወጉን፣ እጅ ሊያሰጡን የሞከሩ በርካቶች ሲሆኑ ፋሽስቱ ሞሶሎኒ ቀዳሚው ነው።

የግብፅ ተቆጥሮ አያልቅም። ሶማሌም እንዳቂሚቲ በለስ ቀንቷት አዋሽ አርባ ድረስ መጥታ ነበር። ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው አንድ ነገር ቢኖር የአንበሳን ክርን እየቀመሱ መመለሳቸው ነው። አንበሳው ስብር ስብርብር እያደረጋቸው እያነከሱ መመላለሳቸው የጋራ የሽንፈት ታሪካቸው በመሆኑ ተመሳስሏቸው ግዙፍ ነው።

እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያና ግብፅ የረዥም ዘመን (ወይም ጥንታዊ) ግንኙነት አላቸው ከሚባሉት ሀገራት ፊት መሪዎቹ ናቸው። ከመንፈሳዊው ጀምሮ ዓለማዊና ፖለቲካዊው ግንኙነት ድረስ የዘለቀ ትስስሮሽ የነበራቸው ስለ መሆኑ በሁለቱም ሀገራት በኩል ያሉ ድርሳናት ያስረዳሉ። የዓለም ታሪክም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ግንኙነታቸው አንድነታቸው ጎልቶ ሲወጣ አልታየም። ለምን?

አሁንም እንደሚታወቀው እንበልና እንደሚታወቀው ፤ ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ከድንበሯ አልፋ በመሄድ የሰው ሀገርን ሉዓላዊነት ደፍራ አታውቅም። ካልመጡባት በስተቀር አንድም ጊዜ በሌሎች ላይ ተኩሳ አታውቅም። ወዘተ። ይሁን እንጂ ግብፅን ጨምሮ በኢትዮጵያ ላይ ጣቱን ያልቀሰረና እየቀሰረም ያለ፤ በሀገርና ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያልገባ ሀገር (በተለይ በተለምዶ “ኃያላን“ የሚባሉቱ) የለም። “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ የተነሳ ሁሉ “አይዞህ፣ ከኋላህ እኔ አለሁ፤ በርታ” የማይል ማግኘት ከባድ ነው።

በተለይ ኢትዮጵያና ግብፅ እንደ ጥንታዊነታቸው ሁሉ ግንኙነታቸውም የዳበረ ሊሆን ሲገባው ጉዳዩ የተገላቢጦሽ መሆኑ ለብዙዎች ሁሌም እንቆቅልሽ ነው። ግብፅ በኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ላይ ሁሌም ለምን ጣቷን እንደምትቀስር ለማንም ግልፅ አይደለም። በፊት ለፊት ሲያቅታት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጀርባ ሁሌም ለምን እንደምትቆም እንኳን ሌላው፣ ራሳቸው የግብፅ መሪዎችም እሚያውቁት አይመስልም።

እነዚህ እንደ የዓባይ ውሃ፣ የአፍሪካ ቀንድ ደህንነት፣ የባህር ወንጀልና የሸብር ተቃውሞ ትግል ባሉ እንቅስቃሴዎች የጋራ አቋም ያሏቸው (አንዳንዶች ይህንን የሁለትዮሽ ግንኙነት “ከሌሎች አንፃር ልዩ ገፅታ ያለው ግንኙነት“ ይሉታል) ሀገራት ልዩነት እንኳን ቢኖራቸው ልዩነቶቻቸውን በጋራ መድረክ ሊፈቱ እየተገባ የግብፅ ምርጫ ሁሌም ለምን የማያዋጣት ጦርነት እንደ ሆነ ግልፅ ባይሆንም፤ የጋራ መድረኮቻቸው ግን ብዛታቸው (የአፍሪካ ህብረትንና እሱን መሰሎች ሳንጨምር) እንኳን ለሁለቱ ለሌሎችም መትረፍ የሚችሉ ናቸው።

ሁለቱ ሀገራት (ሱዳንን ጨምሮ) ከለጋሽ ሀገሮች ጋር በመተባበር በውሃና ኃይል ምንጭ ዘርፎች የሦስቱን ሀገሮች ጥረት በማቀናጀትና በመደጎም ረገድ ይንቀሳቀስ የነበረው የምስራቅ ዓባይ ተፋስስ ቴክኒክ ቢሮ -ENTRO- አባል ሀገራት ናቸው፡፡

ሁለቱ ሀገራት የመላ ዓባይ ተፋሰስ ሀገሮችን ትብብር ኢላማ አድርጎ በ1999 እ.ኤ.አ የተዋቀረውና በሰፊው የተፋሰሱን ሕዝብ ፍላጎት እንዳረጋገጠ የሚነገርለት የዓባይ ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ማህበር አባል ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የህዳሴው ግድብ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ኀገራት ናቸው፡፡ ይሁኑ እንጂ፣ ግብፅ በእነዚህ ሁሉ መድረኮች ፊት “ችግር” ያለችውን ይዛ በመቅረብ ለመፍታት ጥረት ስታደርግ አይታይም። ምን ጊዜም ምርጫዋ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ጦር ሰበቃ ወዘተ ነው።

ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብራቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከአንድ በሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያለው የሶወይዲ ኤሌክትሪክ ኬብል ፋብሪካ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክትን ጨምሮ በርካታ የግብጽ የኢንቨስትመንት ፕሮክቶች በኢትዮጵያ በሰፊው ተሠራጭተው ይገኛሉ፡፡ ታዲያ አልሲሲ ምን ቢነካቸው ነው …? ታሪካዊ ጠላትነት የአርባ ቀን እጣ ፈንታ ይመስል ለምን መንግሥታቸው ከዚህ አይነቱ አዙሪት ለመውጣት አልደፈረም?

የአሁኑ የግብፁ መሪ ወደ ሥልጣን ሲመጡ (ጁን ወር 2014) በሥልጣን ርክክቡ ወቅት በአሰሙት ንግግር “የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ለሚፈጠር ውዝግብ ምክንያት እንዲሆን አልፈቅድም” ማለታቸውን ረስተው ብቻ አይደለም በነጭ ሰርዘው እነሆ ነጋ ጠባ ያዙኝ ልቀቁኝ እንዳሉ አሉ።

በ2018 እ.ኤ.አ ኤክዋቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባዔፕሬዚዳንት አልሲሲ በተሳተፉበት ወቅት ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ የተፋሰሱ አባል ሀገር በሌላው የተፋሰሱ አባል ሀገር ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርስ ሀገሩን የማልማት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ባለ ሰባት ነጥብ መግለጫ ማውጣታቸውም ትዝ ያላቸው ሁሉ አይመስልም። ብቻ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዓይናቸው እንደ ቀላ ይኸው ግድቡ አለቀ።

ባጠቃላይ፣ የወደብም ሆነ ከወደብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ወደ ጦርነት እንደማያስገቡና (ሌሎች ጉዳዮች ከሌሉ በስተቀር) በዓለም አቀፍና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መፍትሄ እንደሚያገኙ እየታወቀ፤ የአሁኑ የግብፅ ከመቋዲሾ መንግሥት ጀርባ መሰለፍና በግልፅ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ መፎከር ከትዝብት ያለፈ አይደለም።

ሶማሊያን ከወዳጅ ሀገራት ከማጋጨት፣ ሰላሟን ከማሳጣትና ግዛቱን የአልሻባብ መፈንጫ ከማድረግ ባለፈ ምንም የሚያስገኘው ፋይዳ የለምና የሚመለከታቸው ሁሉ ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ ታሪክ ሳይቀር ግድ ይላቸዋል። ታሪካዊ ጠላትነት የአርባ ቀን እጣ ፈንታ (ወይም፣ ደዌ) አለመሆኑን ተገንዝበው ጉዳዩን ወደ ታሪካዊ ወዳጅነት ጥግ ሊያመጡት ይገባል እንላለን።

 

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You