ሀዋሳ:-ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ፍስሐ ጌታቸው (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርምርና የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑና ራሳቸውን እንዲችሉ ከተለዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ራስ ገዝ ሲሆን የሚሠራባቸው አምስት ዘርፎች ተለይተው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
“ግብርናና ላይፍ ሳይንስ፣ የጤና ሳይንስና ሕክምና፣ ፊዚካል ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስና ሂዩማኒቲስ እንዲሁም የመምህራን ሥልጠና የተለዩ አምስቱ ዘርፎች ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።
በእነዚህ አምስት ዘርፎች ብቁና ተመራማሪ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በእነዚህ ዘርፎች የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ የበዙ መርሐ ግብሮችንም ወደ አንድ የማምጣትና ሥርዓተ ትምህርት የማዘጋጀት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ከዘርፎች ልየታ ጎን ለጎን ትምህርቶችን በዲጂታል ታግዞ ለመስጠት፣ በቤተ መጽሐፍት የሚኖሩ የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍት ክምችትን ለማሳደግ እና ተማሪዎችም መጽሐፍቱን ባሉበት ቦታ ሆነው መጠቀም የሚያስችላቸው መሠረተ ልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
መምህራን ትምህርቶችን በቪዲዮ ምስል አስደግፈው መስጠት የሚችሉበት ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለ400 መምህራን የኦን ላይን ሥልጠና መሰጠቱንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።
ለዚህም በዩኒቨርሲቲው የተሟላ መሣሪያ ያለው የመልቲ ሚዲያ ስቱዲዮ በማቋቋም ሙሉ ዝግጅት መደረጉንም ነው የገለጹት።
በተያዘው ትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።
በትምህርት ዘመኑ በ267 የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱንና ከእነዚህ የትምህርት መስኮች 35 በመቶ የሚሆኑት በቅድመ ምረቃ የሚሰጡ የትምህርት መስኮች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢንጂነር ፍስሐ (ዶ/ር) እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው በፀደቀው የትምህርት ካላንደር መሠረት የመማር ማስተማር ሥራው በመጪው መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም ይጀመራል።
ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ጥራት በሰጠው ትኩረት ውጤት የታየ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ለእዚህም አምና ካስመረቃቸው ተማሪዎች 90 በመቶ የመውጫ ፈተናው ማለፋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም